ቤት ውስጥ ሆኖ መጸለይ 

አካላዊ ቃል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስ ለድኅነተ ሰብዕ ለድኅነተ ዓለም ሰው ሆኖ በምድር በተመላለሰበት ወቅት በተግባርም በቃልም ካስተማራቸው የክርስትና መሠረታውያን ውስጥ አንዱና ዋነኛው “ጸሎት” ነው። አድርጉ ከማለቱ በፊት አድርጎ የሚያሳይ መምህር እንደመሆኑ ጸልዩ ከማለቱ በፊት ጸልዮ አሳይቶናል።  የጌታችንን አሰረ ፍኖት የተከተሉ ቅዱሳን ሐዋርያት ሐዋርያነ አበው ሊቃውንት ጻድቃን ቅዱሳን ሁሉ በቃልም በጽሑፍም የጸሎትን ኃይልና አስፈላጊነት በጉልህና በተረዳ ሲያስተምሩ ኖረዋል። በህይወታቸውም ጠላትን ድል ሲያደርጉበት አሳይተውናል። 

ሐዋርያዊ ትውፊትን የምትከተል እናት ቤተ ክርስቲያንም ሥርዓተ አምልኮዋ በጠቅላላ በጸሎት የሚከወን የነገረ ሃይማኖት ድርሰቶቿ ሳይቀር በጸሎት የሚቀርቡባት ምድራዊ ሠረገላ “ቤተ ጸሎት” ናት። በዚህ አጭር ክታባችን ግን የጸሎትን ምንነትና አስፈላጊነትን በተመለከተ ዝርዝር  ትምህርት ማቀበል ሳይሆን ጸሎታችን የት መደረግ አለበት በመኖርያ ቤት ወይስ በቤተ መቅደስ የሚል ይሆናል። ጥቂት መጸሐፋዊ ንባቦችን ማንሻ በማድረግ የርዕሳችንን ትንታኔ እንመለከታለን። ጉዳዮም በግል የሚደረግ ጸሎት ላይ የሚያተኩር ነው።

በየትኛውም መንገድ ቢሆን ቤተክርስቲያን ሄዶ አለመጸለይን የሚያበረታታ ትምህርትም ሆነ ምክር ፍጹም ተቀባይነት ሊኖረው የማይችል ጉዳይ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። በተለይ ደግሞ “እግዚአብሔር የልብን ያውቃል” በሚለ ቅንነታዊ አባባል በሰማያዊት ኢየሩሳሌም አምሳል ባለችው ቤተክርስቲያን ውስጥ ካሉ የአምልኮ ሥርዓቶች መራቅ እንዳይፈጠር አስተውሎት የሚሻ ጉዳይ ነው። ቤተክርስቲያን ከቤተክርስቲያን ውጪ  ሆነን ጸሎት ማድረግን የምትደግፈው “እግዚአብሔር የልብን ያያል” በሚል ልዩ ሐሳብ አይደለም። ይልቁንስ የጸሎት ሕይወትን ከማበረታታ በዕለት ዕለት ሕይወታችን ውስጥ ጸሎት እጅግ አስፈላጊ መሆኑን ከማሰብ አንጻር ነው። ጥቂት ማሳያ ነጥቦችን እናንሳ።

ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በአንቀጸ ጸሎት ትምህርቱ የፈሪሳውያንን የጸሎት ሁኔታ በተቸበት ጊዜ በእልፍኝ ገብቶ መጸለይን አስተምሯል “ስትጸልዩም እንደ ግብዞች አትሁኑ፤ ለሰው ይታዩ ዘንድ በምኩራብና በመንገድ ማዕዘን ቆመው መጸለይን ይወዳሉና፤ እውነት እላችኋለሁ፥ ዋጋቸውን ተቀብለዋል።አንተ ግን ስትጸልይ፥ ወደ እልፍኝህ ግባ መዝጊያህንም ዘግተህ በስውር ላለው አባትህ ጸልይ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።” ይህ ገጸ ንባብ እግዚአብሔር ከሚመለክበት ቦታ በምኩራብ  ከመጸለይ ይልቅ ከቤት በእልፍኝ የሚደረግ ጸሎትን  የሚያበረታታ ይመስላል። ነገር ግን ዋና ትርጉሙ ይሄ ብቻ አይደለም የወንጌል ትርጓሜ ይህንን ሲመልስ እንዲህ በማለት ነበር 

“….በምኵራብማ መጸለይ እንዲገባ ለማጠየቅ እግዚአብሔር ሙሴን ወንድምህ  አሮን ድምፅ ያለው ልብስ  ለብሶ ያን ‘ እያሰማ ገብቶ ይጸልይ ሕዝቡም እሱን  አብነት  አድርገው ፡ ገብተው ይጸልዩ  ብሎት  የለምን  ቢሉ ‘ በምኩራብ ሦስት ክፍል ነበረው መካነ ጸሎት  መካነ  ትምህርት  መካነ ተግሣፅ  አለ ። ፈሪሳውያን  ግን መካነ ጸሎቱን  ትተው ሰው በሚበዛበት በመካነ  ተግሣፅ ቁመው  ይታያሉና።…” ስለዚህ ጌታችን በምኩራብ መጸለያቸውን ሳይሆን የተቸው የጸሎት አቀራረባቸውንና ለጸሎት ከተዘጋጀበት ክፍል ተለይተው ለታይታ የሚያደርጉትን ጸሎት ነው።

በዕልፍኝህ በቤተህ ገብተህ ጸልይ የሚለው ንባብም ሁለት መሠረታዊ ፍቺዎች ይዟል የመጀመርያው ቃል በቃል በምትጸልይበት  ጊዜ ከቤትህ ገብተህ ደጅህን ዘግተህ  ወደ  ሰማያዊ  አባትህ  ጸልይ ። “ወኣቡከ ዘይሬእየከ  በኅቡዕ  የዓሥየከ  ክሡተ።” (ተሰውረህ ስትጸልይ  የሚያይህ  አባትህ  ዋጋህን  ይሰጥሃል) የሚል ሲሆን ሁለተኛው ደግሞ በምትጸልይበት  ጊዜ  ሕዋሳትህን  ሰብስበህ  በሰቂለ  ኅሊና  በነቂሐ ልቡና  ሆነህ  ወደ  ሰማያዊ አባትህ  ወደ  እግዚአብሔር አመልክት የሚል ነው።  በጥቅሉ ከታይታ የራቀ በሰቂለ ኅሊና የሚደረግ ጸሎትን የሚደግፍ ገጸ ንባብ መሆኑን እናስተውላለን።

ፍትሕ መንፈሳዊ በአንቀጽ 14 ላይ ስለ ጸሎት ደንብና ሥርዓት ባሰፈረበት ንባብ ውስጥ ስለዚህ ጉዳይ ያብራራል። በተለይ በቤትና በቤተክርስቲያን የሚጸለዮባቸውን ጊዝያቶች ለይቶ ያስቀምጣል።

<<የጥዋትና  የማታ  ጸሎት  በቤተ  ክርስቲያን  ውስጥ ይሁን  ይልቁንም  በቅዳሜና  በእሑድ ቀን  ደዌ  ሳያገኘው  ወደኋላ  ያለ ይለይ  ሕመምተ ኛው  መምጣት ቢቻለው  አይዘግይ ከቅዳሴው ጠበል  ጠጥቶ  ከዘይቱ  ተቀብቶ ድኅነትን  ያገኝ  ዘንድ  መምጣት የማይቻ ለው  ሕመምተኛ  ቢሆን ግን  የሚያውቁት ዘወትር ይጠይቁት ።የሦስቱን ሰዓትና  ከእርሱ በኋላ ፡ (ቀጥሎ)  ያለውን  የሰዓት  ጸሎት  በቤት መጸለይ ይገባል።>>

በዚሁ የሕግ አንቀጽ ላይ አንድ ክርስቲያን በቤቱ መጸለይ አይደለም የማይመች ቦታ ድምጽ አሰምቶ መጸለይ የማይችልበት ሁኔታ ላይ ቢሆን እንኳን በልቡ መጸለይ እንደሚችል ይናገራል <<ከእነዚህ  ጊዜያቶች በአንዲቱ  የመጸለያው  ጊዜ ቢደርስ  ምእመንም ለመጸለይ  ከማይችልበት  ቦታ  ቢሆን በልቡ  ይጸልይ  (ያስብ)፤>> ይላል።

በእልፍኝ በቤት ሆኖ መጸለይ በአንቀጸ ጸሎት ላይ ያለና የማያስነቅፍ ሲሆን በቤተክርስቲያን ውስጥ ከሚደረግ ጸሎት ጋር ግን አንጻራዊ ልዮነት አለው ለዚህም አባ ጊዮርጊስ ዘጋስጫ በመጸሐፈ ምሥጢር ድርሰቱ ላይ ያለውን ልዮነት በጉልህ ይገልጸዋል <<ሰው በቤቱ ቢጸልይ የአምላኩ ምሥጋና እንዳይቋረጥበት በጎ ሥራ ሠራ መግባትን ግን አልገባም። የንጉሥን ፊት እያየ አፍ ለአፍ እንደሚያናገር ሰው ባለሟልነትን ባያገኝም ሐሳቡን በመልእክተኛ አንደበት ወደ ንጉሥ እንደሚያደርስ እንደዚያች ኃይል ይሆንለታል።>> አባ ጊዮርጊስ በቤቱ የሚጸልይ  ሐሳቡን በመልእክተኛ ወደ ንጉሥ በሚያደርስ ሰው ይመስለዋል ቤተክርስቲያን ሆኖ የሚጸልየውን ደግሞ ንጉሥን አፍ በአፍ በሚያናግር ሰው አድርጉ መስሎታል። ነገር ግን  በቤት ሆኖ መጸለይን የሚያበረታታ ሁለት ነገሮችንም አስፍሯል የመጀመርያው የአምላኩ ምሥጋና እንዳይቋረጥበት በቤቱ መጸለዩ በጉ ሥራ መሆኑን ሲገልጽ ሁለተኛ ደግሞ በቤቱ መጸለዩ ጸሎቱ ቅድመ እግዚአብሔር እንደሚደርስና ኃይልን እንደሚያደርግ ነው። 

ማጠቃለያ:-

ጸሎት በሁሉም ቦታ ቢደረግ ድንቅ ያደርጋል

እስክንድሮስ ሊያጠፋው ሲነሣ ሕዝቡ ከልቡ ገና የአምልኮ ጣዖት ስላልጣፋ “18 ፓትርያርኮች ያልነኩትን አንተ ለምን ታፈርስብናለህ?” ብለው ተቃወሙት፡፡ እለ እስክንድሮስም ሕዝቡን መክሮና አስተምሮ የሳተርን በዓል ይውልበት በነበረው ዕለት የቅዱስ ሚካኤልን በዓል እንዲያከብሩ አውጆ ቤተ ጣዖቱንም በቅዱስ ሚካኤል ስም ሰይሞ ቤተክርስቲያን አደረገው፡፡ ይላል የረከሰ ቤተ ውስጥ ስለምን ጸሎት ይደረጋል አይባልም። ጸሎት በበረሐ በዱር በቤት በመኝታ በጉዞ በማኅበር ቢደረግ የሚጠቅም እንጂ የሚጉዳ አይደለም። በቤተክርስቲያኒቷ የሚደረጉ ቋሚ የማኅበረ ጸሎቶች ሥርዓተ ቅዳሴን ጨምሩ ከቅጥሯ ውጥቷ ይደረግ ዘንድ አይቻልም።የጊዜ የቦታ ሁኔታ የተመቻቸለት በቤተመቅደስ ጸሎቱን ቢያደርግ መልካም ነው ይህም ንጉሥን አፍ ለአፍ እንደማናገር ነውና። 

Share your love

7 አስተያየቶች

  1. Aba Gebrekidan siastemiru bet huno kemetseley betekirstian derso memeles yisgalal bilawal.
    Lemisale and sew Twat bet kemitseliy betekirstian bitseliy yishalal bilo betekirstian bitseliy ena betekirstian kidase binor. Kidaseun mascheres baychil.
    Yetignaun new mareg yalebet yalebet

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *