በትምህርት ቤት የማውቀው አንድ ወንድሜ ሁልጊዜ ከምንለዋወጠው የተለየ ደብዳቤ ላከልኝ፡፡ እንደተለመደው መስሎኝ ደብዳቤውን ከፍቼ እስከማየው ቸኮልሁ፡፡ ገና የመጀመሪያውን መስመር ሳነበው ደም የሚያደርቅ ንባብ ተጽፎበት አገኘሁት ደግሜ አነበብሁት፤ አገልግሎት ላቆም ነው ይላል፡፡ መጨረስ ቢያቅተኝም መጨረስ ስለነበረብኝ እየመረረኝ ጨረስሁት፡፡ የመጨረሻው መስመር ላይ እየቀለድሁ ነው የሚለኝ መስሎኝ እጠብቅ ነበር፡፡ ግን አልሆነም፡፡ መረረኝ፤ ሰዎች አላሠራኝ አሉ፡፡ ቤተ ክርስቲያኒቱማ ሕጓ የቀና፣ ሥርዓቷ የተስተካከለ ዜማዋ የሚናፍቅ፣ ማኅሌቷ የሚደነቅ፣ ቅዳሴዋ የሚመስጥ ነበር ነገር ግን በሰዎች ግፊት ከዛሬ ጀምሮ ሁሉንም ትቼ ወጥቻለሁ አለኝ፡፡
አገልግሎት ይቋረጣል? ሰው ያለ አገልግሎት ይኖራል? አገልግሎቴን ላቆም ነው ማለትስ ምን ማለት ነው? በቅንነት በሚያገለግሉ አገልጋዮችስ ላይ ተስፋ የሚያስቆርጡ ሰዎች የሚበዙት ለምንድነው? የሠራኸው አይመቻቸውም፤ እንዳይሠሩት ዐቅሙም ፍላጎቱም የላቸውም፡፡ እያልሁ በጥያቄ ራሴን አስጨነቅሁት፡፡
አይሁድ በሞሏት በኢየሩሳሌም አገልግሎትን መጀመር እንዴት ከባድ ነው? ድውይ ብትፈውሱ ሰንበት ነው ይሏችኋል፡፡ ውኃ ከዐለት ላይ ብታፈልቁ “ደጋ ስለሆነ ውርጩን እያረጋ ውኃ አፈለቅሁ ይላል እንጅ ቆላ ቢሆን አይችልም ነበር” ብለው ያሟችኋል፡፡ ትምህርታችሁን ይወዳሉ፤ ነገር ግን አባቱን የምናውቀው የዕገሌ ልጅ አይደለምን? ብለው ያናንቋችኋል፡፡ እንደዚህ ካሉ ሰዎች ጋር ማገልገል እንዴት ይቻላል? ከእነዚህ ሰዎች መካከል መኖር በጣም ከባድ ነው፡፡ ግን የእግዚአብሔር ፈቃድ እንዲሁ ነውና ሆነ፡፡
ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት የጀመረችው በክፉዎች አይሁድ መካከል ነው፡፡ እጅ መንሻ የያዙ ሰዎች ክርስቶስ ወደ ተወለደበት ቦታ መጡ እንጅ ክርስቶስ እጅ መንሻ ወደ ሚያቀርቡለት ነገሥታት ከተማ ሂዶ አልተወለደም፡፡ በተወለደበት ቦታ ያሉ ሰዎች አላወቁትም አብረውት ያደጉ የናዝሬት ሕጻናትም አላከበሩትም፡፡ ሁሉም ክፉዎች ስለነበሩ አብረውት ካደጉት መካከል ለደቀ መዝሙርነት መዐርግ የበቃ ማንም የለም፡፡ በክፉዎች መካከል ተመላለሰ፡፡ የቤተ ክርስቲያንን አገልግሎት ከዕለተ ምጽአት በፊት ንስሐ መግባት በማይችሉት ክፉ ሕዝቦች መካከል መሠረታት፡፡ በጣም የሚገርመው እንደ እስራኤላውያን ትንቢት ተገልጾላቸው ሱባኤ ገብተው ባያውቁትም የክርስቶስን መምጣት በፍልስፍናቸው በጥበባቸው ተመራምረው አግኝተው ቀኑን እየጠበቁ የነበሩ አሕዛብ ነበሩ፡፡ ፍርዱ ለኛ ቢሰጠን “ከሀገራችን ውጣልን” ማቴ 8÷34 ብለው ከሚለምኑ ሰዎች መካከል ከሚኖር የሐዋርያትን መምጣት እየተጠባበቁ በነበሩ በግሪክ ፈላስፎች ጉባኤ መካከል ቢኖር ደስ ይለን ነበር፡፡
አንድ አስደናቂ ለፍርድ የሚያስቸግር የሥነ ፍጥረት ታሪክ ላጋራችሁ፡፡ ውኃ ልህሉህ ነው፤ ነገር ግን በደደረው የዐለት ደረት ላይ እንዲፈስ መደረጉ ለምንድነው? መሬት ጽኑ ነው ነገር ግን በልህሉህ ውኃ ላይ እንዲንሳፈፍ ሆኖ መፈጠሩ ለምንድነው? እኔ ሲገባኝ ውኃ ንጽሕናውን ጠብቆ እንዲኖር በጠነከረ ዐለት ላይ መፍሰስ አለበት፡፡ የውኃ መንገዱ እንዳይቋረጥ ከተፈቀደለት ውቅያኖስ ድረስ ለመፍሰስ ከድንጋይ ጋር እተጋጨ መቀጠል ግድ ሆኖበታል፡፡ ድንጋዩ ከቆመበት ፈቀቅ ባለማለቱ፤ በውኃው መንገድ ላይ ቆሞ አንዳንዴ ውኃው መንገዱን ለቅቆ እንዲሄድ ቢያደርግም ውኃውን በመሬት ውስጥ ሰርጎ የመሬት ሲሳይ ሆኖ ከመቅረት የታደገው ዐለቱ ድንጋይ ነው፡፡
ውኃና ድንጋይ ቢካሰሱ መንገዴን ይልቀቅልኝ፤ አፈሩን ጠርጌ ባወጣሁት መንገድ መካከል እየገባ አስቸገረኝ ቢላችሁ ለማን ትፈርዳላችሁ? ከላይ ስናየው ውኃ ያቀረበው ክስ እውነት ነው፡፡ ነገር ግን ድንጋዩ ቢነሳ ዐለቱ ተሰብስቦ ቢወገድ የውኃን መንገድ ማን ያጸናለታል፡፡ ውኃ መንገዱን ጠብቆ እንዲሄድ በሜዳ ፈስሶ እንዳይቀር ዳርና ዳሩን ማን ይጠብቅለታል? በዳር ያለው አፈር ተደርምሶ የውኃን መንገድ እንዳይዘጋ ጠባቂ ሆኖ የተቀመጠውን ድንጋይ ከውኃ ጋር መጋጨቱን አንዳንድ ጊዜም የውኃን መንገድ ማስቀየሱን የተመለከተ ሰው ድንጋዩን ለማስወገድ ጥረት ያደርግ ይሆናል፡፡ አለበለዚያም ለውኃ ሌላ ድንጋይ የሌለበት መንገድ መፈለግ ያምረው ይሆናል፡፡
እስኪ አስቡት ባክኖ፣ በሜዳ ፈስሶ ከመቅረት ያዳነውን፤ ከመሬት ጋር ተቀላቅሎ ውበት ንጽሕናውን አጥቶ እንዳይኖር የጠበቀውን ዐለት ውኃን የሚያማታው፣ እንዲጮኽም የሚያደርገው እሱ ነውና ይውጣ አለበለዚያም መንገድ እንቀይርለት እንዴት ይባላል?
በኛም የአገልግሎት ስፍራ እንዲሁ ነው፡፡ ክፉ ሰዎች የሌሉበት አገልግሎት ያለው በሰማዩ ቤተ መቅደስ ብቻ ነው፡፡ እዚያ ገብተን ማገልገል እስክንጀምር ድረስ በሃይማኖት የሚመስሉን ከሆነ ከሁሉም ሰው ጋር እንሰለፋለን፡፡ እነዚህ ሰዎች ላወቀባቸው ሰው የጸጋ ምንጭ ናቸው፡፡ እንደዛማ ባይሆን ኖሮ ጌታ በቅዱስ ወንጌል “ሲነቅፏችሁና ሲያሳድዷችሁ በእኔም ምክንያት ክፉውን ሁሉ በሐሰት ሲናገሩባችሁ ብፁዓን ናችሁ ዋጋችሁ በሰማይ ታላቅ ነውና ደስ ይበላችሁ” ማቴ 5÷11 ባላለንም ነበር፡፡ የዚህ ቃል ኪዳን ተጠቃሚ የምንሆነው እንዲህ ካሉ ሰዎች ጋር ታግለን ስናሸንፍ እንጅ መንገድ ስንቀይር አለበለዚያም አገልግሎት ስናቋርጥ አይደለም፡፡
የቆሎ ተማሪዎች ሆነን ልመና ስንወጣ የአንበሳ ደቦል የሚያኽል ውሻ ያጋጥመናል፡፡ አለመለመን ለረሀብ አሳልፎ ይሰጣል፤ መለመንም ከውሻ ጋር ያታግላል፤ እልፍ ካለም ያስነክሳል፡፡ ሆኖም ግን የተማሪው ምርጫ ከውሻው ጋር ታግሎ እንጀራ ማግኘት ነው፡፡ አንድ አገልጋይም በአገልግሎት ጎዳናው ላይ የሚያደናቅፉት ሰዎች ቢኖሩ እነዚያን ከአንበሳ ዝቅ የሚሉ ውሾች ታግሎ እንጀራ እንዳገኘ ታግሎ ጸጋ እግዚአብሔርን መውረስ ነው፡፡
ባሳለፍነው ጊዜ ረሀቡን የታገሥነው፤ ፊታችን ላይ ጓደኞቻችን ትምህርት ፍለጋ መጥተው በቆላ ወባ (ወረርሽኝ) ተነድፈው ሲሞቱ እያየን ቀብረን ተመልሰን ትምህርታችንን የቀጠልነው ቤተ ክርስቲያኒቱን አስበን እንጅ እነዚህን ሰዎች አስበን አይደለም፡፡ በደመና ጊዜ ፀሐይ ቢያምረን ደመናው እስኪያልፍ መታገሥ ግድ ነው፡፡ ደመናውን ማን ይገፋዋል? ደመና ወደ ሌለበት ስፍራ በፍጥነት መዘዋወርስ ለማን ይቻለዋል? ደግነቱ ደመናው አላፊ ነው፤ ፀሐይ ግን ለዘወትር የሚኖር ነው፡፡ ክረምት የሚረገረገው ደመና የበጋውን ፀሐይ ካስረሳን ችግሩ እኛ ላይ ነው፡፡ ሁል ጊዜ ከደመናው ጀርባ ፀሐይ መኖሯን አስተውሉ፡፡ ፀሐይ ስትወጣ ደግሞ ይሄ ሁሉ ቆፈን አድራሻው እንደማይገኝ ልብ በሉ፡፡ አገልግሎታችንን አንተውም፤ ትግላችንንም ከሰዎቹ ጋር አናደርግም፡፡ ብዙ ጊዜ ሰዎችን በየደረጃው ካለው አገልግሎት የሚያርቃቸው ትግላቸውን ከሰዎች ጋር ስለሚያደርጉት ነው፡፡
ሰዎችን ለመለወጥ አትሞክር ሥራህን አስተካክለህ ቀጥል፡፡ ጌታ ጸሐፍት ፈሪሳውያንን ለመለወጥ ጊዜውን አላባከነም፡፡ ለቤተ ክርስቲያን ሊያሳያት የሚገባውን አገልግሎት ግን በሚገባ አከናወነ፡፡ ፈሪሳውያን በጥያቄ ሲፈትኑት፣ ከነገሥታት ነገር ሲሠሩበት፣ በቤተ መቅደስ ሲዶልቱበት ስለእነሱ “ዘለፋ ካህናትን” ማቴ 23÷1 ካስተማረበት ጉባኤ በቀር የትምህርቱ ርዕስ አድርጓቸው አያውቅም፡፡ እኛ ግን የወሬ ርዕስ የምናደርገው የሚያግዙንን የሚረዱንን ሰዎች ሳይሆን አላሠራን ያሉትን ሰዎች ነው፡፡ ደጋግመን የምንሰብከው አንቀፀብፁዓንን ሳይሆን ዓሌ ለክሙን ነው፡፡ መሸነፍ ከዚህ ይጀምራል፡፡
አንተ ግን ይህን አታድርግ! እባብና ጊንጥ በበዛበት በረሀ ቢጥሉህም ለተራበ አንበሳ ቢሰጡህም፤ በነደደ እሳት ቢከቱህም፤ ሰይፍ እየሳሉ ብታያቸውም፤ አገልግሎትህን እተዋለሁ አትበል፡፡ ከአርባ ሐራ ሰማይ አንዱ አክሊል ለመቀበል አንድ ቀን ሲቀረው አገልግሎቱን ቢያቋርጥ ከወንድሞቹ ተለይቶ ከክብር ጎድሎ ሞተ፡፡
አንተ በአገልግሎትህ አክሊል የምትቀዳጅባት ሰዓት ያች አገልግሎትህን ተስፋ ቆርጠህ የተውክባት ሰዓት ብትሆንስ? ወደ እግዚአብሔር የምትጠራባት ዕለት ያች ብትሆንስ ምን ታውቃለህ? አገልግሎት የሚቋረጥ ቢሆን ኖሮ ዮሐንስ መጥምቅ ከሞተ በኋላ እንዲያርፍ እንጅ የተቆረጠች አንገቱ ክንፍ ተሰጥቷት እየዞረች ለሰባት ዓመታት ስትሰብክ ባልሰማናትም ነበር፡፡ አየህ በሕይወት ሳለ ስድስት ወር ብቻ የሰበካትን ወንጌል ከሞተ በኋላ ግን ሰባት ዓመት ሰበካት፡፡ ዓላማ ካለህ አገልግሎትህን እንኳን ሰዎች ሞት አያቋርጥህም፡፡
ማስታወሻ:- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
ፀጋውን ያብዛሎት መምህራችን ትልቅ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር። እውነት ነው አገልግሎት አይቋረጥም
ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር…!
ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህር..!
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
በእውነት መምህር ቃለ ህይወትን ያሰማልን
መለሱኝ የኔታ ትላንት በአንዳንድ ምክንያቶች ከአገልግሎት ትንሽ ለማረፍ ወስኜ ለወንድምና እኅቶቼ ተነግሬ ነበር አጋጣሚ ሆኖ ይኼን አነበብኩ የሚገርመው እስካሁን የማንበቡ ፍላጎት ቢኖረኝም ከፍቼ አንብቤ አላውቅም ነበር ሥላሴ ዓላማ አለው🙏
ቃለ ሕይወት ያሰማልን🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
Kale hiwot yasemaln melkam eyitan enday adrgognal
ለፍሬ ያድርግልን
አባታችን ቃለ ህይወትን ያሰማልን ትልቅ ትምህርት ነው የወሰድኩት
ቃለሕይወት ያሰማልን።
እግዚአብሔር ይስጥልን የኔታ።
(የዮሐንስ ራእይ 3 :10-11 )
———-
” የትዕግሥቴን ቃል ስለ ጠበቅህ እኔ ደግሞ በምድር የሚኖሩትን ይፈትናቸው ዘንድ በዓለም ሁሉ ላይ ሊመጣ ካለው ከፈተናው ሰዓት እጠብቅሃለሁ።
፤ እነሆ፥ ቶሎ ብዬ እመጣለሁ፤ ማንም አክሊልህን እንዳይወስድብህ ያለህን አጽንተህ ያዝ።”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
መምህር ይህን ፅሁፍ በግሩፕ ቴሌግራም ላይ አነበብኩት ስጀምር እንደ ልብ ወለድ ተመስጬ ነበር ነገር ግን የሆነ ቦታ ላይ ቀየረኝ በጣም ጉልበት ህይወት የሚሆን ትልቅ ምክር ተግሳፅ የታከለበት ተነቦ ብቻ የማይታለፍ ወደ ህይወታችን የምንቀይረው በተግባር የሚተገበር መሆኑን አሳየኝ
ደጋግሜ ባነበው በውስጤ ባስቀረው በተግባር ብተገብረው ተመኘሁ እግዚአብሔር አምላክ በቤቱ ያለ መሠልቸት በተሠጠን መክሊት ፀንተን የምናገለግል የበረከቱ ተቋዳሽ እንዲያደርገን ይርዳን
አሰበ መምህራንን ያድልልን
አባ ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
በጣም ድንቅ ጥበብ ያለበት፣ ሰውን ከሌላ ሰው ሳይሆን፣ ከገዛ ራሱ ፍርሃት ነጻ የሚያወጣ ትምህርት ነው የሰጡን።
ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ሐይማኖታችን ፈተናዎች፣ ተግዳሮቶች እና ችግሮች ንጽህናችንን እንድንጠብቅ የሚያግዙን እና በመጨረሻም የምንቀዳጀውን የድል አክሊል የሚያስገኙልን ጥቅሞቻችን እንደሆኑ የምናይበትን የጥበብ ዓይናችንን የሚያበሩ ብቻ ሳይሆን በትክክለኞቹ የጦር እቃዎች የሚያስስታጥቁን እነዚህን የመስሉ እስተምህሮቶች እንዳሏት ብናውቅ ኖሮ የሩቅ ምስራቁን እና የምዕራቡን ዓለም አስተምህሮቶችና ፍልስፍናዎች አንቀላውጥም ነበር።
ፈተናን መቋቋም እንደሚያሸልም ሁላችንም በሚያስብል ድረጃ አብዛኞቻችን እናውቃለን። ግን ስንቶቻችን በተግባር አዋልነው? መልሱ ግልጽ ነው። ለዚህ ደግሞ ከምክንያቶቹ ዋነኛው ፈተናን መቋቋማችን የሚያስገኝልን ጥቅም የሚነገረን እንዲሁ በደረቁ እንጂ የጥበብ ዓይናችንን በሚያበራና “አሃ!” በሚያስብል ደርጃ ባለመሆኑ ነው።
አምላከ ቅዱሳን እንደ እርስዎ ያሉ መምህራንን ያበርክትልን! አሜን!
Kale heywet yasemalen abatachen
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
እግዚአብሔር ይስጥልን ፤ መምህራችን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
በእውነት መምህር ቃለ ህይወትን ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን የኔታ የአገልግሎት ዘመኖትን ይባርክልን
ዋ!!! ዋ!!! ድንቅ ትምህርት ምን ያደርጋል ይህ ትምህርት ቀደም ብለው ብዙ ውንድሞች እህቶቻችን ቢስ ሙት ጥሩ ነበር በብዙ መገፋት እያዘኑ ከአገልግሎት እርቀው የሸሹ ቤት ይቁጠራቸው ።
አሁንም ተከፍተው ሊወጡ የተዘጋጁ እግዚአብሔር ያበርታችሁ እያልን ይህን መልእክት ብናጋራቸው መልካም ነው ።
እናተዪ ለካ አገልግሎት የሚቋረጠው ከዝች ዓለም ድካም በእረፍት ሲገቱ ብቻ ነው ።
እግዚአብሔር ይስጥልን ይኔታ !!!
ቃለ ህይወት ያሰማልን መምህራችን
“ሰዎችን ለመለወጥ አትሞክር ሥራህን አስተካክለህ ቀጥል”
ቃለ ህይወትን ያሠማልን!!
ቃለ ሕይወት ያሰማልን ሊቀ ሊቃውንት!
ድንቅ ትምህርት