| ጃንደረባው ሚድያ | ታኅሣሥ 2016 ዓ.ም.|
አዲስ አበባ – ኢትዮጵያ
የመድኃኔዓለም ክርስቶስን በዓለ ልደት ዋዜማ ምእመናን በዝማሬ እንዲያከብሩ በማሰብ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ (ኢጃት) “የአእላፋት ዝማሬ”ን ከመስከረም 2 2016 ዓ.ም. ጀምሮ ይፋ ማድረጉ ይታወሳል::
“የአእላፋት ዝማሬን” ለማካሔድ የታሰበበት የመጀመሪያው ቦታ መስቀል አደባባይ የነበረ ሲሆን የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ ጽሕፈት ቤት ኅዳር 15 2016 ዓ.ም. ለመንግሥት አካል ደብዳቤ በማስገባት እና በግንባር ተገኝቶ ለሚመለከተው አካል “የአእላፋት ዝማሬን” ምንነት በማስረዳት መንግሥት ለዝማሬው ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጥያቄ ቀርቦ ነበር:: በመንግሥት አካላትም ሀገሪቱ ካለችበት ነባራዊ ሁኔታ አንጻር በመስቀል አደባባይ ሁነቱን ለማካሔድ እንደሚያስቸግር ምላሽ የተሠጠ በመሆኑና አዘጋጅ ኮሚቴውም በኤግዚቢሽን ማእከል ባለው የንግድ ትርዒት ምክንያት ቀድሞ የተያዙ ነገሮች እንቅፋት ሊሆኑ እንደሚችሉ በዘርፉ ልምድ ካላቸው የቤተ ክርስቲያን ልጆች መረጃ በማግኘቱ በጥያቄው ላይ ብዙም ሳይገፋበት ቀርቶአል::
ሁለተኛው “የአእላፋት ዝማሬ”ን ለማካሔድ የተመረጠው ሥፍራ የጃን ሜዳ ጥምቀተ ባሕር ሥፍራ ነበረ:: በሥፍራው ዝግጅቱን ለማድረግም በሀገረ ስብከቱ በኩል ከሚመለከተው የመንግሥት ቢሮ ሓላፊዎች ጋር ደብዳቤ ገብቶ ምላሽ በመጠባበቅ ሒደት ላይ ቆይቶአል::
ይህ በሒደት ላይ እንዳለ ደግሞ “የአእላፋት ዝማሬን” ወደ ጃን ሜዳ ለማድረግ ከመታሰቡ አስቀድሞ በጠቅላይ ቤተ ክህነት በኩል እና ከሚመለከተው አካል ተገቢው ፈቃድ ተጠይቆበት ሊካሔድ በነበረው በ”ተዋሕዶ ኤክስፖ” ላይ የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድም ተሳታፊ ከነበሩ የቤተ ክርስቲያን ማኅበራት አንዱ ነበረ:: በመሆኑም በሥፍራው ኢጃት በተሠጠው ቦታ ላይ ከዲዛይን ጀምሮ ብዙ ወጪ በማውጣት የማሳያ ቦታ ግንባታ ካደረገ በኋላ ባልተጠበቀ መልኩ ዝግጅቱ በመቋረጡ እና ዕቃዎቻችሁን አንሱ በመባሉ ከአቻ ማኅበራት ጋር የሥነ ልቡና ፣ የገንዘብ እና የጊዜ ኪሳራን አስተናግደናል::
ይህ በእንዲህ እንዳለ “የአእላፋት ዝማሬ”ን በጃን ሜዳ ለማካሔድ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ደብዳቤ የተጻፈ ሲሆን ብፁዕነታቸው ከሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጅና ከአእላፋት ዝማሬ ተወካዮች ጋር በመሆን ከከተማው የጸጥታ ሓላፊዎች ጋር ስብሰባ በመቀመጥ የአእላፋት ዝማሬን ዓላማና ለሀገር ገጽታም ሆነ ለወጣቶች ሕይወት ያለውን ማኅበራዊ ፋይዳ በማስረዳት መንግሥት ተገቢውን ትብብር እንዲያደርግ ጠይቀዋል:: በመንግሥት ሓላፊዎች በኩል ለመሠረታዊ ሃሳቡ ያላቸውን በጎ ሃሳብ በመግለጽ “ፈቃድ ለመሥጠትና ጥበቃ ለማድረግ ግን ከጸጥታ አካላት ጋር ተነጋግረን እናሳውቃለን” የሚል ተስፋ ተሠጥቶ እስከ አሁን በመጠባበቅ ላይ ነበረ::
በመጨረሻም ለሀገረ ስብከቱ ጽሕፈት ቤት የተሠጠው ምላሽ “ከፍተኛ የጸጥታ ሥጋት ስላለ እና መንግሥት ባለው መረጃ መሠረት በመንፈሳዊ መድረክ ሰበብ ሊፈጸሙ የሚችሉ የሽብር ድርጊቶችም ሊኖሩ ስለሚችሉ ታኅሣሥ 27 የታሰበውን ዝግጅት በጃንሜዳ ማከናወን አይቻልም” የሚል ነው::
በዚህ ምክንያት የታኅሣሥ 27 2016 ዓ.ም. የመጀመሪያው የገና “የአእላፋት ዝማሬ” በቦሌ ደብረ ሳሌም መድኃኔዓለም ቤተ ክርስቲያን እንዲካሔድ የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ሄኖክ መመሪያ ሠጥተዋል:: በዕለቱም ቅዱስ ፓትርያርኩ ተገኝተው ሕዝቡን እንዲባርኩ ለማድረግና ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም ተገኝተው ስብሐተ ልደቱን ለሚካፈሉ ምእመናን ቡራኬ እንዲሠጡ ሀገረ ስብከቱ ጥሪ እንደሚያደርግና የአእላፋት ዝማሬው ባማረ ሁኔታ እንደሚካሔድ ገልጸዋል::
ብፁዕነታቸው አያይዘውም “ይህ የአእላፋት ዝማሬ በሀገረ ስብከታችን የተፈቀደበት ዓላማ ምእመናን ጾሙን በመንፈስ ሲጾሙ ቆይተው ፍጻሜውን በሥጋ እንዳይጨርሱና ከቅዱሳን መላእክት ጋር በዝማሬ እንዲያከብሩ ለማድረግ በመሆኑ ለአእላፋት ዝማሬ ስትዘጋጁ የነበራችሁ ልጆቻችን ከቦታ ለውጥ በስተቀር የታሰበውን ዝማሬ ከመሆን የሚያስቀረው ምንም ነገር ስለሌለ የጀመራችሁትን የዝማሬ ዝግጅት እንድትቀጥሉና በዕለቱ እንድትገኙ ቤተ ክርስቲያን ጥሪዋን ታስተላልፋለች” ብለዋል::
የኢትዮጵያዊው ጃንደረባ ትውልድ ላለፉት ሦስት ወራት የአእላፋት ዝማሬን ለማካሔድና ልደቱን ለባለልደቱ በሚገባ ምስጋና ለማክበር ብዙ ሥራዎችን ሲያከናውን መሰንበቱ ይታወቃል:: በዐሥር አድባራት የመሐረነ አብ የጸሎተ ምሕላ ጉዞ በማድረግም ወጣቶች ወደ ተወለደው የአይሁድ ንጉሥ ሰብአ ሰገላዊ የጸሎት ጉዞ ሲያደርጉ ሰንብተዋል:: ከሃምሳ ስምንት ሺህ ሰዎች በላይ ዝማሬውን ሲለማመዱና በሥራ ቦታቸውና በየሥፍራው በመዝሙር ሕሊናቸውን ሲቀድሱ ከርመዋል:: በሚያስደንቅ ሁኔታ የሙዚቃ ኮንሰርት በማዘጋጀት የሚተዳደሩ አካላት ሳይቀር “የትርፋቸው ተስፋ” ስለተነካባቸው በመቆጣት ፈንታ “እስከዛሬ ለሠራነው ንስሓ እንዲሆነን ምን እናግዛችሁ?” ብለው እስከመጠየቅ ደርሰው አስገርመውናል::
ምንም እንኳን የመጀመሪያውን ዙር የአእላፋት ዝማሬ ለማካሔድ ባሰብንበት ቦታ ላይ ማድረግ ባለመቻላችን እጅግ ብናዝንም ክርስቶስም ሊወለድ በጠየቀበት ሥፍራ እንዳልተወለደ እናውቃለን::
“በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው” የሚለው ቃልም በሕሊናችን የተጻፈ ነው:: ለተወለደው ንጉሥ ለመዘመርም እንኳንስ ወደ ቤተ ክርስቲያን በዘመኑ ቢያኖረን ወደ ከብቶች በረትም በሔድን ነበር::
ስለዚህ ምእመናን የልደቱን ምስጋና “በአእላፋት ዝማሬ” ከማክበር በምንም ምክንያት ሳትረበሹና ሳትዘናጉ እንደ ሰብአ ሰገል የተወለደውን ንጉሥ አድራሻ መፈለጋችሁን እንዳትተዉ እና የከንፈራችሁን ፍሬ ይኸውም የምስጋና ሥጦታችሁን “ለተወለደው አምላክ” እንድታቀርቡ በትሕትና እንጋብዛለን:: የአእላፋት ዝማሬ ብዙ ውጣ ውረዶችን አልፎ እዚህ የደረሰው አንዳች መንፈሳዊ በረከትን ስላዘለ ነውና በቀሩት ቀናት ለዝማሬው በትጋት እንድትዘጋጁና ኦርቶዶክሳውያን ሁላችሁ ከመላእክትና ከእረኞች ጋር ለመዘመር በሥፍራው እንድትገኙ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን::
“በእግዚአብሔር ቤት በመቅደሱ እንገናኝ” ነህ. 6:10
“በእንግዶችም ማደሪያ ስፍራ ስላልነበራቸው በግርግም አስተኛችው”
ሉቃ.2:7 ተመስገን!
እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሁን!🤲
በጣም ጥሩ ነው እናመሰግናለን
እግዚአብሔር ያርዳችሁ ለፋታችሁን ይይላቹ
እውነት ብላቹሀል ክርስቶስም ሊወለድ በጠየቀበት ስፍራ አልተወለደም! ገና ከዚህም በላይ ስለክርስቶስ ከዚ በላይ እንሰደዳለን!!! እግዚአብሔር ከኛ ጋራ ይሁን
እግዚአብሔር ጥንካሬውን ይስጣችሁ።
ፈተና ለክርስቲያን ጌጡ ነውና በፈተና በመፅናት የታሰበውን ዝግጅት በስኬት እንፉፅመው ዘንድ እርዳታው አይለየን።
አይዞአችሁ ኢትዮጵያውያን የቃልኪዳን ሀገር እግዚአብሔር ይጠብቀናል
ክቡራን የአእላፋት ዝማሬ አዘጋጆች ይህንን ሐሳብ አላሰባችሁትም ብሎ ማሰብ ቢከብደኝም ግን ሁሉም ሰው በአንድ ቦታ ተሰብስቦ ሊከበር የታሰበው ባይሳካም እግዚአብሔር በፈቀደው ቦታ እንዲሆን በሀገረ ስብከቱ መሪነት ተወስኗል። የኔ ሐሳብ ሁሉም በደብሩ ተገኝቶ የሚያከብርበትና የሚከናወንበት ቢሆን የሚል ነው። ከዚህ በፊት ለነነዌ ፆም ምህላ እንደተካሄደው። ይህ እንዲሳካ ደሞ ከአእላፋት ዝማሬ ተወካዮች ከየ ደብሩ ሰንበት ት/ቤት ጋር ቢነጋገርበት መልካም ሐሳብ ይመስለኛል። ከተቻለ ሕዝቡ ለምርጫ እንዲሰጥበት ቢደረግ አመሰግናለሁ።
#ከቤተልሔም ግርግም እስከ ቀራንዮ ኮረብታ #በፍቅር የተከተለንን #አምላክ እና አባት እንከተለዋለን ፥
ስለ ሁሉም ነገር እግዚአብሔር ይመስገን