ጌታችን እና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስለ ምጽአቱ ሲናገር ሁለት የሚቃረኑ ምሳሌዎችን ተጠቅሟል፦ ሙሽራ እና ሌባ። ሙሽራ በደስታ እና በእልልታ የሚጠበቅ ነው። ሌባ ደግሞ ሳያስቡት መጥቶ የሰውን ሕይወት የሚያመሰቃቅል እና ንብረቱን የሚያጠፋ ነው።
ታዲያ ጌታችን በአሥሩ ደናግል ምሳሌ ነቅተን በእልልታ መብራት ይዘን፣ ነጭ ለብሰን ልንጠብቀው የሚገባን ሙሽራ እንደሆነ ነግሮናል፦
“እኩል ሌሊትም ሲሆን፦ እነሆ፥ ሙሽራው ይመጣል፥ ትቀበሉት ዘንድ ውጡ የሚል ውካታ ሆነ። በዚያን ጊዜ እነዚያ ቆነጃጅት ሁሉ ተነሡና መብራታቸውን አዘጋጁ። ሰነፎቹም ልባሞቹን፦ መብራታችን ሊጠፋብን ነው፤ ከዘይታችሁ ስጡን አሉአቸው። ልባሞቹ ግን መልሰው፦ ምናልባት ለእኛና ለእናንተ ባይበቃስ፤ ይልቅስ ወደሚሸጡት ሄዳችሁ ለራሳችሁ ግዙ አሉአቸው። ሊገዙም በሄዱ ጊዜ ሙሽራው መጣ፥ ተዘጋጅተው የነበሩትም ከእርሱ ጋር ወደ ሰርግ ገቡ፥ ደጁም ተዘጋ።” (ማቴ. 25፥6-10)
በሌላ ቦታ ደግሞ “ጌታችሁ በምን ሰዓት እንዲመጣ አታውቁምና እንግዲህ ንቁ። ያን ግን እወቁ፤ ባለቤት ከሌሊቱ በየትኛው ክፍል ሌባ እንዲመጣ ቢያውቅ ኖሮ፥ በነቃ ቤቱም ሊቈፈር ባልተወም ነበር። ስለዚህ እናንተ ደግሞ ተዘጋጅታችሁ ኑሩ፥ የሰው ልጅ በማታስቡበት ሰዓት ይመጣልና፤” ይላል። (ማቴ. 24፥42-44) ቅዱስ ጳውሎስም ይህን የጌታችን ትምህርት ይዞ “የጌታ ቀን፥ ሌባ በሌሊት እንደሚመጣ፥ እንዲሁ ይመጣ ዘንድ ራሳችሁ አጥብቃችሁ አውቃችኋልና፤” ይላል። (1ኛ ተሰ. 5፥2)
ወዳጄ፥ አምላካችን ክርስቶስ ስለ ምጽአቱ ሁለት ምስሎችን ስሎልናል፦ የሙሽራ እና የሌባ። እርሱ ‘መጣብን’ የሚባል ሌባ ሳይሆን ‘መጣልን’ የሚባል የሚወደድ ሙሽራ ሆኖ እንጠብቀው ዘንድ ነው በጎ ፍላጎቱ። እኛ በፍቅር ሆነን ነቅተን ካልጠበቅነው ግን እርሱ የሚፈልገው ያ ባይሆንም እንኳ በእኛ ችግር ምክንያት እንደ ሌባ ሆኖ ይመጣል። የእርሱ ጽኑ መሻት ግን እልል እያልን እንደ ተወዳጅ ሙሽራችን በጉጉት እንድንቀበለው ነው። ንጉሣችን እንደ አእዛብ ነገሥታት በፍርሃት የሚገዛን ሳይሆን እንደ ሙሽራ መወደድን የሚመርጥ ነውና። ክብሩ በማዳኑ የሆነ ድንቅ ነውና። እኛ ግን እንደ ምን ልንቀበለው እየተዘጋጀን ነው? እንደ ሙሽራ ወይስ እንደ ሌባ?
ክርስቶስ የሚመጣው በታላቅ ክብር ነው። “መብረቅ ከምሥራቅ ወጥቶ እስከ ምዕራብ እንደሚታይ፥ የሰው ልጅ መምጣት እንዲሁ ይሆናልና፤” እንዲል። (ማቴ. 24፥27) ነገር ግን ይህ ክብር ተዘጋጅተው ለሚጠብቁ ምዕመናን ለመደነቅ እና እልል ብሎ ለማመስገን የሚያነሣሣ እንጂ የሚያሸብር አይደለም። የሚወደድ እንጂ ባልመጣብን የሚባል አይደለም። እነ ቅዱስ ጴጥሮስ በታቦር ተራራ ላይ ክብሩን ሲያዩ ከግርማው የተነሣ ቢፈሩም ነገር ግን የሚወደድ ስለሆነ በዚህ መሆን መልካም ነው ብለዋል።
የእግዚአብሔር ክብር ሲገለጥ ቅዱሳንን በፍቅር ይስባል፤ ከፍርሃታቸው አጽንቶ በዚህ እንሁን ያስብላል። ለዓመጸኞች ግን የሚገቡበት ቀዳዳ እስኪያጡ የሚያስጨንቅ ይሆናል። ሌባ ሲመጣ እንደሚያሸብረው እንደዚያ ይሆናል። ጸሐይ፣ ጨረቃ፣ ከዋክብት እና ሌሎች ፍጥረታት ሁሉ የጌታችን መምጣት አብረው ያከብራሉ። ይህ ሁሉ ለቅዱሳን ሙሽራውን የመቀበል ሥርዓት አካል (cosmic celebration) ነው፤ ደስታና እልልታን የተሞላ ትእይንት ነው።
የክርስቶስን ማዳን ችላ ላሉ ግን የፍጥረታት እንግዳ እንቅስቃሴ ከሽብር ላይ ሽብር የሚፈጥር ዱብ እዳ ነው።
አምላካችን እንደ ሙሽራ እልል እያልን በፍቅር እንቀበለው ዘንድ እንጂ እንደ ሌባ መምጣት አይፈልግም።
ለአንዳንዶቻችን ግን በንስሐ ካልተመለስን ይህ መሆኑ አይቀርም። የእርሱ ፍላጎት ሁላችንም በደስታ እንቀበለው ዘንድ ስለሆነ “ንቁ!” “አስተውሉ!” “ተዘጋጅታችሁ ጠብቁ!” እያለ በፍቅር ቃል ቀድሞ በተደጋጋሚ ተናግሮናል። ምን እያደረግን ነው? ለሙሽራው እንዘጋጃለን ወይስ ሌባ በድንገት እንደሚመጣ አስጨናቂው ቀን በድንገት ይደርስብን ዘንድ ተዘልለን ተቀምጠናል? ይልቁንም የመጨረሻው ዘመን እየደረሰ እንደሆነ እያሰብን ራሳችን እንመርምር። “መንፈሱና ሙሽራይቱም፦ ና ይላሉ።” (ራእይ 22፥17)
እጅግ መልካም ጥያቄ ነው,
ቃለ ህይወት ያሰማልን በትረካም ተዘጋጅተው በጃንደረባው ሚዲያ የ Youtube ቢለቀቅልን። አመሰግናለሁ
አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን
እጅግ ጠቃሚ የሚያነቃቃ መልዕክት ነው በተለይ አብዝተን ለተኛን ወጣቶች
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!