ከቅዱሳን ፓትርያርኮችና ከብፁዓን አበው ጋር የተደረጉ ልዩ ልዩ ታሪካዊ የቃለ መጠይቆችን ስብስብ ክፍል ሁለት

ጥያቄ:- በግል ሕይወትዎ እመቤታችን ያደረገችልዎት ተአምር አለ?

ብፁዕ አቡነ ሰላማ :- አንድ ጊዜ ወደ እመቤታችን ቤተ ክርስቲያን ልናከብር እንሔዳለን:: ምንጭ ዳር ተቀመጥን:: ላይ ገደል አለ እልም ያለ ገደል ነው:: ከዚያ የድንጋይ ናዳ እየተወረወረ ወደ እኛ ይመጣል:: መጥቶ ከኋላዬ ሲደርስ ዝም ብሎ ቆመ:: ሰዎች ደነገጡ:: ብድግ ስንል ሳለ ተመልሶ ሔደ ይህ የተደረገልን አንዱ ተአምር ነው::

ሁለተኛ ደግሞ አክሱም ፍልሰታ ሚካኤል ላስቀድስ እየሔድሁ እያለ ሾፌሩ መኪናውን ሳያጠፋው   ቀርቶ ወርዶ እኔ ውስጥ እንዳለሁ መኪናው ወደኋላ ሔደ:: መኪናዋ ጤፍ ረግጣ በቆሎ ረግጣ ተንከባልላ ከተማ ገባች:: እኔ ግን ሳላውቀው አንድ ወንድና አንዲት ሴት ይዘው ከመኪናው ውስጥ አወጡኝ:: ቅዱስ ሚካኤልና እመቤታችን ናቸው:: ሾፌሩ ሞተዋል ብሎ ሲጮህ እኔ ኪዳን እያደረስሁ ነበር::

አንድ ቦታ ደግሞ ታቦት እናስገባለን ብለን ስንሔድ አንድ የተማረ ሰው ነፍሰ ገዳዮች ቀጥሮ ወደ ገደል እንዲጨምሩኝ አስቀምጦ ነበር:: እኔ በዚያ ሳልፍ የተቀመጠበት ድንጋይ ተንዶ ሞተ:

እመቤታችን አሁንም ድረስ በገሐድ ነው የምትረዳኝ:: እርስዋ የለመንዋትን የማትነሣ የነገርዋትን የማትረሳ ናት:: …. ክፉ ሰዎች ሲነሡብኝ ይግባኝ ለሥላሴ ይግባኝ ለእመቤታችን ነው የምለው:: 

ብፁዕ አቡነ ሰላማ

ከምክሖን ለደናግል ሚድያ ጋር

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለ ሃይማኖት እግዚአብሔር የጠራቸው ፓትርያርክ ነበሩ:: ክፉውን ጊዜ በፈሊጥ አልፈውት ነበር:: በደርግ መንግሥት ብዙ ጫና ሲደርስባቸው በትዕግሥት አሳልፈውት ነበር:: መንግሥት የሥላሴን በር በዘጋበት ጊዜ ሰዎች ሲጮኹ እርሳቸው “ቤተ ክርስቲያኑ ጨርሶ አልተዘጋም:: ባለው በር ግቡበት:: አካኪ ዘራፍ ብንል ጨርሶ ይጣሉናል” ይሉ ነበር::

ወደ መስኮብ ሀገር በሔዱ ጊዜም የመስኮቡ ፓትርያርክ መክረዋቸው ነበር:: “አባታችን እኛ በመስኮብ ለውጥ ሲሆን አይሆንም ብለን ተቃውመን ብዙ ቅርሶች አጥተናል:: ብዙ አባቶች አጥተናል:: እነርሱን ማውገዝ ትተው ዝም ብለው ትምህርትዎን ያስተምሩ” ብለው መክረው ስድስት ላንድሮቨሮች “ይህንን በቤተ ክርስቲያንዋ ስም ለመንግሥት ሥጡ:: ቤተ ክርስቲያንዋን እንዳይጣሉ” ብለው ሠጥተዋቸዋል:: በዚህ ምክንያት መንግሥቱ ኃይለ ማርያም እርሳቸውን በልዩ ዓይን መንከባከብ ጀመረ:: ሲታመሙም ውጪ ልከን እናሳክማቸዋለን ይል ነበር:: ያንን የጨለማ ጊዜ በፈሊጥ ነው ያሳለፉት::

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ እውቀታቸውም ምናኔያቸውም ለቤተ ክርስቲያንም የነበራቸው ሃሳብ የተለየ ነበረ:: አንድ ጊዜ ሰዎች ያላሉትን ብለዋል ብለው ሰዎች ከመንግሥቱ ኃይለ ማርያም ጋር አጋጭተዋቸው ነበረ:: “በሐዋርያዊ ድርጅት እና በትንሣኤ ዘጉባኤ ለእርዳታ ከውጪ የሚመጣውን ሀብት ሲኖዶስ እያወቀው ይምጣ” ብለው አንድ ጽሑፍ ጽፈው ነበር:: ሰዎች ይህንን ለውጠው “ደርግ ለሚወስደው ገንዘብ ለምን እርዳታ ትሠጣላችሁ?” ብለው ለውጪዎቹ ጽፈዋል ብለው አጋጩአቸው:: መንግስቱ ኃይለ ማርያም ሲጠይቃቸው የጻፉትን ይዘው ሔዱና አሳዩት:: የፓትርያርኩ እንደራሴ ነበሩ ያንን ሥራ ትተው ሔዱ:: መናኝ ናቸው ዝዋይ ሆነው ብዙ የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን አስተምረዋል:: ብዙ መምህራንን አፍርተዋል::

ብፁዕ አቡነ ቄርሎስ

ከEOTC ጋር ያደረጉት ታሪክን ወደኋላ የሚያስቃኝ ውይይት

ከሁሉ ደግሞ የሚያሳዝነው ሠዓሊዎቻችን የተሻሻልን መስሏቸውም ይሁን ባለማወቅ እንጃ ከፈረንጆች ፎቶፍራፍ እየቀዱ ሥዕል መሣል ጀምረዋል፡፡ ምነው! ወርቁ ቢጠፋ ሚዛኑ ይጥፋ! እንደሚባልወ ሁሉ የብዙ ሠዓሊዎች አገር ናት ኢትዮጵያ፤ ያውም እንደዛሬው ሁሉ ተዘጋጅቶ በማይገኝበት ዘመን አባቶቻችን ቅጠል ቀቅለውና ደቁሰው ቀለም አውጥተው የሣሏቸውን ሥዕሎች አያዩም ወይ? ብራና ፍቀው ቀለም በጥብጠው የሣሏቸው ሐረጎችስ ወዴት ደረሱ?

በመሠረቱ ሥዕል የሚሣለው ለሀገሩ ሕዝብ በሚገባው ሁኔታ ነው፤ ሥዕል ራሱ ቋንቋ ነውና፡፡ ስለዚህ የኢትዮጵያ ሠአሊዎች ጌታን በሊቀ ካህናትነት መንበሩ እንዳለ አድርገው እመቤታችንን በዙፋን አስቀምጠው መላእክትን የኢትዮጵያ አርበኞች የሚለብሱትን ልብስ ቀሚስና የወርቅ ለምድ አልብሰው ሰማዕታትን በፈረስ ላይ እንዳሉ አድርገው በአርበኛ ገጽታ በሰማዕትነት ሲሞቱም ከነደማቸው የተገደሉበት መሣሪያ ሳይቀር አብረው ያስቀምጡ ነበር፡፡ ይህ ነው እንግዲህ ለተተኪው ትውልድ ማስተማሪያ የሚሆነው፡፡

ዘመናዊ ሥዕል መሳል ራሱን አስችሎ ነው፡፡ መደባለቅ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ ሠሪውን አያስመሰግንም፤ ቤተ ክርስቲያንንም ይጎዳል፡፡

የዚህች አነስተኛ ጽሑፍ ዓላማ የቤተ ክርስቲያናችንን ቅርሶች እንድናውቅና እንድንጠብቅ፤ ሠዓሊዎቻችንም ሥዕለ ቅዱሳንን ሲሥሉ የነበረበትን ትውፊት እንዳይለወጡ ለመምከር ነው፡፡ ያለዚያ ግን እጀ ሰባራ ይሆናሉ፡፡

የልብሰ ተክህኖ አሰፋፍና ቀለሞቻቸው በየጊዜው እየተለዋወጡ ነው፤ ካህናት ሲቀድሱ በራሶቻቸው ላይ የሚቀዳጅዋቸው ኩፋሮችም የምዕራቡን ጤያራ መስለው ስለሚያስደነግጡ ብዙ የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ወገኖች እየታዘቡን ነው፡፡

ባጠቃላይ ምእመናኑም ሆኑ ካህናቱ ለቤተ ክርስቲያናቸው ሀብት የባለቤትነት ኃላፊነት ስላለባቸው ካህቱ የንዋየ ቅድሳት መልክና ቅርጽ ለይተው ተረድተው ለምእመናን መመሪያ ይስጡ፡፡ ገንዘብ አውጥተው የሚገዟቸውን ንዋየ ቅድሳት ከመግዛታቸው በፊት ዕቃውን በቀለሙም ሆነ በቅርጹ በቤተ ክርስቲያናችን የሚታወቅ መሆን አለመሆኑን ከካህናት መጠየቅና መረዳት ደግሞ የምእመናን ድርሻ ነው፡፡ ይህ ካልሆነ ግን በቤተ ክርስቲያናችን ችግር ይፈጠራል፡፡

አሁን በቅርቡ በናዝሬት ቅድስት ማርያም ቤተ ክርስቲያን ተገኝቼ እንዳየሁት ስማቸውን ያልያዝሁት አንድ የትሩፋት ሰው አሜሪካን አገር ልጃቸውን ለማሳከም ሂደው ሲመለሱ የገንዘቡን ልክ ባላውቀውም ብዙ ገንዘብ አውጥተው ባለ ሐር ጥብጣብ ከከፋይ የተሠራ የአምስት ልዑካን ልብስ ገዝተው ስእለት አስገብተዋል፡፡ ግን የልብሰ ተክህኖው ቅርጽ የአንገሊካን ቤተ ክርስቲያን ካህናት የሚለብሱት ነው፡፡ ወዲያው እንዳሳዩኝም በገንዘባቸው መክሰር አዝኜ ስእለትዎን እግዚአብሔር ተቀብሎታል ግን ይኽ በኛ ቤተ ክርስቲያን ለአገልግሎት የማይውል ነው ብየ ለካህናቱም ነገርኳቸው፡፡ ወዲያውም ታቦቱ ሲወጣ ዲያቆናቱ ለመልበስ ሲሻሙበት አየሁ፤ አዲስ ነገር ነውና፡፡

እንዲህ ያለው ችግር የሚፈጠረው የራስን ይዞታ ካለማወቅ ስለሆነ በዚህ ነገር ካህናቱና ምእመናኑ ሊያተኩሩበት ይገባል፡፡

ሠዓሊዎቻችንም በጥንት ግዜ የተሣሉ ሥዕሎች ወዳሉበት ቤተ ክርስቲያን እየዞሩ እያዩ በጥንቃቄ ቢሥሏቸው ለሀገራችንም ለቤተ ክርስቲያናችንም ማንነት ምልክት ይሆናሉ፡፡ የዛሬውን አያድርገውና በቀድሞ ጊዜ ሥዕለ ቅዱሳንን የሣሉ አባቶቻችን በቀለሙ ውስጥ እንባቸውን እየቀላቀሉ በፍርሃትና በሱባኤ ነበር፤ እንዲህም ስለሆነ የሠሩትም ያምር ነበር፡፡ የዚያን ጊዜውንና የአሁኑን ስናስተያየው የፊተኛው በጣም በልጦ የምናየው በሌላ ምክንያት አይደለም፤ የዚያን ግዜው እግዚአብሔርን በመፍራት፣ በመጨነቅ፣ በመጠበብ ሲሆን በዛሬው ግን በድፍረት ብቻ ስለሆነ ነው፡፡

ብፁዕ አቡነ ጎርጎርዮስ ካልዕ

ዜና ቤተ ክርስቲያን፣ 41ኛ ዓመት ቁ.106 እና 107፣ 1979 ዓ.ም

Share your love

7 አስተያየቶች

  1. እግዚአብሔር ፡ ይስጥልን ፡ ብዙ ፡ ነገርን ፡ እንድማርበት ፡ ስላደረጋችሁኝ።

  2. እጅግ አሰተማሪ የሆነ መልዕክት ነው እያስተላለፋቹ ያላቹሁት እግዝአብሔር ያበርታቹ።

  3. አባታችን ትክክለኛ መልእክት ነዉ ያስተላለፉት እራሳችንን እድንታዘብ እና እድናስተካክል ይረዳናል ብዬ አስባለው ለቤተክርስቲያን መሰናክል የሆነባት የኛው የዕውቀት ማነስ ነውና።

    • የመጨረሻው ደግሞ በድምፅ ቀርቦ ብዙ ሰው ጋር ቢደርስ አሪፍ ነበር የማንበብ በሀላ እየቀነሰ ስለሆነ እላለሁ

  4. በጣም ደስ ይላል እግዚአብሔር ያክብርልን ትንሽ ሰፋ ቢል ደግሞ ጥሩ ነበር ።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *