የተስፋ አቅጣጫው ከልዑል እግዚአብሔር ከሆነ፤ ተስፋ መልካም ነው፡፡ የሰውን ሕይወት ያለ ተስፋ ማሰብ እጅግ ከባድ ነው፡፡ ከተፈጥሮውም ሰው ለተስፋ የተመቸ ፍጥረት ነው፡፡ በተለይም ሰው በሕይወቱ፤ እጅግ ሸለቆ የሆነ ቦታ ላይ ራሱን ሲያገኝ ተስፋን ይራባል፤ ተስፋን ይጠማል፡፡ ምግብን በእጅጉ ስንራብ ከመራባችን በፊት ምግብ ተመግበን የምናውቅ፤ እንዲያውም አማርጠን እና ተጠናቀን የተመገብን እስከማይመስለን ድረስ ምንም ዓይነት ይሁን ምግብ ይናፍቀናል፡፡
የተስፋም ነገር እንዲሁ ይመስላል፡፡ ተስፋን የምንራብበት ጊዜ አለ፡፡ የመኖር፤ ደህና የመሆን፤ እውነተኛ ደስታን የማግኘት፤ የማደግ …. ተስፋን እንናፍቃለን፡፡ ነገር ግን ለመኖር፤ ደስታን ለማግኘት፤ ደህና ለመሆን እና ለማደግ የሚጠቅመንን ተስፋ ስንናፍቅ በዚያ ናፍቆታችን ውስጥ እግዚአብሔር ከሌለ ተስፋችን ተስፋ አይሆንም፡፡ የተስፋችን አካል ብቻ አይደለም፤ ዋናው ተስፋችን እግዚአብሔር ካልሆነ ቆም ብለን ማስተዋል ይገባናል፡፡
ቅዱስ ዳዊት በተደጋጋሚ እንዲህ ይላል፡-
መዝ 27፡ 14 “እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ፤ በርታ፡ ልብህም ይጽና፤ እግዚአብሔርን ተስፋ አድርግ”
መዝ 141፡ 5 “አቤቱ ወደ አንተ ጮኽኩ፤ አንተ ተስፋዬ ነህ፡፤ በሕያዋንም ምድር አንተ ዕድል ፈንታዬ ነህ”
ሰው በኀጢአት ምክንያት ቢወድቅ እንኳን፤ የመነሳት ተስፋው ላይ ለመድረስ ብዙ ደክሟል፡፡ ተስፋን ለማግኘት፤ ተስፋውም እውን ይሆን ዘንድ ብዙ መሥዋዕት ሠውቷል፤ ብዙ መከራንም ተቀብሏል፡፡ የቀደሙ ደጋግ አባቶችን እና የነቢያትን ሕይወትና አገልግሎት እናስባለን፡፡ ነገር ግን “አሁን ተስፋዬ ማነው? እግዚአብሔር አይደለምን?” (መዝ 39፡ 7) የሚለው ጥልቅ ጉዳይ ላይ ከደረሰ በኋላ የሰው ልጅ ታሪክ ታላላቅ ምሥጢራትን አገኘ፤ ተቀበለ፡፡ ንግግሩ ተስፋን የናፈቀ የንጉሥ ዳዊት ነው፡፡
መዝሙረኛው ሲጠይቅ “ተስፋዬ ምንድነው?”፤ “ምን ነገር ነው?” አላለም፤ “ተስፋዬ ማነው?” አለ እንጂ፡፡ ተስፋ አካላዊ (አካል ያለው) ነው ማለት ነው፡፡ ከላይ ያነሳናቸው እና ሌሎችም ደጋግ ነገሮችን ከባለቤታቸው (ከእግዚአብሔር) ጋር የሚመጡልን፤ የምናገኛቸው ከሆነ እውነተኞች እንሆናለን፡፡ ነገር ግን እኛ መልካም የመሰሉንን ነገሮች ያለ እግዚአብሔር ለማግኘት የምንመኝ ከሆነ ምኞታችን ከንቱ ይሆናል፡፡ ከተስፋዎች ሁሉ በላይ የሆነ ተስፋ እግዚአብሔር ነው፡፡
ከወደቅንበት የሚያነሳን፤ ከተረሳንበት የሚጎበኘን፤ ከጠፋንበት የሚፈልገን እውነተኛው ተስፋችን መድኅን ክርስቶስ ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ነቢያት መሥዋዕቶቻቸውን ካቀረቡ እና እግዚአብሔርን ለማገልገል ከደከሙ በኋላም የዘለዓለም ድኅነትን ስላላገኙ፤ ተስፋን እንዲሰጣቸው ብቻ ሳይሆን ተስፋ እንዲሆንላቸው እግዚአብሔርን ለመኑ፡፡ እርሱም ተለመናቸው፡፡ ቃል የተገባላቸው ተስፋ፤ ሰው ሆኖ ከንጽሕት ድንግል ማርያም ተወለደላቸው፡፡ ነገር ግን አሁን (በጾመ ነቢያት) ተስፋን በተስፋ የመጠበቅ ጊዜ ላይ ነንና ወደ እርሱ እንመለስ፡፡ ከክርስቶስ ልደት በፊት ሰው መልካሙን ነገር ተስፋ አላደረገም፤ ተስፋን ተቀበለ እንጂ፡፡
ተስፋ በማድረግና ተስፋን በመቀበል መካከል ሰፊ ልዩነት አለ፡፡ ተስፋን (ከልዑል እግዚአብሔር) መቀበል በውስጡ እውነትነት አለው፤ ከሕይወት መንገድም አያስወጣም፡፡ ሰው በራሱ እንዲሁ ተስፋ የሚያደርገው ግን፤ ለእውነትም ለሕይወትም ዋስትና የለውም፡፡ ቢሆንም ግን ተስፋን መቀበል በርግጠኝነት መልካም ሆኖ ሳለ፤ በቀላሉ ያለ ድካም ተስፋው ጋር ይደረሳል ማለት ግን አይደለም፡፡ ከክርስቶስ ልደት አስቀድሞ በቅዱሳት መጻሕፍት የተመዘገቡት መቅሠፍታት፤ ግዞቶች፤ እና ሌሎች ሲታዩ መልካም ያልሆኑ ነገሮች ሁሉ ወደ ዋናው ተስፋ አድራሾች ነበሩ፡፡ በመዝሙረ ዳዊት ውስጥ “ፈርዖንንና ሠራዊቱን በኤርትራ ባሕር የጣለ፤ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና”፤ “ብርቱዎችንም ነገሥታትን የገደለ፤ ምሕረቱ ለዘለዓለም ነውና” … የሚሉትን አነጋገሮች ቀደም ብለን ያነሳነውን ሓሳብ የሚያጸኑ ናቸው (መዝ 135)፡፡
ታላቁን ተስፋ ለማግኘት ሰው በብዙ ድካም ውስጥ ማለፍ አለበት፡፡ ቀድሞም እስራኤል ከግብጽ ባርነት ነጻ በመውጣት ከነዓን የመግባት ተስፋ ቢሰጣቸውም፤ ያንን ተስፋ ላይ ለመድረስ በብዙ ፈተናዎች መካከል ማለፍ ነበረባቸው፡፡ ብዙዎችን ጥርጥር፤ ክህደት፤ ማጉረምረም፤ ዝሙት፤ አመንዝራነት እና ሌሎችም ተስፋቸው ላይ እንዳይደርሱ ያስቀሯቸው እኩያት ናቸው፡፡ ከዚህ በተቃራኒው መልካም አድረገው፤ ሲወድቁ ዳግም በመነሳት ተስፋን ለመቀበል ሲዘጋጁ የኖሩ አሉ፡፡ እነርሱ ተስፋ ሥግው ሆኖ (ሥጋን ለብሶ) ተወልዶላቸው በዘለዓለም ሕይወት አግኝተውታል፡፡ ተስፋችን መድኅን ክርስቶስ ነው!
አሁንም ተስፋ ክርስቶስ በእርሱ ረድኤት በሚሠሩት መልካም ሥራ፤ በነፍሳቸው (በመንፈሳዊ አኳኋን) እንዲወለድ የሚናፍቁ እውነተኞች ክርስቲኖች ናቸው፡፡ ቃሉን በመጠበቅ፤ ፈቃዱንም በማድረግ ለእርሱ እናትም ወንድምም የሚሆኑት አሉ (ማቴ 12፡ 48 – 50)፡፡
የማይመረመር ቸርነቱ ምን ይደንቅ! ነገር ግን ከዚያ በፊት ተስፋነቱን መናፈቅ፤ እርሱንም ለመቀበል እንደ ወርቅ በእሳት (በልዩ ልዩ ፈተናዎች) ይፈተናሉ፡፡ ያልደከምንለትና ያልናፈቅነው ቢመጣ ደስታችን ፍጹም አይሆንምና፡፡ ነገር ግን በትክክል ለናፈቁትና በመልካም ሥራ ራሳቸውን ላዘጋጁት ግን ተስፋ (ክርስቶስ) ይገለጥላቸዋል፡፡ ደስታ፤ ብርሃን፤ ጣዕም፤ ጸጋ ይሆናቸዋል፡፡ በእርሱ ተስፋነት ሌሎች መልካም ነገሮችንም ሊቀበሉ ይችላሉ፡፡ ከሁሉ የሚበልጠው ግን የእርሱ ተስፋነት ነው፡፡ ደስታ እና ተስፋ የሆነ ክርስቶስ የልደቱን ብርሃን ይግለጥልን! አሜን፡፡
kalehiwotin yasemalin
ቃለ-ሕይወትን ያሰማልን!
Kale hiweten yasemalen
እግዚአብሔር ይስጥልን። የልደቱ ብርሃን ይብራልን።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
Kale hywet yasemaln
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለሂወት ያሰማልኝ
አሜን፡ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።
የአገልግሎት ዘመንህን እግዚአብሔር አምላክ ይባርክ።