ብዙዎቻችን ከቤተክርስቲያን የምንርቅበትን ወይም ከክርስትና የወጣንበትን ምክንያት ስንገልጽ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ አገልጋዮችን እንደምክንያት እንጠቅሳለን። የእናንተን አላውቅም እኔ ግን እንደዛ እል ነበር። እንደሚመስለኝ ብዙ ሰዎች ከጳጳሳቱ ጀምሮ እስከታች እስካሉት ዲያቆናት ማንነት እየጠቀሱ ምን ያህል አስመሳዮች እና ኃጢአተኞች እንደሆኑ በመናገር፣ ሁሉም ውሸታሞች ስለሆኑ ከክርስትና እንደራቁ ይናገራሉ።
እንዲህ የሚሉ ሰዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ የተጠቀሱ ቅዱሳንን ምን ያህል እንደሚያውቋቸው አላውቅም። ማወቅ ስል በእውነት ከምር ማወቅን ነው እንጂ በስም እና በታሪካቸው ማለቴ አይደለም። መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ቅዱሳንን እነሱ በነበሩበት ሰዓት አይቶ ወደ ቤተክርስቲያን የመጣ ክርስቲያን ፥ በርግጎ ነው ከቤተክርስቲያን የሚወጣው እና መቼም የማይመለሰው። ለምሳሌ እነዛ ቅዱሳን በዚህ ዘመን ያሉ ናቸው ብለን እንውሰድ።
ኖኅ የሚባል በዕድሜው ያረጀ ትሑት የእምነት ሰው እና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ የታወቀ አባት ነበር፤ ይሄ ሰው “ብዙ ሰዎችን አጥምቆ ክርስቲያን አድርጓል” ግን ምን ያደርጋል ጥቂት ሰዎች ደግሞ በወይን ጠጅ ሰክሮ ራቆቱን ሲንገዳገድ እና የሌሎች እምነት ተከታዮች አይተው ሲሳለቁ እና በክርስትናው ላይ ሲያሾፉ አየተው ፥ እርም ብለው ከቤተ ክርስቲያን ርቀዋል።
እና አንድ ሰው የአብርሃምን እምነት አይቶ ቤተ ክርስቲያን መጣ። ወዲያው ግን አብርሃም ምን ያህል ፈሪ እንደሆነ እና የራሱን ሕይወት ለማትረፍ ሚስቱን አሳልፎ እንደሰጠ ያያል። ከዛ ይሄ አስመሳይ ነው ብሎ፣ “እውነተኛ መስሎኝ እንጂ ሚስቱን እኅቴ እያለ የራሱን ሕይወት ለማትረፍ የሚሳሳ ፈሪ” ብሎ ከቤተ ክርስቲያን ይጠፋል።
አንዷ በቀደም መጥታ ደግሞ እንዲህ አለችኝ። “ይሄ ቤተ ክርስቲያን የጥቂት ብሔሮች ነው፣ የሰሜኖቹ ነው” አለችኝ። “ለምን?” ስላት ፥ ስለማርያም እየተንዘከዘከች ተናገረች። “ቆይ ፥ ቆይ ስለየትኛዋ ማርያም ነው የምትይው?” አልኳት ደንግጬ። “የታላቁ ነቢይ ሙሴ እህት ናታ፣ ከበሮ እያነሳች መዘመር የማይሰለቻት፣ እንደውም ባለፈው የመከራን ባሕር እግዚአብሔር ከፍሎ ሲያሻግረን የሷን መዝሙር አይደለ እንዴ የዘመርነው፤ ትዝ አይልህም ፥ ‘በክብር ከፍ ከፍ ብሎአልና ለእግዚአብሔር ዘምሩ፤ ፈረሱንና ፈረሰኛውን በባሕር ጣለ’ የሚለው መዝሙሯ” አለችኝ። “አዎ! አወኳት” ስላት ፥ “በማስረጃ እንዴት ዘረኛ እንደሆነች ፥ ወንድሟ ከሌላ ዘር በማግባቱ ቁም ስቅሉን እያሳየችው መሆኑን እና ሚስቱን ሲፓራን ማስለቅስ ልማዷ መሆኑን” ነገረችኝ። “እንደውም ወንድሟ ያ ካህኑ አሮንም የማርያምን ሀሳብ ደግፎ ቆሟል ነው የሚባለው” አለችኝ። እኔም ይሄን የጸና የዘር ደዌ ቤተክርስቲያን ላይ ያሉ አንዳንድ ሰዎች ላይ አይቼ ስለተከፋው ለዚች ልጅ ምን ብዬ እንደማጽናናት ግራ ገባኝ። ሌላ ጊዜ ተገናኝተን ለማውራት ቀጠሮ ይዘን ብንለያይም ፥ እሷ ግን “የሷ ዘር ሰዎች በቅርብ ያቋቋሙት ሲኖዶስን መቀላቀሏን እና ከኔ ጋር መነጋገር አስፈላጊ እንዳልሆነ” ቴክስት ላከችልኝ።
ሌላው ደግሞ ሳምሶንን ዓይቶ፣ በጸጉሩ ማማር ተማርኮ፣ በጀግንነቱ እና ስለቤተክርስቲያን (እስራኤል) ያለው ቅናት አስደምሞት ቤተ ክርስቲያን መምጣት ይጀምራል። ይሄ ሰው ለሚስቱ ታማኝ ስለሆነ የሚዘሙት ሰው ሁሉ ይጠየፋል። ከዛ ሳምሶንን ሲዘሙት እና ከብዙ ሴቶች ጋር ያልተገባ ድርጊት ሲሰራ ያየዋል፣ ይሄ ብቻ ሳይሆን ለሴት ሲል ያ አስደማሚ ጸጉሩን ተላጭቶ ይመለከተዋል። “ሁሉ ነገር ውሸት ነው፣ አታላዮች እና አስመሳዮች ናቸው፣ እዛ የተሰበሰቡት ሁሉ ሌቦች ናቸው!” እያለ ቤተክርስቲያን ካሉ ሰዎች ይልቅ በዓለም ያሉ ሰዎች መልካም እንደሆኑ እየተናገረ ከቤተክርስቲያን ይጠፋል።
የቅርብ ጓደኛዬ ደግሞ በድምጹ ማማር፣ በበገና አደራደሩ፣ በመዝሙሮቹ ግጥም ጥንካሬ እና ውበት፣ ለክብሩ ሳይጨነቅ እግዚአብሔርን ጨርቁን ጥሎ ያመለከውን ዳዊትን ዓይቶ ቤተክርስቲያን ይመጣል፣ ሰንበት ትምህርት ቤት እየመጣ የዳዊትን መዝሙሮች ይከታተላል፣ ዳዊት አለ በተባለበት ጉባኤ ሁሉ ይገኛል። ከዛ ከእለታት አንድ ቀን ዳዊትን ከኦርዮ ሚስት ቤርሳቤህ ጋር ሲማግጥ ያየዋል፤ የሚያየውን ማመን ተሳነው። ያ ዳዊት፣ ያ በበገናው አጋንንት ሲያሶጣ ያየው ዳዊት፣ ያ ጨርቁን ጥሎ እግዚአብሔርን የሚያመልከው ዳዊት፣ ያ ጀግናው ዳዊት ሲልከሰከስ ዓየው፤ ይሄን ለማስታረቅ ተቸግሮ እና በግራ መጋባት ውስጥ እያለ ከሁነኛ ወዳጁ “ዳዊት ቤርሳቤህን እንዳስረገዘ እና ኦርዮን ሰምቶ እንዳያዋርደው ኦርዮንን ማስገደሉን” ይሰማል። ክሩን በጠሰ። ጾሙን አቆመ። ነጠላውን ወረወረ። ድሮም ሲሉኝ አልሰማ ብዬ እንጂ ሁሉም አጭበርባሪ እና አታላይ ናቸው አለ። ሁለተኛ ቤተክርስቲያን ላይሄድ እና መስቀል ላይሳለም ማለ። “ክርስትና ከነበረም ድሮ ነው። ሁሉም ከክርስቶስ ጋር ወይም በዛ ዘመን አብቅቶለታል” ብሎ ደመደመ።
አንዲት ሴት ደግሞ አስቴርን ተመልክታ መጣች። ይሄን የመሰለ ውበት እና እውቀት ኖሯት ከቤተክርስቲያን አለመራቋ እና በኪነጥበብ ክፍል ውስጥ ያላትን አገልግሎት ተመልክታ እሷም ቤተክርስቲያን ለመቅረት ወሰነች። አስቴር በዘመኑ የነበረውን ኃያል ጄኔራል አገባች። ሰውዬው ክርስቲያን አልነበረም። በዛ ላይ ክርስቲያን የሚጠሉ ሰዎችን እንደ ሃማ ያሉትን ነው በዙሪያው የሰበሰበው። ይሄ ግራ ገባት። ድሮ የምታቃት አስቴር አልሆንልሽ አላት። ስለዚህ ቤተክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች ሁሉ የስጋ ምኞታቸው እስከሚፈጸም እዛ ያሉ መስሎ ታያት። ቀስ እያለች ቤተክርስቲያን መምጣቷን ቀነሰች። ለሷም ለአስቴርም ወዳጅ የነበረች ልጅ “አስቴር ጄኔራሉ አብያተክርስቲያናት እንዲቃጠሉ ማዘዙን ሰምታ ምንም አለመናገሯ ሳያንስ ወንድሟ አስልኮባት ራሱ ጄኔራሉን ባሏን ተው ብላ ለመገሰጽ እያመነታች” መሆኑን ስተሰማ ፥ ከቤተክርስቲያን ቀረች ቀረች።
አሁን በቅርቡ ደግሞ ጴጥሮስ የተባለው የቤተክርስቲያን መሪ እና ቤተክርስቲያኒቷ አለኝ የምትለው ታማኝ፣ ፈጣን አቧቷ ባለፈው በሀገር ደረጃ በመንግስት አቀነባባሪነት ቤተክርስቲያንን ለማሳደድ፣ ከተቻለም ለማጥፋት በተነሳው መከራ ሰዓት እና ቤተክርስቲያኒቷን ቁም ስቅሏን መንግስት ሲያሳያት ፥ በአደባባይ “መንግስት ምንም ኣላደረገም፣ እኔ ምስክር ነኝ ፥ ችግሩ እንደውም ከቤተክርስቲያኒቱ ነው” ብሎ መናገሩ ቀላል የማይባሉ ክርስቲያኖችን አሳዝኗል። እሱ ብቻ ሳይሆን አንዳንዶች “አባ ጴጥሮስ እንደዛ እያሉ እኛ የማን ቤት ነን ቤተክርስቲያንን የምንጠብቀው እና መንግስት ጋር እሰጣ ገባ የምንገባው” ብለው ከቤተክርስቲያን ከቶውንም ርቀዋል። በርግጥ ጥቂት ሰዎች “አባ ጴጥሮስ በተናገሩት ነገር እጅጉን ተጸጽተው ማልቀሳቸውን አይተው” ተናግረው ነበር። ግን ሰው የተናገሩትን በአደባባይ ስላየ እና መጸጸታቸውን በይፋ ስላልተመለከተ ወሬውን አላመነውም። እኔም ራሱ አባ ጴጥሮስ እንደዛ ማድረጋቸው ደብሮኝ እርም ክርስቲያን ብያለው።
የሚገርመው እኮ ከአንዱ ጳጳስ ውጪ ሁሉም፣ በዛ መንግስት በቤተ ክርስቲያን ላይ ግፍ በሚፈጽምበት ወቅት ፥ ከክርስቲያኖች ጋር ተገኝቶ የቤተ ክርስቲያንን መከራ የተካፈለ የለም። አባ ናትናኤል ብትል፣ አባ ፊሊጶስ ብትል፣ አባ ያዕብቆ ብትል፣ በርተለሜዎስ፣ አባ እንድርያስ ሁሉም እኮ ነው ሸሽተው የተደበቁት። ያ ምስኪን ዝምተኛ አባት፣ አባ ዮሐንስ ብቻ ናቸው እስከመጨረሻው ከምዕመናን ጋር ጸንተው የታዩት።
ይሄ እንግዲህ በምናብ መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያሉ ቅዱሳን እና ሐዋርያት በዛሬ ዘመን ቢኖሩ በማለት እና ለሰሯቸው ኃጢአቶች የኛ ግብረ መልስ ምን ሊሆን እንደሚችል በማሳየት የተጻፈ ነው።
ጥቂት ነገር ልጨምር። የቤተ ክርስቲያን ራስ ክርስቶስ ነው ፥ ከቶ የማይጥለን፣ ከቶ ታምነንበት አንገታችንን የማያስደፋን እርሱ ብቻ ነው። ወደ ቤተ ክርስቲያን የምትመጡ ሰዎች ሆይ ፈጥናችሁ ይሄን የቤተ ክርስቲያን ራስ ተመልከቱ። ሁለተኛው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሦስት ጊዜ ለካደው ቅዱስ ጴጥሮስ የመንግስቱን ቁልፍ የሰጠ አምላክ ነው(ቁልፍ በጣም ለታማኝ ሰው፣ ከዚህ ቀደም ምንም ዓይነት የክህደት ታሪክ ለሌለው ሰው የሚሰጥ ነበር)። ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ያሉ ሰዎች አስመሳዮች ናቸው ካላችሁ በጣም ልክ ናችሁ ምክንያቱም እኔም ነኝ። የመጣነው ማስመስል ስለደከመን ነው። አንድ ቀን ፈጽሞ ከዚህ በሽታ ወደሚፈውሰን የቤተ ክርስቲያን ራስ ወደ ሆነው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለመጣን ግን ፍጹም ደስተኞች ነን። በሽተኞች ሆይ ኑ ፥ እሱም በውጋት በሽታ የሚሰቃየውን፣ ለቤተ ክርስቲያን ያለውን ንዴት መቆጣጠር አቅጦት እስጢፋኖስ የሚባል ምስኪን ወጣትን በድንጋይ አሶግሮ ያስገደለውን ፥ በልብሱ ጥላ ግን በሽተኞችን የሚፈውሰውን የክርስቶስ አገልጋይ ቅዱስ ጳውሎስን በቤተ ክርስቲያን ታገኙታላችሁ።
ቃለህይወትን ያሰማልን
በእውነት ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
በመጀመሪያ ቃለ ህይወት ያሰማልን ስለእዉነት ሁል ጊዜ ለኔም ጥያቄ የሚፈጥርብኝን ጉዳይ ነው ያነሳሀዉ እኔም በዛ መንገድ አልፌ ነበር ይሔንን ምክንያት አድርጌ መራቅ, አንዳንዴ ግን እኛ የምንሔድበትን ምክንያት እንጂ የማናዉቀዉ የአገልጋዮች ድክመቶችን ባንመለከት መልካም ነዉ።
የሕይወትን ቃል ያሰማልን! ግሩም እይታ ነው::
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን
እግዚዐብሔር የምናስተውል ልቦና ይስጠን🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን!
ድንቅ የሆነ እይታና አፃፃፍ ነው ። የአገልግሎት ዘመንህን ይባርክልህ
ቃለህይወትን ያሰማልን!!!
ማጠቃለያ ሃሳቡን በጣም በሰፊዉ ጠበቄዉ ነበር
ቢሆንም መልካም ነበር።
በእውነት ቃለ ህይወትን ያሰማልን ።
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለህይወት ያሰማህ አሜን ግን እኔ ስለ እኔ ሀሳብ እራሱ በደንብ ጠንቅቄ ማወቅ ተ ስኖኛል ግን የዛን ቀን ምን እንደነካኝ አላውቀውም መመረጥ የለበትም እያልክ ስጮህ ነበር ለዛውም እየተሳደብኩ እግዚአብሔር ይቅር ይበለን አሁን መዳን መጀመሪያ ከራስ እንደሚጀምር ተረድቻለሁ አመሰግናለሁ
ቃለህይወትን ያሰማልን::
እውነት ብለሃል ወንድማችን:: ቤተክርስቲያን የምንሄደው ካህኑን ወይም መምህሩን ወይም ሌላ አገልጋይ ሰው ብለን ወይም አይተን ሳይሆን እግዚአብሔርን ለማምለክና ለራሳችን በረከትና የኃጢያት ሥርየት ለማግኘት መሆን አለበት::
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
እጅግ ልብ የሚነካ ድንቅ ትምህርት ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ቃለህይወት አሰማልን
ድንቅ አስተውሎት ነው።
እንግዲህ ምን እንላለን፣ ብዕርህን እግዚአብሔር ያበርታልህ ነው እንጂ።
በእውነት ቃለ ሕይወት ያሰማልን! ውብ ስብከት እና ውብ ምናባዊ ድርሰት ሲዋሀዱ እንዲህ ዘመናት የማይሽሩትን ትምህርት ለትውልድ ያስቀምጣሉ። መቼም ቢሆን አልረሳውም!