ከቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ ጋር ባለፈው ሳምንት ወግ ጀምረን ነበር:: የመጨረሻውን ክፍል እነሆ ተጋበዙ የማታውቀውን ሕይወት ወደ ትክክለኛው ሕይወት የሚያደርስ ብለክ እንዴት ትጽፋለህ አሉኝ::
አሁን ግን ማመን ማምለክ ይቻላል ግን እምነት በተበላሸ መንገድ የሚገለጽበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው።
አሁን እኛ እየኖርን ያለነው ያልተመጣጠነ እድገት ነው፡፡ በአካል እናድጋለን፣ አእምሯዊ እድገት አለ በመንፈሳዊነት ግን መቀጨጭ አለ፡፡
ጃንደረባው፡ ከትምህርት በቃኝ ካሉ በኋላስ ወደምን ተሸጋገሩ:-
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ:- ትምህርት ላይ ነበር የቆየሁት ስለዚህ በጣም ተወጥሬ ስለነበር ፋታም ስላልነበረኝ ከተማሪነት ጊዜ በኋላ ለሁለት ዓመት እረፍት ወሰድኩኝ። እና በዛ የእረፍት ጊዜ ውስጥ የፒ.ኤች.ዲ መመረቂ ጽሑፌን (dissertation) ወደ አንባቢያን ለማድረስ እንደገና ማዘጋጀት ነበረብኝ። የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፌ Theanthropic Ethics in Conversation with Autonomy and Heteronomy ይባላል። አሁን Amazon ላይ ይገኛል። ዋጋው ትንሽ ወደድ ይላል። እዚህም ሳሳትመው አኩል ለአንባቢያን ለማድረስ በኋላ ዋጋውን እቀንሰዋለሁ። ከዛ በኋላ ወደ ዩኒቨርሲቲው ወደ መምህሬ (professor) ተመለስኩኝ። Research Associate ሆኜ ለሁለት ዓመት አብሬው ሠራሁ።
በሥራው ውስጥ ግን ምንም ራሴን ማግኘት አልቻልኩም ነበር። እዛ ለመማር ነው እንጂ ለመስራት ሲሆን ትንሽ የከብዳል። ግን ምንድነው የምሠራው? ለማን ነው የምሠራው? የማንን አላማ ነው የማሳካው? ኅሊናዬ የሚያነሣቸው ጥያቄዎች ነበሩ። የምንሰራውን ፕሮጀክት የሚያመጣው ፕሮፌሰሩ ነው። እነሱ እሚፈልጉትን ነው የምሠራው እና በእርግጥ ጥሩ ይከፍላሉ፣ ኑሮ በጣም የተመቸ ነው። ነገር ግን ውስጤ ክፍተት ነበረው። እኔ በዚህ ሁሉ ውስጥ ያለፍኩት እና ይሄንን ሁሉ የተማርኩት እነሱን ለማገልገል አይደለም። ስለዚህ ሥራ ለማቆም ወሰንኩ እና አቆምኩ። ደግነቱ እዛ አንድ ሁለት ዓመት ከተሠራ በኋላ ጥቅማጥቅሙ ይቀራል እንጂ እስከ ሁለት ሦስት ዓመት ድረስ ሙሉ ደሞዝ ይከፈልሻል። እና እኔም ፊቴን ወደ በትረ ሃይማኖት መጽሐፍ ወደ ማዘጋጀት አዞርኩ።
ጃንደረባው፡ እስቲ ስለ በትረ ሃይማኖት እንጨዋወት። መቼ ነው የተጻፈው?
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ቅድም እንደገለጽኩት ሥራ አቁሜ ደሞዝ ግን እየተከፈለኝ እረፍት ላይ በነበርኩበት ጊዜ ነው በትረ ሃይማኖትን የጻፍኩት። በበትረ ሃይማኖት ትምሀርት ላይ ሳለሁ ሲነገሩ የምሰማቸው የነበሩ አመለካከቶች፣ መመለስ አለባቸው ብዬ የያዝኳቸውን የፍልስፍና እሳቤዎች እና የኦርቶዶክስ አስተምህሮ ሳይሆኑ በማወቅም ባለማወቅ ወደ እኛ ውስጥ የገቡ የኛ የሚመስሉ ነገር ግን ምንፍቅናዊ ሽታ ያላቸው እና ምላሽ ሳያገኘኙ የቆዩ እሳቤዎችን ነው እያወጣሁ ለመመለስ፣ ለመሞገት እና ለማስረዳት የሞከርኩት። ርዕሱም የሚገልጸው እሱን ነው። በትረ ሃይማኖትን ጽፎ ለመጨረስ ሁለት ዓመት ነው የፈጀብኝ። ከመውጣቴ በፊት እዚህ “ክርስቲያናዊ ሕይወት” የምትል በእስጢፋኖስ ማኅበርተኞች የምትታተም እና ለባንክ ሠራተኞች በአንድ አንድ ብር የምትሰጥ መጽሔት ላይ ወደ ሦስት የሚሆኑ ጽሑፎች ነበሩኝ።
እንዲያውም አንድ ጊዜ ምን አጋጠመኝ ከእነዚህ ጽሑፎች መካከል አንዱ “ወደ ትክክለኛ የትዳር ሕይወት እንዴት መድረስ ይቻላል” የሚል ጽሑፍ ነበር። ይህን ጽሑፍ አርሙልኝ ብዬ ለመምህር ሉሌ መላኩ ሰጠኋቸው እና ርእሱን አዩና “ለመሆኑ አንተ አግብተሃል?” ብለው ጠየቁኝ እና “አይ አላገባሁም” ስላቸው “ታዲያ የማታውቀውን ሕይወት ወደ ትክክለኛው ሕይወት የሚያደርስ ብለክ ትጽፋለህ” ያሉኝና የማልረሳውን ገጠመኛቸውን አጫወቱኝ። እና በክርስቲያናዊ ሕይወት ላይ ይወጡ የነበሩ ጽሑፎች በኋላ አማርኛ አልጻፍኩም ነበር። ቤልጅየም ለትምህርት ዘጠኝ ዓመት ነው የቆየሁት። ከዛ ደግሞ ሥራ ብቻ በአጠቃላይ ከ14 ዓመት በኋላ ነው ወደ አማርኛ ጽሑፍ የተመለስኩት።
እና በትረ ሃይማኖት በቃ በአማርኛ የመጻፍ ፍላጎቴን እና ስሜቴን ነው የተወጣሁበት። እንደው በአማርኛ መፃፍ እረስቼ ይሆን እንዴ ምናልባት ሥነ ጽሑፋዊ ይዘቱ እንዳይበላሽብኝ እንዳልሳሳት ስለሰጋሁ እየመላለስኩ እያነበብኩ በድጋሚ እያስተካከልኩ እያሸሁ ነው የጻፍኩት። አንዳንዶች አሁን ከባድ ሆነብን የሚሉ አሉ። እኔ ግን አንባቢያን እጃቸው ላይ ይዘው ሳይረዱት እንዳይቀሩ ስል በተብራራ መልክ ለመግልስት ሞክሪያለሁ። ጥሩ መጽሐፍ እንደሆነ የሚገልጹ አስተያየቶች እሰማለሁ። መቼና እንዴት እንደማደርገው ባላውቅም በበትረ ሃይማኖት መጽሐፍ መነሻነት ነገረ መለኮት ጥልቅ ውይይት የሚደረግበት ዐውድ እንዲፈጠር እመኛለሁ።
በእያንዳንዱ ምዕራፍ ላይ የተነሡ አስተምህሮዎች ዛሬ በዘመናችን ከሚነሡ ሃይማኖታዊና ፍልስፍናዊ እሳቤዎች አንጻር ትምህርታዊ ውይይት ቢደረግባቸው ብዙ የምናጠራቸው ነገሮች ይኖራሉ ብዬ አስባለሁ። እንግዲህ ልክ ሸንኮራና ብርቱካን ከክፍለ ሀገር ይዞ ወደ ቤቱ እንደሚመጣ በአንዱ እጄ የእንግሊዘኛውን የዶክትሬት መመረቂያ ጽሑፍ (dissertation) በሌላኛው እጄ ደግሞ የአማርኛውን መጽሐፍ በትረ ሃይማኖትን ወደ ሀገሬ መጣሁ።
ጃንደረባው፡ እስቲ ከውጭ ከተመለሱ በኋላ የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ዲን የሆኑበትን ወቅት ያጫውቱን።
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- መቼ እንደሆነ ጊዜውን ባላውቀውም አንድ ቀን ጠቅልዬ ወደ ሀገሬ እንደምመለስ እርግጠኛ ነበርኩ። ግን እንድመለስ ሁኔታዎች የተመቻቹበት ወቅት ተፈጠረው የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ ዋና ጸሐፊ ሆኜ ኢትዮጵያ መጥቼ በነበረበት ወቅት ነው። እንደሚታወቀው ለ26 ዓመት ያህል በቤተ ክርስቲያናችን የውጭና የውስጥ ሲኖዶስ የሚል መለያየት ተፈጥሮ ነበር። ይህ ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያን አንድነት እንዲመለስ በሁለቱም ወገኖች ውስጥ ያገለግሉ የነበሩ በአውሮጳ፣ በካናዳና በሰሜን አሜሪካ 24 አባላት ያሉት ካህናትና ምእመናን የተቋቋመ ኮሚቴ ነው። ለዚህ ዓላማ ከኮሚቴው ሰብሳቢ ከመልአከ ሕይወት ሀረገወይን ብርሃኑ እና ከዶ/ር ንጉሱ ለገሰ ጋር ከቅዱስ ሲኖዶስ ደብዳቤ እንዲጻፍልን ለመጠየቅ ወደ እዚህ መጥተን ነበር። በዚያን ወቅት ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ጥናታዊ ጽሑፍ አቅርቤ ነበር። ከጥናታዊ ጽሑፉ በኋላ ብፁዕ አቡነ ጢሞቴዎስን “መጥቼ ባገለግል ደስ ይለኛል” ብዬ ስጠይቃቸው “እናንተ ከመጣችሁልን ደስ ብሎን እንቀበላችኋለን” አሉኝ። ያኔም ወደ ቤልጅየም እንድሄድ የፈቀዱልኝ ብፁዕነታቸው ናቸው። ዛሬም ከዚህ ሁሉ ዓመት በኋላ ሊቀበሉኝ ፈቃዳቸው መሆኑን ሲገልጹልኝ ደስ ነው ያለኝ።
ወደ ኢትዮጵያ ስመጣ ዲን እሆናለሁ ብዬ አላሰብኩም ነበር። ወደ ኢትዮጵያ ሁለት ዓላማዎችን ነው ይዤ የመጣሁት። አንደኛው ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የተማርኩበት ተቋም ነው፤ ስለዚህ በአስተማሪነት ማገልገል አለብኝ። በዛ ላይ ማስተማር ከመጻሕፍት ጋር እንድኖር ስለሚያደርገኝና በትምህርት ዓለም ውስጥ ስለሚያቆየኝ በጣም የምወደው ሙያ ነው። ሁለተኛው ደግሞ ሥነ ምግባር ላይ መሥራት ነው። ያጠናሁት ጥናት ለመንፈሳዊነትና ለሥነምግባር የቀረበ ነበር። እዚህም ውጭም ሀገር ሄጄ እስከ ዶክትሬት ድረስ የሠራሁት ሥነ ምግባር ወይም Moral Philosophy ስለነበር ከደከምኩበት ሙያ ጋር የተያያዘ ሥራ መሥራት እንዳለብኝ አስብ ነበር። ሥነ ምግባር ላይ መሥራት እንዳለብኝ አስባለሁ እንጂ እንዴት መሥራት እንዳለብኝ አላውቅም ነበር።
የእርቀ ሰላም ሂደቱ ተጠናቅቆ ቅዱስ ፓትርያርኩ ወደ ኢትዮጵያ ከተመለሱ በኋላ ወደ ቤልጅየም ሄጄ እራሴን አዘጋጅቼ ጠቅልዬ ወደ በአንድ ልቤ ወደ ኢትዮጵያ መጣሁ። እንደመጣሁ በአስተማሪነት ነበር የተመደብኩት። ከአንድ ዓመት በኋላ ቀድሞ የኮሌጁ ዲን የነበሩት ወደ መጡበት ሀገር ሲመለሱ ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ ዲን ሆኖ መጣ። በጣም ወዳጆች ስለነበርን ቤተ ክርስቲያንን ለማገልገል እንመነኩሳለን ስንል ከነበርነው አምስቱ መንድሞች ሁለቱ እኛ ስለነበርን አብረን ልንሠራ የምንችልበት ወርቃማ ጊዜ እንዳገኘን ነበር የምናስበው።
ስለዚህ ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ የኮሌጁ ዲን ሆኖ ሲመደብ እኔ ደግሞ የአካዳሚክ ምክትል ዲን እንድሆን ላስተዳደር ጉባኤ ሀሳብ አቅርቦ፣ ውሳኔው በቋሚ ሲኖዶስ ጸድቆ በቅዱስ ፓትርያርኩ የተጻፈ የተመደብኩበት ደብዳቤ ደረሰኝ። እርሱ የኮሌጁ ዋና ዲን ሆኖ እኔም በአካዳሚክ ምክትል ዲንነት ብንሠራ በጣም መልካም ነበር። ነገር ግን ይህንን ያልፈለጉ ሰዎች መሀላችን ገብተው ብዙ ነገሮች እንዲበላሹ ሆነ። በመጨረሻ ተቋሙን ከግለሰብ ለይተን መመልከት ነበረብን። ከተስማማን ብዙ የተሻለ ነገር ማምጣት እንችላለን ካልሆነ ግን እኛ ግለሰቦች እንደ ግለሰብ ቀርተን ተቋሙ እንደ ተቋም መቀጠል ነበረበት። ኮሌጅ በነበረበት ጊዜ በአካዳሚክ ምክትል ዲንነት ዩኒቨርሲስቲ ከሆነ በኋላ ደግሞ በአካዳሚክ ምክትል ፕሬዚደንትነት በአጠቃላይ ለ4 ዓመት አገልግያለሁ።
በዚህ ጊዜ ውስጥ ኮሌጁን ወደ ዩኒቨርስቲ ለማሳደግና ውስጣዊ ይዘቱ የከፍተኛ ትምህርት ተቋም መልክ እንዲይዝ የምችለውን ጥረት አድርጌአለሁ። በተለይ ሥርዓተ ትምህርቱን ለማስተካከል ብቻ የሁለት ዓመት ጊዜ ወስዶብናል። በምችለው መጠን የተሻሉ ናቸው ይጠቅማሉ የምላቸውን ነገሮች ለማስቀመጥ ሞክሬአለሁ። አሁን ኃላፊነቱን ካለፈው ዓመት ታኅሣሥ ወር ጀምሮ አስረክቤ በመምህርነት እያገለገልሁ እገኛለሁ።
ጃንደረባው፡ በሁለቱም በኩል የተሳለ መሆን ማለትም በዘመናዊ ትምህርት የላቀ እንዲሁም በክህነትም ቤተክርስቲያንን ማገልገል ለቤተክርስቲያናችን ያለው ፋይዳ ምን ይመስላል ይላሉ በተለይ ደግሞ በአሁኑ ጊዜ?
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ካህናት የዘመናዊና የቤተ ክርስቲያን ትምህርትን ይዞ መገኘት በተለይ በዚህ ባለንበት ዘመን ግድ ነው። እጅግ ጠቃሚ መሆኑ ምንም የሚያጠራጥ አይደለም። ይህን ጥያቄ ከማስተምረው ኦርቶዶክስ መንፈሳዊነት (orthodox sprituality) ከሚለው ትምህርት ጋር አያይዤ ለመመለስ ልሞክር። ኦርቶዶክሳዊ መንፈሳዊነት ንጽሐ ሥጋ፣ ንጽሐ ነፍስ እና ንጽሐ ልቦና ምን ማለት እንደሆነና በየደረጃቸው እንዴት መድረስ ወይም እውን ማድረግ እንደምንችል የምናጠናበት ትምህርት ነው። ሁለተኛው ደረጃ ወይም ንጽሐ ነፍስ ማለት በአእምሮ የማወቅ አቅም መረዳት የምንችለውን ተረድተን ከአእምሮ በላይ የሆነውን ደግሞ በእምነት የምንቀበልበት ደረጃ ነው። ይህ በነገረ መለኮት ትምህርት contemplation/illumination ይባላል።
አእምሯችን የሚረዳውና እግዚአብሔር የሚገልጠው እውነት ላይ መድረስ ማለት ነው። ፍልስፍናው rationalism ነው የሚለው ማለትም በነፍስ አዋቂ ወይም አዋቂት ነፍስን ንቁ ማድረግ ላይ ነው የሚያተኩረው። አንድ ካህን ወይም አገልጋይ በአመክንዮ እና በመንፈሳዊነት በሁለቱም በኩል እምሮን ወይም የማወቅን አቅም ማሳደግ አለበት ማለት ነው። ይህ ማለት መጽሕፍት በማንበብ፣ መምህራንን በመጠየቅ፣ ከጓደኞቹ ጋር በመወያት በአእምሮው ማወቅ የሚችለውን ጥግ ድረስ መሄድ አለበት። ሁሉን ደግሞ በአእምሮ ማወቅ ስለማይቻል በተለይም ደግሞ ክርስትና ስላነበብኩ፣ ስለተረዳሁ፣ ስለሰማሁ አውቀዋለሁ የምንለው አደለም።
እንዳወቅን ሲሰማን የመናውቀው ነገር፤ እንደተገለጠልን ሲመስለን የተሸፈነ ነገር እንዳለ የምንመለከትበት ሕይወት ነው። ምክንያቱም እግዚአብሔርን በእኛ አእምሮ ተረድተን የምናውቀው ምሥጢሩ በአእምሯችን ሞልቶ የሚቋጭ አይደለም። የሃይማኖትን ነገር በእጃችን ሰፍረን፣ ጨብጠን የምንለካው አይደለም። ክርስትና ዕውቀትና ኩነት ነው። የምናውቀው አእምሯዊ ግንዛቤ ነው የምንሆነው ክርስቲያናዊ ማንነት ነው። ልክ እንደ ኒቆዲሞስ ነው የአይሁድ መምህር ሆኖ በጥምቀት ከእግዚአብሔር የመወለድን ነገር ሲነግረው ሊገባው አልቻለም ምክንያቱም የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ነገር በሥጋዊ የሚረዱት ሳይሆን በተግባር እውን የሚያደርጉት ነው። ከውሃ መወለድ ከእናትና አባት በሥጋ ከመወለድ ጋር የሚገናኝ አይደለም። ይህ እውቀትም እምነት ይፈልጋል።
ይህን ያነሣሁት የመንፈሳዊነትን ትምህርት በሰፊው ለማስተማር አስቤ ሳይሆን ካህናት ነጽሐ ነፍስ ላይ መድረስ ያለባቸው መሆኑን ለመግለጽ ነው። ሁሉም ክርስቲያኖች ንጽሐ ሥጋን፣ ንጽሐ ነፍስንና ንጽሐ ልቡናን እውን እንዲያደርጉ የተጠሩ ናቸው። ከሥልጣነ ክህነትና ለምእመናን አብነት ወይም ምሳሌ ከመሆን አንጻር ስንናገር ግን ዲያቆናት ንጽሐ ሥጋን፣ ቀሳውስት ንጽሐ ነፍስን፣ ጳጳሳት ደግሞ ንጽሐ ልቡናን እውን ማድረግ አለባቸው። በየደረጃቸው ንጽሕናን እውን ባላደረጉበት ሁኔታ አገልግሎታቸውን መፈጸም ማሳካት አይችሉም።
ንጽሐ ነፍስ የቀሳውስት የሆነበቱ ምክንያት ቀሳውስት ካህናት መሪዎች፣ የወንጌል መምህራንና የንስሐ አባቶች ወይም በጎቻቸውን የሚያሰማሩና የሚጠብቁ እረኞች ናቸው። ስለሆነም አእምሯዊ ዕውቀትንና መንፈሳዊ ማንነትን ወይም በአእምሮ አቅምና በእምነት ኃይል ካልተገኙ በቀር ልጆቻቸውን መጠበቅ አይችሉም። ካህናት ልጆቻቸው የሚያነሷቸውን ጥያቄዎች መመለስ ይቸገራሉ።
የምዕመናን ጥያቄዎች ከዕውቀት ማነስም ከእምነት መጉደልም ሊነሡ ይችላሉ። ስለዚህ ካህናት ምእመናን በአጠቃላይ ሰዎች የሚያነሷቸውን ፍልስፍናዊ፣ ሥነ ልቦናዊ፣ ከቴክኖሎጂ ጋር የሚገናኙትን፣ ከሥነ መንግሥት፣ ከምጣኔ ሀብት፣ ከማኅበራዊና ባሕላዊ ጉዳዮች የሚነሡ ጥያቄዎችን በሙሉ መመለስ አለባቸው። ካህናት ጋር የተጠማ ሰው መጥቶ ሳይረካ መመለስ በፍፁም የለበትም። በተለይ በዚህ ዘመን ምዕመናን በረካታ መረጃዎችን በሚሰሙበትና የተለያዩ ፍልስፍናዊ አስተምህሮዎች በሚነገሩበት ዘመን ካህናት የቤተ ክርስቲያንን ዕውቀት ይዘው በዘመናዊው ትምህርት የሚነገሩትን ትምህርቶች ማወቅ አለባቸው።
ዛሬ ዓለምን የምንመለከትበት የዕይታ መነፅር (worldview)፣ ሕይወትን የምንመዝንበት መንገድ ብንመለከት በምዕራቡ ዓለም በዘመናዊነት (modernism) ፍልስፍና የተቃኘ ነው። ይህ የተዛባ ወይም የተበላሸ ፍልስፍና ቤተሰባዊ ሕይወታችንን፣ ማኅበራዊ ግንኙነታችንን፣ አገራዊ ማንነታችንን አበላሽቶታል። ዛሬ በብዙ መልኩ የዘመናዊነት ፍልስፍናና ባሕል ያስከተለውን ውጤት እየተጋፈጥን ያለንበት ወቅት ነው። ቤተክርስቲያን ደግሞ ራሷ ዓለምን የምትመለከትበት እይታ አላት። የህልውና ምንነትን እምትገልፅበትን፣ ማህበራዊ ሥርዓት የምትዘረጋበት አስተምህሮዎች አሏት። እነዚህ ትምህርቶች ወደ ማህበረሰቡ አልተበተኑም አሁንም ድረስ የምንተነፍሰው የዘመናወነትን (modernism) ፍልስፍና ነው። ምእመናን የሚያውቁት እሱን ነው።
በሶሻሊዝም እና በኮሙኒዝም ሥርዓት ጭራሹኑ አምላክ የለም የሚሉና ማምለክ አይቻልም የሚሉ ነገሮች ነበሩ። አሁን ግን ማመን ማምለክ ይቻላል ግን እምነት በተበላሸ መንገድ የሚገለጽበት ሁኔታ ውስጥ ነው ያለነው። ስለዚህ ፍልስፍና እራሱ የሚያነሳቸውን ጥያቄዎች በሙሉ በነገረ መለኮት አስተምህሮ መመለስ የሚችሉ ካህናት መኖር አለባቸው። እንደ ማኅበረሰብም እንደ አገርም እንደ ዓለምም ዛሬ ያለንበትን ሁኔታ በሚገባ ተረድተው ሊያስተምሩ፣ ሊያስተካክሉ፣ ሊመሩ የሚችሉ ካህናት የሚያስፈልጉበት ዘመን ላይ ነው። ስለዚህ እውነት ነው በሁለቱም ወገን የተሳሉ ካህናት ያስፈልጋሉ።
ጃንደረባው፡ እስቲ ስለ ኢትዮጵያ ሥነ-ምግባር ማዕከል አመሠራረት፣ ዋና ዓላማ እና አሁን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ እንጨዋወት?
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ሥነ-ምግባር የተጨቆነ፣ የሚፈለግ ግን የሚገባውን ቦታ ያላገኘ የማንነት ትምህርት ነው። ሥነ ምግባር ያላስተናገድነው፣ ቤታችን ያላስገባነው፣ እንፈልግሃለን ግን እዛው ደጅ ቁም የተባለ ጉዳይ ነው። ለምሳሌ በየመሥሪያ ቤቶች በራፍ ላይ ታማኝነት፣ አገልጋይነት፣ ግልፀኝነት የሚባሉ የሥነ-ምግባር መርሆች ወይም እሤቶች ይቀመጣሉ። ግን በእውነት እንመራበታለን ወይ ነው ዋናው ጥያቄ። ከተመራንበት መልካም ነው። ካልሆነ ግን ሥነ ምግባራዊ እሤቶችን ለሌላ ዓላማ እየተጠቀምንባቸው ነው ማለት ነው። ያለሥነ ምግባር ደግሞ ምንም ማድረግ አይቻልም።
ከቤልጅየም እንደመጣሁ ከአንዳንድ ወንድሞች ሦስት አራት ሆነን በተቻለ መጠን የሕክምና ተቋማት፣ ጤና ሚኒስቴር፣ ትምህርት ቤቶች እና የተለዩ የንግድ ተቋማት ላይ እንደ ዳሰሳ ጥናት ዓይነት በማድረግ ሥነ-ምግባር ያለበትን ኹኔታ ለመመልከት ሞክረናል። በጤና ዘርፉ ላይ የሜዲካል ኤቲክስ ኮርሶች ሥልጠናዎችም ይሰጣሉ። እንደውም የማስተማሪያ ሞጁሎች ሰጥተውን ነበር፡፡ በሌሎች ቦታዎች ውስጥ ግን በተለይ በንግዱ ዓለም አይታወቅም ማለት ይቻላል። እንደ መግቢያ የምርጫ ትምህርት ተደርጎ ነው የሚሰጠው በሕክምናውም ቢሆን በቂ ነው ማለት የሚያስደፍር አይደለም። በቅርበት የማውቃቸው በተለያየ አጋጣሚ የቀረብኳቸው ወይም የቀረቡኝን ጠርተን በጉዳዩ ላይ መነጋገር ጀመርን። የቻሉቱ በሃሳቡ እየተስማሙ የመጡት committed እየሆኑ ጉዳዩን በይበልጥ ማጥናት ጀመርን።
በተለይ ሥነ-ምግባር እና ፖለቲካ፣ ሥነ-ምግባር እና ትምህርት፣ ሥነ-ምግባር እና ቤተሰብ ፣ ሥነ-ምግባር እና ቤተሰብና ፆታ፣ ሥነ-ምግባር እና ቴክኖሎጂ፣ ሥነ-ምግባር እና ሚዲያ እና ሥነ-ምግባር እና ንግድ ብለን ወደ ሰባት በሚሆኑት ላይ ስንወያይ ረጅም ጊዜ ቆየን። አንድ ተቋም መጀመሪያ ምንድነው ሚሠራው፣ ማንን ነው የሚያገለግለው እና ሥነ-ምግባር በዛ ተቋም ውስጥ ያለበት ሁኔታ እና እንዲሁም ሥነ-ምግባር ባይኖር በዛ ተቋም ሊደርስ ሚችለውን የከፋ ሁኔታ እና እኛ ምን መፍትሔ መስጠት እንችላለን የሚሉ ጥያቄዎችን ወስደው እያጠኑ እየተወያየን ነው የቆየነው። የሁሉም ጥናቶች ውጤት የሚያሳየው ችግሩ እጅግ ከፍተኛ ሆኖ ነው ያገኘነው።
በመጨረሻም አንድ ተቋም ማቋቋም ግድ እንደሆነ ወስነን በ2013 ዓ/ም ሕጋዊ ሰውነት ይዘን ሥራችንን አጠናክረን መሥራት ቀጠልን። ወደ ውጪ የወጣነው እና ሥራችንን በይፋ ለሕዝብ ያሳወቅነው ግን ከCCRDA ጋር እና ከGlob Ethics ጋር በትብብር የሁለት ቀን ኮንፈረንስ ወደ ስምንት ጥናቶች የቀረቡበት እና ትልቅ ውይይት የተደረገበት ሥነ-ምግባር እና የከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለማኅበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ በሚል በተዘጋጀ ኮንፈረንስ ነበር፡፡ Glob Ethics ዓለም አቀፍ የሥነ-ምግባር ተቋም ነው ጄኔቭ ላይ ያለ ነው CCRDA ደግሞ እንደምናውቀው የተለያዩ ማኅበራዊ ጉዳች ላይ የሚሠራ ድርጅት ነው። የተቋማችንን ሎጎንና ልናሰራ ያሰብነውንም ትልቅ የሥነ-ምግባር አካዳሚ የሕንፃ ንድፍ ያስመረቅነው ዶ/ር ሳሙኤል ክፍሌ የዛን ጊዜ የትምህርት ሚኒስቴር ስቴት ሚኒስቴር የነበሩት በተገኙበት ነው። እንግዲህ እንደዚህ እጅግ አስፈላጊ ነገር ሆኖ የሥነ ምግባር ባለሙያ እንኳን የለም።
እንግዲህ የተማርኩት ሥነ ምግባር ነው የሚል ሰው እስካሁን አላጋጠመንም። እኛ ያላወቅናችሁ እንደው ካላችሁ እባካችሁ ኑ እና አብረን እንሥራ እንላለን። ማህበራዊ ሳይንስ፣ ሳኮሎጂ ያጠኑ ሰዎች ናቸው የሚያስተምሩት፡፡
እንግዲህ ሥነ-ምግባር ክፍተት የፈጠረው ችግር ይሄ ነው የሚባል አይደለም፡፡ ሁልጊዜ የምናነሳው ደ/ር እጓለ ናቸው የተናገሩት ያኔ ከ50 ዓመት በፊት አካባቢ የተረዱት ነው። እና እሳቸው ምን ብለዋል “እውቀት ያስፈልጋል በምንልበት መጠን ልክ ነው ሥነ ምግባርም አብሮ መሄድ ያለበት፡፡ የአንድ መሰላል ሁለት አሃዝ ናቸው እውቀት እና ስነ-ምግባር” ብለው ነው የተናገሩት እና ወደ ከፍታ፣ ልዕልና እና ሥልጣኔ ለመውጣት በዚህ እውቀት በዚህ ደግሞ ሥነ-ምግባር ያስፈልጋል ብለው ነው የገለፁት በጣም ውብ በሆነ መልኩ፡፡ ስለዚህ እውቀት ባለበት ዘርፍ ውስጥ ሁሉ ሥነ-ምግባር ይገባል፡፡ የሰው ልጅ የተሰማራበት ቦታ ላይ ሁሉ ሥነ-ምግባር እኩል ያስፈልጋል፡፡
በፍልስፍና እንዳውም አንዳንዶች ነገረ ህልውና ይቅደም ይላሉ፣ አንዳንዶች ደግሞ ነገረ እውቀት ይቅደም ይላለሉ፣ እኛ ደግሞ ሥነ-ምግባርን ማወቅ ይቅደም ነው የምንለው፡፡ ምክንያቱም ያለ ሥነ-ምግባር እንረዳው ብንል ትክክል ባልሆነ እና በተበላሸ መንገድ ነው የምንረዳው፡፡ ይህን ለማስተካከል ብዙ መስራት እንዳለብን ነው የተረዳነው፡፡ የተረዱ ወንድሞች አሉ እያገዙን ያሉ፡፡ አሁን ወደ ማህበረሰቡም ወጥተናል፡፡ ስለምንሰራው ስራ ገለፃዎችን እያደረግን ነው፡፡ ከተለያዩ ተቋማት ጋር አብሮ ለመሥራት እየተነጋገርን ነው፣ ስልጠና በመስጠት እና በማስተማር፣ በየትምህርት ቤቶችና እና በየ መስሪያ ቤቱ እንዲሰጡ ከትምህርት ሚኒስቴር ጋርም ተነጋገረናል የመግባቢያ ሰነድም ለመፈራረም ጨርሰናል፡፡ ብዙ ተቋማት አሉ አፍሪካ ዩኒየንም አናግረናል ብዙ ልንሰራቸው ምንችላቸውን ስራዎች ተመልክተናል፡፡ ዲያሎግ ኮሚሽንም ጋር ተነጋገረናል፡፡
ከባንኮችና ከሕክምና ተቋማት ጋር ተያያዥ የሥነ ምግባር ሥልጠናዎች ልንሰጥ ስለምንችልበት መንገድ እየተነጋገርን ነው። አሁን የተጠመድንበት ስራ ወደ ሰባት የሚሆኑ የማስተማሪያ ሞጁሎችን እያዘጋጀን ነው፡፡ የሀላፊነት ስነ-ምግባር እጅግ ወሳኝ ነገር ነው እና እሱም በዚህ ዘመን ስነ ምግባርን የምንገልፅበት ሰፊው ሃሳብ የሀላፊነት ስነ-ምግባር ነው። እሱን የምናስተምርበት ሞጁል አዘጋጅተናል፡፡ አንድ ደግሞ እንደዚሁ የሥነ ምግባር ሰው የሚል ማስተማሪያ ሰነድ አለን፡፡ አንድ ሰው ስነ-ምግባር አለው ስንል ምን ማለታችን ነው በምንስ ነው የሚገለፀው የሚለውን የያዘ ለሁሉም ሰው መሰጠት የሚችልም ተዘጋጅቶ አልቋል፡፡ ሌሎቹ አምስቱ የማሰልጠኛ ሞጁሎች ናቸው። እነሱም በመጠናቀቅ ላይ ናቸው፡፡ ሃሳባችን እጅግ ትልቅ እና ጥልቅ ነው።
ትልቅ የስነ-ምግባር አካዳሚ መክፈት ድረስ ነው የምናስበው። ብዙ የሚስፈልጉን የእውቀት፣ የሰው፣ የገንዘብ እና ሌሎችም እገዛዎችን የሚፈልጉ ጉዳች አሉብን። በአሁኑ ሰዓት ግን አተኩረን እየሰራን ያለነው እነዚህን የማሠልጠኛ ማኑዋሎች የማዘጋጀት እና ከተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር ነው።
ጃንደረባው፡ እርሶ ከሚታወቁባቸው ጉዳዮች ውስጥ አንዱ የሥነ-ምግባር ጉዳይ ዋናው ነው እና ከእርሱ ጋር ተያይዞ አሁን ላለው ትውልድ ምን ይመክራሉ?
ቀሲስ ዶ/ር መዝገቡ :- ሰው መልካም ከሆነ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ቀላል ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ቤተክርስቲያን ስነ-ምግባርን ስናስተምር መንፈሳዊነት ነው። ክርስትና ማለት ፍፁም መሆን ማለት ነው፡፡ የሰማይ አባታችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ነው የተባልነው። እና ክርስቲያኖች ቅዱሳን ነው መሆን ያለባቸው፡፡ እማይቻል ከባድ ነገር እየተናገርኩ ሊመስል ይችላል ግን መጽሐፍ ቅዱስም የሚያስተምረን አባቶቻችንም የኖሩት እንደዛ ነው፡፡ በስጋ የሚመገብ ሰው ስጋው መፋፋት እና ማደግ አለበት፣ ትምህርት ቤት ሄዶ የተማረ ሰው አእምሮው ማደግ እና ብዙ ማወቅ አለበት ስለዚህ ቤተክርስቲያንም የሚሄድ ሰው የመንፈሳዊ ሕይወቱ አድጎ ቅዱስ መሆን አለበት። ይሄ በቃ የሚጠበቅ የእድገት ሂደት ነው።
አሁን እኛ እየኖርን ያለነው ያልተመጣጠነ እድገት ነው፡፡ በአካል እናድጋለን፣ አእምሯዊ እድገት አለ በመንፈሳዊነት ግን መቀጨጭ አለ፡፡ ስለዚህ እንዲመጣጠን አድርገን በሁሉም በኩል እንዲያድግ ማድረግ እንደ ክርስቲያን ግዴታችን ነው፡፡ እንደ ሃገር እና እንደሰው ግን ከማያምኑ እና ሌላ እምነት ካላቸው ጋር ስንኖር ግን መግባቢያችን ስነ-ምግባር ነው፡፡ ትክክለኛው ሰውነትን እያሳዩ መኖር ግዴታ ነው፡፡
እውነተኛ ሰው ማለት ከተበላሹ እሳቤዎች እና ከዓለም ከሚመጡ የተበላሹ እሳቤዎች የፀዳ ሰው ማለት ነው፡፡ ይህንን ስንረዳ በማህበረሰብ ውስጥ ያለንበትን ቦታ እና ምክንያት እንረዳለን፡፡ ስለዚህ እኛ ከንቱ ነገር አይደለንም የሆነ የምንጠቅምበት እና የምንደፍነው ቀዳዳ ይኖራል እና ያ ለመኖር ምክንያት እና አቅም ይሆነናል፡፡ ከዛም በተጨማሪ ያለንን ስጦታ እስከ መጨረሻው ድረስ አሟጦ ለመጠቀም ቀና እና መልካም መሆን ይጠይቃል። ነገር ግን መልካም ያልሆነ ሃሳብ ካለ ወደፊት ለመራመድ በጣም ከባድ ነው የሚሆነው። ስለዚህ መልካም መሆን እና በስነ መግባር መመላለስ ግዴታ ነው የሚሆነው፡፡ ስለዚህ ያለ ስነ-ምግባር ስልጣኔ አይታሰብም፣ ያለ ስነ-ምግባር እድገት አይታሰብም ወዴትም መድረስ አይቻልም፡፡
እውቀት ከበጎነት ጋራ ካልተባበረ እና አብሮ ካልሰራ ምናልባትም ያ እውቀት በጎ ነገር ለማምጣት ከምንተቀምበት ይልቅ ለክፋት እና ለተንኮል ሊውል ይችላል፡፡ የምሁር አጥፊ የመሆን እድሉ ከፍተኛ ነው። ስለዚህ ለሌላ መትረፍ አይቻልም፡፡ እኔ ብቻ የሚል ሰው እኔ እኔ ሲል ኖሮ የአንድ መስሪያ ቤት ሃላፊነት ላይ ቢቀመጥ እራሱን እንዴት መጥቀም እንዳለብት ብቻ የሚያስበው። ይህም ከሥነ ምግባር ጉድለት ችግር የሚመጣ ነው፡፡ ተቋማት ሲገዝፉ በዛው ልክ የገዘፈ ማንነት ያለው መሪ ይፈልጋሉ። ተቋም መሸከም የሚችል ትከሻ ይፈልጋሉ። ከጠባብ ማንነት ወጥቶ በተቋማዊ ማንነት ልክ ካላደግን ተቋሙን ልንመራ አንችልም። ስለዚህ ሥነ-ምግባር የምርጫ ጉዳይ አይደለም፡፡ እና ይሄን ለማሳካት ነው እየሠራን እየደከምን ያለነው።
ጃንደረባው :- ዕድሜ ይሥጥልን!
እናመሰግናለን ዕድሜ ከጤና ያድልልን!
የህይወት መንገድዎ ተስፋን እና ብርታትን ይለግሳሉ ።
ፅሑፎችዎ አግኝተን ብናነብ እንማርበታለን። ጥቆማ ቢሰጡን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ሰው መልካም ከሆነ ሌሎች ነገሮች ሁሉ ቀላል ናቸው ብዬ አስባለሁ፡፡ እንደ ቤተክርስቲያን ስነ-ምግባርን ስናስተምር መንፈሳዊነት ነው። ክርስትና ማለት ፍፁም መሆን ማለት ነው፡፡ የሰማይ አባታችሁ ቅዱስ እንደሆነ እናንተም ቅዱሳን ሁኑ ነው የተባልነው
ቃለ ህይወት ያሰማልን
It is inspiring. !!!
ዕድሜ ይሥጥልን!
ቃለ ህይወት ያሰማልን ግሩም ነው! የጃንደረባው(ኢጃት) አባል ለመሆን ምን ማድረግ ይጠበቅብናል?
ቃለ ሕይወት ያሰማልን