ንፁህ እና እውነተኛ ፍቅር ለምንወደው ሰው ያለ ምንም ገደብ ታላቅ ነፃነትንና ሰላምን ይሰጣል። ይህም ሰላም እና ነፃነት የሚፈጠረው ከምንም በላይ አብልጠን የምንወደው ሰው ከቶ በኛ ቁጥጥር ውስጥ እንዲሆን ባለመፍቀዳችን ነው። ማለትም አንድን የምንወዳትን ወፍ በማሰርያ ውስጥ አስረናት የኛ እንድትሆን ከማድረግ ይልቅ እንደልቧ እንድትበር ፈቅደን ነገር ግን ቤት አዘጋጅተንላት በነጻነት በራሷ ፍላጎት ተመልሳ ወደሰራንላት ቤት እንድትመጣ ነፃነትን መስጠት እንደማለት ነው።
እግዚአብሔር ለኛ ያለው ፍቅርም እንዲህ ያለ ነው። ከእርሱ የተሰጡን ትእዛዛቱም ቢሆን የሚገድቡ ሳይሆኑ ይህን ነጻነት በመጠቀም ወደ ላይ እንድንወጣ የሚያስችሉን ናቸው። ሐዋርያው ጳውሎስ ለቆሮንቶስ ሰዎች በጻፈው መልእክቱ የፍቅርን ምንነት ባማረ ሁኔታ ገልጿል:: የፍቅርን ታጋሽ፣ ደግ እና ከራስ ወዳድነት ነፃ የሆነውን መገለጫዎቹን አፅንዖት ሰጥቷል። (ቆሮ 13፥4-7)። ይህ በእውነተኛ ፍቅር ውስጥ ያለውን ነፃነት ለመረዳት መሠረት ይጥላል። ሆኖም በዚህ ነፃነታችን ሁሉም ነገር ተፈቅዶልናል ወይም ፈጣሪ ለእኛ ደንታ እንደሌለው የሚያመለክት እንዳልሆነ ልብ ማለት ያስፈልጋል። ይልቁንም፣ እግዚአብሔር በእኛ ላይ በኃይል መጫንን ሳይሆን ከእርሱ ጋር ያለን ግንኙነት በፈቃዳችን እና በምርጫችን ላይ የተመሠረተ ግንኙነት እንዲሆን ስለሚፈልግ ነው።
በራእይ መጽሐፍ ውስጥ የክርስቶስ በነፍሳችን ደጃፍ ላይ ቆሞ መገኘቱ በፍቅር የተሞላ እና የነፍሳችን በር እንድንከፍት የሚያበረታታ ለስለስ ያለ ማንኳኳት ሆኖ ተገልጧል። “እነሆ፣ በደጅ ቆሜ አንኳኳለሁ። ማንም ድምፄን ቢሰማ ደጁንም ቢከፍትልኝ ወደ እርሱ እገባለሁ ከእርሱም ጋር እራት እበላለሁ እርሱም ከእኔ ጋር ይበላል።” (ራእይ 3፥20) የሚደንቀው ነገር ግን በምንታመምበትና በችግር ውስጥ ባለንበት ሰዓት እራሱ በኃይል ከመግባት ቁጥብ መሆኑ ነው። “መዳን ትፈልጋለህ ?” ብሎ ይጠይቃል። (ዮሐንስ 5፥6 ፣ ማርቆስ 10፥51) ይህም ለእኛ ለተሰጠን ነፃነት ያለውን አክብሮት በይበልጥ ያሳየናል።
በቅዱስ ቃሉ “የራሳችሁ አይደላችሁም ፤ በዋጋ ተገዝታችኋል ። ” (1ኛ ቆሮንቶስ 6፥20) ተጽፎ ብናገኝም በሌላ በኩል ደግሞ በደሜ ገዝቻችኃለውና ብሎ ባርነትን አለመጣሉን፣ በፍቅሩ የነጻነትን ካባ እንዳለበሰን ሲያሳየን ኢሳይያስ በትንቢቱ “እርሱ ግን ስለኅጢአታችን ቈሰለ፤ ስለ በደላችንም ታመመ፤ የሰላማችንም ተግሣጽ በእርሱ ላይ ነበረ፤ በእርሱም ቍስል እኛ ተፈወስን።” (ት.ኢሳ 53፥5) ሲል ይነግረናል። ፍቅራችን ንፁሕና እውነተኛ ከልብ የመነጨ ሲሆን ገደብ እና ወሰን ሊኖረው አይችልም።
እንወደዋልን ያልነው ሰው ድርጊት እና ለኛ ፍቅር ያለው ምላሽ ያንን ሰው መቼም ቢሆን እንድንጠላው አያደርገንም ተግባሩ / ምላሹ ላያስደስተን ይችላል ልክ ክርስቶስ በንጹህ ፍቅሩ ስለወደደን ብዙ ጅራፍ ሲገርፉት እንደታገሠ ሁሉ የወደድነው ሰው ድርጊት ቆስለን እንኳ ውስጣችን ያለው ፍቅር ንጹሕ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከዚያ ሰው ምንም አይነት ምላሽ የማይፈልግ ሲሆን ያን ሰው ልንጠላው አንችልም። ምክንያቱም “ፍቅር ታጋሽ ነው፤ ደግሞም ቸር ነው። ፍቅር አይመቀኝም፤ አይመካም፤ አይታበይም፤ ተገቢ ያልሆነ ነገር አያደርግም፤ ራስ ወዳድ አይደለም፤ አይበሳጭም፤ በደልን አይቈጥርም። ፍቅር ከእውነት ጋር እንጂ በዐመፃ ደስ አይሰኝም።ፍቅር ሁልጊዜ ይታገሣል፤ ሁልጊዜ ያምናል፤ ሁልጊዜ ተስፋ ያደርጋል፤ ሁልጊዜ ጸንቶ ይቆማል።” (1 ቆሮ 13፥4-7)
ስለሆነም በዚህ በሰጠን ፍጹም ነጻነት ምክንያት ክርስቶስ ዘወትር የነፍሳችንን በር የማንኳኳትን ጨዋነት ይጠብቃል፣ ከእርሱ ጋር ያለንን ግንኙነት በፈቃዳችን ላይ ያተኮረ እንዲሆን ይፈልጋል፤ እንዲህ ዓይነቱ ፍቅር መለኮታዊ የነፃ ምርጫ ስጦታ ነውና። ማለትም በመሠረታዊነት፣ በምርጫ ላይ የተመሠረተ እና የአንድ ግለሰብ ፍቅርን ለመቀበል እና ለመመለስ የሚደረግ ውሳኔ ላይ ይመሰረታል። ይህም ፍቅር ጥልቅ እና ነፃ የሚያወጣ በሁለት ልቦች መካከል ያለ መጣበቅ ነው። ለዚህም ነው ሊቁ አውግስጢኖስ “ለእግዚአብሔር በሙሉ ልብ መገዛት ከሁሉ የላቀ ፍቅር ነው፤ እርሱን መሻት ትልቁ የሕይወት ጉዞ ፤ እሱን ማግኘት ደግሞ ትልቁ የሰው ልጅ ስኬት ነው” በማለት የተናገረው።
“ይህ እንዴት ይሆናል ለሰው ይህ እንዴት ይቻለዋል? እኛ ይሄን እንዴት ልናደርግ ያቻለናል?” የሚል ጥያቄን ሊጭርብን ይችላል። ነገር ግን ክርስቶስ ከእመቤታችን ሥጋን በተዋሐደበት ወራት አምላክነቱ ሳይለወጥ ፍጹም ሰው ሆኖ አልነበረ? ፍቁረ እግዚእ ቅዱስ ዮሐንስ “ያም ቃል ሥጋ ሆነ፤ በእኛም አደረ፤ ለአባቱ አንድ እንደ ሆነ ልጅ ክብር ያለ ክብሩን አየን፤ ጸጋንና እውነትን የተመላ ነው” (ዮሐ 1:14) ብሎ የተናገረው ስለ ክርስቶስ አይደለምን? ቅዱስ ጳውሎስስ ወደ ዕብራውያን በጻፈው መልዕክቱ “ሊቀ ካህናታችን ለድካማችን መከራ መቀበልን የማይችል አይደለምና፤ ነገር ግን ከብቻዋ ከኀጢአት በቀር እኛን በመሰለበት ሁሉ የተፈተነ ነው። እንግዲህ ምሕረትን እንድንቀበል፥ በሚያስፈልገንም ጊዜ የሚረዳንን ጸጋ እንድናገኝ፥ ወደ ጸጋው ዙፋን በእምነት እንቅረብ” (ዕብ 4:15-16) በማለት የተናገረው ስለ ክርስቶስ አይደለምን? እናስ እርሱ ይህ ፍቅር በሰው ዘንድ የሚቻል መሆኑን ወድዶ አሳይቶን የለ? ይሄስ ማለትም ለሰው ይቻላል ማለት ነው::
ክርስቶስ ባረገበት ጊዜ ቃል በቃል “ትእዛዜ ይህች ናት፤ እኔ እንደ ወደድኋችሁ እናንተም እርስ በርሳችሁ ተዋደዱ” ብሎን ትእዛዝ ሠጥቶን ዐርጎአል:: (ዮሐ 15፥12) ይህ የሚያሳየን የሚቻል መሆኑን ብቻ ሳይሆን እንድናደርገው የታዘዝነው መሆኑንም ጭምር ነው። ለኔ አይቻለኝም እንዳንልም ጌታ በወንጌል “ ለምኑ፤ ይሰጣችሁማል፤ ፈልጉ፤ ታገኙማላችሁ፤ መዝጊያን አንኳኩ፤ ይከፈትላችሁማል። የሚለምነው ሁሉ ይቀበላልና፤ የሚፈልገውም ያገኛል፤ መዝጊያንም ለሚያንኳኳ ይከፈትለታል።” (ማቴ 7፥7-8) በማለት ተናግሯል።ሲጀምር እኛ ያለእሱ ምንም ማድረግ አንችልም ይህንንም ጌታ እራሱ “ እኔ የወይን ግንድ ነኝ ፤ ቅርንጫፎ ቹም እና ንተ ናችሁ፤ በእኔ የሚኖር እኔም በእ ርሱ፥ ብዙ ፍሬ የሚያፈራ እርሱ ነው፤ ያለ እኔ ምንም ማድረግ አትችሉምና” (ዮሐ 15፥5) ብሎናልና።
እናም እርሱ ይህን ማድረግ እንደሚያስችለን በመጀመሪያ “ ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” (ፊልጵ. 4፥13) በማለት የሚቻለን መሆኑን ማመን ይጠብቅብናል። ምክንያቱም ክፉውን ለማድረግ ስንነሣ አጋንንት እንደሚተባበሩን ሁሉ መልካሙን ማድረግ ስንነሣ ረድኤተ እግዚአብሔር ወደ እኛ ትቀርባለች በዚህ ሒደት ውስጥ ክርስቶስን መምሰልን ገንዘብ እናደርጋለን:: እርሱ ጌታን ወደመሆን የቀረበው ሰው ደግሞ ዓለም ሳይፈጠር ክርስቶስ ያዘጋጀለትን ሽልማት ይቀበላል። ክርስቶስን በሕይወቱ ብዕር ለመሳል ደክሟልና፥ የጌታ የምሕረት እጆችም ይዘረጉለታል፤ በእርሱም እቅፍ ለዘለዓለም ይኖራል።
This is a very good and touching message!
Please keep up with it. May the Lord bless you!
እግዚአብሔር ይስጥልን፣
ቃለህይወት ያሰማልን፣
መንግስተ ሰማያት ያዋርስልን።
ደስ የሚል ትምህርት ነዉ። እግዚአብሔር ፍቅርን ያብዛልን 🙏🙏🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን 🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወትን ያሰማልን! ፍቅሩን እንድንረዳውና እርሱ እንድናየው እና እንድናውቀው በሚፈልገው መልኩ እንረዳው እናውቀውም ዘንድ ልቦናችንን በፍቅሩ ብርሃን ይግለጥልን።
እግዚአብሔር አምላክ የህይወትን ቃል ያሰማልን ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያዋርስልን በቤቱ ያጥናልን ።
ቃለ ህይወትን ያሰማልን
Waaqayyo sagalee jireenyaa si haa dhageessisu.
ለእግዚአብሔር በሙሉ ልብ መገዛት ከሁሉ የላቀ ፍቅር ነው፤ እርሱን መሻት ትልቁ የሕይወት ጉዞ ፤ እሱን ማግኘት ደግሞ ትልቁ የሰው ልጅ ስኬት ነው”
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን ጆ
ቃል ህይወትን ያሰማልን🙏
ልብ ያረሰርሳል የእግዜር ቃል ድንቅ ነው
መዳን መንፃት መድረስ ደም ስጋውን ወስዶ
ይህን ሲጨምር ነው።(እንደኔ)
ቃለ ህይወት ያሰማልን መንግስተ ሰማያት ያውርስልን ወንድማችን 🙏🙏🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን ወንድማችን
እንወደዋልን ያልነው ሰው ድርጊት እና ለኛ ፍቅር ያለው ምላሽ ያንን ሰው መቼም ቢሆን እንድንጠላው አያደርገንም ተግባሩ / ምላሹ ላያስደስተን ይችላል ልክ ክርስቶስ በንጹህ ፍቅሩ ስለወደደን ብዙ ጅራፍ ሲገርፉት እንደታገሠ ሁሉ የወደድነው ሰው ድርጊት ቆስለን እንኳ ውስጣችን ያለው ፍቅር ንጹሕ እና ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከዚያ ሰው ምንም አይነት ምላሽ የማይፈልግ ሲሆን ያን ሰው ልንጠላው አንችልም።😍
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን 🙏
ቃለ ህይወት ያሰማልን ! በቤቱ ያጽናህ
ቃለ ህይወትን ያሰማልን
ይሄን ጽሑፍ እጅግ ወድጄዋለሁ እንዴት እኔ ጋር ማስቀረት ችላለሁ ሁሌ እንዳነበው???
ቃለ ህይወት ያሰማልን
May GOD bless you.
ቃለ ህይወትን ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
Kale hiwot yasemalen
ቃለ ሕይወት ያሰማልን።
ጽሑፋ የሕግ ሁሉ ፍጻሜ ስለሆነው ፍቅር ነው አይደል? ፍቅረ እግዚአብሔር ና ፍቅረ ቢጽ
ፍቅርንም ራሱ መደኃኒታችን እንዳስተማረን እንዳደረገው የሆነው ያየነው እንደሆነ ና ይሕን ፍቅረ ቢጽ ደሞ ለሰው ልጆች ሁሉ ሳናዳላ እንደናደርገው ነው እንጂ ለጾታዊ ፍቅር የተጠቃለለ እንዳልሆነ እረዳለሁ
እግዚአብሔር ይስጥልን፣
ቃለህይወት ያሰማልን፣
መንግስተ ሰማያት ያዋርስልን።