ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ:- ለስድስት ዓመታት ተኩል ወኅኒ ቤት ታስሬ ስለቀቅ ለአንድ ዓመት ያክል በቁም እስረኝነት ከቤቴ እንዳልወጣ መንግሥት አዝዞ ነበር:: ስለዚህ ወደ ደርግ መንግሥት እንዲህ ብዬ አመለከትሁ “አሁን ተፈትቼያለሁ:: ወደነበርኩበት ሀገር ሔጄ ትምህርቴን እንድጨርስና ሀገሬን እንዳገለግል ፍቀዱልኝ:: ይህን የማትፈቅዱ ከሆነ ደግሞ ወደ ወኅኒ ቤት መልሱኝ:: ወኅኒ ቤት ውስጥ ሳስተምራቸው የነበሩ ምእመናን ስላሉ ሔጄ ላገልግላቸው” አልኩኝ::
ተፈቀደልኝ:: ይሆናል ብዬ ባልጠበቅሁት ሁኔታ ወደ ውጪ ሀገር እንድሔድ ተፈቀደልኝ:: በዚያም ሔጄ ትምህርቴን ጨረስሁ:: በየል ዩኒቨርስቲ ዲቪኒቲ ስኩል የመጀመሪያውን ዲግሪዬን አገኘሁ:: ከዚያም በፕሪንስተን ፒ ኤች ዲዬን ለመሥራት ሔድሁ::
ለዓሥር ዓመታት ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ቴዎፍሎስ እስከጠሩኝ ጊዜ ድረስ ለዐሥር ዓመታት በስደት ቆየሁ:: ኢትዮጵያ በጥልቁ የልቤ ክፍል ውስጥ ነበረች:: በልቤ ውስጥ ሌላ ምን ሊኖር ይችላል? ምክንያቱም ከኢትዮጵያ ውጪ እኔ ምንም ነኝ:: ምክንያቱም ኢትዮጵያዊ ነኝ:: ሕይወቴ ፣ መከበሬ ፣ መደመጤ ወይም ማንኛውም ሌሎች የሚያሳዩኝ ነገር ሁሉ ኢትዮጵያዊ በመሆኔ የተገኘ ነው::
ኢትዮጵያዊ ማንነቴን ልለውጠው አልችልም::
ስለዚህ ሕይወቴ የኢትዮጵያ ሕይወት ነበረ::
ኢትዮጵያን ለማገዝ በእኔ የሚሆን ነግር ባደርገው እወድ ነበር:: ቢያንስ ግን ላደርገው የምችለው በሔድሁበት ሁሉ ኢትዮጵያዊ መሆን ነው::
ወደነበርሁበት አሜሪካን ሀገር ብዙ ኢትዮጵያውያን ያለ ፍላጎታቸው ተሰድደው ነበር:: በዚህ የተነሣ በእንግድነት በመጡበት ሀገር ለመኖር ዝግጁ አልነበሩም:: በዚህ የተነሣ ጠፍተው ነበር:: በቋንቋቸው የሚያናግራቸው ሰው ያስፈልጋቸው ነበር :: ሰብሳቢም ይሹ ነበር:: ስለዚህ አብያተ ክርስቲያናትን አቋቋምኩ:: በየሳምንቱም አስተምር ነበር:: የሚመጡትንም ሰዎች ተጨማሪ ሰው ይዘው እንዲመጡ ሁልጊዜ እናገር ነበር:: ወጣቶቹም የተረጋጋ ሕይወት እንዲኖራቸው ለማድረግ እሞክር ነበር:: በዚህ ምክንያት በሀገራቸው ያሉያህል ይሰማቸው ነበር:: ጋብቻቸውን የሚፈጽሙ ሰዎችንም በሀገራቸው ወግ እንድራቸው ነበር::
በአሜሪካን ላሉ ምእመናን እንዲህ እላቸው ነበር:: “በዚህ ሀገር እጅግ ስኬታማ ብትሆኑና ለመቶ ዓመታት ብትኖሩ እንኳን ከመቶ ዓመታት በኋላም የሀገሩ ሰዎች “ሀገራችሁ የት ነው?” ብለው ይጠይቋችኋል:: ይህ የሚያሳምም ጥያቄ ነው:: ለዚህ ሀገርንና ባሕልን ማወቅ የሚያኮራ እንጂ የሚያሳፍር አይደለም::
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ
ከMEET ETV ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ የተወሰደ
ጥያቄ:- የሰርክ ጉባኤን ያስጀመሩት እርስዎ ነዎት ይባላል እውነት ነው?
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል:- አዎን እውነት ነው:: የኢየሩሳሌም ሊቀ ጳጳስ ሆኜ እስከሔድሁበት ጊዜ የምኖረው ልደታ አካባቢ ነበረ:: ፍልሰታ ላይ ታዲያ ሌሊት ሰዓታትና ቀን ቅዳሴ ነበረ:: እኔ ማታ ማታ ጸሎት አደርግ ነበር:: ፍልሰታ በገባች በሁለተኛው ቀን መንፈስ “ለምን ማታ ማታ ለሕዝቡ የሰርክ ጸሎት አትጀምርም?” እያለ በውስጤ ይነግረኝ ጀመር:: አንዱን ዲያቆን ሒድና ከቤቴ ጡሩምባ አምጣልኝ አልኩት:: ድምፅ ማጉሊያ ነበረኝ እሱን አመጣልኝ:: አሁንም አለኝ:: ከዚያም ሰዎች እንዲመጡ ጥሩምባ መንፋት ጀመርሁ:: “እንደምን ዋላችሁ? እንደምን ዋላችሁ? እንደምን ዋላችሁ?
ከዛሬ ጀምሮ ትምህርት አለ እንማራለን:: ፍልሰታው የትምህርትም ጊዜ ነውና” ብዬ ተናገርኩኝ:: አባቶችም ደስ አላቸው:: ጾሙን በትምህርት ጨረስነው:: ከዚያ “ሆይ ጉድ” እየተባለ ተስፋፋ::
በልደታ የማታ ትምህርት ተጀመረ:: ከዚያ በተክለ ሃይማኖት በጊዮርጊስ እየጠራሁ ማስተማር ጀመርሁ:: እያለ በሁሉም ተስፋፋ::
ጥያቄ:- ገዳማት በከተማ ውስጥ ይመመረታሉ:: ተገቢ ነው ይላሉ?
ምንኩስና በከተማም ሊኖር የሚችል ሕይወት ነው:: ነገር ግን ምን ዓይነት ከተማ ነው? የሚለው ጥያቄ ወሳኝ ነው:: ወሮበላ ከተማ ከሆነ እውነት ነው አይሆንም:: ምናምንቴ ምናምንቴ ያለበት ከተማ ከሆነ አይሆንም:: በስመ ከተማ ግን ብዙ ቅዱሳን አሉ:: ብዙ ትምህርት ቤት አለ:: ሁሉም ትምህርት ቤት ጫካ አይደለም::
እንደ ዋልድባ ባለጫካ የምንኩስና ሕይወት የሚኖሩ እንዳሉ ሁሉ እንዲሁም በከተማ ቅርብ ሆነው እንደዚያ የሚኖሩ አሉ:: ከድሮ ጀምሮ በግብፅ ሁለት ዓይነት ምንኩስና ነበረ:: አንደኛው የከተማ ትልልቅ ገዳማት ነበሩ:: ሆኖም ለከተማ ቅርብ ቢሆኑም የታጠሩ ናቸው:: ጫካ ውስጥም ነበሩ:: በዋሻም ነበሩ:: ለየብቻ በየዋሻው መሆን የመጀመሪያው ሥርዓተ ጳኩሚስ ነው:: በማኅበር ሆኖ መጻሕፍት እያነበቡ በጋራ የሚኖሩበት ምንኩስና ደግሞ ሥርዓተ ባስልዮስ ይባላል:: እርሱ በኋላ ቢመጣም ያሸነፈው ሥርዓት ነው:: ጫካ ውስጥ ተነጥሎ መኖር አውሬነት እንዳይሆን ሰዎች ባሉበት አካባቢ ይሁን ይላል:: እኛ ጋር የሚበዙት ገዳማት ሥርዓት ጳኩሚስን ይከተላሉ:: አሁን ግልፅ ያልሆነ ሥርዓት ይታያል:: ከተሜነትም ያለባቸው ያልታጠሩ ገዳማት ይታያሉ::
ብፁዕ አቡነ ገብርኤል
ከመጨረሻ ቃለ መጠይቃቸው የተወሰደ
ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ:- ወደ ጃማይካ የላኩኝ ፓትርያርኩ ብቻ አልነበሩም:: አፄ ኃይለ ሥላሴም ጭምር ናቸው:: እንደ አምላክ የሚያያቸውን ማኅበረሰብ ወንጌል እንዳስተምር የላኩኝ ራሳቸው ናቸው:: እርሳቸው ባይልኩኝ ኖሮ የጃማይካ ሕዝብም አይቀበለኝም ነበር:: ስለዚህ የራስተፈሪያውያን ማኅበረሰብ ቤተክርስቲያንን ለመቀበላቸው ትልቁ መሣሪያ የሆኑን ንጉሡ ናቸው::
ራስተፈሪያውያን ጸጉራቸውን በማሳደጋቸው ላይ ምንም ተቃውሞ አልነበረኝም:: ሰው በገፅታው ምክንያት ሊወገዝ ይገባል ብዬም አላምንም:: በሒደት ግን አባ ማንደፍሮ (የምንኩስና ስሜ) ራስተፈሪያን አባት ነው ማለት ጀመሩ:: ጸጉራቸውን እንዲህ አድርገው ሥራ ሊሠሩ እንደማይችሉ እነግራቸው ነበር:: አብዛኞቹ ግን አፍሪካ ስንሔድ እንሠራለን ይሉ ነበር:: ቀስ በቀስ ወደ ሥራው ዓለም አስገባሁዋቸው::
ቦብ ማርሌይም ከነ ቤተሰቡን ተጠምቆ ነበር:: ያው ከትዳሩ ውጪ ከብዙ ሴቶች ጋር ሌላ ሕይወት ነበረው:: ይህም በራስተፈሪያንስ ብዙ ሚስት የነበራቸው የዳዊትና የሰሎሞን ዘር ተከታዮች ነን በሚል ብዙ ማግባት ችግር የለውም የሚል አስተሳሰብ ስለነበረ ነው:: እኔ ግን አፄ ኃይለ ሥላሴ የነበራቸው አንድ ሚስት ብቻ እንደሆነ ነገርሁት:: እርሳቸውን ተከተል ስለው ተቀብሎኝ ነበር:: “እሺ አባ ያሉትን አደርጋለሁ” ነው ያለው::
ቦብ ማርሌይ በተጠመቀ ጊዜ ለግማሽ ሰዓት ያህል አልቅሶ ነበር:: በዕንባው እየታጠበ ነበር:: ይህም ትልቅ ንስሓ ነው:: የተጠመቀው ሊሞት ሰባት ወር ሲቀረው ነበር::
ብፁዕ አቡነ ይስሐቅ
ከጃማይካ ቴሌቭዥን ፕሮግራም ጋር
ጥያቄ:- ምንኩስናን የመረጡት እርስዎ ነዎት? ወይስ ምንኩስና እርስዎን መረጠ?
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ :- ተመራረጥን ብል ሳይሻል አይቀርም:: እግዚአብሔር ይህንን የሕይወት መንገድ አዘጋጅቶልኝ ነበር:: በዚህ ሕይወት እንድኖር የምንኩናን ፍቅር በልቤ የጨመረው እሱ ነው:: ስለዚህ እኔ በምንኩስና ስኖር ምንኩስናም በእኔ ውስጥ መኖር ጀመረ:: ስለ ምንኩስና የጻፍሁት ግጥም ነበረ:: ገና የአርት ተማሪ እያለሁ ወደ ገዳም ከመግባቴ ከሰባትና ስምንት ዓመታት በፊት የጻፍኩት ነው::
እንግዳው ይሰኛል::
“እንደ እንግዳ በዓለም ላይ ኖርሁ
እንደ አባቶቼ ጎብኚ ሆንሁ
(ከመዝሙረ ዳዊት የተወሰደ ሃሳብ ነው)
መንገዴ ሃሳቤ ምኞቴ
ማንም በማይገባው ልክ ከሰው ይለይ ነበረ
ሰዎች በሁከት ዓለም ሲኖሩ
እኔ በሰላም ውስጥ ነበርኩ
መጠለያ ያጣው እንግዳ
ከዓለምን ውበት ተነጠልኩ
አንዱንም ሳላጥመው
ሸሽቼ ከእርሱ አመለጥኩ
አንዴም ጆሮዬን ሳልሰጥ
የሰዎችን ጥሪ ሳልሰማ አሳለፍኩ
በራሴ በገና በራሴ መለከት
ከፈጣሪዬ ጋር በቅዱስ ሰዓታት
እዘምር ነበረ
ሊረብሸኝ የሚሞክር ጋኔን ሲመጣ
ሒድ ከእኔ ወግድ
እንደ አባቶቼ እንግዳ ነኝ ለዓለም እለው ነበረ” የሚል ነው::
ይህንን ግጥም ስጽፍ ገና ተማሪ ነበርኩ:: እኔ ወደ ምንኩስና ሳልገባ በፊት ምንኩስና እኔ ውስጥ ገብቶ ነበር:: እስክመነኩስ ድረስ እንዲህ ያለ ሃሳብ ያላቸው ግጥሞች እጽፍ ነበረ:: ወደ ገዳማዊ ሕይወት እያዘነበልኩም የሰንበት ትምህርት ቤት መጽሔት ላይ የጻፍኩት ግጥም ነበረ::
ባሕታዊው ይሰኛል::
በበረሃ ለብቻዬ
ጣልቃ ሳልገባ በሰው ጉዳይ
የእኔ ብቻ በሆነ ቦታ
በኮረብታዎቹ ጫፍ ላይ
አንድ ቀን እሔዳለሁ ወደማላውቀው ሀገር
አሁን ግን እኖራለሁ በበረሃ ውስጥ ስዞር
በረሃው ቤቴ ነውና ገዳም የለኝም ለእኔ
በግድግዳ አልታጠርኩም ከአምላኬ ጋር በመሆኔ
ጎጆ እንደማይሻ ምስኪን ወፍ እበርራለሁ በዚህ ዓለም
የትም ውዬ የትም ባድር የምመርጠው ቦታ የለም
ዓለምን የሚያስጨንቃት እኔን አያስጨንቀኝም”
ይሄን የምጽፈው እንግዲህ በዓለም ውስጥ እየኖርሁ ነበር::
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ከCYC ጋር ካደረጉት ቃለ መጠይቅ የተወሰደ
በእውነት ክበሩልን።ትልቅ ስራ ነው።ትልቅ እውቀት ነው።እየቸራችሁን ያላቹት።
ምን አልባት እንዚህ ፅሁፎች ወደፊት በመፅሐፍ አልያም በመፅሔት መልክ ይወጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ።ሆኖም ግን ደጌግመን ለማንበብ ለሰው ለማጋራት ይመች ዘንድ pdf ብታደርጉልን(ብታስቀምጡልን) መልካም ይመስለኛል።አመሰግናለሁ።
መልካሙ ዮሐንስ ከ ሐዋሳ ኢጃ. ት።
በእውነት ክበሩልን።ትልቅ ስራ ነው።ትልቅ እውቀት ነው።እየቸራችሁን ያላቹት።
ምን አልባት እንዚህ ፅሁፎች ወደፊት በመፅሐፍ አልያም በመፅሔት መልክ ይወጣሉ የሚል ተስፋ አለኝ።ሆኖም ግን ደጋግመን ለማንበብ ለሰው ለማጋራት ይመች ዘንድ pdf ብታደርጉልን(ብታስቀምጡልን) መልካም ይመስለኛል።አመሰግናለሁ።
በርቱልን, ሁሌም አዲስ ነገር ነው የማየው, ልትመሰገኑ ይገባል::
በእውነት አስተማሪ በጠፋበት ወጣቶች ሰብሳቢ ባጣንበት በዚህ ጊዜ በሚገባን እና ቀለል ባለ መልኩ ይህን የመሳሰሉ ትምህርቶች ማግኘት እድግ በጣም ደስ ይላል።የቅዱሳን አምላክ መንገዳችሁን ያቅናው
በጣም ደስ የሚል ነው የአባቶቻችን በረከት ይድረሰን
ቃሎ ሕይወት ያሰማልን
Am Very interested. But if you have a mobile APP that’s good!!
የአባቶቻችን በረከት በሁላችን ላይ ይደር! እግዚአብሔር አምላክ አባቶቻችንን ይጠብቅልን!