በቅኔ ድርሰት ታሪክ ውስጥ የቅዱስ ያሬድ ድርሻ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ለመላው ሕዝበ ክርስቲያንና በአጠቃላይ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ካበረከተቻቸው ዘመን የማይሽራቸው ጊዜም የማይለውጣቸው ብርቅና ድንቅ የሆኑ አእምሮአዊ ሀብቶችና መንፈሳዊ ቅርሶች መካከል አንዱ ቅኔ ነው። “ቅኔ” ቀነየ – ገዛ ወይም ተቀንየ – ተገዛ የሚለውን የግእዝ ግሥ ያስገኘ ጥሬ ዘር ሲሆን ቀጥተኛ ትርጉሙ መግዛት፣ መገዛት፣ አገዛዝ፣ ተግባር፣ አገልግሎት ማለት ነው። ቃሉ ከያዘው ሰማዊ ፍቺና ጭብጥ አንጻር በተለይ በግእዝ ቋንቋ ፍጡር ለፈጣሪ፤ ገዥ ለተገዥ፤ ተመሪ ለመሪ፤ ታዛዥ ለአዛዥ የሚታዘዝበትንና የሚያገለግልበትን የገዥና የተገዥ የመሪና የተመሪ ግንኙነት፣ ሥርዓት፣ ስምምነት ወይም ግዴታ እንዲገልጽ ሆኖ በመጻሕፍት ይጻፋል በቃልም ይነገራል። 

ይሁን እንጂ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከትምህርት፣ ከመንፈሳዊ አገልግሎትና ከሥርዓተ አምልኮት ጋር በተያያዘ ቅኔ የሚለው ስያሜ ሲነሣ የቃሉ ፍቺና መሪ አሳብ እንደተጠበቀ ሆኖ በሰማዕያን አእምሮ ቀድሞ የሚታሰበው ለትምህርትና ለምስጋና የሚደረሰው፣ የሚዘራው፣ የሚዜመውና የሚራቀቀው በኅብረ ቃል፣ በምሳሌ፣ በንጽጽርና በምርምር ተከሽኖ በሰምና በወርቅ ተከፍፎ በጥቂት ንባብ ብዙ ምሥጢር በአንድ ማሠሪያ መንታ መልእክት የሚያተላልፈው ልዩ የምስጋና ድርሰት ነው። 

በርግጥም ቅኔ ከሌሎች ድርሰቶች በተለየ መልኩ ትርጉም የሌለው የማይመሠጠር ቃል ሐረግ እንዳይገባ፣ ቤት እንዳይፈርስ ወይም እንዳይገጥም፣ ዜማ ልክ እንዳይሰብር፣ አገባብ እንዳይጥስ አእምሮን አስጨንቆ ልቡናን በርብሮ በልዩ ጥንቃቄ የሚደረስ ድርሰት በመሆኑ ባለቅኔ ቅኔን ለመድረስ አካሉን፣ አእምሮውንና ልቡናውን በማስገዛት የሚያደርገው ዝግጅት ከዝግጅቱም በኋላ ታጥቆ አደግድጎ አንደበቱን ከአእምሮው አእምሮውን ከአንደበቱ አስማምቶ አግባብቶ እርሱንም ሰሚውንም ደስ በሚያሰኝ ሁኔታ ቅኔውን መቀኘቱ ቅኔውን ለሚያቀርብለት ፈጣሪ በአካልም በመንፈስም መገዛቱን በተጨባጭ የሚያሳይ በመሆኑ ድርሰቱ ቅኔ መባሉ ቅኔም የዚህ ድርሰት ዋንኛ መጠሪያ መሆኑ አሳማኝ ነው። 

ትርጉሙን በተመለከተ ቅኔ የሚለው ቃል የወጣው “ቈንቈነ-ነቀዘ/በነቀዝ ተበላ” ማለት ነው፤ ነቀዝ እንጨትን እንደሚበላ እርሱም የደራሲውን ልቡን እየበላ ያደክማል ብለው የሚተርጉሙ መምህራን አሉ። ቅኔ ባለቅኔውንም ሆነ ሰሚውን ደስ የሚያሰኝ፣ በዕውቀት ለመራቀቅ ኅሊናን የሚያነሣሣ የሚያነቃቃ፣ ልናገር፣ ላመሥጥር፣ ልፈላሰፍ የሚያሰኝ የኅሊና እርሾ ሆኖ ሳለ ደኅናውን እንጨት ቆረጣጥሞ ከማበላሸት በቀር እንዳች በማይጠቅም በነቀዝ መመሰሉ የሚገባ ባይሆንም ውሳጣዊ አካልን መፈተሹ መበርበሩ ግን ሐቅ ነው። ምናልባትም ሊቁ ቅዱስ ያሬድ ርቱዐ ሃይማኖት በሆነ በንጉሥ ገብረመስቀል ፊት በዜማ ሲያመሰግን አዳማጭ የነበረው ንጉሡ ብቻ ሳይሆን ራሱም በሚያዜመው ዜማ ለጊዜው የነበረበትን ቦታውን ሁናቴውን ሁሉ ረስቶ ኅሊናው ሰማየ ሰማያትን ፈለከ ፈለካትን እየቃኘ ምስጋናውን እስኪጨርስ ድረስ የንጉሡ ጦር በእግሩ ላይ መቆሙን ደሙም መፍሰሱን ሳያስተውል እንደቆየ ያሉበትን እስከመዘንጋት በአጠገብም የሚሆነውን ማጤን እስካለመቻል የሚያደርስ ተመስጦ ውስጥ ሊያስገባም ይችላል። 

በአፄ ኢያሱ ዘመነ መንግሥት እንደሆነው፤ አንድ መምህር በቅጽረ ቤተ ክርስቲያን ጉባዔ ዘርግቶ ሲያስተምር ሳለ አፄ ኢያሱ እጅ ለመንሣት ወደ ቤተ ክርስቲያን ይገባሉ፤ ደቀ መዛሙርቱ ንጉሡን አይተው ተነሥተው ሲያሳልፉ መምህሩ ሳይነሣ ይቀራል፤ እጅ ነሥተው ሲመለሱ አሁንም ተቀምጦ ያሳልፋቸዋል፤ ነገሩ ቢደንቃቸው መጨረሻውን ሊያዩ አልፈዉት ተቀመጡ። በሙያው ያከብሩት ነበርና የወርቅ ዳረጎት ጣሉበት፤ እርሱ ለተማሪዎቹ አንዱን ቅኔ ቆጥሮ ተማሪዎቹ ያን የነገራቸውን እስኪያጠኑት ድረስ ሌላውን ቅኔ በኅሊናው እያዘጋጀ ነበርና የወርቅ ዳረጎቱ ድንገት ሲያርፍበት አፈፍ ብሎ ተነሥቶ ንጉሥ መሆናቸውን ዐውቆ ወዲያው “በእስጢፋኖስ አዕባን እንዘ የኀልቁ፤ ዘበጠኒ ኢያሱ በወርቁ።  ደንጊያዎች በእስጢፋኖስ ላይ ሲያልቁ እኔን ኢያሱ በወርቁ መታኝ” ብሎ ተቀኝቷል።                            

ከትርጉሙ ሳንወጣ ታልቁ የግእዝ ቋንቋና የትርጓሜ መጻሕፍት የብዙ ሴማውያት ቋንቋዎችም ሊቅ የነበሩት አለቃ ኪዳነወልድ ክፍሌ “አማርኛ ሰዋስው ወግሥ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ” በተባለ መጽሐፋቸው ቅኔ የሚለውን ቃል ሲፈቱ ግጥም፣ ሙሾ፣ ቅንቀና የፍትሐት፣ የልቅሶ፣ ዜማ ፣ የማኅሌት ቁዘማ ማለት ብለዋል። (ኪዳነወልድ ክፍሌ 1955 ገጽ 798) ፍቺው የቅኔን ጠባይ፣ ቅርጽ፣ አደራረስና ይዘት በሚያሳይ መልኩ የተሰጠ ይመስላል። በተመሳሳይ መልኩ ዎልፍ ሌስላው የተባለ ግእዝና አማርኛን ጨምሮ በርካታ የኢትዮጵያን ሴማዊያት ቋንቋዎች ያጠናና መጻሕፍትን የጻፈ ፖላንዳዊ ምሁር ቅኔ የመንፈሳዊ አገልግሎት አካል የሆነ የኢትዮጵያ የግጥም ድርሰት እንደሆነ በመግለጽ ጽፏል። (ቮልፍ ሌስላው 19 ፡ ገጽ ) ቅኔ የሚል ስያሜ የተሰጣቸው ቅኔ ልምሰል የሚሉ ድርሰቶች በብዙ አገሮች ቢኖሩም በሀገራችን ያለውን የመሰለ የተራቀቀ ቅኔ በሌላ ሥፍራ የማይገኝ በመሆኑ ሌስላው “የኢትዮጵያ” ማለቱ የሚያስመሰግን አገላለጽ ነው። ጥቅሙን በተመለከተ ግን በዋነኝነት ለመንፈስቅዱስ አገልግሎት የሚቀርብ የምስጋና ድርሰት መሆኑ የታመነ ቢሆንም ቅኔ ከመንፈሳዊ አገልግሎት በተጨማሪ በማንኛውም ጊዜ፣ ቦታና ሁኔታ ለኀዘን፣ ለደስታ፣ ለጥናት ለምርምር ሊደረስና ሊቀርብ የሚችል ጥበብ በመሆኑ በምስጋናነቱ ብቻ መገደብ ያስቸግራል። በጥንት ጊዜ ሊቃውንት የግልና የማኅበር ጉዳዮቻቸውን ለሹማምንት፣ ለአሳዳሪዎች ለማቅረብ፣ ብሶታቸውንና ደስታቸውን ምሬታቸውንና ተስፋቸውን ለመግለጽ፣ ምሥጢር ለማካፈል ዕውቀትና ታሪክ ለማስተላለፍ ቅኔን በመሣሪያነት ተጠቅመውበታል ዛሬም የሚጠቀሙበት ይኖራሉ። ብዙ የአካባቢ፣ የሀገርና የዓለምን ታሪክ ሊያስታውሱ የሚችሉ ቅኔዎች በጥንት የብራና መጻሕፍት ኅዳጋት በብዛት ይገኛሉ። 

የዚህ ጽሑፍ ዐቢይ ርእስ ወደሆነው የቅኔ ድርሰት አጀማመር ታሪክና የቅዱስ ያሬድ አስተዋጽኦ ከመግባታችን በፊት በተያያዥነት ያነሣነውን የቅኔን ጠቀሜታ በጥቂቱ እንመልከት፤ የቅኔና የመጻሕፍት ትርጓሜ ሊቅ መልአከ ብርሃን አድማሱ ጀምበሬ “መጽሐፈ ቅኔ” በተባለ መጽሐፋቸው የቅኔን ጠቀሜታ ሲገልጹ ቅኔ የመጻሕፍት መክፈቻ፣ የድርሰት መልመጃ፣ የአእምሮ ማጎልመሻ ነው ብለዋል። (አድማሱ ጀምበሬ 1963 ገጽ 15)

“የመጻሕፍት መክፈቻ” የሚለው የሊቁ አገላለጽ ምናልባት የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳት መጻሕፍት ጥንቱ በግእዝ ቋንቋ ስለተጻፉ ወይም ከጽርዕ፣ ከዕብራይስጥና ከኮፕት ዐረብ ወደ ግእዝ ቋንቋ ስለተተረጎሙ መጻሕፍቱን ለማንበብ ወይም ወደ ሌላ ቋንቋ ለመመለስ የሚቻለው ግእዝ ወይም ቅኔ በመማር ነው የሚል እንድምታ የያዘ መስሎ ሊታይ ይችላል። ኃይለ ቃሉ ግን በዚህ ብቻ የሚወሰን አይደለም። የመጻሕፍትን ምንባባት በጎላ በተረዳ ነገር ለማወቅ ቃል በቃል መመለስ ወይም መተርጎም ብቻ በቂ አይደለም፤ ይህ ዓይነት አካሄድ ወደተሳሳተ አመለካከት ቢጎትት እንጂ ትክክለኛውን መልእክት ወደማግኘት ሊያደርስ አይችልም፤ የቋንቋ ጠባዩ አመሉ ብዙ ስለሆነ ሊተረጎም በሚችልበት ሁኔታ ሁሉ በተለያየ አቅጣጫ ተርጉሞ አመሥጥሮ መረዳት ያስፈልጋል። ቅዱስ ጳውሎስ “ንባብ ይቀትል ወትርጓሜ የሐዩ ንባብ ይገድላል ትርጉም/ጓሜ ግን ያድናል” ማለቱ ሮሜ ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችንም መጻሕፍትን አንድም ብላ ፈትታ አብራርታ ንባቡን ከትርጓሜ አስማምታ ማሳየቷ ማስተማሯ ከዚህ የተነሣ ነው። የመጻሕፍት ትርጓሜ/ አንድምታ ትምህርት በቤተ ክርስቲያናችን ልዩ ትኩረት የሚሰጠውና ሌላውን ትምህርት ንባቡን፣ ቅዳሴውን ዜማውን፣ ቅኔውን፣ አቋቋሙን ከተማሩ ዕውቀት ካደላደሉ በኋላ በስፉሕ አእምሮ የሚማሩት ትምህርት ነው። 

ይህን ትምህርት አከነዋውኖ መማር ማጥናት የሚቻለው ቅኔን ከነአመሉ ጠንቅቀው የተማሩ እንደሆነ ነው፤ ጥንቱን መጻሕፍቱንም አንድም ብለው በላይ ቤት በታች ቤት የተረጎሙና ያራቀቁት በቅኔ ትምህርት የበሰሉና የተራቀቁ ሊቃውንት መሆናቸው ጥያቄ ውስጥ የማይገባ ሐቅ ነው። ለጥሩ ባለ ቅኔ የመጻሕፍትን ትርጓሜ ማጥናትም ሆነ ያጠኑትን አስፋፍቶ አራቆ ማቅረብ ቅኔ ከመዝረፍ ወይም ከመቁጠር የተለየ አስቸጋሪ አይደለም፤ የቅኔ ትምህርት ሳይደላደልላቸው የመጻሕፍትን ትርጓሜ እናጠናለን ለሚሉ ግን መንገዱ በብዙ ጭንቅ ወጣሁት ካሉ በኋላ አንሸራቶ ወደነበሩበት የሚመልስ ዐቀበት ሊሆንባቸው የግድ ነው። ስለዚህም ኃይለ ቃሉ ቅኔ ቅዱሳት መጻሕፍትን አራቀን አመሥጥረን ለምንማርባቸው ትርጓሜያት ምንጭ መሆኑን የሚያሳይ ኃይለ ቃል ነው ማለት ይቻላል።

 “የድርሰት መልመጃ” የሚለውም አገላለጽ እንዲሁ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለጸሎትና ለምስጋና የምገለገልባቸው መልክእን፣ ነግሥን፣ አርኬን የመሳሰሉ በግጥም መልክ የተደረሱ እንዲሁም የግጥምነት ይዘት ሳይኖራቸው ለምስጋናና ለዘክሮተ ቅዱሳን የተጻፉ ድርሳናትን ገድላት የመሳሰሉ ድርሰቶች ሁሉ እንደ መጻሕፍት ትርጓሜ ሁሉ የቅኔ ዕውቀታቸው ከፍ ባለ ሊቃውንቱ የተደረሱ መሆናቸውን በየሚያስታውስና አሁንም የጥበቡ ምላት ስፋት ርቀት የተጻፈን መተርጎም ብቻ ያይደለ አዲስ ድርሰት መድረስ የሚያስችል መሆኑን ያሳያል።

ቅኔ እንደሌሎቹ የምስጋና ድርሰቶች አንድ ጊዜ የተደረሰና በሌላ ጊዜ እየተደጋገመ የሚደረስ የሚዘመር ድርሰት አይደለም። በየጊዜው አዲስ ቅኔ ይቀርባል እንጂ፤ ቤተ ክርስቲያናችን ነቢየ እግዚአብሔር ዳዊት “ሰብሕዎ ለእግዚአብሔር ስብሐተ ሐዲሰ እግዚአብሔርን በአዲስ ምስጋና አመስግኑት” መዝ 149፡1 ያለውን ምዕዳን የምትፈጽምበት የምስጋና ድርሰቷ ቅኔ ነው። በቅኔ ትምህርትና አገልግሎት አንድ ጊዜ የተቀኙትን ቅኔ ደግሞ መቀኘት ወይም ሌላ ሰው የተቀኘውን ደግሞ ማቅረብ የስርቆት ያህል ወንጀል ነው። በመሆኑም ባለ ቅኔ የሆነ ሁሉ በቤተ ክርስቲያን ውስጥም ይሁን ከቤተ ክርስቲያን ውጪ በማንኛውም አጋጣሚ ቅኔ የሚያቀርብ ወይም የሚቀኝ ከሆነ አውጥቶ አውርዶ ንባቡ ያማረ ምሥጢሩ የሠመረ አዲስ ቅኔ መቁጠር ይኖርበታል። በዚህም ላይ ቅኔ አሳብ በግልጽ የሚተላለፍበት ነጠላ ግጥም ሳይሆን ሰምና ወርቅ ያለው አስበው ተመራምረው የሚደርሱበት እንጂ እንደሰሙት ወዲያው በቃኝ ዐወቅሁት የማይሉት ረቀቅ ያለ ድርሰት በመሆኑ ባለቅኔ አዲስ ቅኔ ለመድረስ ሁል ጊዜ ሲመራመር ሲራቀቅ ነው የሚኖረው። እንዲህ በብዙ ምርምር ቆጥሮ ቀምሮ የሚቀኘውንም ቅኔ የሚሰሙ ሰዎች በቃላት አሰካኩ በምንባባት አሰዳደሩ በምሥጢሩ በምርምሩ መመሰጣቸውና ልቡና ሐሤት የአእምሮ ሲሳይ ማግኘታቸው አይቀርም። ሊቁ እንግዲህ ቅኔ “የአእምሮ ማጎልመሻ” ነው ማለታቸው ከዚህ አንጻር ነው።

አሁን ቅኔን ማን ደረሰው? መቼ ተደረሰ? ወደሚሉት ነጥቦች እንምጣ፡ ስለ ቅኔ ድረሰት አጀማመር ሁለት የተለያዩ ታሪኮች ይነገራሉ፤ ከ16ኛው ክ/ዘ ጀምሮ ከቅኔ ትምህርት መስፋፋትና አልፎ አልፎም በጥቂት ነጥቦች ላይ የተለያየ አመለካከት በመያዝና የየራሳቸውን አካሄድ በመሄድ ምክንያት አንዳቸው ከሌላቸው ተለይተው በየራሳቸው የተስፋፉትና አሁንም በዚሁ መልኩ የሚገኙት ዋሸራ፣ ዋድላ እና ጎንጅ ከሚባሉት የቅኔ ቤቶች (ዋና ማዕከሎች ለማለት ነው) መካከል ጎንጅ የተባለው የቅኔ ቤት ሊቃውንት ቅኔን የደረሰው ተዋነይ የተባለው ሊቅ እንደሆነ ይናገራሉ። ተዋነይ በ15 ኛው ክ/ዘ የነበረ ሊቅ ሲሆን የጎንጅ ቅኔ ቤት መሥራች ነው። እንደሊቃውንቱ አገላለጽ ተዋነይ ቅኔን ከመድረሱ በፊት ወደ ግሪክ በመሄድ ሰባት ቋንቋዎችን/ ጥበባትን ተምሯል። ከሰባቱ አንዱ ቅኔ ሲሆን ሲመለስ ለአፄ እስክንድር (14) እና ለሌሎች አስተምሯል። ይሁን እንጂ የኢትዮጵያ ቅኔ በኢትዮጵያ እንጂ በሌላው ዓለም ያለተገኘና የማይገኝ በመሆኑ ከጎንጅ በስተቀር የሌሎቹ ቤቶች ሊቃውንት አሳቡን አይቀበሉትም። 

የዋድላ ቅኔ ቤት (ማእከል) ሊቃውንት ስለቅኔ አጀማመር የሚተርኩት ታሪክ ከዚህ የተለየ ነው። ሊቃውንቱ ቅኔን ያስፋፋውና የዋድላን ቅኔ ቤትም የመሠረተው ዮሐንስ ገብላዊ /ዘገብሎን እንደሆነ ቢመሰክሩም የቅኔ ጀማሪ ብለው የሚያምኑት ቅዱስ ያሬድ እንደሆነ ነው። ዮሐንስ ገብላዊ የዋድላ ሰው ሲሆን በ15ኛው ክ/ዘ የነበረ ሊቅ ነው። ሊቁን ቅኔን ለማስፋፋት ያነሣሣው የቅዱስ ያሬድ ጅምር የቅኔ ድርሰት ነው። ቅዱስ ያሬድ ምዕራፍ በተባለው ድርሰቱ ለድርሰቶቹ መለያ የሰጣቸውን ሚ በዝኁ ዋዜማ ሥላሴ ዘይእዜ መውድስ ክብር ይእቲ ዕጣነ ሞገር የሚሉትን ስያሜዎች ተመልክቶ ቅኔ ተገልጾለት እንደነበረ በማመኑና ለርሱ የተገለጸለት ይህ መንፈሳዊ ጥበብ እንዲገለጽለት በመመኘቱ ደብረ ታቦር በምትባል አፄ ይኩኖአምላክ በቦረናና በአማራ ሳይንት መካከል እንደመሠረቷት በሚነገርላት ከተማ ሱባዔ ገባ። ሱባዔውን ሲፈጽም መንፈስቅዱስ ለቅዱስ ያሬድ የገለጸውን የቅኔ ጥበብ ገልጾለት አምልቶ አስፍቶ ተናግሮታል። የቅኔዎቹን ስያሜያቸውንም ከቅዱስ ያሬድ የድጓ አርእስት ስያሜ አያይዞ ሰይሟቸዋል።

ከዮሐንስ ዘገብሎን ተምሮ ቅኔን ለሠምረክርስቶስ ያስተማረው አባ ወልደገብርኤል ነው፤ ሠምረክርስቶስ በሚያስተምር ጊዜ ከንጉሥ በእደማርያም ጋር ተጣላ፤ ንጉሥ በእደማርያም አንተና መምህርህ ዐወቅን ተራቀቅን ስትሉ አገኝ አጣውን ተቀባጥራላችሁ ብሎ ሠምረአብን ገሠጸው፤ ሠምረአብም ከመንፈስቅዱስ የተገኘ እንጂ ቅኔ የሰው ፈጠራ አይደለም፣ ልታውቅ ብትወድስ ሱባዔ እንግባ አለው። ንጉሡም በዚህ ተስማምቶ ሁለቱም ሱባዔ ገቡ። ከዚህ በኋላ ለዮሐንስ እንደተገለጸለት መንፈስቅዱስ ለንጉሥም ገልጾለት

 “ድኅረ ተሰብረ አጽንዖ ለሰብእናነ ልሑክት፤
ኢየሱስ ክርስቶስ በማየ ሐዲስ ጥምቀት”

ብሎ ተቀኘ። ቅኔውም ጉባዔ ቃና ተባለ፤ ዕለቱ የቃና ዘገሊላ ዕለት ነበርና። አንዳንድ ሊቃውንት ጉባዔ ቀና ሲሉ ነው ይላሉ፤ በሸዋ ጉባዔ ቃና በተባለ ሥፍራ ስለተደረሰ ነው የሚሉም አሉ። ሠምረአብም የአምላኬ ነገር እንዲህ ነው ሲል በደስታ ዘአምላኪየ (ባለ 3 ቤት) ቅኔ ተቀኘ። ከዚህ በኋላ እየተቀባበሉ ሙሉ ቤት ተቀኝተዋል። 

የንጉሡ ባለቅኔ መሆን ለቅኔ ትምህርት መስፋፋት አስተዋጽኦ ማበርከቱ ግልጽ ነው። ጉባዔ ሰፍቷል ተማሪዎችም በዝተዋል። 

 ከሠምረአብ ቀጥሎ ልሒብ እና ኤልያብ የሚባሉ ሊቃውንት ተከታትለው ተነሥተዋል። ኤልያብ ድድቅ ወልደማርያም እና ተዋነይን አስተምሯል። በእነርሱ ዘመን ግራኝ መሐመድ ሀገር ወረረ። የወረራውን ጊዜ (1215-1530 ዓ/ም) ድድቅ ወልደማርያም ጨረቃ ወደምትባል ሥፍራ በዳውንት ተዋነይም በደቀ እስጢፋ ጣና ተሸሽገው አሳለፉ። ድድቅ ወልደማርያም ከሰው ባለመለየቱ ቅኔውንም አገባቡንም እንደያዘ ወጥቷል፤ ተዋነይ ግን ጉባዔ ስላልነበረው አገባቡ ጠፍቶበት ቅኔውን ብቻ ይዞ ወጥቷል። ሲወጣ መምህሩ ስላልነበረ ከጓደኛውም መጠየቅ ስላልወደደ በጎጃም ጎንጅ በሚባል ሥፍራ ቅኔውን ብቻ እያስተማረ ኖረ፡ በዚህም ምክንያት በጎንጅ የዋድላን ያህል ብዙ አገባብ አይገኝም እርባ ቅምርም የለም።

እንግዲህ የጎንጅ ቅኔ ቤት ቅኔን የደረሰው ተዋነይ ነው ማለታቸውን ሌሎቹ ሊቃውንት የማይቀበሉት ከዚህ አንጻር ነው፤ ከፍ ብሎ በተተረከው ታሪክም እንዳየነው ተዋነይ በቅኔ ዐዋቂነቱ በእጅጉ የሚመሰገን ሊቅ ተመራማሪ ቢሆንም ጥበቡን ከኤልያብ ተምሮት እንጂ ከራሱ አንቅቶት አላስተማረም። የኤልያብንም ትምህርትና ጥበብ አመጣጥ ስንመረምር የታሪክ ሐረጉን ጫፍ በዮሐንስ ዘገብሎን በኩል አልፎ ቅዱስ ያሬድ ጋር እናገኘዋለን። እንግዲህ ቅዱስ ያሬድ የዜማ ብቻ ሳይሆን የቅኔም ደራሲ መሆኑን ያለማቅማማት መመስከራችን ከዚህ የተነሣ ነው።

አንዳንድ ባለቅኔዎች የቅዱስ ያሬድን ደራሲነት ተቀብለው ነገር ግን ቅኔዎቹ ቤት የሚመቱ እንዳልነበሩ ቤት እንዲመታ ያደረጉት የኋላ ሊቃውንት እንደሆኑ ይገልጻሉ፤ እንደማስረጃነትም “ተትሕተ ያሬድ ዘኢተትሕተ፤ ለቅኔያቲሁ ደቂቅ እስመ ኢሐነጸ ቤተ” ብሎ ስሙ ያልታወቀ (ተች) ባለቅኔ የተናገረውን የቆየ ቅኔ ይጠቅሳሉ። ነገር ግን ይህ አባባል በምንም መንገድ እውነት ሊሆን ቀርቶ ሊመስል አይችልም፤ ምክንያቱም የቅኔ ቅርጽ አላቸው የሚባሉ ድርሰቶቹ በርግጥ እንደ ቅኔ ቤት የሚመቱ እንደነበሩ በሚከተሉት ሁለት ድርሰቶቹ ማየት ይቻላል፡

1. ነያ ደብተራ፣ እንተ ርእያ እዝራ፣ 
ይሔውጽዋ ዘሰማይ ሐራ።

2. በጾም ወበጸሎት ፍትወተ ሥጋ አግርሩ፣ 
ከመ አንስርት በአክናፍ ትሥርሩ፤  

እኒህ ድርሰቶች ምንም እንኳ በሂደት እየተሻሻለ መጥቶ አሁን ያለውን ወጥ የሆነ የዜማ ልክ የጠበቁ ባይሆኑም ቤት የሚመቱ፣ በሰምና ወርቅ ተደራራቢ መልእክት የሚያስተላልፉ ቅኔዎች ናቸው። ይህን የመሰሉም ብዙ አሉ። ከዚህም በተጨማሪ ቅዱስ ያሬድ ራሱ የደረሳቸውና ከ22ቱ የቅኔ ዓይነቶች ውስጥ የሚቆጠሩ በተሠራላቸው ጊዜም የሚደርሱ ቁጥራቸው ከክብር ይእቲና ከዕጣነ ሞገር የሆነ ድርሰቶች አሉት፤ አንዱ በምሴተ ኀሙስ የሚደረሰው

“ሐዋያቲሁ ከበበ፣ እግረ አርዳኢሁ ሐጸበ፣
ኮኖሙ አበ ወእመ ወመሀሮሙ ጥበበ”


የሚለው ነው። 

እንግዲህ እኒህና እኒህን የመሳሰሉ ድርሰቶቹ በግልጽ እየታዩ የቅዱስ ያሬድን የቅኔ አባትነት ጥያቄ ውስጥ ማስገባት በምንም መንገድ አሳማኝ ሊሆን አይችልም። የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ያሬድን የምታከብረውና የምታዘክረው ዜማና ከቅኔ ቅኔን ከዜማ ሳትነጥል የዜማም የቅኔም ደራሲም መሆኑን በመመስከር ነው። 

ማስታወሻ :- መጋቤ ምሥጢር ዶ/ር አባ ኅሩይ ኤርምያስ የቅኔ መምህርና የበርካታ መንፈሳዊ መጻሕፍት ደራሲ ናቸው:: መዝገበ ታሪክ ፣ መርኆ ምሥጢር ፣ መጽሐፈ ምሥጢር ትርጉም ፣ ገድለ ታዴዎስን ወዘተ የመሳሰሉ መጻሕፍትና ጥናታዊ ጽሑፎችን ያበረከቱ ሲሆን በጀርመን ሀገር በአገልግሎትና በምርምር ሥራ ላይ ይገኛሉ::

Share your love

7 አስተያየቶች

  1. ሰላም ጤናን እረጅም እድሜን እግዝአብሔር አምልክ ለአባታችን ይስጥልኝ ቃለህይወትን ያሰማልን ጥሩ ግዜ ነበር የቅኔን ድርሰት እንደዚህ አንብበን ከአባታቸች ሰማን የአገልግሎት ዘመናቸውን ይባርክልን አሜን !!

    • ቃለ ሕይወት ያሰማልን አባታችን! እድሜን ከጤና ያድልልን:: ቅዱስ ያሬድ ብዙ ለትውልድ የሚተላለፉ ባለ ተሰጥኦ ነው:: ቅኔን ከዜማ ጋር ብቻ ሳይሆን ድምፀ መረዋ መሆኑም ላይ ብዙ ሊፃፍለት የሚገባ ቅዱስ ነው:: አባታችን በሌላ ጊዜ እንደሚመለሱበት አምናለሁ:: በነገራችን ላይ ጸሐፊው ራሳቸው ደቂቀ ያሬድ ናቸው:: ስለ ቅዱሱ አባታችን ብዙ ማለት ይችላሉ በምግባረ እውቀት እሱኑ እየመሰሉ ነውና::ቸር ያሰማን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *