በ18ኛው መቶ ክፍለ ዘመን የኖረ ፈረንሳዊው ፈላስፋ ጂያን ጃክ ሩሶ “ሰው ነጻ ሆኖ ተወለደ፤ ነገር ግን የትም ቦታ በሰንሰለቶች ታስሮ ይታያል” በማለት እንደተናገረ በስፋት ይጠቀሳል፡፡ ይህን አነጋገር በቀላሉ ዐይተው የሚያልፉት ዓይነት አይደለም፡፡ እንደ ክርስትና አስተምህሮ በሰው በደል ምክንያት ሰውም የሚኖርባትም ዓለም በአንድነት ስለወደቁ፤ በወደቀው ዓለም ውስጥ ሰው የተለያዩ ፍላጎቶቹ እስረኛ እንደሆነ እንማራለን፡፡ ሰው የተፈጠረበትን ዓላማ (ማለትም ከልዑል እግዚአብሔር ጋር በጸጋ ተዋሕዶ መኖር) ሊኖር የሚችለው ከፍላጎቶቹ ሁሉ በፊት እግዚአብሔርን እንዲያስቀድም፤ እርሱንም በፍጹም ልቡ እንዲወድ የሚያዙትን ትእዛዛት ሲጠብቅ ነው፡፡ ልዑል እግዚአብሔር ከፍላጎቶች ሁሉ ውስጥ እንደ አንዱ ሳይሆን ብቸኛው ፍላጎታችን እንዲሆን በኦርቶዶክሳውያን አባቶች ዘንድ ሰፊ ትምህርት አለ፡፡ ከእግዚአብሔር የሚለዩን ፍላጎቶቻችን አድራሻዎቻቸው ቁሳቁሶች፤ ማኅበራዊ እና “መንፈሳዊ ጉዳዮች” ውስጥ ሊገኙ ይችላሉ፡፡ የትኞቹም ቢሆኑ እግዚአብሔርን እንዳናስቀድም፤ ለእርሱ ብቻም እንዳንገዛ የሚከለክሉን እንቅፋቶች ከሆኑ ግን የምንጎዳባቸው ናቸው፡፡
በወንጌል ተጠቅሶ የምናገኘው ወጣት፤ ትእዛዛትን ሲፈጽም ለመኖሩ እውነት ቢሆንም፤ መድኅን ክርስቶስ ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ሰጥተህ ተከተለኝ ብሎታል (ማቴ 19፡ 21)፡፡ ይህ ትእዛዝ ለመፈጸሙ አንዱ መገለጫው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደተናገረው፤ አንድ ሰው ሀብት ንብረቱን ሸጦ በፍጹም ልቡ ክርስቶስን ለማገልገል ከዓለም ወጥቶ ወደ በረሃ (ወደ ገዳም) ሲገባ ነው፡፡ ቅዱሳን የሚሆኑ እንጦንስ፤ መቃርስና ሌሎችም አባቶች በዚህ የሚጠቀሱ ናቸው፡፡ ሁሉን ሽጦ ክርስቶስን ስለመከተል የሚያዘው ትእዛዝ ለመፈጸሙ ሌላኛው መገለጫ ቡሩካን የሚሆኑ ሰዎች በአካል ከዓለም ሳይወጡ ነገር ግን ዓለምን ከልባቸው ያወጡ ናቸው፡፡ መነኩሴው ክርስቶስን ብቻ ያገኝ ዘንድ ከዓለም እና በዓለም ካሉ ነገሮች ተላቆ ገዳም እንዲሄድ፤ እንዲሁ ክርስቲያንም ምንም በዓለም ቢኖር እንኳ ዓለምን እና ፍላጎቶቿን ከውስጡ በማስወጣት ክርስቶስን ያገኝ ዘንድ አባቶች ያስተምራሉ፡፡ ለዚህም ምሳሌ የሚሆኑ ብዙ ቅዱሳን ተገኝተዋል፡፡ ከላይ ባነሳናቸው በሁለቱም ሁኔታዎች ውስጥ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ ይኸውም ራስን ለእግዚአብሔር እንጂ ለሌሎች ፍላጎቶች አለማስገዛት ነው፡፡ ሙሉ ለሙሉ ራስን ለእግዚአብሔር አሳልፎ መስጠት ነው፡፡ ከራስ ፈቃድ ይልቅ ፈቃድን ለእግዚአብሔር ለመስጠት እግዚአብሔርን በፍጹም ልብ ማመን ነው፡፡
መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ወጣቱን ያለህን ሁሉ ሸጠህ ለድሆች ሰጥተህ ተከተለኝ አለው፡፡ “አለኝ፤ የኔ ነው” ብሎ የሚስበውን ሁሉ በፈቃዱ ካልተወ በቀር በእውነት ክርስቶስን መከተል (መምሰል) አይችልምና ይህን ተባለ፡፡ ክብር ይግባውና ጌታችን በመዋዕለ ሥጋዌው፤ ተገልጦ በሥጋ እግሮች በእኛ መሐል ሲመላለስ፤ ምድራዊ ሀብት ራሱንም የሚያስጠጋበት ጎጆ እንኳን እንደሌለው የተወደደ ወንጌላዊ ሉቃስ ጽፎልናል (ሉቃ 9፡ 58)፡፡ የጌታ በሥጋ የመገለጡ አንዱ ምክንያት ሰው እንዴት ባለ አኗኗር ከእግዚአብሔር ጋር መኖር እንደሚገባው በተግባር ለማሳየት በመሆኑ የጌታ አኗኗር፤ ከላይ ላነሳነው ዐቢይ ጉዳይ ዋና ምሳሌ ይሆነናል፡፡ አባቶችም በእውነት እርሱን ተከተሉት (መሰሉት)፡፡ በዚህ ዓለም ሲኖሩ እንደተከተሉት፤ እንዲሁ እርሱ ወደ ገባባት ክብርም በጸጋ ተከትለውት ገብተዋል (2 ቆሮ 3፡ 18)፡፡ እግዚአብሔርን ማመን ማለት ስለ እግዚአብሔር ጥሩ ስሜት መሰማት ሳይሆን እርሱን ከጊዜያዊ ፍላጎቶች ሁሉ ማስቀደም፤ እርሱንም ብቸኛ ፍላጎት ማድረግ መሆኑ የታወቀ የተረዳ ነው፡፡
ከቤተ ክርስቲያን አባቶች አንዱ የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው (St. John of the Ladder) የክርስትና ሕይወትን (ተጋድሎን) ያዕቆብ በሕልሙ ባያት መሰላል አምሳል መስሎ በሰፊው ያስተምራል (ዘፍ 28፡ 12)፡፡ እንደ ቅዱስ ዮሐንስ ትምህርት ክርስቲያን የመጨረሻው ንጽሕና ላይ ደርሶ ከእግዚአብሔር ጋር በጸጋ ተዋሕዶ ለዘለዓለም ከመኖሩ በፊት ሠላሳ የሚሆኑ የብቃት ደረጃዎችን ማለፍ ያስፈልገዋል፡፡ ክርስቲያኑ እኒህን ሁሉ የሚያልፋቸው በእግዚአብሔር ጸጋ እና በብዙ መከራ እንደሆነ ይናገራል፡፡ ከእነዚህ ሠላሳ ደረጃዎች ሁለተኛው ከነገሮች መላቀቅ እንደሚገባ (“on detachment” – “επί αποκόλλησης”) የሚናገረው አንቀጽ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው “ዓለምን ወደ መጥላት የደረሰ ሰው ከመከራ አመለጠ፡፡ ዳሩ ግን ከሚታዩ ነገሮች ሁሉ ጋር የተጣበቀ ሰው ገና ከኀዘን አልተላቀቀም፡፡ የምንወደውን በማጣታችንስ እንዴት የማናዝን ልንሆን እንችላለን?” በማለት የተናገረው ከላይ ካነሳነው ሐሳብ ጋር የተስማማ ነው፡፡ በዚህ አባት ትምህርት ውስጥ ሰው ከነገሮች ጋር በመጣበቁ ምክንያት ለኀዘን እንደሚዳረግ በግልጽ ይናገራል፡፡
አንድ በሀያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የሚኖር ወጣት በጣም መብላት የሚፈልገው ምግብ ቢኖርና እርሱን ዐይቶ ነገር ግን እንዳሰበው ለመብላት ባይችል ከሚወደው የምግብ ዓነት ጋር በስሜት የተጣበቀ (የተቆራኘ) በመሆኑ ምክንያት የሚጎዳው የስሜት ጉዳት ይኖራል፡፡ የስሜት ጉዳቱ ትንሽ ቢሆን እንኳ ይህ ጠባይ በሰፋና በተደጋገመ ጊዜ በጾም እና በሌሎች ሥራዎች ከእግዚአብሔር ጋር በአምልኮት ለመገናኘት እጅጉን እየከበደውና ሕይወቱን እያጣ ይኖራል፡፡ ከዚህ አንጻር መብል፤ መጠጥ፤ ልዩ ልዩ ጨዋታዎች፤ ማኅበራዊ ሚዲያዎች፤ ቤተሰብ፤ ጓደኞች፤ እና ሌሎችም ነገሮች የእኛን ጥንቃቄ የሚሹ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ክርስቲያን ከእነዚህ ነገሮች ጋር በትክክል ካልተገናኘ እና መንፈሳዊ ሕይወቱን በሚጎዳ መልኩ ከእነዚህ ነገሮች ጋር ከተጣበቀ ክፋትን በመተው እግዚአብሔርን በፍጹም ልቡ ወደ መውደድ ማደግን ሊያገኝ አይችልም፡፡ በቀላል አገላለጽ ከላይ የተጠቀሱት ነገሮች ጋር ትክክለኛ እና ልከኛ የሆነ መልኩ ግንኙነት ሊኖረው ይገባል ማለታችን ነው፡፡
ሎጥ እና ቤተሰቡ ከልዑል እግዚአብሔር በታዘዙ መላእክት ከሰዶም እንዲወጡ ሲሆኑ፤ የተነገራቸው ትእዛዝ አንድ ብቻ ነበር፡፡ ይኸውም ከሰዶም ሲወጡ ወደ ኋላ ዞረው እንዳይመለከቱ ነበር፡፡ ሎጥ እንደታዘዘ አደረገ፤ የሎጥ ሚስት ግን ዞራ ወደ ሰዶም ተመለከተች፡፡ የሎጥ ሚስት ከሰዶም ቅጣት የዳነች ብትሆንም ወደ ኋላ በመመልከቷ ምክንያት እስከመጨረሻው ድረስ ድኅነቷን (መዳኗን) አላጸናችም፡፡ ክርስቲያንም ምንም እንኳን በክርስቶስ አምኖ በመጠመቁ ከፍዳ ከመርገም ቢድንም፤ በዓለም ላይ ሲኖር ራሱን ከነገሮች ካላላቀቀ ራሱን ለእግዚአብሔር በፍጹም ልብ ሆኖ ማቅረብ ስለማይችል ከሕይወት መንገድ የመውጣት አደጋ ላይ ይወድቃል፡፡
በጻድቁ አባታችን በአቡነ ተክለ ሃይማኖት ገድል ላይ በተደጋጋሚ ተመዝግቦ የምናገኘው አንድ ሁነት አለ፡፡ ይኸውም ጻድቁ በአባ በጸሎተ ሚካኤል እና በአባ ኢየሱስ ሞዐ ገዳማት በእያንዳንዳቸው ከ10 ዓመታት በላይ ከኖሩ በኋላ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከገዳማቱ ወጥተው እግዚአብሔር ወዳዘዛቸው ቦታ እንዲሄዱ ሲነገራቸው ያለምንም ማመንታት ፈቃደ እግዚአብሔርን ለመፈጸም እንደተነሱ እናያለን፡፡ ከ 10 ዓመታት በላይ ከሌሎች መነኮሳት ጋር በአንድነት እና በፍቅር መኖር በቀላሉ የሚታይ አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን ጻድቁ ከእኒያ መነኮሳት ጋር መኖራቸው ስለ እግዚአብሔር ብለው እንጂ ስለ ራሳቸው ብለው ባለመሆኑ፤ ተነስተው ወደ ሌላ ቦታ እንዲሄዱ ሲታዘዙ ያለምንም ማቅማማት ፈቃደ እግዚአብሔርን መፈጸማቸው መጽሐፈ ገድላቸው ያስተምረናል፡፡ ይህ ከነገሮች የመላቀቅ (Detachment) አንዱ ማሳያ ሆኖ ሊወሰድ ይችላል፡፡ የንጹሓን አባቶች የመጀመሪያም የመጨረሻም ፍላጎታቸውና ናፍቆታቸው ልዑል እግዚአብሔር ነው፡፡
ከላይ ያነሳናቸውን ነጥቦች ስናነሳ ሰው ለነገሮች ምንም ዓይነት ፍላጎት አይኑሩት፤ ፍላጎቱንም አያሳይ ማለታችን ነው? በፍጹም አይደለም፡፡ ነገር ግን ከፍላጎታችን ጽናት የተነሳ ከነገሮች ጋር በመጣበቅ (በመቆራኘት)፤ በዚህም የተፈጠርንበትን ዓላማ በመዘንጋት ከሕይወት እንዳንወጣ ነው እንጂ፡፡ ሕይወት ከሌላቸው ነገሮች ጋር ያለን ቁርኝት አለ፡፡ ከቤተሰብ፤ ከጓደኞች ከሌሎች ጋር ያለን አግባብ ያልሆነ ስሜት መጣበቅ አለ፡፡ ከራሳችን ጋር ያለን ከባድ መጣበቅ አለ፡፡ ይህ ደግሞ ከሁሉ ይልቅ አስቸጋሪው ነው፡፡ ይኸውም ከሰዎች ስለራሳችን መስማት የምንፈልገው መልካም ነገር፤ ከሌሎች ማግኘት የምንሻው ክብር እና የመሳሰሉትን የሚይዝ ነው፡፡ እንደ ኦርቶዶክሳውያን አባቶች ትምህርት ሰው ትልቁን መንፈሳዊ ውጊያ የሚዋጋው ውጫዊ በሆኑ ዐውደ ውጊያዎች አይደለም፡፡ ነገር ግን ሰው ራሱን ያልሆነውን አድርጎ እንዲስል ክብርን ለማግኘት ከሚያስመኘውና ብዙ ክፋቶችን እንዲያደርግ ከሚያነሳሳው ራስ ወዳድነቱ ጋር በልቡ ሜዳነት ይገጥመዋል፤ ይዋጋዋል፡፡ በእውነት ሆኖ ከተዋጋ በእግዚአብሔር ረድኤት ድል የሚነሳበት ጊዜ አለ፡፡ የሚሸነፍበት፤ ማንም ረዳት አጠገቡ የሌለ፤ እግዚአብሔርም እንደራቀው የሚሰማበትም ጊዜ አለ፡፡
እኒህ ሁሉ ግን አንድ ሰው ራሱን ከላይ ካነሳናቸው እንቅፋቶች ራሱን ለማላቀቅ ሲጥር የሚቀበላቸው የተባረኩ መከራዎች ናቸው፡፡ እንደ አባቶች ትምህርት ይህ የክርስትና ሕይወት መሠረታዊ ምንነት ነው፡፡ እርሱም ራስን (ፈቃድን) እየተዋጉ ለእግዚአብሔር ለመገዛት መታገል ነው፡፡ ከዚህም ሌላ ጥቂት የማይባሉ ክርስቲያኖች ጋር የሚታይ ሌላ ጉዳይም አለ፡፡ ይኸውም ከዚህ በፊት በአንድም ሆነ በሌላ መልኩ አገኘሁት ካሉት እግዚአብሔር ስጦታ (ልዩ የቸርነት ሥራዎች፤ መገለጥ፤ ራዕይ፤ … ) ጋር መጣበቅ ነው፡፡ እኒህ ስጦታዎች እውነት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተገኙ ቢሆኑ እንኳ፤ ክርስቲያን ራሱን ለስጦታዎቹ የማይገባ መሆኑን ዘወትር በማሰብ ራሱን ከስጦታዎቹ መለየት ያስፈልገዋል፡፡
ወደ ጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖት ታሪክ ዳግመኛ ስንመለስ አንድ የምናገኘው ቁምነገር አለ፡፡ ይኸውም ምንም እንኳ ጻድቁ በሕጻንነት ዕድሜያቸው ጀምሮ በእግዚአብሔር ጸጋ እና በረከት የሚኖሩ ቢሆኑም፤ ብዙ ገቢረ ተአምራት ቢደረግላቸውም በሥጋ ሕይወታቸው ፍጻሜ ላይ ለራሴ ምንም ፍሬ ሳላፈራ ኖርኩ ያሉትን እናስተውል፡፡ ነገር ግን በተቃራኒው ክርስቲያን ራሱን ከእግዚአብሔር ዘንድ ተሰጡኝ ካላቸው ስጦታዎች ጋር ራሱን ሳያላቅቅ (አቆራኝቶ) ቢኖር ያለ ጥርጥር በትዕቢት የሚወድቅ ይሆናል፡፡ እንዲያውም ምንም እንኳን ልዑል እግዚአብሔር በቸርነቱ ስጦታዎችን ቢሰጥም ሰው ከእነዚህ ስጦታዎች ጋር ያለውን ግንኙነት በጥንቃቄ ማየት ይገባዋል፡፡ በተቃራኒው ራሱን መከራ እና ሕማማት የሚገቡት አድርጎ ከልቡ የሚቆጥርና በአግባቡ የሚቀበላቸው ቢሆን ታላቁን ጸጋ ከልዑል እግዚአብሔር ዘንድ ይቀበላል፡፡
ቅዱስ ዮሐንስ ዘሰዋስው ሰው ዓለምን ካልተወ፤ ራሱንም ከነገሮች ካላላቀቀ በቀር አክሊልን ተቀብሎ ወደ ሙሽራው አዳራሽ እንደማይገባ ከላይ በጠቀስነው የቅዱሱ ድርሳን ላይ በግልጽ ይናገራል፡፡ እንግዲያውስ በጥልቅ የተቆራኘናቸው ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን አንድነት ሊጎዱ የሚችሉ ነገሮችን ምን ምን እንደሆኑ ማሰብ፤ ማሰላሰል ከእኛ ይጠበቃል፡፡ በልዑል እግዚአብሔር ረድኤት ምን ምን መሆናቸውን ከለየን በኋላ ከእነርሱ የምንላቀቅባቸውን ሥራዎች መሥራት ይገባናል፡፡ በክርስቶስ ጸጋ፤ በንጽሕት እናቱም ምልጃ ክፋትን እየተዋጋን ለመኖር ያብቃን፡፡ የቅዱስ አባት ዮሐንስ ዘሰዋስውን ማሳሰቢያ የጹሑፋችን መዝጊያ እንድርገው፡-
“ማንም ሰው ከምንም ነገር ጋር እንዳልተጣበቀ (እንዳልተቆራኘ) ቢያስብና፤ ነገር ግን ይህንኑ በማጣቱ ቢያዝን፤ እንግዲያውስ እርሱ ፈጽሞ ራሱን እያታለለ ነው”
ቀላል ብዬ ያስብኳቸው እንደ ቀልድ ግን መላቀቅ ያልቻልኳቸው ብዙ ነገሮች አሉ። እና ወንድሜ መልእክትህ ደውል ሆኖኛል አመስግናለሁ ቃለ ህይወት ያሰማልን።
Yigermal, eyandandwa Kal betam melekte alat. Yastemiral yatsnanalim. The ladder of Devine Ascent betam yemwedewe hiywet yemizera metsehaf newe, le manugawim huneta refernce yemihon, Chigirochin ametatachewin kene mefetehawe yemiyasreda dink metsehaf.
Kene gar uemetawera eskimeslege derese tsehufehe westa gebtwal.
Kale hiywet yasemalin, becherenetu yemaren.
ቃለ ህይወት ያሰማልን
“…እግዚአብሔርን ማመን ማለት ስለእግዚአብሔር ጥሩ ስሜት መስማት ሳይሆን እርሱን ከጊዜያዊ ፍላጎቶች ሁሉ ማስቀደም ፤ እርሱንም ብቸኛ ፍላጎት ማድረግ መሆኑ የታወቀ የተረዳ ነው።…”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
ከባድ ፈተና!ቃለ ሕይወትን ያሰማልን!
በእውነት ሆኖ ከተዋጋ በእግዚአብሔር ረድኤት ድል የሚነሳበት ጊዜ አለ፡፡ ጥዑም ነው ቃለ-ህይወት ያሰማልን!!!
THANK YOU.
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
ቃለህይወት ያሰማልን