በክርስትናው ዓለም ትምህርት ውስጥ አንድ ወጥ የሆነ ትርጉም ለመስጠት ከሚያስቸግሩ ቃላት መካከል አንዱ መንፈሳዊነት የሚለው ቃል ነው። ይኽም ሊሆን የቻለው እያንዳንዱ የእምነት ድርጅት ቃሉን የሚረዳበትና የሚተረጉምበት መንገድ ድርጅቱ ስለ እግዚአብሔር፣ እርሱንም ስለ ማምለክና ከእርሱ ጋር ስለ መኖር ባለው መረዳትና አስተምህሮት ላይ የተመሠረተ በመሆኑ ነው።
ለአንዳንዱ መንፈሳዊነት የእግዚአብሔርን ሕልውና ማመን ብቻ ይመስለዋል።ለሌላው ደግሞ መንፈሳዊነት “ኢየሱስን የግል አዳኝ አድርጎ መቀበል” ነው። ለተቀረውም መንፈሳዊነት በጎ ሥራ ለሌላው መሥራት ነው። ለእነዚህ ሁሉ አካላት መንፈሳዊነት ወይ አንድ ግለሰብ ከእግዚአብሔር ጋር ያለው ግንኙነት ነው፤ አለያም ከሌሎች ሰዎች ጋር በሚኖረው ትስስር ላይ የተመሠረተ ነው።
የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ስለ መንፈሳዊነት ያለቸውን መረዳት ስናጤንም እንዲሁ የተለያየ ሆኖ እናገኘዋለን። መንፈሳዊነት ዘወትር ቅዳሴ ማስቀደስ ብቻ፣ የተለያዩ ገዳማትን መሳለም ብቻ፣ የተቸገረን መርዳት ብቻ፣ ቃለ እግዚአብሔርን ማወቅ ብቻ፣ አብያተ ክርስቲያናትን ማሳነፅ ብቻ፣ በተለያዩ ዘዴዎች ሌሎችን ወደ ቤተ ከርስቲያን ማምጣት ብቻ፣ የሰበካ ጉባኤ፣ የሰንበት ትምህርት ቤት፣ የሰንበቴ ወይም የአንድ መንፈሳዊ ማኅበር አባል መሆን ብቻ፣ መመንኮስ ወይም በሥርዓተ ጋብቻ በቅዱስ ቁርባን ማግባት ብቻ፣ በተለያዩ የመገናኛ ብዙኃን ላይ ስለ ቤተ ክርስቲያን፣ ስለ አባቶች ካህናት ድካምና ጥንካሬ መጻፍና ማንበብ ብቻ፣ ከጥሩ “መንፈሳውያን” ቤተሰብ መገኘት ብቻ ወይም ስመ ጥር ከሆነ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ከብፁዓን አባቶች፣ ከቀሳውስት፣ ከመነኰሳት፣ ከዲያቆናት፣ ከመዘምራን ጋር ጥሩ ወዳጅ መሆን ብቻ…. የሚመስላቸው ወገኖች አሉ።
በመሠረቱ መንፈሳዊነት አንድ ዘለላ ቃል ሆኖ ሳለ ፈርጀ ብዙ የሆነ ትርጉምና መሠረት ያለው ቃል ነው። መንፈሳዊነትን ለመተርጎመም ሆነ መንፈሳዊ ለመሆን ሁለት መሠረት ነጥቦችን ትኩረት ሰጥቶ ማየት ያስፈልጋል። እነዚህም የሰው አፈጣጠርና የሰው የድኅነት መንገድ ናቸው።
1. የሰው አፈጣጠር
ነቢዩ ቅዱስ ዳዊት “ግሩምና ድንቅ ሆኜ ተፈጥሬአለሁና አመሰግንሃለሁ” በማለት የሰው ተፈጥሮው “ግሩምና ድንቅ” መሆኑን መስክሯል። መዝ. 138፡14። ይኽ “ ግሩምና ድንቅ” የተባለው የሰው አፈጣጠርም በሊቀ ነቢያት በሙሴ አንደበት “እግዚአብሔርም አለ፦ ሰውን በመልካችን እንደ ምሳሌያችን እንፍጠር” ተብሎ የተገለጠው ነው። ዘፍ. 1፣26። ከዚህ ዐረፍተ ነገር ሰው ከሌሎቹ ፍጡራን ሁሉ ተለይቶ ከፍ ባለ ክብርና ቅድስና በእግዚአብሔር “መልክና ምሳሌ” መፈጠሩን እንረዳለን። በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ በመፈጠሩም እግዚአብሔር በባሕርይው አምላክ፣ ቅዱስ፣ ሁሉን አዋቂ፣ ብርሃን፣ ጻድቅ፣ ፈራጅ እንደ መሆኑ ሰዎችም ከጸጋ እግዚአብሔር የተነሣ አማልክት ዘበጸጋ፣ቅዱሳን፣ አዋቂዎች፣ ብርሃን፣ ጻድቃን፣ ፈራጅ.. ይሆኑ ዘንድ ተሰጥቷቸዋል። ሰዎች የተፈጠሩበትን መልክና ምሳሌ ይዘው ሲገኙም መንፈሳውያን ይባላሉ።
በእግዚአብሔር መልክና ምሳሌ የተፈጠረው ሰው የተሰጠውን ትእዛዝ ተላልፎ ከዕፀ በለስ በበላበት ወቅት “የሁለቱም ዓይኖች ተከፈቱ፤ እነርሱም እራቁታቸውን እንደ ሆኑ አወቁ” ተብሎ እንደ ተነገረው ከጸጋ እግዚአብሔር ተለዩ። ዘፍ.3፣7። ይኽም መንፈሳዊነታቸውን አጡ ማለት ነው። መንፈሳዊነታቸውን ማለት የተፈጠሩበትን መልክና ምሳሌ ሰላጡም “ሰው ግን ክቡር ሆኖ ሳለ አያውቅም፤ እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ”ተብሎ ተነገረባቸው። መዝ.48፣12።
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ ጢሞቴዎስን “…እግዚአብሔርን ለመምሰል ግን ራስህን አስለምድ፤ ሰውነትን ለሥጋዊ ነገር ማስለመድ ለጥቂት ይጠቅማልና፤ እግዚአብሔርን መምሰል ግን የአሁንና የሚመጣው ሕይወት ተስፋ ስላለው ለነገር ሁሉ ይጠቅማል። ይኽ ቃል የታመነ ሁሉም እንዲቀበሉት የተገባ ነው። ይኽን ለማግኘት እንደክማለንና፤ ስለዚህም እንሰደባለንና” በማለት መክሯል። 1ጢሞ. 4፣7-10። ሐዋርያው “እግዚአብሔርን ለመምሰል” በማለት የገለጠው ሰው የተፈጠረበትን “መልክና ምሳሌ” ለማግኘት መሆኑን አስተውሉ። ይኽ ደግሞ የእግዚአብሔር አምላካዊና ዘላለማዊ ዓላማ ነው። በሊቀ ነቢያት በሙሴ “ለእስራኤል ለጆች ማኅበር ሁሉ እንዲህ በላቸው፦ እኔ እግዚአብሔር አምላካችሁ ቅዱስ ነኝና እናንተ ቅዱሳን ሁኑ” በማለት የተነገረው ቃል ሰው የተፈጠረበትን ቅዱሱን “መልክና ምሳሌ” ይዞ መገኘት እግዚአብሔር ከሰው የሚፈልገው ነገር መሆኑን ያስረዳናል። ዘሌዋ. 19፣2።
ከላይ ከቀረቡት አስረጂዎች በመነሣት መንፈሳዊነት የተፈጠሩበትን “መልክና ምሳሌ” መያዝ ወይም “እግዚአብሔርን መምሰል” መሆኑን እንረዳለን።
2. ነገረ ድኅነት
መንፈሳዊ፣ መንፈሳዊነት የሚሉ ቃላትን ለመረዳትና ከዚያም በላይ ደግሞ “መንፈሳዊ” ለመሆን የሰው ልጅ ከዘላለም ሞት የዳነበትን ወይም አጥቶት የነበረውን የእግዚአብሔርን መልክና ምሳሌ ያገኘበትን ሁኔታ በጥልቅ መረዳት ይገባል።
ድኅነታችን የተፈጸመው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ እርሱም ድኅነታችንን የፈጸመው ከልዕልና ከክብር ከመውረድ ጀምሮ እስከ መስቀል ላይ ሞቱና እስከ ትንሣኤ ድረስ በደረገው የማዳን ጉዞው ነው። በዚህ ጉዞው ውስጥ ጌታችንና በመድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሁለት ታላላቅ ሥራዎችን ያከናውን ነበር። እነርሱም የቤዛነትና የአርአያነት ሥራዎች ናቸው። ጌታችን ወደዚህ ምድር በሥጋ ከመጣበት ጊዜ ጀምሮ በክብር እስካረገበት ድረስ በፅንሰቱ፣ በስደቱ፣ በዕድገቱ፣ በጥምቀቱ፣ በጾሙ፣ በጸሎቱ፣ በማኅበራዊ ተሳትፎው፣ በትምህርቱ፣ በተአምራቱ፣ በፈተናዎቹ፣ በሕማማቱ፣ በሞቱ….ካሳ ይክስልን ወይም ቤዛ ይሆነንና አርአያነቱን ይሰጠን ነበር።
ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ በመልእክቱ “የተጠራችሁለት ለዚህ ነውና ክርስቶስ ደግሞ ፍለጋውን እንድትከተሉ ምሳሌ ትቶላችሁ ስለ እናንተ መከራን ተቀብሎአልና” በማለት ጌታችን በዚህ ዓለም ባደረገው የመዳን ጉዞ ውስጥ ታላቅ ምሳሌነትን ለሚያምኑበት ሁሉ እንደ ሰጠ አስረድቷል። 1ጴጥ. 2፣21።
ያም በክርስቶስ የተሰጠን ምሳሌነት መንፈሳውያን የምንሆንበትና መንፈሳዊነትን ገንዘብ የምናደርግበት መንገድ ነው። ጌታችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በፈጸመልን ነገረ ድኅነት ውስጥ መንፈሳዊነትን የሚያጎናጽፉን ሁለት ነገሮችን እናገኛለን። ከእነዚህም የመጀመርያው ድኅነታችንን በፈጸመልን በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመን ነው። የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት አስተካክሎ ማመንም ብፅዕናን ያስገኛል።
ቅዱስ ጴጥሮስ በዘመኑ የነበሩ ሰዎች ስለ ክርስቶስ ካላቸው የተሳሳተ አመለካከት ተጠብቆ በአጭር ቁመት በጠባብ ደረት ተወስኖ የተወለደውን ጌታ አካል ከባሕርይ፣ ባሕርይ ከአካል ሳይለይ ሳይቀላቅል ያለመለወጥ በተዋሕዶ አንድ አድርጎ “አንተ ክርስቶስ የሕያው እግዚአብሔር ልጅ ነህ” ብሎ መሰከረ። ይኽ ሐዋርያ ይኽን መሰል እውነተኛ ምስክርነት በመስጠቱ በጌታችን አምላካዊ አንደበት “የዮና ልጅ ስምዖን ሆይ በሰማያት ያለው አባቴ እንጂ ሥጋና ደም ይኽን አልገለጠልህምና ብፁዕ ነህ” በማለት ለመመስገን በቃ። ማቴ.16፣15-20። ቅዱስ ጴጥሮስን በጌታችን አንደበት “ብፁዕ ነህ” ለመባል ያበቃው ስለ ክርስቶስ ማንነት በትክክል መረዳት መቻሉ ነው። ይኽም መንፈሳዊ ከሚያሰኙ ነገሮች መካከል ተቀዳሚውና ዋናው ነገር ነው።
ሁለተኛውና በጌታችን የማዳን ጉዞ ውስጥ ያገኘነውና መንፈሳውያን እንድንሆን በእጅጉ የሚያስፈልገን ነገር ጌታችን የተወልን ምሳሌ ነው። እንደ መጻሕፍት ቃል የጌታችንና የመድኃኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስን የባሕርይ አምላክነት አምኖ የተቀበለ ሰው መንፈሳዊ ለመሆን በኑሮው መድኃኔዓለምን መምሰል አለበት። በእርሱ ለሚያምኑ ሁሉ ማመናቸው መንፈሳዊነትን እንዲያጎናጽፋቸው ቅዱስ ዮሐንስ “በእርሱ እንዳለን በዚህ እናውቃለን፤ በእርሱ እኖራለሁ የሚል እርሱ እንደ ተመላለሰ ራሱ ደግሞ ሊመላለስ ይገባዋል” ብሏል። 1ዮሐ. 2፣5-6። ይኽም በቅዱስ ጳውሎስ ቃል “የልጁን መልክ እንዲመስሉ አስቀድሞ ደግሞ ወስኖአል” ያለውን ቃል የመሰለ እውነታ ነው። ሮሜ 8፣29።
ሕገ እግዘአብሔርን ተላልፎ ከጸጋው ተራቁቶ “እንደሚጠፉ እንስሶች መሰለ” የተባለው ሰው የተፈጠረበትን “መልክና ምሳሌ” እንዲያገኝ እግዚአብሔር ልጁን በሥጋ ላከ። ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ “ሰዎች የእግዚአብሔር ልጆች ይሆኑ ዘንድ የእግዚአብሔር ልጅ የሰው ልጅ ሆነ” እንዳለው በባሕርይ አምላክነቱ አምነንበት በሥጋው ወራት በተመላለሰበት ምሳሌ ማለት እንደ ሰውነቱ በኖረበት የኑሮ ሥርዓት ተመላልሰን “የልጁን መልክ እንድንመስል” እግዚአብሔር ወደደ። ሐዋርያው ይኽን የእግዚአብሔርን ፈቃድ ፈጽሞ እንዲህ አለን፦”እኔ ክርስቶስን እንደምመስል እኔን ምሰሉ”። 1ቆሮ.11፣1። ሐዋርያው በጌታችንንና በመድኃኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አምላክነት አምኖ በኑሮው ሁሉ ጌታን መሰለ። አርሱ እንደ መሰለውም እንድንመስለው መከረን።
እንግዲህ ከላይ ለመግለጥ እንደ ተሞከረው ጌታችን እኛን ለማዳን ባደረገልን የማዳን ጉዞ ውስጥ መንፈሳዊነት ማለት በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት አምኖ ጌታችን በዚህ ዓለም በሥጋ እንደ ተመላለሰው መመላለስ መቻል ነው። በእርግጥ ይኽ ከመ ቅጽበት የሚደረስበት ሳይሆን በሂደት የሚደረስበት እውነታ ነው። ስለሚቻልም ነው ቅዱስ ጳውሎስ “እኔ ክርስቶስን እንደምመሰል እኔን ምሰሉ” ያለው። ይኸው ሐዋርያ በሌላ መልእክቱም “ፊተኛው ኑሮአችሁን እያሰባችሁ እንደሚያታልል ምኞት የሚጠፋውን አሮጌውን ሰው አስወግዱ። በአእምሮአችሁም መንፈሰ ታደሱ፤ ለእውነትም በሚሆኑ ጽድቅና ቅድስና እንደ እግዚአብሔር ምሳሌ የተፈጠረውን አዲሱን ሰው ልበሱ” ብሏል። ኤፌ. 4፣22-24።
ከእነዚህ ሁሉ አስረጂዎች ተነሥተን መንፈሳዊነት በቅዱሳት መጻሕፍት አስተምህሮ መሠረት በቅድስት ሥላሴ እንድነትና ሦስትነት ፣ በኢየሱስ ክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት፣ ጽድቅና ኵነኔ መኖሩን አምኖ ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እየተካፈሉ ጌታችን እንድንመላለስበት በሰጠን ምሳሌነት እየተመላለሱ የተፈጠሩበትን መልክና ምሳሌ አጽንቶ መያዝ ማለት መሆኑን እንረዳለን።
አስቀድመን አንዳንድ የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን ስለ መንፈሳዊነት ያላቸውን ግንዛቤ በጠቀስንበት ውስጥ የዘረዘርናቸው ነጥቦች የአንድ ሰው መንፈሳዊነት እንዲጠነክር እንዲያብብ የሚረዱ ናቸው። የሚረዱትም በተሟላና በተስተካከለ ሁኔታ ተሟልተው ሲገኙለት ነው። በቅድስት ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ መሠረት አንድ ሰው መንፈሳዊነቱን ማለት እግዚአብሔርን መምሰሉን፣ በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በክርስቶስ የባሕርይ አምላክነት ማመኑን፣ የቤተ ክርስቲያን ምሥጢራት ተካፋይ በመሆን ጌታችን በሥጋው ወራት በዚህ ዓለም እንደ ኖረው እንዳይኖር ዘወትር የሚፈታተኑትን ድል ለመንሣት የሚከተሉትን ነጥቦች አጥብቆ ትኩረት በመስጠት ሊፈጽማቸው ይገባዋል”።
1. ጸሎት
ወደ ፈተና እንዳትገቡ ትጉና ጸልዩ በተባለው መሠረት ዘወትር ጧት፣ ማታ፣ ቀን፣ በነገሮች ውስጥ ሁሉና ለነገሮች ሁሉ መጸለይ አለበት።
2. ቅዳሴ ማስቀደስ
በዕለተ ሰንበተ ክርስቲያን በቤተ ክርስቲያን በሚፈጸመው የኅብረት ጸሎት ማለት በቅዳሴ ላይ መሳተፍ ይገባዋል።
3. ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን መሳተፍ
ንስሐ መግባት፣ ቅዱስ ቁርባን መቀበል በድንግልና ተጠብቆ ለዐቅመ አዳም ወሔዋን ሲደርሱ በሥርዓተ ቤተ ክርስቲያን በትዳር መወሰን ወይም በድንግልና ጸንቶ መኖር
4. በጾም መበርታት
በቤተ ክርስቲያን ሥርዓት መሠረት የሚፈጸሙትን ሰባቱን አጽዋማት ልቡናን ከቂም አንደበትን ከሐሜት ሕዋሳትን ከኀጢአት አርቆ መጾም
5. አስራትና ምጽዋት ማውጣት
አስራት ማውጣት የክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ግዴታ ነው። ይኽም እግዚአብሔር ምእመናን ከሚያገኙት ከማንኛውም ዓይነት ገቢ ላይ ከአስር አንድ ለቤተ ክርስቲያን እንዲሰጡ ባዘዘው መሠረት የሚፈጸም ነው። ምጽዋትም ባልጀራችንን እንደ ራሳችን ከመውደዳችን የተነሣ ብቻ ሊፈጸም ይገባዋል። በቅዱሳን ስም መጽውቼ በረከት አገኛለሁ በማለት ብቻ የሚፈጸመው ምጽዋት ለበረከት ያለንን ፍላጎት የሚያስረዳ ሲሆን ለነዳያን የምንመጸውተው ምጽዋት ግን ወገኖቼ ናቸው ረሃባቸው ጥማቸው መራቆታቸው ይሰማኛል በማለት ሊሆን ይገባል።
6. ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ
መጽሐፍ ቅዱስን፣ ገድለ ቅዱሳንን፣ ድርሣናትን የቤተ ክርስቲያን ታሪኮችንና የአበውን አባባል ማንበብ ለመንፈሳዊነታችን ጉልህ አስተዋፅዖ አለው።
7. ትምህርት
የመጽሐፍ ቅዱስ ጥናት፣ መሠረታዊ የቤተ ክርስቲያን ትምህርቶችን፣ ስብከቶችን መማር በጉባኤ ተገኝቶ፣ ከምናውቃቸው መምህራነ ቤተ ክርስቲያን ወይም ከተለያዩ የቤተ ክርስቲያኒቱ የትምህርት ተቋማት ገብቶ መማር ያስፈልጋል።
8. ተልእኰ
የቤተ ክርስቲያንን ተልእኰ በዕውቀት፣ በጉልበትና በገንዘብ መርዳት ይገባል። ይኽም እኛ ያገኘነውን ሕይወት ሌሎች እንዲያገኙ ላቅ ያለ አስተዋፅዖ ከማበርከቱም በላይ ቤተ ክርስቲያን ተልእኰዋን እንድትወጣ ያስችላታል።
9. በሁሉ ለሁሉ አርአያ መሆን
በአንደበታችን፣ በሥራችን፣ በውሎአችን፣ በትዳራችን በእያንዳንዱ እንቅስቃሴያችን ለሚያምኑትም ሆኑ ለማያምኑት ምሳሌ መሆን ያስፈልጋል።
እነዚህ ከ1-9 የተጠቀሱት ነጥቦች ልንደርስበት ልንሆነውና ልንኖረው የምንናፍቀውን መንፈሳዊነት እንድንደርስበት እንድንሆን እንድንኖር የሚያግዙን ናቸው። እነዚህ ነጥቦች የመንፈሳዊነታችን ምዕራፍ ወይም ግብ ሳይሆኑ ወደ ምዕራፋችን እንድንደርስ የሚያግዙን ናቸው። ከእነዚህ መካከል የተወሰኑትን ወይም ሁሉንም ፈጸምን ማለት መንፈሳዊነታችን ፍጹም ሆነ ማለት አይደለም። መንፈሳዊነታችን ፍጹም የሚሆነው በሥላሴ አንድነትና ሦስትነት፣ በምሥጢረ ሥጋዌ አምነን ከምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን እየተሳተፍን ጌታችን እንደ ተመላለሰው ተመላልሰን ከእግዚአብሔር በጸጋ የተሰጠንን “መልክና ምሳሌ” ከ1-9 በተዘረዘሩት ነጥቦች አጥርነት ጠብቀን በክብር ሩጫችንን ስንጨርስ ነው። ስለሆነም ነው ቅዱስ ጳውሎስ ምንም እንኳን አሥራ አራት መልእክታትን የጻፈ፣ ሕዝብና አሕዛብን አንድ አድርጎ ያስተማረ፣ እስከ ሦስተኛው ሰማይ ድረስ ያረገ፣ ሰማያዊውን ምሥጢር ለማየት የታደለ ምርጥ ዕቃ የተባለ ቢሆንም በመልእክቱ “አሁን እንዳገኘሁ ወይም አሁን ፍጹም እንደ ሆንሁ አይደለም…. ወንድሞች ሆይ እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ። በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ” ያለው። ፊል.3፣12-14።
መንፈሳዊነት እንደ ምድራዊ ሩጫ ለተወሰኑ ሰዓታት ተሩጦ የሚፈጸም አይደለም። መንፈሳዊነት በመስቀል የተሰቀልንን ጌታ በፍቅር እያሰቡ እንደ ሐዋርያው ቃል “ሸክምን ሁሉ ቶሎም የሚከበንን ኀጢአት አስወግደን የእምነታችንንም ራስና ፈጻሚውን ኢየሱስን ተመልክተን በፊታችን ያለውን ሩጫ በትዕግስት መሮጥ” ነው። ዕብ. 12፣2።
ነገራችንን ከማጠቃለላችን በፊት ለእርስዎ ለውድ አንባቢ አንድ ጥያቄ እናቅርብ። እስቲ ከላይ ስለ መንፈሳዊነት በተጠቀሱት ነጥቦች መሠረት የእርስዎን መንፈሳዊነት ይመርምሩት። በእርግጥ እርስዎ መንፈሳዊ ኖት? ሕይወትዎ መንፈሳዊነትን መሠረት ያደረገ ነው? በእርግጥ እርስዎ የእግዚአብሔርን መልክና ምሳሌ እንደያዙ ነው ያሉት? ያንን በጥምቀት ዳግም ሲወለዱ ያገኙትን እግዚአብሔርን መምሰልና የእግዚአብሔርን ልጅነት ይዘዋል? በእርግጥ በኑሮዎ ሁሉ አስተሳሰብዎት፣ አሠራርዎትና አኗኗርዎት ጌታ እንደ ተመላለሰው ነው? እንዲህ ከሆኑ በእርግጥ እርስዎ መንፈሳዊ ኖት።
ካልሆኑ ግን ላለፈው ንስሐ ገብተው ከላይ የጠቀስናቸው ነጥቦችን በሕይወትዎ በመያዝ መንፈሳዊ ለመሆን ይጋደሉ። የእግዚአብሔር መንግሥት ሰማያዊትና መንፈሳዊት ናት። የሚወርሷትም መንፈሳውያን የሆኑት ብቻ ናቸው። ምክንያቱም በሥጋ ያሉት እግዚአብሔርን ደስ ሊያሰኙት አይችሉም። ሮሜ 8፣8። መንፈሳዊነት ደግሞ እግዚአብሔርን ደስ የምናሰኝበት መንገድ ነው። ስለዚህ መንፈሳዊ ከሚመስሉ ነገር ግን እጅጉን ከተሳሳቱ አካሄዶች ተጠብቀን መንፈሳውያን ሆነን እንድንገኝ የእግዚአብሔር ቸርነት የእመቤታችን የቅድስት ድንግል ማርያም አማላጅነት አይለየን። አሜን።
አንድ ጥያቄ አለኝ ከላይ የተጻፈው መንፈሳዊ ጽሁፍ ግሩም ነው ያንጻል ወደ ቤተክርስቲያንም አዘውትሬ እሄድ ነበር አሁን አሁን ግን ቀንሻለሁ በአውደምህረት የሚሰጠው ትምህርት/ስብከት ዝማሬ እንደበፊቱ በደንብ አይሰማኝም በተለይ ዝማሬው በሞንታርቦና በዝማሬ መሣሪያ ታጅቦ ከቃሉ ከዝማሬው ግጥም ወይም መልእክት ይልቅ የሞንትርቦው ጩኸት የመዝሙር መሣሪያው ጩኸት ያደነቁራል ስለዚህ እንዴት እንደማመጥ ምን ትሉኛላችሁ
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መንፈሳዊነት ልክ እዚህ ላይ እንደተጻፈው በእኛ ምዕመናን ላይ ቢታይ ጥሩ ነበር።ግን ይሄ መልእክት እየደረሳቸው ያለው ጥቂት ምዕመናን ናቸዉ።ይህ ሀሳብ የኔም ሀሳብ ስለነበረ እንዴት በሰፊው ሁሉም ምዕመናን ላይ እንዲዳረስ እና የቀን በቀን ስራ ማድረግ ይቻላል….ከስብከት ውጪ?
…….. ”መንፈሳዊነት የተፈጠሩበትን “መልክና ምሳሌ” መያዝ ወይም “እግዚአብሔርን መምሰል” መሆኑን እንረዳለን።”…….
ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን🙏 ያነበብነውን ለመኖር ያትጋን
…….. ”መንፈሳዊነት የተፈጠሩበትን “መልክና ምሳሌ” መያዝ ወይም “እግዚአብሔርን መምሰል” መሆኑን እንረዳለን።”…….
ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን ያነበብነውን ለመኖር ያትጋን 🙏