ቤተ ክርስቲያናችን ኦርቶዶክሳዊ ሐሳብ ያላት አካለ ክርስቶስ ናት። ነገሮቿ በሙሉ ክርስቶሳዊ መዓዛና ውበት ያላቸው ናቸው። የቤተ ክርስቲያን ራሷ እውነት የኾነው ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ኾነ የርሷ የኹል ጊዜ ውግንናዋ በእውነት በኩል ብቻ ነው። ምክንያቱም ከክርስቶስ የተነሣ እርሷ ራሱ የእውነት ቤት (The House of Truth) እየተባለች ትጠራለችና ነው። ስለዚህም ምክንያት ስትቀመስ ጣዕሟ እውነት እውነት የሚል መኾኑን ልብ ይሏል። ቅዱስ ሄሬኔዎስ “አንድ ሰው ከቤተ ክርስቲያን በቀላሉ የሚገኘውን እውነት ከሌሎች መፈለግ የለበትም።” ይላል። One should not seek among others the truth that can be easily gotten from the Church” (St. Irenaeus of Lyons, Against Heresies, III.4)። ይህ እንግዲህ እውነት ኹል ጊዜም ቢኾን በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ የሚገኝ መኾኑን የሚያስረዳ ነው። ይህን አስቀድሞ መረዳት ይገባል።
እውነት የክርስቶስ አካል በኾነችው በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ብቻ ከኾነ የሚገኘው፥ ትችትም ሲቀርብ ይህን የቤተ ክርስቲያንን እውነት መሠረት አድርጎ መኾን አለበት። የሚ’ተቸውም ነገር የሚተቸውም አካል እውነትን ከሳቷት ትችቱም ተተቺውም ከጥቅም ውጭ ይኾናሉ። ስለዚህም ምክንያት የሚተች ሰው ስለሚተቸው ነገር ያለው ግንዛቤ ወይም መረዳት በግል ስሜት ላይ ብቻ የተመሠረተ ወይም በሚተቸው አካል ላይ ካለው ለራሱ ለተቺው ስንኳን ባልታወቀው ጥላቻ መሠረትነት ሊኾን አይገባውም። እውነትን በጥላቻ ውስጥ ኾኖ መግለጥ ጣዕም የሌለው ከመኾንም አልፎ ቤተ ክርስቲያናዊም አይደለምና። ቅዱስ ጎርጎርዮስ ዘኑሲስ “አንድን ነገር ብቻ እንድንጠላ ተፈቅዶልናል፤ ይኸውም ክፋትን እንድንጠላ ነው። ሰውን መጥላት ግን ከሰይጣን ጋር መተባበር ነው” ይለናል። (St. Gregory of Nyssa, Letter 17)። ስለዚህ አንድ ትችት አቅራቢ ሰው በማንም በምንም ነገር ላይ ትችቱን ከማቅረቡ አስቀድሞ ራሱን ከጥላቻ ማጽዳት አለበት። በጥላቻ የተነሣ ሰው ዓይነ ልቡናው ነገሮችን አጥርቶ ከማየት ይወጣልና።
ትችት አቅራቢ ሰው ኦርቶዶክሳዊ አእምሮን ገንዘብ ማድረግ አለበት። ሕይወቱን ቤተ ክርስቲያናዊ አድርጎ በሥርዓቱ በአትሕቶ ርእስ ኾኖ የሚኖር ካልኾነ ነገሮችን በአግባቡ ሊተችና ሊያርም አይችልም። በዋነኛነትም በስሜቱ የሚመራ እና ነገሮችን ሥርዓት ባለው መንገድ የማያርም፥ ይልቅስ የራሱን ሐሳብ ብቻ ትክክል አድርጎ ለማጽደቅ የሚዳዳ ይኾናል። ይህ ደግሞ ነገሮችን በሙሉ ያበላሻል። ቤተ ክርስቲያናዊ ከኾነ ለራሱ ሐሳብ እንኳን አያደላም፥ የሚተቸውንም አካል ለማሳመን መረጃዎችን በአግባቡ እያቀረበ ስሕተት የኾነውን ያርማል። ስሕተት ነው ብሎ ያሰበውን ነገር በሥርዓቱ ነቅሶ የሚተቸውን ሰው አክብሮ ይጠይቃል፥ ይሞግታል እንጂ የራሱን እያጸደቀ የሚተቸውን አካል እያንኳሰሰ አይተችም። ይህ እንግዲህ ተግባራዊ የክርስትናን ሕይወት የሚመለከት ነው። ትችት አቀርባለሁኝ ብሎ የሚያስበው አካል ራሱን የቤተ ክርስቲያን አካል ሳያደርግ ማለት ከተነሣሕያን ውስጥ ሳይገባ የሚቆረቆር መስሎት የሚታየው ከኾነ ስሕተት ነው። እውነተኛውን የቤተ ክርስቲያን ሕይወት ቸል ብሎ ስለ ቤተ ክርስቲያኔ እቆረቆራለሁኝ ማለት እርስ በእርሱ የማይስማማ ነውና። በቤተ ክርስቲያናዊ አኗኗር ውስጥ ከኾነ ግን ሲተችም ሥርዓት ባለው መንገድና ቤተ ክርስቲያናዊ በጎ ጣዕም የሚቀመስበት አቀራረብ በማቅረቡ ይታወቃል፥ ከፍሬያቸው ታውቋቸዋላችሁ እንደ ተባለ። በክርስትና ሕይወቱ ውስጥ ቤተ ክርስቲያን መታየት አለባት። ምክንያቱ እውነተኛ ክርስቲያን ማለት ተንቀሳቃሽ ቤተ ክርስቲያን (Movable Church) ነውና። በእርሱ ትችት ውስጥ ቤተ ክርስቲያን ግልጽ ኾና ትታያለችና።
ትችት አቅራቢ ሰው የሚተቸውን ሰው ሐሳብ በአግባቡ ለመረዳት አስቀድሞ እጅግ በጣም መጣር አለበት። ምክንያቱም ተተቺው ሰው ያላሰበውን እንዳሰበ፥ ሊለው የማይችለውን እንዳለ አድርጎ ከተነሣ እርሱ ራሱ ስሕተት ውስጥ ሊገባ ይችላል። ምናልባትም አንዳንድ አገላለጹ ለእኛ ትክክል መስሎ ስላልታየን ብቻ ትክክል አይደለም ሊባል አይችልምና። አርጌንስ እንዲህ ዓይነት ነገር እንደ ገጠመው ራሱ ጽፎ ነበር። ራሱ እንዲህ ብሎ ነበር “አብዛኛዎቹ ከሚገባኝ አብልጠው ይወዱኛል፤ ጹሑፎቼንና ትምህርቶቼን ያደንቃሉ፡፡ ሌሎች ደግሞ ትምህርቶቼን ይነቅፋሉ፣ የእኔ ያልኾኑ ያልተናገርኳቸውን ሐሳቦች የእኔ እንደ ኾኑ አድርገው ይናገራሉ፡፡ ከተገቢው በላይ የሚወዱንም ከተገቢው በላይ የሚጠሉንም ኹለቱም የእውነትን ሕግ አልጠበቁም፡፡ ምክንያቱም አንዳንዶች ከመጠን ባለፈ ፍቅር ላይ ሲኾኑ አንዳንዶች ደግሞ ከመጠን ባለፈ ጥላቻ ላይ ናቸው፡፡” በማለት ኹለት ጽንፎችን ይነግረናል (Origen of Alexandria, In Joshua, Homily 9.3)፡፡ ስለዚህ የተተቺውን ሐሳብ አጥርተን መረዳት አለብን፥ ካልኾነ ትሕትና ባለበት መንገድ ጥያቄዎችን ማቅረብ ይገባል እንጂ ወደ ችኩል ድምዳሜ መሄድ የለብንም። በቃ! ይሄን ያለው እንዲህ ማለት ፈልጎ ነው፥ ወይም እንዲህና እንዲያ ሲል ነው እያልን በየግላችን የሰዎችን ሐሳብ በችኩል የምንተረጉም ከኾነ ይህ ድርጊታችን በራሱ ኃጢአት ነው። ችኩልነት ጎጂ መኾኑን እናስተውል። ችኩልነት በተጠቃ አእምሮ ወደ ማሰብ ይወስደናል፥ እንደ አይሁድም አጥርቶ የማየት አቅማችን ላይ ችግር ይፈጥራል። ብዙዎቻችን በእግዚአብሔር የፍርድ ወንበር ለመቀመጥ እንፈጥናለን። የተሳሳቱ የመሰሉንን አካላት ስናንጓጥጣቸውና ያልተገባ ትችት በማቅረብ ስማቸውን ስናጠፋ ሰይጣን በእኛ ምን ያህል እየሠራ እንደ ኾነ ኹሉ አይገባንም። ስሕተቱ የተረጋገጠ እንኳን ቢኾን ሰዎች የሚሳሳቱ መኾናቸውን ማሰብ ያቅተል፥ ይልቅስ ቶሎ ብሎ በተገኘው የስሕተት በር በኲል እየገባን ብዙ የጥላቻ ዱላዎችን መወርወር እንጀምራለን። በጥበብ ማድን የሚባል ነገር በሕሊናችን ለአንድ አፍታ እንኳን አይመጣም። ይህ በጽኑዕ የጉዳት ደረጃ ውስጥ መኾናችንን አመልካች መኾኑን ማን ይንገረን! ማንንስ እንሰማ ይኾን?
ኦርቶዶክሳዊ ትችት አቅራቢ አካል ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው መኾን አለበት። ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለውን ሰው ዮሐንስ ዘሰዋስው “እግዚአብሔርን መፍራትን ገንዘብ ያደረገ ሰው በውስጡ የማይጠፋ ዳኛ – የገዛ ሕሊናው አለና ሐሰት መናገርን ተወ።” ይላል። (ሳሙኤል ፍቃዱ (ተርጓሚ)፣ ምዕራግና ድርሳን፣ 2011 ዓ.ም፣ ገጽ 172)። በፈሪሐ እግዚአብሔር ውስጥ ኾኖ የሚተች ሰው እውነተኛ ዳኛ የመኾን ዕድሉ ከፍ ያለ ነው። ቅዱስ ዮሐንስ ሐፂር ደግሞ “ትሕትናና ፈሪሓ እግዚአብሔር ደግሞ ከበጎ ምግባራት ኹሉ ይበልጣሉ።” ይላል + St. John the Dwarf, The Sayings of the Desert Fathers። ስለዚህ ፈሪሐ እግዚአብሔር ያለው ሰው ትችት ሲያቀርብ እግዚአብሔርን እያሰበ ሥርዓት ባለው መንገድ ያደርጋል። አቀራረቡ ጣዕም ያለውና ተቀባይነት ያለው ይኾንለታል። ስለዚህ አንድ ትችት አቅራቢ ሰው በዚህ ውስጥ ራሱን ለማድረግ በእጅጉ መትጋት አለበት፥ ይህ የማይኾን ከኾነ በትችቱ ከሚጠቅማቸው የበለጠ የሚጎዳቸው ሊበዛ ይችላልና።
ትችት አቅራቢው ከትችት በፊት አቅሙን ጠንቅቆ ማወቅ አለበት። ምክንያቱም በማያውቀው ነገር ውስጥ ገብቶ እንዳያበላሽና ሰዎችን ባልተገባ መንገድ እንዳይጎዳ። ስለ ቤተ ክርስቲያን ነገረ ሃይማኖታዊ ጉዳይ የተጻፉ መጻሕፍትን በለብ ለብ ንባብ ልተች ብሎ ትችቱን አቅራቢው ራሱ በአደገኛ ስሕተት ውስጥ እንዳይገኝ በእጅጉ መጠንቀቅ ያስፈልጋል። ለዚህም ይስሐቅ ዘሶርያ ያለው ምክር ጠቃሚ ነው። እንዲህ ይላል “ማንም ሰው ያለጊዜው ከእርሱ በላይ የኾነ ነገር ለመሥራት ቢጀምር፡ ምንም አያገኝም፤ ነገር ግን በራሱ ላይ ብቻ ጉዳትን ያመጣል እንጂ።” ይላል። Whoever prematurely begins a work that is above his strength receives nothing, but only brings harm upon himself. (St. Isaac the Syrian, Homilies, 11)።
ትችት አቅራቢ ሰው ከቅናት መንፈስ የጸዳ መኾን አለበት። በቅናትም ተነሣሥቶ ሌሎችን ባልተገባ ትችት እንዳይተች ውስጡን ረጋ ብሎ መመርመር አለበት። ሊቁ ጎርጎርዮስ ታላቁ “ቅናት የግጭት ወላጅ ነው ይለንና በዝርዝር አንድ በቅናት ውስጥ ያለ ሰው ምን ዓይነት ክፉ ድርጊቶችን ሊፈጽም እንደሚችል ሲያብራራ ” ከቅናት ጥላቻ፣ አግባብነት የሌለው አስተያየት ወይም ትችት፣ ሐሜት፣ በጎረቤት መጥፎ አጋጣሚ መደሰት፣ በጎረቤት ብልጽግና አለመደሰት ይወለዳሉ።” ይላል። Moralia Job 31: 45። እንግዲህ እነዚህ እጅግ አሳዛኝና ክፉ ሥራዎች ኹሉ ከቅናት እንደ ልጅ ኾነው ይወላዳሉ ማለት እነዚህ ድርጊቶችን ቅናት ይበልጣቸዋል ማለት ነው። ብዙ ሰዎች ከቅናት የተነሣ የሚያቀርቡትን ትችት ትክክል ተደርጎ እንዲወሰድላቸው ብዙ ለምዶችን ያለብሷቸዋል። በሕሊናቸው ውስጥ የወሰኗትን አስተያየት ጳውሎስ፣ ጴጥሮስ ቢመጣ እንኳን እንዲያጸድቁላቸው እንጂ እንዲቃወሟቸው አይፈልጉም። እንዲህ ሲሉ የዚያ ነገር ትክክለኝነት መለኪያው እኛ ነኝ እያሉ መኾኑንንም ይረሱታል። በቅናትም ውስጥ መኾናቸውን ስለማይረዱት እኔ ቅናት የለብኝም በማለት የበለጠ ምልክቱን በመናገር ባላወቋት ቅናት ውስጥ መኾናቸውን ይመሰክራሉ።
አንዳንድ ሰዎች ባይረዱትም ስለ ኾነ ጉዳይ ለመተቸት ይፈጥናሉ። ክፉ ያሰቡ አይመስላቸውም ቅናታቸው ከራሳቸው ተሰውሮባቸው እንዴት እያከፋቸው እንደ ኾነ አይረዱትም። በመኾኑም ደርሰው አግባብነት የሌለው ሊያንጽ የማይችል ጥላቻን መሠረት ያደረገ አስተያየትን በሌሎች ላይ ያቀርባሉ።
ይህን በማድረጋቸውም ውስጣቸው ደስ ይለዋል! እንዴት አንድን ሰው በመንቀፍ ደስታ ይገኛል? ምናልባትም ሰውዬው ያላለውን ብለሃል ብለው ሊከሱትና እኔ እንዲህና እንዲህ ማለቴ ነው ቢልም አይሰሙትም በቃ ይህና ይህ ነው ብለው የሰውዬውን ሐሳብ አሽቀንጥረው ጥለው የራሳቸውን ብቻ ትክክል አድርገው የሚቀመጡ የቅናት ድብቅ ምሽጎች አሉ። ራሳቸውን በዚህ ጽኑዕ በሽታ አቃጥለው ከጨረሱ በኋላ የግድ ሌላውንም ካላቃጠልን የሚሉ በማያውቁትም ጉዳይ ዐዋቂዎቹ እኛ ብቻ ነን ብለው የሚደመድሙ ብዙ ሰዎች አሉ። ስለዚህ ኦርቶዶክሳዊ ትችት አቅራቢ ሰው ከዚህ መንፈስ የጸዳ መኾን አለበት።
ኦርቶዶክሳዊ ትችት አቅራቢ ሰው፥ የሚተቸውን አካል የሚያክም የትችት አቀራረብን መምረጥ አለበት። ምክንያቱም ዓላማው ስሕተትን ማረም እንጂ ተተቺውን አካል ማብሸቅ አይደለምና። ኾነ ብሎ ስውን ለማብሸቅ የሚተች ሰው አስቀድሞውኑ በሰይጣን ዱላ ተደብድቦ የቆሰለ መኾኑን ማወቅ አለበት። ትችቱ መድኃኒት ኾኖ የአተቻች መንገዱ መርዝ ከኾነ ተተቺው አካል በአተቻቹ ምክንያት ብቻ ትችቱን ውድቅ ሊያደርገው ይችላል። ፍቅር የሌለው ትችት ትክክል ቢኾን እንኳን ጣዕም አይኖረውም። ስለዚህ ተቺው ሰው ለምን ትችቴ ተቀባይነትን አላገኘም ከማለቱ በፊት አቀራረቡ ጣዕም ያለው መኾን አለመኾኑን መመርመር አለበት። ትችቱ ትክክል ስለ ኾነ ብቻ ተቀባይነትን ማግኘት አለበት ማለት ሰይጣንም ኢየሱስን “ቅዱሱ እግዚአብሔር ልጅ ሆይ” በማለቱ ምክንያት ተቀባይነት ማግኘት ነበረበት እንደ ማለት ነው። ይህ በእጅጉ ስሕተት ነው።
ኦርቶዶክሳዊ ትችት አቅራቢ በሚተቸው ሰው ላይ ማፌዝ የለበትም። ቅዱስ ኤፍሬም ሶርያዊ ይህን በተመለከተ “ፌዝና ተሳልቆን ካፈቀርክ አንደኛህን እንደ ሰይጣን ኾነሃል ማለት ነው። በወንድምህ ላይ ከተሳለቅህ የዲያብሎስ አፍ ነህ። ስሕተቶችና ድክመቶች ላይ የምታጠነጥን፣ አቁሳይ በኾነ ስም ማጥፋት የምትደሰት ከኾነ ሰይጣን ከነመፈጠሩም የለም ማለት ነው፤ ምክንያቱም አንተ በኃይል ቦታውን ይዘኸዋልና። አንተ ሰው ሆይ ራስህን ከዚህ አርቅ። ይህ ኹሉ ጎጂ ነውና። በደኅና መኖር ከፈለግህ ከኃጢአቱና ከቅጣቱ ጋር ወዳጅ እንዳትኾን ከተሳላቂ ሰው ጋር አብረህ አትቀመጥ። ሙሉ በሙሉ የልቅሶ ምንጭ የኾነውን ስላቅ ጥላው፥ የስላቅ መሣሪያ የኾነውን ሳቅም ጥላ። በአጋጣሚ ተሳላቂ ሲሳለቅ ብትሰማ የማትመኘው ከኾነ በመስቀል ብርሃን ራስህን አማትብ፥ እንደ ድኩላም ፈጥነህ ከዚያ ሰው ሽሽ። ሰይጣን በሚያርፍበት ቦታ ክርስቶስ በምንም ጥበብ ሊኖር አይችልም። የሰይጣን ሰፊ እልፍኝ በወንድሙ ላይ የሚሳለቅ፥ የሚያሾፍ ሰው ነው። የጠላት ዲያብሎስ ቤተ መንግሥት የፌዘኛው ልብ ነው። ሰይጣን በዚህ ሰው ላይ ሌላ ምንም መጨመር አይፈልግም። ሹፈት ለሁሉም ክፉ ሥራዎች መንሥኤ ለመኾን በቂ ነው።” በማለት በአጽንዖት አስተምሯል። (Nicene and post Nicene Fathers 2nd Series V 13)። ስለዚህ አግባብነት ያለውን ትችት ለማቅረብ የሚፈልግ ሰው ኹል ጊዜም ቢኾን ከማብሸቅና ከመናቅ መንፈስ የጸዳ መኾን አለበት። አንድ ሰው በንግግሩም ኾነ በጽሑፉ ቢሳሳት ያንን ሰው መናቅ፥ ወይም በእርሱ ላይ መሳለቅ፥ ወይም ማፌዝ የተቺውን በሽታ የሚያሳይ እንጂ ሌላ ምን ሊባል ይችላል። በማፌዝና በመናቅ ሰዎች ላይ የሚቀልዱ አካላትን ልንሰማቸው አይገባም። ስንኳንስ ተተቺውን ትችቱን የሚያነቡትንም አካላት ሊመርዝና ዋዛ ፈዛዛ የኾነ ነገር የተፈቀደ እንዲመስል በር ይከፍታልና።
ኦርቶዶክሳዊ ትችት አቅራቢ በፍጹም ከስድብ መንፈስ መውጣት አለበት። ስደብ “የስድብ አፍ ተሰጠው” የተባለውን አውሬው ዲያብሎስን የሚያስመስል መርዝ ነው። ደንቆሮን “ደንቆሮ” ማለት ለገሃነም ፍርድ የሚያበቃ መኾኑ ከተገለጸ እንዴት ነው ሰዎችን በስድብ ልናስነውራቸው የምንችለው? ተተቺው አካል ተሳስቷል ብለን እያሰብን፥ ስሕተትን በስሕተት ለማስተካከል መሞክርስ ሌላ ስሕተት መኾኑ ይጠፋናልን? እንግዲህ በእርጋታ ማስተዋል ይገባል። እኛ በቤተ ክርስቲያን መንፈስ ልንጓዝ ይገባል እንጂ ቤተ ክርስቲያንን በእኛ ሐሳብ ለማድረግ አንሞክር። በስድብ የታጀበ አስተያየት ወይም ትችት ትችቱ መልካም ቢኾን ራሱ ቅይጥ መኾኑ ጣዕሙ ያመረዋል። ይህ በሬን ከአህያ ጋር ጠምዶ እንደ ማረስ ነውና። ብዙዎቻችን ለሃይማኖት የተቆረቆርን እየመሰለን ብዙ ስሕተት እንሠራለን። በስድብ የተመሉ ጥላቻን የለበሱ ትችቶችንም እውነት የያዙ ስለመሰለን ብቻ እናደንቃለን፤ ተቺውንም ልቡናው በታሰረበት ስሑት ትችት እንዲቀጥል የምቅታ ስሜትም እንዲሰማው ለማድረግ በብዙ እንጥራለን። ደጋፊና ነቃፊ በመኾን ጎራ ለይተን እርስ በእርስ እንበላላለን። ስለዚህ ጥንቃቄ ያስፈልጋል። ወደ ስድብና ብሽሽቅ የሚወስዱ መንገዶችን በሰከነ መንፈስ ኾኖ መለየትና ራስን መጠበቅ ያስፈልጋል።
አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን በእያንዳንዱ ንግግራችን ውስጥ የምንሰገስገው ችግራችንን ነው ዞር ብለን እንድናይ ያነቁን የምናውቀው ግን የማናስተውለው ልማድ ነው ማስተዋሉን ያድለን!
እናመሰግናለን
አስተያየት መዝሙር ጥናት መች የጀመራል ስለ አልኩ ብቻ ብሎክ ወይ ሚድያ እኔ ጋር እዳየመጣ አደርጋችዋል እዴ ማለት ብሎክ የሚያስናብት ከመሆኑ እኔ አላውቅም ይቅርታ አላወቁም ነበር
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
በጣም በጉጉት እየጠበኩ ነው የማነበው። ቴሌገራምና ፌስቡክ ስገባ ብዙ ጊዜ ሀሳቤ ይጠለፋል። ይህ ብሎግ ግን በጣም ተመችቶኝ እያነበብኩት ነው በርቱ።