እማሆይ ፈንታነሽ ገዳሙ በካሴት ሥራ የታወቁ የመጀመሪያዋ የሴት ዘማሪት ናቸው:: ሙዚቃ ቤቶች ወደ መዝሙር ቤትነት ለመቀየራቸው ምክንያት ከሆኑ የመዝሙር ሰዎችም ተጠቃሽ ናቸው:: ከእማሆይ ጋር ይህንን አጭር ቆይታ አድርገናል::
ጃንደረባው :- እማሆይ ፈንታነሽ እስቲ ልጅነትዎ ምን ይመስል ነበር?
እማሆይ ፈንታነሽ :- በልጅነቴ ነው ወደ ቤተ ክርስቲያን የገባሁት:: ያደግሁት ፒያሳ ጊዮርጊስ ነበረ:: በሕፃንነቴ እንዳልዳር ብላ ወደ ከተማ ያመጣችኝና ወደ ትምህርት ቤት ያስገባችኝ እኅቴ ነበረች:: በትምህርት በጣም ጎበዝ ነበርሁ:: በዚህ ጊዜ ግን በከፍተኛ ሕማም ስሰቃይ ቆይቼ በቅዱስ ጊዮርጊስ ተራዳኢነት ከሞት ተረፍኩ:: መታመሜም ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ምክንያት ሆነልኝ:: በልጅ አእምሮዬ ዘፋኝ ለመሆንና ትምህርቴን ስጨርስ ካሴት ለማውጣት እመኝ ነበር:: ቀስ በቀስ ግን ወደ መዝሙር አገልግሎት ገባሁ:: በገነተ ጽጌ ቅዱስ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ማገልገል ጀመርሁ::
ጃንደረባው:- ሴት ልጅ ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ብዙም በማትታሰብበት ጊዜ እርስዎ እንዴት ዘማሪት ሊሆኑና ካሴት ሊሠሩ ቻሉ?
እማሆይ ፈንታነሽ :- ምስካየ ኅዙናን መድኃኔ ዓለም ገዳም እየሔድሁ በማገለግልበት ጊዜ ሊቀ ትጉኃን አባ መዓዛ የሚባሉ አባት ነበሩ:: እርሳቸው ሲያስተምሩ በዚያ እማርና እዘምር ነበረ:: እርሳቸው መናገሻ ማርያም ዝክር ሲያደርጉ በዚያ ሳገለግል አንዲት የንስሓ ልጃቸው ሰማችኝ:: እርስዋ ሙዚቃ ቤት ካላቸው ሰዎች ጋር ድምፄን እንዲቀርጹኝ አደረገችልኝ:: መዝሙሩ ሲቀረጽ ምንም ክፍያ አልነበረኝም:: ሽጪ ተብሎ የተሠጠኝንም ኮፒ እንዲሁ ሸጬ ብሩን ለእነርሱ እንድሠጣቸውና አንድ ላይ እንዲከፍሉኝ ተነጋግረን አምኜያቸው ነበረ::
በኋላ ግን ዘፋኝ ካልሆንሽ ብለው ያስጨንቁኝ ጀመር:: “እኔ ዘፋኝ መሆን አልፈልግም:: ዘፋኝ ሁሉ ይኮነናል አልልም:: ማዕተባቸውን እስካልበጠሱ ለንስሓ ያበቃቸዋል:: እኔ ግን መንገዱን አውቄያለሁ:: ማዳኑን አይቻለሁ:: ሰውና መላእክት እርሱን ለማመስገን እንደተፈጠሩ ካስተማረኝ በኋላ ዘፍኜ ብመጸውትለት የቃያን መሥዋዕት ይሆንብኛል” አልኳቸው:: “እንግዲያውስ ገንዘቡንም አንሠጥሽም ከፈለግሽ ክሰሺ” አሉኝ:: “እግዚአብሔርን የምታመልኩ ከሆነ ለእግዚአብሔር ብላችሁ ሥጡኝ:: ብር የምታመልኩ ከሆነ ደግሞ አምልኩበት” አልኳቸው:: የመጀመሪያው የመዝሙር ሥራ በዚህ መልኩ ተጠናቀቀ:: እግዚአብሔር ይመስገን ትዕግሥት ተምሬበታለሁ::
ጃንደረባው:- ሰማንያዎቹ ከፍተኛ የተሐ** እንቅስቃሴ የነበረበት ጊዜ እንደነበር ይታወሳል? እርስዎ በዚያ ጊዜ በመዝሙር ማገልገልዎ ምን አይተው ነበር?
እማሆይ ፈንታነሽ :- እውነት ነው:: በዚያን ወቅት ሌላው ፈተና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ገብተው ሌላ ዓላማ የሚያራምዱ ሰዎች ነበሩ:: ቅድስት ሥላሴ አዳራሽ ውስጥ አኮርድዮን የሚባል መሣሪያ ይዘው ገብተው የሚጨፍሩ ተልዕኮ ያላቸው ሰዎች ነበሩ:: በጉባኤያቸው ተጠርቼ ስሔድ ባየሁት ነገር በጣም አዘንኩ:: ለመዘመር ስወጣ “እኔ ሦስት እናት አለኝ:: እመቤታችን ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ሀገሬ ናቸው:: እነዚህን ከመካድ ይሰውራችሁ” ብዬ “የዘላለም ቤቴ” የሚል መዝሙሬን ዘመርሁ:: ብዙ ስድብ ቢወርድብኝም ሳያውቅ የገባው ሰው ግን እንዲነቃ ምክንያት ሆንኩኝ::
ጃንደረባው:- መዝመር የማሳተም ነገርስ በዚያው ቀረ?
እማሆይ ፈንታነሽ :- አልቀረም:: የመጀመሪያው መዝሙሬ በየቦታው ተሰሚነት አግኝቶ ነበረ:: በተለይ ወደ አውቶቢስ ተራ መሔጃ ማርስ ሙዚቃ ቤት እየከፈቱ እንደሚያሰሙ አንዲት ልጅ ነገረችኝና “መዝሙር እንዲያሠሩሽ እናናግራቸው” የሚል ሃሳብ አቀረበችልኝ:: እሺብዬ አብረን ሔደን ስንጠይቃቸው መዝሙር ሊያሠሩኝ ሲፈልጉኝ እንደነበረ ነግረው በደስታ ተቀበሉኝ:: ገና መዝሙሩ ወጥቶ ሳይሸጥ በፊት ቀድመው ገንዘብ ከፈሉኝ::
በመዝሙሩ ሥራ ላይ በመሣሪያ ያጀበኝ ዘውዱ አማረ ነበረ:: ቁጥር ሁለትና ሦስትም መዝሙር ሠራሁ::
ከዚያ በኋላ ማርስ ሙዚቃ ቤትም ስሙን ቀይሮ “አርያም መንፈሳዊ መዝሙር ቤት” ተባለ:: መዝሙርም ዘማርያንም በዙ:: በወረፋ መሥራት ጀመረ:: ከአራት በኋላ አልቀው የተቀመጡትን ጨምሮ እስከ ቁጥር ስምንት ደርሻለሁ:: ከሆነ ጊዜ በኋላ መዝሙሩ ወደ ውድድር ሔደ:: ሌሎቹም ከቤተክርስቲያን ውጪየሆኑ እየገቡበት ሲመጣ ወደ ራሴ መንፈሳዊ ሕይወት አተኮርሁ::
ጃንደረባው:- በመዝሙር አገልግሎትዎ ወቅት ከነማን ጋር አብረው ሠርተዋል?
እማሆይ ፈንታነሽ :- መዝሙሮቼን ስሠራ አቶ ዓለማየሁ ፈንታ ፣ ቀሲስ አካሉ ዮሴፍ ወዘተ አጅበውኝ ነበር:: በአንድ ወቅት በችግር ወቅት የሙዚቃ መሣሪያ ወደ ቤተ ክርስቲያን መዝሙራት ገብቶ ነበር:: እን መጀመሪያ ካሴት ስሠራ ግን በሙዚቃ መሣሪያ ለመዘመር ፈቃደኛ ስላልነበርሁ ዘውዱ አማረ ክራር እንዲያጅብ ተጠርቶ መጥቶ በዚያው ተዋወቅሁት:: በብዙ ሥራዎችም ለብዙ ዘመን ሲረዳኝ ኖሮአል::
በ1985 ዓ.ም. ሰሎሞን ደነቀ የሚባል (“መሃረቤን ያያችሁ” በሚል ዘፈን የሚታወቅ ዘፋኝ የድምፄን ሜጀር ለመያዝ ኪቦርድ ሊጫወት መጣ:: በዚያው “የዘላለም ቤቴ” የሚለውን መዝሙር እየሰማ ቆይቶ አብሮኝ አጀበ:: የወለጋ ልጅ ሲሆን ዲያቆን ነበረና ደስ ብሎት አብሮኝ መዝሙሩን አጃቢ ሆኖ ተቀርጾአል:: በጥሩ ቤተሰብ ያደገ ልጅ ነበር:: ድምፁ ለመዝሙር አለመዋሉ ያስቆጫል::
ጃንደረባው :- ለዚህ ዘመን ዘማርያን ምን ይመክራሉ?
እማሆይ ፈንታነሽ :- በተሠጣቸው ጸጋ ያገልግሉ:: ነገር ግን ግጥሙን ይመርምሩ:: የሃይማኖት ምሥጢር የሚያፋልሰውን ይለዩ:: በቀድሞ ጊዜ የዘማርያን አለኝታ እንደ ኪነጥበብ ነበረ:: ለአሁንም የእርሱን ዘማርያንን ፈለግ ተከተሉ እላለሁ:: ቀዳሜ ጸጋ የሚባል ልጅ ሲዘምር አይቼ እጅግ ደስ ብሎኛል:: ጥሩ ልጆች እየታዩ ነው:: ሴቶቹም አለባበሳቸው ሥርዓት ይጠብቁ:: ብርሃናችሁ በሰው ፊት ይብራ የሚለውን አገልጋዮች አርኣያ መሆን አለባቸው እላለሁ::
ጃንደረባው :- ዕድሜ ይሥጥልን!
ለእማሆይ እድሜ የስጥልን። ባለውለታዎቻችንን ስላስታወሳችሁን እግዚአብሔር ይስጥልን
በርቱ
እንዲህ ያለውን ሳነብ እጅግ ደስ ይላል እማሆይ እድሜና ጤናን ያድልልኝ።
ስለመዝሙር አዘማመር ከተነሳ ጥያቄ እየሆነብኝና እስካሁን መልስ ያላገኘሁለት ከቅዳሴ አገልግሎት በኋላ ቤተ መቅደስ ውስጥ ክራር አንግበው እየተነሱ ስለሚዘምሩት፣ (ማለት እንኳን ይከብዳል) እንደገና ታቦተ ህጉ እንደቆመ ወረብ የሚያጅቡም ብቅ ብለዋል።ለመቃወምም እውቀት ያስፈልገዋልና ምን ትላላችሁ?
መልካሙን ተመኘሁ።
እማሆይ እድሜና ጤናን እንዲያድሎት እመኛለሁ። የአገልግሎት ዘመኖ ይባረክ። እንዲህ ያሉትን አገልጋዮች ያብዛልን። እኔም በተሰጠኝ ፀጋ እግዚአብሔርን በዝማሬ ማገልገል ነው ምኞቴ። የእማሆይን መዝሙሮች በማህቶት ቲዩብ ወይም በጃን ሚዲያ ላይ ማግኘት ብንኝል እላለሁ
ለእማሆይ እድሜና ጤና ይስጥልኝ ። እናንተንም እግዚአብሔር ይክበርልኝ ።
እማሆይን ስለ አገልግሎታቸው ስለ ሕይወት ልምዳቸው ስላጋሩን እግዚአብሔር ይስጥልን የአገልግሎት ዘመናቸውን ይባርክልን ። እግዚአብሔር በብዙ መንገዶች ይናገራል ለእኔም ዛሬ እንዲህ ሆነልኝ።ለጃንደረባው ሚድያ እግዚአብሔር ይስጥልኝ።