ምጽዋትና ውዳሴ ከንቱ 

ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ስለምጽዋት ሲያስተምር አንድ ባለጸጋ ወደ እርሱ ቀርቦ ምጽዋት መመጽወት እወዳለሁ ወዳሴ ከንቱን መመሰገንንም እወዳለሁ አለው። ዮሐንስም ወዳሴ ከንቱውን ትተህ በትህትና መጽውት አለው። ይህ ባለጸጋ ግን አይሆንም ሁሉንም እወዳለሁ መስጠቱንም መመሰገኑንም እፈልጋለው ይህ ከቀረ ምጽዋቱም ይቅር አለው። እንኪያስ አትተወው መጽውት ሰው ዘር ይዘራል ባይጠብቀው ለእሸት ያህል አያጣለትም አንንተም ያዚያን ያህል ዋጋ አታጣምና ስጥ ብሎታል።

ውዳሴ ከንቱ የሚለው ቃል የማይረባ የማይጠቅም  ምስጋና የሚል ትርጓሜ ያለው ሲሆን  ውዳሴ  ብጡል (የተናቀ፤ ተርታ) ውዳሴ ተብሎም ይጠራል፡፡ የበቁትን ሳይቀር ሰይጣን ድል የሚነሳበት መሣርያ ይህ ከንቱ ውዳሴ ሲሆን በብዙ ታሪኮችና ትምህርቶችም ውስጥ የተማርነው በመጻሕፍት ውስጥ ደግሞ ያነበብነው ጉዳይ ሆኖ እናገኝዋለን። ማንም ቢሆን የዚህ የክርስትን ሕይወት ጸር በሆነው ውዳሴ ከንቱ ታስሮ እንዳይቀር የበቁ አባቶች በብዙ ድርሰቶቻቸው ላይ አጽንኦት ሰጥተው መክረውበታል። ጥንተ ጠላት ሰይጣን የመወደቁ ምክንያት ይህን ምስጋና መሻቱ ነበር።   ከሁሉ ልቆና ከብሮ የተፈጠረውም ሰው ከክብሩ የወረደው ይህን ለሰው ልጅ የማይገባውን ምስጋና በመፈለጉ ነው። ከመላእክት ጋር ያመሰግን ዘንድ የከበረ ኃብት የተሰጠው አዳም የአምላክነትን ምስጋና ሻተ ይህም እሾክና አሜኬላ ወደበዛባት ምድር እንዲወርድ ምክንያት ሆነው። ውዳሴ ከንቱን መሻት በብዙ መንገዶች ሊፈጸም እና ሊከወን ይችላል ነገር ግን በየትኛውም መንገድና ሁኔታ ቢፈጸምም የውዳሴ ከንቱ መልካም የለውም። ዋናው የጽሑፋችን ርእስ ስለ ውዳሴ ከንቱ አብዝቶ መገለጽ ሳይሆን ምጽዋትና ውዳሴ ከንቱ እንዴት ማነጻጸር አልያም ደግሞ ማቀራረብ ይቻላል በሚለው ጉዳይ ላይ ብቻ ስለሆነ ወደዋናው ጉዳያችን እናቀናለን። 

ለጽሑፋችን መነሻ ያደረግነው አጭር ታሪክ በማቴዎስ ወንጌል ትርጓሜ ላይ የሰፈረ ማንሻ ታሪክ ነው። መመጽወትና ምስጋናን መሻት አንድ ላይ የማይሔዱ በወንጌል ገመድነት ያልተሳሰሩ ጫፍና ጫፍ ያሉ ተግባራት ናቸው።  አካላዊ ቃል ወልድ ኢየሱስ ክርስቶስም ስለ ምጽዋት ባስተማረበት አንቀጽ ላይ ይህንኑ ሐሳብ ሲገልጽ እናየዋለን  “አንተ ግን ምጽዋት ስታደርግ ምጽዋትህ በስውር እንዲሆን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ በስውር የሚያይ አባትህም በግልጥ ይከፍልሃል።”— ማቴዎስ 6፥3-4። በዚህ ገጸ ንባብ ውስጥ ያገኝነው መሠረታዊው የምጽዋት ትምህርት የሚሰጥ ሰው በልግስን ይሰጥ ዘንድ እንጂ በሰጠው ልክ ምስጋናን እንዳይሽት ነው። የምጽዋት ደንቡ በገሐድ መስጠት ሳይሆን በስውር ተርታ ሰው ሆኖ መስጠት ነው። እንዲህ ዓይነት ምጽዋት ለውዳሴ ከንቱ የተመቸ አይደለም ለዚህም ነው ጌታችን ምጽዋትህ በስውር ይሁን ማለቱ ። ምጽዋት በብሉይ ኪዳን እና በሐዲስ ኪዳን እንዲሁም በአዋልድ መጻሕፍት ላይ  በሰፊውና በግልጽ የተጻፈ ከክርስትና መገለጫዎች መካከል ውስጥ አንዱ የሆነ ዐቢይ የትሩፋት ሥራ ነው። ይህ በእግዚአብሔር ዘንድ የተወደደው በጎ ምግባር ፍጹም እንዲሆን ግን ከከንቱ ምስጋና የራቀ መሆን እንዳለበት መጻሕፍት አብዝተው ይናገራሉ።

ቀድሞ መነሻ ወዳደረግነው የቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ታሪክ እንመለስ መመጽወትንም መመሰገንንም የሚፈልገውን ሰው ካለመሰጠት መስጠት ጥቂትም ቢሆን ዋጋ እንዳለው አስተማረው። ከንቱ ምስጋናን ውሉ እያደረ ይተወዋል ምጽዋቱ ግን ለተራቡት መጽናኛ ለደከሙት እረፍት ይህናል ለእርሱ ደግሙ የእሸት ያህል ዋጋ እንደማያጣበት መከረው። ስለዚህ መምህር ወመገሥጽ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ ያለ ውዳሴ ከንቱ መመጽወት አስፈላጊ እንደሆነ ቢረዳም ለባለጸጋውም በሚገባ ቃል በግልጽ ቢነግረውም የባለጸጋውን የመንፈሳዊነት ደረጃ በመረዳቱ ግን ከፍ ወዳለው የመንፈሳዊነት ደረጃዎች እስኪበቃ ድረስ እንዳይመጸውት አላዘዘውም ይልቁንስ ምጽዋቱም ምስጋናውም አይቅርብኝ ቢለው “ይሁን ስጥ የእሽት ያህል ዋጋ አታጣበትም” አለው። ምስጋናና ከመሻት በላይ የሆነው ምጽዋት በእግዚአብሔር ዘንድ ያለውን ክብር እንድንመለከት የሚያሳየን ታሪክ ነው። ወንጌል ትርጓሜ ላይ ይህን ታሪክ የሚያጸናለን አልያም የመስጠትን ኃይል የሚያሳይ አንድ ታሪክ ሰፍሮ እናገኝዋለን። 

አንጢላርዮስ ባለጸጋ  ንፉግ ሰው ነበረ። ነዳያን በመንገድ ሲያልፍ አይተውት ይህ ጽኑ ጨካኝ ባለጸጋ ለሰው አያዝንም እያሉ ያወሩበታል። ከመካከላቸው አንዱ ግን እኔ ሔጄ ሰጥቶኝ በልቼ ብመጣስ ብሎ ከተቀሩት ጋር ተወራረዶ ወደ ንፉጉ ባለጸጋ ሔደ። አንጢላርዮስም ምግቡን አቅርቦ እጁን ታጥቦ በሚመገብበት ጊዜ ነዳዩ ጠጋ ብሎ ስም እግዚአብሔር ጠራበት። እንዳይሰጠው ተርቧል እንዳይነሣው ስመ እግዚአብሔር ጠርቶበታል ተናዶ ዳቦውን ወርውሮ ግንባሩን ገመሰው። ይህም ነዳይ ደሙን አብሶ ዳቦውን ጎርሶ ለምልክት ጥቂት ይዞ ወጀ ወዳጆች ሔደ። በዚህ ሌሊት ባለጸጋው አንጢላርዮስ ራእይ ያያል። ነፍሱ ከሥጋው ተለይታ መላእክተ ጽልመት እያዳፉ ይዘውት ሲሄዱ መላእክተ ብርሃን ሲከተሏት እናተ ከእዚህ ምን አላችሁ ሲሏቸው ምነው ትላንተ ለድኃ ሰጥቶ የለም ይሏቸዋል። የጨለማው መላእክትም መታው እንጂ መች ሰጠው አሏቸው ይመስክር ተባብለው ወደ ነዳዩ መጥተው መስክር አሉት። ከረኃቤ ጽናት የተነሳ ከአጠገበኝ ውጪ ደም እንደፈሰሰኝ አልታወቀኝም ብሎ መሠከረ። በዚህም ምሥክርነት መሠረት የብርሃን መላእክት ነፍሱን በእጃቸው ሲያደርጓት አየ። ሲነጋ በዚህ ዓለም ሳሉ በገንዘብ ቢያውቁበት እንዲህ ያለ ጥቅም አለን ብሎ ነዳያንን ሰብስቦ ያለ ገንዘቡን ጨርሶ መጽውቶ ሲሄድ ነዳያንን ከመንገድ አገኙት ገንዘብ ትሰጣለህ ቢሉን መጥተን ነበር አሉት ቀደም ብላችሁ ብትመጡ ቢሆን ከፍዬ እሰጣችሁ ነበር አሁንማ ጨርሻለሁ አላቸው እንደምን እንሁን ቢሉት እኔን ሸጣችሁ ተካፈሉ አላቸው ለሠላሳ ወቄት ሸጠውታል።

ተመልከቱ ባለጸጋው አንጢላርዮስ ምጽዋቱን ወዶ ፈቅዱ በደስታ ሆኖ አልሰጠም ለተራበው ነዳይ በበጉ አንደበት አለመጸወተውም ነገር ግን ነዳዩ ከተጉዳው ይልቅ ያስታገሰለትን ረሐብ አስቦ በጉውን ነገር መሠከረለት። ስለዚህ ካለመስጠት መስጠት እንደሚሻል ተማርን።  ምጽዋት በንጽሕና እንዲሁም በመልካም ሥነ ምግባር በደስታና በፍቅር የሚደረግ ቢሆንም ቅሉ ላላወቀበት አእምሮ መንፈሳዊ እስኪሳልበት ድረስ ይቆይ አትመጽውት ተብሎ አይመከረም። እንደ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ የእሸት ያህል ዋጋ አታጣበትምና ዝም ብለህ ስጥ ተብሎ ይመከራል እንጂ። ብጹዕ ማር ይስሐቅ ሳትለያይ መጽውት ይህ አረማዊ ነው ይህ አህዛብ ነው አትበል እንዳለው ባለመሰጠት ከምንኖረው ሕይወት ይልቅ በመስጠት የምናገኝው በረከት የሚልቅ መሆኑን ማሰብ እጅግ ማትረፍያ ነው። ምጽዋትን ከነሙሉ ጉድለታችን እናድርግ ስንል በእኛ ምጽዋት እግዚአብሔርን የሚያመሰግኑ ብዙ ሰዎች ስላሉ ነው የኛ መስጠት በተስፋ እንዲያድሩ የሚያደርጋቸው ብዙዎች አሉ። 

ጌታችን ቀኝህ የምትሠራውን ግራህ አትወቅ፤ብሎ የተናገረውን ቃል አባቶች  ግራ የተባለችው ሚስት ናት ብለው ትንታኔ በሚሰጡበት አንቀጽ ላይ

“…..ቅንነቱማ ካለ ሁሉ ያለ በእጁ አይደለምን ከዚያው አውጥቶ ይስጥ ይህም ስርቆት አይሆንበት ቢሉ  ይንገራት አይሆንም ብትለው ግን ይለያዩ ጥንቱን መጋባታቸው ሰጥተው መጽውተው ሊጸድቁ ነውና……” በማለት የትዳር ምሰሶ መካከል አንዱ መመጽወት መሆኑን አስረድተዋል። 

እንዲህ እያልን የምጽዋትን ጉልበትና ኃይል አብዝተን መግለጽ ይቻለናል። ይህን የትሩፋት ሥራ በብዙ ደካማ ጠባዮቻችን ምክንያት ከማቆም በመሥጠት ጥቂትም ቢሆን ዋጋ ማግኝት የተሻለ ምርጫ ነው።

ወዳጄ የመጸወትካቸው ሰዎች ከሚመርቁህ ምርቃት በላይ ምን ዓይነት ምስጋና ትሻለህ። በመስጠትህ በአደባባይ እና በሰገነት ላይ ከምትመሰገነው ምስጋና ይልቅ ርኃቡን ያስታገስክለት ሰው ብቻውን ሆኖ የሚመርቅህ ምርቃት እልፍ በረከት ነው። ብዙዎች ከሚመሰክሩልህ ይልቅ አንጢላርዮስን የቀየረው የነዳዮ ምሥክርነት ነፍስህን ይታደጋታል የነዳዩን ምርቃት ሻት። ይህ ባይሆንልህ ግን ሰው ዘር ይዘራል ባይጠብቀው ለእሸት ያህል አያጣለትም አንተም ያዚያን ያህል ዋጋ አታጣምና ስጥ ። 

👉ማጠቃለይ

አስቀድመን እንደገለጥነው በመጻሕፍት ስለ ምጽዋት ብዙ ተብሏል ለጽሑፋችን መቋጫ እንዲሆነን ግን ከመጸሐፍ ሲራክ አንድምታ ያሰናኘውትን የምጽዋት ድንቅ ምክር ላስፍር።

# ልጄ ሆይ ደሀውን ኑሮውን አትከልክለው የሚኖርበትን ልመናውን አትከልክለው። ዓይኖችህንም ከሚለምንህ አትመልስ ትክ ብለህ እየው። ያዘነች ሰውነትን አታሳዝን ቀድሞ በማጣቱ አዝኗል የለም ያልከው እንደሆነ ጨርሶ ያዝናልና ያዘነንም ሰው በመንሳት አታበሳጭ። የተከዘውንም ልቡና አታስደንግጥ ይሰጠኛል ብሎ ሲለምን የለም ወግድ ከደጄ ያልከው እንደሆነ ይደነግጣልና። 

# የሚለምንህንም አትለፈው  ከደሃውም ፊትህን አትመልስ።ዓይንህንም ከሚለምንህ እንዳላየ አይተህ አትመልስ።  ለሚረግምህም ለደሃው ነገ ተመለስ ብለህ  ምክንያት አትስጠው ረኀብ ቀን አይሰጥምና።

# ልቡናውን አሳዝነህ ገንዘብህን ለወራሻ ቤትህን ለተኳሽ ያድርገው ብሎ ቢረግምህ ፈጣሪው ጸሎቱን ፈጥኖ ይሰማዋልና በብዙ ሰዎች ዘንድ የተወደድክ  ሁን።

# ለደሀውም  ልመናውን በጆሮህ ሰምተህ ቢኖርህ ስጠው ባይኖርህም ወንድሜ ቀን ይመልስህ ብለህ በገርነት በጎ ቃል መልስለትደ  ገንዘብህን ሰጥተህ ከረኀብ አድነው ለሱ መፍረድንም ቸል አትበል።

# አባት ለሌለው ልጅ አባቱ ተንከባክቦ እንዲያሳድገው ተከባከበው። ለእናቱም ባሏ ጠበቃ  እንዲቆምላት ዋስም ጠበቃም ሁናት። እንዲህ ያደረግህ እንደሆነ እንደ እግዚአብሔር ልጆች እንደ ነቢያትና እንደ ሐዋርያት እንደ ጻድቃንም ትሆናለህ እናትህ አንተን ከምትወድህ  አንተም እናትህን ከምትወዳት ይልቅ ይወደሀል ።

Share your love

4 አስተያየቶች

  1. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን! የምጽዋትን ዋጋ ተረድተን በልግስና እንሰጥ ዘንድ እግዚአብሔር ይርዳን!

    ጃንደረባው ሚድያ ስለ ሰፊ አገልግሎታችሁ እግዚአብሔር ይስጥልን:: በቻልኩት መጠን እንደዚህ አይነት ጽሁፎችን ስታወጡ ለማንበብ ሞክራለሁ:: ከይዘቱ እና አስተማሪነቱ በተጨማሪ አቀራረቡ ያስደንቀኛል:: እዚ ላይ ብቻ ግንጥቂት የቃላት ግድፈትን አስተውያለሁ:: ዋናው ጉዳይ ባይሆንም አስተያየት መስጠቱ ገንቢ ይሆናል ብዬ ነው:: እግዚአብሔር ይስጥልኝ!

  2. አሜን እግዚአብሔር ይምስገን ቃለህይወትን ያሰማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *