ምድር ከጥፋት ውኃ መድረቅ በኋላ በኖኅ መርከብ ውስጥ ከነበሩ እንስሳትና አራዊት በቀር ሌላ አንዳች ፍጥረት አልነበረባትም። በምድር ላይ የሚርመሰመሰውን ሥጋ ለባሽ ፍጥረት ሁሉ ለጥፋት የዘነበው ውኃ ሙልጭ አድርጎ ደምስሶታል። ኖኅ ከመርከብ ሲወጣ ምድርን በዝሙታቸው ያበላሿት የቃኤል ልጆች በከተሞቻቸው አልነበሩም። ቅዱስ መጽሐፍ “በምድር ላይ ስማቸው የታወቀ ኃያላን ሆኑ” ዘፍ 6፥4 ብሎ የሚጠራቸው ኔፊሊሞች አሁን የሉም። የደብር ቅዱስ ባህታውያንን በውበታቸው ያሳቱ የቃኤል ቆነጃጅትም እንደ ቀድሞው በከተሞች መካከል ሲመላለሱ አይታዩም።
እግዚአብሔር ከተቆጣ ጉልበት አያድንም፤ ውበትም ልብ አያራራም፤ ደም ግባትም አያኖርም፤ ሀብትና ዝናም መሸሸጊያ ሊሆን አይችልም። የእግዚአብሔር ትዕግሥት ምድርን ከዝሙቷ ካልመለሳት በቀር ከቁጣው የሚያስጥላት ምንም ነገር የለም።
ምድርን ሁሉ ባዳረሰው በዚያ ጥፋት መካከል ራሱንና ቤተሰቡን ማትረፍ የተፈቀደለት ኖኅ ብቻ ነበረ፤ በእግዚአብሔር ፊት ብቻውን ጻድቅ ሆኖ ተገኝቷልና። ከገነት ያስወጣችን ኃጢአት በዚህ ምድርም ከመኖር ከለከለችን። በገነት ሳለን እርግማንን አመጣችብን፤ በዚህ ምድርም ላይ የጥፋት ዝናምን አዘነመችብን። ወዮ! ከኃጢአት የተነሣ በሰው ላይ የደረሰው መከራ ብዛቱን ማን ቆጥሮ መጨረስ ይችላል?
እሳት ከሰማይ ቢዘንብብን፣ ንፍር ውኃ ቢያቃጥለን፣ ምድር ተከፍቶ ቢውጠን፣ ረሀብና ቸነፈር ቢያጠቃን፣ ድርቅ ምድራችንን እንዳታበቅል ቢያደርግብን፣ እርስ በእርሳችን መስማማት ቢያቅተን ይህ ሁሉ የሆነው በሌላ አይደለም፥ በኃጢአት ምክንያት ነው። ወደን በሠራነው ኃጢአት የማንወደው መቅሰፍት እየመታን እንኖራለን። ጣፍጦን የፈጸምነው ኃጢአት መራራ ሞትን እያስፈረደብን ወደ ሲዖል ያወርደናል። እኛ ኃጢአትን መሥራታችንን፣ ኃጢአትም እኛን ማስጠፋቷን ቀጥላለች።
ከአባታቸው ጻድቅነት የተነሣ ከሞት የተረፉት የኖኅ ልጆች ከመርከብ ከወጡ በኋላ በሌላ መንገድ ኃጢአት በራቸውን ስታንኳኳ ተመልክተናል። ለካ ያ ሁሉ ምድርን ለመቶ ሃምሳ ቀናት የሸፈናት ውኃ ኃጥአንን እንጅ ኃጢአትን ከምድር ላይ አላጠባትም ኖሯልና ኃጢአት አሁንም በሰዎች ልብ ውስጥ ሥር መስደድ ጀመረች። ሰይጣን አዲስ አዲስ የኃጢአት አሠራሮችን ማምጣት ልማዱ ነው። ከመርከብ የወጣው ትውልድ እንዳያመልጠው የቀደመውን ኃጢአት ይዞ አልቀረበም፤ አዲስ የኃጢአት አሠራር ይዞ ብቅ አለ እንጅ። እስካሁን የአባቱን ዕርቃን አይቶ በገዛ አባቱ የሚሳለቅ ትውልድ አልነበረም ዛሬ ግን ከሦስቱ የኖኅ ልጆች መካከል አንዱ የሆነው ካም የአባቱን ዕርቃን አይቶ ተሳለቀ፤ ብቻውንም አይቶ ሊቀር ስላልፈለገ ለወንድሞቹ ሁሉ የአባታቸውን ሀፍረት እንዲያዩ ቅስቀሳ አደረገ። “የከነዓን አባት ካምም የአባቱን ዕራቁትነት አየ ወደ ውጭም ወጥቶ ለሁለቱ ወንድሞቹ ነገራቸው” ዘፍ 9፥22 እንዲል።
ሰይጣን ዘመናዊ ነው፤ አሠራሩም ለትውልድ እንዲስማማ አድርጎ ማቅረብም ልዩ ችሎታው ነው። የአንድ ዘመን ትውልድ የተቀጣበትን ኃጢአት ለሌላ ትውልድ በማቅረብ ተከታይ ማጣት አይፈልግም። ስለዚህ ምን ያደርጋል መሰላችሁ፥ የፅንሰ ሀሳብ ልዩነት ባይኖረውም የንድፈ ሀሳብ ልዩነት አድርጎበት በሌላ መንገድ ያቀርበዋል። ያን ጊዜ ተከታዮችን ማግኘት ይችላል ማለት ነው። በዓለም ላይ ታላላቅ ጥፋቶችን ያስከተሉ ታላላቅ ኃጢአቶች ከአዳም ኃጢአት {አምላክነትን መሻት} ጀምሮ እስከ ሞተ ወልደ እግዚአብሔር ድረስ ሰባት ናቸው። እነዚህን ለአዲሱ ትውልድ በሌላ መንገድ ያቀርባቸዋል እንጅ ሌላ አዲስ ኃጢአት አያቀርብም።
ዮሐንስ በራእዩ የተመለከታቸው ሰባቱ የአውሬው ራሶች የተባሉትም እነዚሁ እንደሆኑ የሐዲስ ኪዳን መምህራን ያስተምራሉ ራዕ 13፥1 ከመርከብ በወጣው ትውልድ መካከል የገባችው ይህች የዛሬዋ በደል ኖኅ ወደ መርከቡ ከመግባቱ በፊት የነበረው ትውልድ የማያውቃት ሌላ በደል ናት − እሷም የአባትን ዕራቁትነት ማየት ናት። አዳም ዕራቁቱን በነበረ ጊዜ በገነት ዕፀዋት መካከል መሸሸጉ ዕራቁትነት አሳፋሪ ነገር በመሆኑ ነው። እግዚአብሔርም ዕርቃኑን ያሳይበት ዘንድ የገነትን ዕፀዋት በቅጠላቸው እንዳይሠውሩት አላደረጋቸውም። ዕርቃንን መግለጥ የማይገባ ስለሆነ ነው።
ሴምና ያፌት እንደ እግዚአብሔር ሆነዋል፤ የኖኅን ዕርቃን አላዩምና። ይህንን ነገር በሰሙ ጊዜ በማስተዋል ያደረጉትን ነገር መጽሐፍ ቅዱስ ይናገርላቸዋል። “ሴምና ያፌትም ሸማ ወስደው በጫንቃቸው ላይ አደረጉ የኋሊትም ሂደው የአባታቸውን ዕራቁትነት አለበሱ ፊታቸውም ወደ ኋላ ነበረ የአባታቸውንም ዕራቁትነት አላዩም” ዘፍ 9፥23 ተባለላቸው።
አስተዋይ ትውልድ እርቃንን በማየት አይደሰትም። እርግማን ከምድራችን ላይ እንዲወገድ የሚያደርግ እንዲህ ያለ ትውልድ ያስፈልገናል! ወደ ኋላ ሂዶ የታሪክ ዕርቃንን የሚሸፍን። እንዲህ ያለ ዘመን እንዲመጣልን እንጸልያለን፤ የአባቱን ሀፍረት ላለማየት በትክሻው ላይ ልብስ የሚያኖር ትውልድ እንዲሰጠን። ሴምና ያፌት በዚህ ዘመን ሊኖሩን ያስፈልገናል።
የሆነ ዘመን ላይ ከጭንቅ ያወጡን፣ ክፉውን ዘመን ያሻገሩን ሰዎች ጥቂት ኅፀፅ ስናገኝባቸው በሰዎች ፊት መሳቂያና መሳለቂያ የምናደርጋቸው ከሆነ ሰውነታቸውን ረስተናል ማለት ነው። ያኔ የታላቁ ቀላይ ምንጮች ተነድለው የሰማይም መስኮቶች ተከፍተው ከላይና ከታች የጥፋት ዝናም በዘነመ ጊዜ በጥበባቸው የምንሳፈርበትን መርከብ የሠሩልንን ሰዎች መሆናቸውን መዘንጋት አይገባንም።
ወደ ኋላ ተመልሶ በአባቶቹ የሚሳለቅ ትውልድ መፍጠር ምን ያደርጋል። ምንም ይሁን ምን ከጥፋት ውኃ ያተረፈን አባቶቻችን የሠሩት ሥራ ነው። ያንን ሞት ያለፍነው አባቶቻችን በእግዚአብሔር ፊት ሞገስ ስለነበራቸው ነው። ወደ ኋላ ከተመለስንም የምንሻገርበት መርከብ፤ የምንጠጋበት ወደብ የሠሩልን መሆናቸውን ማሰብ ይገባናል እንጅ ዕርቃናቸውን እያነሣን ብናሳይ ከመረገም በቀር ምንም ጥቅም የለውም።
ከእኛ በፊት የነበሩ አባቶቻችን የሠሩትን ታሪክ ቀድሞ ያጠና ካለ ለሚሰሙት ሁሉ መናገር ያለበት ኖኅ ደክሞ መተኛቱን እንጅ ዕርቃኑን መሆኑን አይደለም። ይህ ዛሬ ዕርቃኑን ያየነው ኖኅ ነው ዛሬ በሕይወት እንድንኖር ያደረገን። በቤተ መንግሥት፣ በቤተ ክህነት፣ በማኅበራት፣ በግለ ሰቦች፣ በመኳንንት፣ በካህናት የደረሱ ጥፋቶች የተነገሩ የማይገቡ ቃላት ሊኖሩ ይችላሉ። ዛሬ ላለው ትውልድ በየቀኑ ብናዘክረው እግዚአብሔር በመርከብ ጭኖ ከሞት ቢያሻግረው ሌላ ሞት እንዲገጥመው ማድረግ ካልሆነ ሌላ ጥቅም የለውም። ይህንን ቀን እንድናይ መጽሐፍ ጽፈው፣ ጉባኤ ዘርግተው፣ አገር ለአገር ዞረው አስተምረው ክፉውን አመል በመልካም አመል እንድንለውጥ አድርገው የደከሙልን ብዙ አባቶች አሉ።
የፖለቲካ፣ የጎሣ፣ የሃይማኖት መሪ የነበሩ ሊሆኑ ይችላሉ። ምናልባት የማይጠቅም ታሪክ ሠርተው እንኳን ብናገኛቸው ለሚመጣው ትውልድ የማይነበብ የሚል ከላዩ ላይ ጽፈንበት እንጅ እንዲሁ ማስተላለፍ አይገባም። ሴምን ያፌትን መሆን ይገባናል። “የሴም አምላክ እግዚአብሔር ይባረክ፤ እግዚአብሔር ያፌትን ያስፋ በሴምም ድንኳን ይደር ከነዓንም ለእነርሱ ባሪያ ይሁን” ዘፍ 9፥26 ብሎ የሚመርቀን አባት የምናገኘው ሴምና ያፌትን በመሰለ ሥራ ብንገኝ ነው። የሌሎችን ኃጢአት በትዕግሥት የራሳችንን ኃጢአት በንስሐ ማለፍ ከቻልን ከጻድቁ ኖኅ አፍ የወጣው የሴምና የያፌት በረከት ዛሬም በኛ ላይ ነው። ከእኛ መካከል የሌላውን ነውር የሚሠውር ሴምና ያፌትን የሚመስል ማነው?
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆን የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ናቸው::
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር በዚህ ዘመን ላለን
ሰውነታቸውን ረስተን የአባቶቻችንን ጉድለት በማያምኑት ደጅ ለምናሰጣ ወደልብ የሚመልስ ጽሑፍ!
እግዚአብሔር አገልግሎታችሁን ይባርክ አሜን!
ቃለ ህይወትን ያሰማልን አባታችን በተቻለ ፍጥነት አንዲ ያሉ ፅሁፎች በፍጥነት ቢወጡ መልካም ነው
ግሩም ትምህርት ከመውቀስ መስራትን የሚያስተምር:: ቃለ ህይወት ያሰማልን::
አስተዋይ ትውልድ እርቃንን በማየት አይደሰትም። እርግማን ከምድራችን ላይ እንዲወገድ የሚያደርግ እንዲህ ያለ ትውልድ ያስፈልገናል! ወደ ኋላ ሂዶ የታሪክ ዕርቃንን የሚሸፍን። እንዲህ ያለ ዘመን እንዲመጣልን እንጸልያለን፤
ቃለ ህይወት ያሰማልን::
ክቡር የምንወዶት ሊቀ ሊቃውንት ስምዓኮነ መልአክ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! በጊዜውስ ኖረን ጊዜን የምናከፋው ሰዎች ከራሳችን ክፋት ሳንርቅ በሰው ድክመት ላይ ለመሳለቅ እና ለማማት የምንሄድበት እርቀት የካምን ያህል የከፋ ነው እግዚአብሔር ልቦናችን ይመልስልን…… ሁሌም በድካም እና በእግዚአብሔር. እርዳታ ካገኙት እውቀት ባሻገር ለትንሹም ለትልቁም የሚያሳዩት ትህትናና ተግባቦት ያስገርመኛል እንደ ሊቅነቶ ሳይኮሩ እንደ ትልቅነቶ ሰውን ሳይንቁ ሁሉን በአንድ አይን አይቶ ለማስረዳት እና ለማስተማር የሚሄዱበትን እርቀት ይበል የሚያሰኝን ነው ። መልካም በረከቶ ይደርብኝ
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን። ለኛም አስተዋይ ልቦና ይስጠን።
አስተዋይ ትውልድ እርቃንን በማየት አይደሰትም!!
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሳማልን በእድሜ በጤና ይጠብቅልን ያገልግሎት ዘመኖን ይባርክልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር
ቃለ ሕይወት ያሰማል
አሜን እግዚአብሔር ይመስገን. ቃለህይወትን ያስማልን