መምህር ቀሲስ ግርማ ባቱ የቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርስቲ መምህር ፣ ደራሲ ፣ ጸሐፊና ተመራማሪ ናቸው:: በዚህ ሰንበት በጃንደረባው ሠረገላ ላይ ይህንን ዘለግ ያለ ቆይታ አድርገዋል::
ጃንደረባው :- ከአስተዳደግዎና ከልጅነትዎ ብንጀምርስ? የመምህር ግርማ ትውልድና አስተዳደግ ምን ይመስላል?
መምህር ግርማ ባቱ:- ሕልም የሚመስል እጅግ የሚናፈቅ አስተዳደግ! ያኔ የአካባቢው ሰው ሁሉ እንደ ወላጅህ ቤተ ሰብና ዘመድህ ሆኖ በምትኖርበት ዘመን፣ ሰውን በሰውነቱ ተቀብሎ በሚገርም አብሮነት በሚኖርበት አካባቢ ዋ! ሆለታ ገነት ልዩ ነበረች፡፡
ተወልጄ ያደግሁት ከአዲስ አበባ በ35 ኪ.ሜ. ርቀት ላይ በምትገኘው በሆለታ ገነት ነው፡፡ ቅድም በትምህርት ቤቴ ጉዳይ አካባቢውን በመጠኑ ለመጠቆም ሞክሬያለሁ፡፡ እናም በሆለታ ገነት በሚገኘው የጦር ካምፕ ምክንያት እንዲሁም ለዋና ከተማዋ (አዲስ አበባ) ካለው ቅርበት የተነሣ ከመላው ኢትዮጵያ የተሰባሰበ ማኅበረሰብ ይኖርባት ነበር፡፡ ነጠላ ማንነት በፍጹም የማይታሰብበት ኢትዮጵያዊነት ሥር የሰደደበት አካባቢ ነበር፡፡ ከአካባቢውም በላይ፣ ከዘጠኝ ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት ስለገባሁ እድገቴን በይበልጥ የማስታውሰው በቤተ ክርስቲያን ከነበረኝ ሕይወት ጋር ነው፡፡
ጃንደረባው :- ወደ መንፈሳዊ አገልግሎትስ እንዴት ሊገቡ ቻሉ?
መምህር ግርማ ባቱ:- በትውልድ አካባቢዬ የቤተሰቤን ከብቶች በምጠብቅበት ጊዜ አንድ ቀን ከጎጃም የመጣ አንድ ልጅ የሌላ ቤተሰብ ከብቶችን ሲጠብቅ ተገናኘን፡፡ ለአካባቢው አዲስ ነው፣ ነገር ግን፤ ያው ልጅነትም ስላለ በቶሎ ተግባባን፡፡ ከዚያም በጊዜው የማላውቀውን ኋላ ተምሬ ስደርስበት የተረዳሁትን እጅግ የሚስብ ዜማ ማዜም ጀመረ፡፡ ምንድን ነው የምትለው ብዬ ጠየኩት፣ አስረዳኝ፡፡ መማር እንደምፈልግ ስነግረው ተቀጣጠርንና በቀጥታ ወደ መምህር ወሰደኝ፡፡ ከዚህ በፊት ፊደል እስከ መዝሙረ ዳዊት የሚያስተምሩ በአካባቢው የታወቁ ሌላ መምህር ነበሩ፡፡ እኚህ ግን መሪጌታ (አለቃ) ተክለብርሃን በጅተሃል ይባላሉ፡፡
በመጀመሪያ ግንኙነት ብቻ ልዩ ነገር ያሳድራሉ፡ እንደልጅ ተቀብለው መንፈሳዊ አባት መሆን የሚችሉ ድንቅ መምህር ናቸው፡፡ ያቺ እርሳቸውን ያገኘሁባት ዕለት በሕይወቴ የማልረሳት ልዩ አጋጣሚ ናት፡፡ የቃል ትምህርት፣ የዜማ ትምህርት፣ አጠቃላይ የሰሞነኛ ጓዝ፣ ምዕራፍ፣ ጾመ ድጓ ያስተማሩኝ እሳቸው ናቸው፡፡
በዚህ መልኩ የሆለታ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን በእናትነት ተቀብላ የአብነቱንም የአስኳላውንም ትምህርት በልዩ ድጋፍ አስተምራኛለች፡፡ እንደተናገርኩት ከ11 ዓመት ዕድሜዬ ጀምሮ በዲቁና ሳገለግል ነበር፡፡ የዚያን ጊዜው የደብሯ አገልግሎት፣ የአካባቢውም ማለት ይቻላል፣ የሥራ ዘርፍ ተመርጦ አይሰጥህም፡፡ ማለትም፡ ሰሞነኛ ቀዳሽ፣ ሰዓታት ቋሚ፣ ወዘተ. የሚል አልነበረም፡፡ ዲያቆናት ከካህናት ጋር ሰዓታት፣ ማኅሌት፣ ስብሐተ ነግህ ይቆማሉ፣ በሰንበት መዝሙር አጥንተው ዕኩል ይሰለፋሉ፣ መዋሥዕቱን አጥንተው ወይም በድምጫ በደንብ አዋሕደው ፍትሐት ይፈታሉ … በቃ ከአገልግሎት በምንም ምክንያት መራቅ የለም፡፡ እኔም በዚህ ውስጥ ነው ያደግሁት፡፡
በዚህ መካከል ደግሞ የዘመናዊው ትምህርት መርሐ ግብር ከተጋጨ ዛሬ ጭምር በጣም የምገረምባቸው አባቶች እኔ ሸፍናለሁ ሂድ ተማር ይሉን ነበር፡፡
የዲቁናን ግብር ተክተው ያሳደጉንን አባቶች እንዴት ልርሳ! በቅርቡ በሕይወት ያሉትን እጅግ አመስግነን፣ ልዩ ካባ በመሸለም አክብረናቸዋል፡፡ በአገልግሎት አብረን ያደግን የዚያን ጊዜ ዲያቆናትም በየወሩ በእናታችን ኪዳነ ምሕረት ስም እየተገናኘን ያንን ደግ ዘመን እንዘክረዋለን፡፡ በሁላችንም ሕይወት ውስጥ ልዩ ፍሬ ያፈራ የሚደነቅ አገልግሎት ነበርና!
ጃንደረባው:- መንፈሳዊ ትምህርትና አገልግሎቱ እንዳለ ሆኖ ብዙ ርቀት የሔዱበት ዘመናዊ ትምህርትስ እንዴት ነበር?
መምህር ግርማ ባቱ :- የመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን የተከታተልኩት ያን ጊዜ “የካቲት 25/67” ዛሬ “ሆለታ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት” ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ በሆለታ ገነት ከተማ ውስጥ፣ ልዩ ስሙ አራዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ፣ የዚያን ጊዜውን ገነት ጦር ት/ቤት፣ ኋላ ሀየሎም አርዓያ ወታደራዊ አካዳሚ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ የተባለውን የጦር ካምፕ ተጎራብቶ የሚገኝ ነው፡፡ የትምህርትና የአገልግሎት መሠረት የሆነችኝ የሆለታ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያንም የምትገኘው በዚሁ ካምፕ ውስጥ ነው፡፡ ትምህርት ቤቱ ከተለያዩ አጎራባች አካባቢዎች የሚመጡ በርካታ ተማሪዎች ይማሩበት የነበረ ትልቅ ትምህርት ቤት ነበር፡፡
በዚህ የተማሪነት ቆይታዬ በተለይ የማስታውሳቸው እና እንደ አባት የምንቆጥራቸው መምህራን ነበሩ፡፡ የተደራጀ ዕውቀት፣ ምሳሌ የሚሆን ሰብእና እና የተከበረ ማኅበራዊ ተሳትፎ የነበራቸው፣ ከዚያም ባለፈ በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ውስጥም የሚገኙ መምህራን ነበሩና፣ አይረሱኝም፡፡
አምስተኛ ክፍል ስደርስ እነዚህን መምህራን የበለጠ የማወቅ ዕድል አግኝቼ ነበር፡፡ ምክንያቱም እኔም የበለጠ ወደ ቤተ ክርስቲያን ትምህርትና አገልግሎት የተሳብኩት በዚያን ጊዜ ስለነበረ ነው፡፡ በሁለቱም የትምህርት ዘርፎች፡ በቤተ ክርስቲያኑም ሆነ በአስኳላው ጥሩ ከሚባሉ ተማሪዎች መካከል ነበርኩ፡፡ በዚህ ምክንያት ወደ ዲቁና አገልግሎት የገባሁት በጣም በጠዋቱ ነው::
የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቴን እንደጨረስኩ የአብነት ትምህርቱን ለመቀጠል የነበረኝ ፍላጎት እጅግ ከፍተኛ ነበርና ወደ ሰሜን ሸዋ፡ ምንጃር፣ ሸንኮራ፣ አረርቲ … አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የዜማ ትምህርትን በመጠኑ ለመማር ሞክሬያለሁ፡፡ ይሁን እንጂ በጤናና በሌሎች ምክንያቶች ብዙ መግፋት ሳልችል ቀረሁ፣ ወደ ሆለታ ገነት በመመለስ በጊዜው አጠራር ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የአሁኑ ቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ጠንካራውን የምዘና ፈተና በማለፍ ለመግባት ቻልኩ፡፡
የመጀመሪያ ዲግሪዬን በዚሁ ኮሌጅ እንደጨረስኩ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሥር፣ በዚያች ባደኩባት ደብር ላይ በስብከተ ወንጌል ኃላፊነት ተመድቤ እያገለገልኩ ሳለ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ፡ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም የሁለተኛ ዲግሪ ትምህርት የመከታተል ዕድል አገኘሁ፡፡ ከአብነት ትምህርት በመቀጠል በሕይወቴ ብዙ የተጠቀምኩበት የትምህርት ቆይታ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ተቋም ውስጥ የነበረኝ ቆይታ ነው፡፡
በትምህርት ዓለም ውስጥ አንዳንድ ጊዜ ዕድለኛ የሚያደርጉህ ገጠመኞች ያሉ ይመስለኛል፡፡ ትምህርቱ በይዘት ተመሳሳይና ያው ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን፤ ያስተማረህ ሰው ማንነት ግን እጅግ በጣም ወሳኝ ነው፡፡ ታዲያ እኔም እንደመታደል ሆኖ ኢትዮጵያዊ ርእዮትን፣ ለኢትዮጵያ ታሪክ፣ ባህልና ሌሎች ሀገር በቀል ዕውቀቶች መመልከቻነት የሚጠቀሙ፣ ነገሮችን ሁሉ በዚሁ መንገድ የሚተነትኑ፣ ዛሬ ባለንበት ሁኔታ የሚቆጩ መምህራን ነበሩ የገጠሙኝ፡፡ በተጨማሪ የትምህርቱ ቆይታዬ ከነባር የኢትዮጵያ ጽሑፎች ጋር በእጅጉ አስተዋውቆኛል፡፡
ለቤተ ክርስቲያኔ እና ለትምህርቶቿ እንዲሁም አጠቃላይ ማንነቷ የበለጠ ክብርና ፍቅር እንዲኖረኝ አድርጎኛል፡፡ ይህን መሰል የ “እህ!/አሃ!” ገጠመኝ በዚያ ሥፍራ ይገኛል ብሎ ማንም ላይጠብቅ ይችላል፡፡ ምናልባትም ከቀደመው የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ክፍተቶች የተነሣ ሊሆን ይችላል፡፡ መቼም ይህን ለመተንተን ጊዜውም አይበቃን፡፡
ከዚህ በኋላ የነበረኝ የትምህርት ቆይታ እንደገና ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅና ወደ ነገረ መለኮት የተመለስኩበት የድኅረ ምረቃ መርሐ ግብር ነው፡፡ አሁንም በመምህርነት አገልግሎት ያለሁበትና የሦስተኛ ዲግሪ ትምህርትንም የቀጠልኩበት ነው፡፡
ጃንደረባው :- ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዴት ገባህ? ብዙዎች እንደሚያደርጉት ሌላ ትምህርት መማር ስትችልስ ለምን መረጥከው?
መምህር ግርማ ባቱ :- እንደ ነገርኩህ መምህሬ ልዩ መንፈስን ማጋባት የሚችሉ መምህር ናቸው፡፡ ዜማ ሲያስተምሩ ከነምልክቱ ይነግሩሃል፣ ሥረይ የሚባል ነገር አለ ፣ ከቦታው አምጥተው በቀላሉ እንድትይዘው ያግዙሃል፡፡ ማኅሌትም ሆነ ማንኛውም አገልግሎት አብረሃቸው ስትቆም የዚህ ትርጉሙ ይህ ነው፣ አሁን እንደዚህ ይደረጋል፣ ትርጉሙ እንዲህ ነው እያሉ ልምድ ብቻ እንዲሆንብህ ሳይሆን ልዩ ማስተዋልን ያለማምዱሃል፡፡ እናም ይህ አስተዳደግ ቤተ ክርስቲያንን በትልቅ ደረጃ የማገልገል ፍላጎትን በውስጤ አሳድሮብኝ ነበር፡፡ ያኔ የነበረኝ ሕልም የተዋጣለት መሪጌታ መሆን ነበር፡፡ ወደሰሜን ሸዋ ሄጄ የነበረበትም ምክንያት ይሔው ነበር፡፡ ይህ ባለመሳካቱና ከእኔም በፊት ከደብሯ ተልኮ በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ የነበረ ታላቅ ወንድማችን በወቅቱ ሊቀ ዲያቆን፣ አሁን መጋቤ ሃይማኖት ግርማ በቀለ ስለነበረ በእርሱ አርአያነት ስለ መንፈሳዊ ኮሌጁ በማወቅ ወደዚህ ልሳብ ችያለሁ፡፡
እውነት ነው ብዙ የቅድስት ሥላሴ ደቀ መዛሙርት ሌላ የትምህርት ዕድል ሰውተው ይመጣሉ፡፡ ሥራና ሌሎች ጉዳዮችም እንደዚሁ ለቅድስት ሥላሴ ምርጫ የሚሰው ናቸው፡፡ እኔ ትንሽ ማስተዋል ከጀመርኩ ጊዜ ጀምሮ ሌላ አማራጭ ታይቶኝም አያውቅም፡፡ እንደው ከዚህ እስከዚህ በማልለውና አሁን ልዘረዝረው በማያስፈልግ ምክንያት ቤተ ክርስቲያን ሁሉ ነገሬ ናት፡፡ ከዚህ ውጪ ያለ ሕይወት አይታየኝም፣ ያኔም አልታየኝም፡፡ ምንም ባደርግ ልከፍለው የማልችል የቤተ ክርስቲያን ታላቅ ውለታ አለብኝ፡፡ ስለዚህ ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ መግባት የማማርጠው ሳይሆን በብቸኝነት ሁሉን ነገር የምሰዋለት ነበረ፡፡ አሁን ሳስታውሰው በእኛ ጊዜ የነበረው የመግቢያ መሥፈርትና መመዘኛ ፈተናው ከባድ ነበር፡፡ በዚያ ምክንያት ፈተናውን ለማለፍ እናደርግ የነበረው የወራት ዝግጅትም አይረሳኝም፡፡ በዚህም እጅግ ደስተኛ ነኝ፡፡
ጃንደረባው :- የመንፈሳዊ ኮሌጅ ቆይታህን እንዴት ትገልጸዋለህ? ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ዩኒቨርሲቲ በመምህር ግርማ ዓይን እንዴት ይታያል?
መምህር ግርማ ባቱ :- የመንፈሳዊ ኮሌጅ ቆይታዬ በብዙ መንገድ ሊገለጽ ይችላል፡፡ በመጀመሪያ ከዕድሜም ይሁን ከአካባቢ ለውጥ ጋር በተያያዘ፣ በግራ መጋባት የጀመረ ቆይታ ነው፡፡ በተለያየ ምክንያት ደንግጠህ የምትጀምረው ትምህርት ነው፡፡ ከቋንቋዎች ዕብራይስጥ፣ ግሪክ፣ ዐረብኛ የማትጠብቃቸውና በፍጹም አዲስ የሚሆኑብህ ትምህርቶች ናቸው፡፡ ነገረ መለኮት የሚነገርበት ደረጃ፣ የሚጠቀማቸው የእንግሊዘኛ ቃላት፣ ሐረጋት፣ እና ሙያዊ ቃላት የትም ሰምተሃቸው የማታውቃቸው ናቸው፡፡ ከእነዚህ ሁሉ ጋር ለመላመድ በምታደርገው ጥረት እወጣው ይሆን? የሚል ጥያቄ ያድርብሃል፡፡ ከአምስቱ ዓመታት ቆይታ ውስጥ የመጀመሪያዋ ሴሜስተር ጭንቅ ናት፡፡ እኔም በ “እወጣው ይሆን?” የጀመረ የትምህርት ታሪኬ የመጀመሪያ ደረጃ ላይ በሚቀመጥ ውጤት ነው የተጠናቀቀው::
የቀደመው ትምህርት ላይ የነበረው ትንሽ ክፍተት፡ በአቀራረብ፣ በብያኔና በይዘት የሚገለጸውን የምሥራቁ ኦርቶዶክስና የምዕራቡ ዓለም የነገረ መለኮት ልዩነት ግልጥልጥ አድርጎ የእኛ ይሄ ነው በሚል ማሠሪያ አለመዘጋጀቱ ነው፡፡ በጊዜ ሂደት እነዚህ ነገሮች ተቀርፈው ትምህርቶችም በተለያየ ዘርፍ ተሰናድተው የሚሰጡ መሆናቸው ግሩም ነው፡፡ አሁን የተጀመረው የአብነት ትምህርት በእኛ ጊዜም የነበረ ቢሆን ትልቅ የጥራት ልዩነት ይፈጠር ነበር፡፡ አሁን በቅድስት ሥላሴ ዩኒቨርሲቲ ውስጥ ከመደበኛው ትምህርት በተጓዳኝ ትርጓሜ መጻሕፍት፣ ቅኔ፣ ቅዳሴ እና አቋቋም በወንበር እየተሰጡ ይገኛሉ፡፡ ይህ አካሄድ በእርግጠኝነት ለውጥ ያመጣል፡፡
ቅድስት ሥላሴ ያን ጊዜም ሆነ አሁን፣ ውስጡም ሆኜ ጭምር ይገዝፍብኛል፡፡ እኔ ብዙ ሰዎች በሚገባው መጠን ይረዱታል ብዬም አላስብም፡፡ በተማሪዎች ረገድ እንኳ ብናየው እጅግ በጣም የሚገርም ኃይል በውስጡ አለ፡፡ ከተለያየ የሙያ ዘርፍ የካበተ፣ በሁሉም የትምህርት ደረጃ የሚገኝ እና በልምድ የታገዘ ዕውቀት ያለቸው ተማሪዎች ናቸው የሚመጡት፡፡ ቀድመው የሚያውቁትን እንደ ቤተ ክርስቲያን ሐሳብ በነገረ መለኮት ለመግራት አስበው የሚመጡ ናቸው፡፡ ይህን የሰው ሀብት ማሰብ፣ እንዴት ልንጠቀምበት እንደምንችል ማጥናት ብዙ የቤት ሥራ ያለው ነው፡፡ በውጪ ላለው ወገን የዩኒቨርሲቲው ሚና አለመገለጡ ዋናው ችግር ነው፡፡ ስለዚህ ሁላችንም በዚህ ዙሪያ መረባረብ አለብን፡፡
ጃንደረባው :- በዩኒቨርሲቲው ቆይታዎ ልዩ ነገር የተማሩበት ፣ የማይረሱአቸው ጊዜ ሁኔታና ሰዎች ካሉ?
መምህር ግርማ ባቱ :- ያኔም ሆነ አሁን በቆይታዬ ሁሉ እንደተማርኩ ነው፡፡ መማር ራሱን የቻለና አስረጂም የማያሻው ነው፡፡ ማስተማር ግን ሁል ጊዜ ለበለጠው የሚያተጋ፣ በተለይ ለንባብ ቅርብ እንድትሆን የሚያደርግ የተመረጠ ሕይወት ነው፡፡ ማንበብ ካቆመ እንኳን መምህር፣ ተማሪም ቢሆን ቁጥሩ ከተማሪ ነው እንጂ ሕይወቱ የጠወለገ ነው፡፡
በጣም የተለየ ግምት የምሰጣቸውና ሁለ ገብ የሆኑት ሊቅ ዶ/ር ዲበኩሉ ዘውዴ ያረፉት ተማሪ በነበርኩበት ጊዜ ነው፡፡ በርካታ ትምህርቶችን አስተምረውናል፡፡
በግል ስትቀርባቸው ምክራቸው አንዳንዴም ተግሣፃቸው አይጠገብም፡፡ የንባብን፣ የአጻጻፍን፣ የሙግትን፣ የመማርን ዘዴ ሁሉ ሳይቀር ከጤናቸው ጋር እየታገሉ በስሜት ይነግሩናል፡፡ አንድን ርእሰ ጉዳይ ለማስረዳት በደቂቃዎች ውስጥ ሃያና ሠላሳ መጻሕፍትን ይጠቅሱልሃል፡፡ ከውስጣቸው ሲንቀለቀል የምትሰማው የቤተ ክርስቲያን ቅንዓት አስገራሚ ነው፡፡ እንደዚያ ያለ ክትት ያለ ዕውቀት እኔ በሆንኩ ያሰኛል፡፡ ድንገት ስናጣቸው የተሰማን ሐዘን አይረሳኝም፡፡ እርሳቸውንም መቼም አልረሳቸውም፡፡
ሌላኛው አሳዛኝ ገጠመኜ በ1997 ዓ.ም በነበረው የፖለቲካው ግርግር እኛም ጸበሉ ደርሶን የገጠመን ፍረጃ ነው፡፡ ፍረጃው በግሌ ሳይሆን ሙሉ የዚያን ዓመት ተማራቂ ተማሪዎች የሚጎዳ ቢሆንም አስተማሪነቱ ሳይካድ በጣም አሳዝኖኝ ነበር፡፡ ይሁ ሁኔታ አሁንም የቀጠለ ነው፣ባልሆንከውና በማታውቀው ነገር ሁሉ በተለያየ መንገድ ትፈረጃለህ፡፡
ጃንደረባው :- የሰባኪያን መምህር እንደመሆንዎ በስብከተ ወንጌል ለሚያገለግሉ ምን ይመክራሉ? መንፈሳዊ ኮሌጅ ለሚማሩስ?
መምህር ግርማ ባቱ :- ለመምከር እንኳ እኔ ትክክለኛው ሰው ነኝ ብዬ አላስብም፡፡ የቅድስት ሥላሴ ተማሪዎች ከሚማሯቸው ትምህርቶች ብዛት የተነሣ ከብዙ መምህራን ጋር ይገናኛሉ፡፡ ለሰባክያኑ የስብከት ዘዴ መምህራን የተሻለ ምክር ሊለግሷቸው ይችላሉ፡፡ ባይሆን በእኛ ዘመን በጋራ ሊያሳስበን የሚገባው ነገር ላይ ሐሳብ መስጠት ግን ተገቢ ነው፡፡ ከጥቂት ሰባክያን በቀር የሚበዛው ስብከት የቤተ ክርስቲያንን ትምህርትና ደረጃ ይመጥናል ብዬ አላስብም፡፡ በአብዛኛው ስሜታዊነት ዐውደ ምሕረቱን ተቆጣጥሮታል፡፡ ሕግና ሥርዓት እንዳለውም ተዘንግቷል፡፡ ስለዚህ ሰባክያን ከማንም የተሸለ ዝግጅት ያስፈልጋቸዋል፡፡ በመምሪያ ደረጃ በሚገባ የተጠና ሥርዓተ ትምህርት ቢኖረው፣ ምእመናንም በዕድሜ፣ በትምህርት ደረጃ፣ በሌሎችም መሥፈርቶች ተለይተው ዘላቂነትና መሠረትነት ያለው ትምህርት ቢያገኙ የሚል ሐሳብ አለኝ፡፡
ጃንደረባው :- ከትምህርቱ ዓለም ወጣ እንበልና በቤተ ክርስቲያኒቱን በብዙ የሥራ ሓላፊነቶች ማገልገልዎ ይታወቃል:: ምን ይመስል ነበር?
መምህር ግርማ ባቱ :- የሥራ ኃላፊነቶች እና እኔ ረጅም ታሪክና ዝምድና ነው ያለን፡፡ ቀደም ሲል የጠቀስኳት የሆለታ ደብረ ገነት ኪዳነ ምሕረት ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ለረጅም ዓመታት በሊቀ ዲያቆናት የአገልግሎት ኃላፊነት፣ በሰበካ ጉባኤ ጸሐፊነት እና ዛሬ ድረስ ሳስበው የሚገርመኝና የሚያስደነግጠኝ በርካታ ሃይማኖታዊና ታሪካዊ ቅርሶች የሚገኙበት ግምጃ ቤት ሓላፊ ሆኜ ሠርቻለሁ፡፡ ምናልባት ዛሬ ቢሆን ይህኛውን ሓላፊነት ለመቀበል ያስፈራኝ ነበር፡፡
የነገረ መለኮት ትምህርቴን እንደጨረስኩ፣ በምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት፣ ወልመራ ወረዳ፣ የሆለታ ደብረ ገነት ቤተ ክርቲያን የስብከተ ወንጌል ኃላፊ ሆኜ ለሦስት ዓመታት ሠርቻለሁ፡፡ ወደ ቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ተመልሼ በሥራ ድርሻ ከመጣሁ ጀምሮ እስካሁን በተለያዩ የሥራ ሓላፊነቶች ሠርቻለሁ፣ እየሠራሁም ነው፡፡ ከእነዚህም መካከል ከ2001 ዓ.ም እስከ 2003 ዓ.ም. በሬጅስትራርነት፣ ከ2006 እስከ 2010 ዓ.ም በምክትል የአካዳሚክ ዲንነት፣ አሁን ደግሞ ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ የጥናትና ምርምር ማዕከል ሓላፊ በመሆን እየሠራሁ እገኛለሁ፡፡
ጃንደረባው:- መምህር ግርማ በጣም ውብና በሳል ብዕር ካላቸው ጸሐፍት መካከል አንዱ ናቸው::
እስቲ ስለ ጽሑፍ ሥራዎችዎ ያጫውቱን?
መምህር ግርማ ባቱ :- በመጻሕፍት ደረጃ የመጀመሪያዬ የትርጉም ሥራ የሆነው እና “The Spiritual Means” ከሚለው የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ መጽሐፍ “ጉዞ ወደ እግዚአብሔር” በሚል የተመለሰው መጽሐፌ ነበር፡፡ ይህ መጽሐፍ፣ አሁንም ድረስ እኔ ከማስበው በላይ ተነባቢ ነው፡፡ ብዙዎች የመንፈሳዊ ሕይወት ጅማሮአቸው ላይ ብዙ ያገዛቸው መጽሐፍ እንደሆነ ይነግሩኛል፡፡
ቀጣዩ ጊዜና ሁኔታዎች ያልተገጣጠሙለትና ብዙም ያልተነበበው አዲሱ ሰው የሚለው መጽሐፌ ነው፡፡ ከዚህ መጽሐፍ በኋላ ለረጅም ጊዜያት ከሕትመቱ ዓለም ርቄ ነበር፡፡ ነገር ግን አልፎ አልፎ በብዕር ስም የወጡ ሥራዎችን ስሠራ ነበር፡፡ ለተወሰኑ ጊዜያትም በጋዜጦች ላይ እንዲሁም በሐመር መጽሔት ላይ (በብዕር ስም) ጽሑፎችን ሳበረክት እስከ 2012 ዓ.ም. ድረስ ቆይቻለሁ፡፡
2012 ዓ.ም. “የነገረ መለኮት መግቢያ” በሚል ርእስ የሚታወቀው መጽሐፍ ታተመ፡፡ መጽሐፉ ራሱን የቻለ ታሪካዊ መነሻ ቢኖረውም እሱን መተረኩ ብዙ ጊዜ ይወስድብናል፣ ላይጠቅምም ይችላል፡፡ ነገር ግን ነገረ መለኮትን በጥልቀት ለመማር የሚያስቡ ሰዎች ከወዲሁ ማወቅ የሚገባቸው ነገሮችን በብዛት፣ እንዲሁም የአቀራረብን (Approach) ነገር፣ በእኛ በኦርቶዶክሳውያኑ እና በሌሎቹ መካከል ያሉ መሠረታዊ ልዩነቶችንም ይዳስሳል፡፡
በቀጣይነት በ2014 ዓ.ም. የታተመው የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ታሪክ ቅጽ ፩ ነው፡፡ የመጽሐፉ አጠቃላይ እይታ (Perspective) ቀደም ሲል ስለ የኢትዮጵያ ጥናትና ምርምር ባነሣሁት ዓይነት አቀራረብ የተዘጋጀ ነው፡፡ በታሪክ ጥናት የጥንት የሚባለውን ክፍል የያዘ ነው፡፡ በመሆኑም የአንድ አምላክ እምነት በኢትዮጵያ የተጓዘባቸውን የታሪክ መንገዶች በሦስቱም ደረጃዎች ማለትም፡ በሕገ ልቡና፣ ሕገ ኦሪትና ሕገ ወንጌል ማኅቀፍ ያስቃኛል፡፡ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያንን በውስጣዊ እይታ፣ ከተቻለም በልጅነት ለማየት እንዲቻል በርካታ ፍንጮችንና ምንጮችን በማቅረብ ለማገዝ የተጻፈ ነው፡፡ ነገር ግን በእኔ እምነት የታሪክ ትምህርት ከይዘቱ ይልቅ አተያዩ እጅግ የገዘፈ ዋጋ ስላለው በታሪክ አጠናን እና አጻጻፍ ዙሪያ ያሉ ውስጣዊ እና ውጪያዊ እይታዎችን፣ ከዚህ የሚነሡትንም ችግሮች እና ቢሆን የምላቸውንም አካሄዶች ለመጠቆም የሞከርኩበት መጽሐፍ ነው፡፡
ከዚህ በኃላ የሚመጡትን ከዚህ በፊት ከነበሩት የበለጠ ዋጋ እሰጣቸዋለሁ፡፡ አሁን በተለይ ሱታፌ አምላክና የቤተ ክርስቲያናችን ታሪክ ቀጣይ ክፍሎች ዙሪያ እጅግ አድካሚና ፈታኝ ዝግጅት እያደረግሁ ነው፡፡ መደበኛ መምህርነት፣ በዚህም ላይ ተማሪነት፣ በተለያዩ ወቅታዊ ጉዳዮችም ተሳታፊነት ስላለ የጽሑፍ ሥራ የሚፈልገውን ጽሙና ላማግኘት ያዳግታል፡፡ ነገር ግን ሕይወት ትግልም አይደል! እየታገልኩ ነው፡፡
ጥናታዊ ጽሑፎቼም በአብዛኛው በሦስት ርእሰ ጉዳዮች ዙሪያ የሚያጠነጥኑ ናቸው፡፡ አንደኛና ሁለተኛ ላይ የሚቀመጡት ነገረ መለኮትና የቤተ ክርስቲያን ታሪክ ናቸው፡፡ ሦስተኛው ግን ሰፊ ሽፋን ያለው የነገረ ሰብእ እይታዎች ዙሪያ በተለይ የሚያጠነጥኑ ጽሑፎች የሚገኙበት ሆነው ለትምህርት ተቋማት የቀረቡና የታተሙ ናቸው፡፡ እነዚህን በሂደት ከቋንቋ ወደ ቋንቋ መልሶ ማስነበብ ያስፈልጋል፡፡
የጻፍኳቸውን መጻሕፍት ይዘት በአንድ ሐሳብ መጠቅለል ሊከብድ ይችላል፡፡ ይሁን እንጂ አብዛኛውን ርእሰ ጉዳይ ወደ አንድ ላምጣው ብዬ ባስብ መንፈሳዊነት ነው የሚሆነው፡፡ ይህ መንፈሳዊነት ተገቢ ብያኔ አግኝቷል ብዬ አላስብም፡፡ ነገረ መለኮታችን በአጠቃላይ የመንፈሳዊነት ጉዳይ ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያን ታሪክ ውስጥም ይህን መንፈሳዊነት በክርስቲያኖች ሕይወት ውስጥ ገዝፎ የታየባቸውን ሁኔታዎች ላማሳየት ነው ጥረት የማደርገው፡፡ ከዚሁ ጋር ሁሉንም አንድ የሚያደርጋቸው፣ (ከትርጉም ሥራ በቀር ማለቴ ነው)፣ የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ያላትን ልዩ ጸጋ አጉልቶ ማሳየትም ሌላኛው ትኩረት ነው፡፡
ጃንደረባው :- የዚህ ዘመን መጻሕፍት ሁኔታ እንደሚጽፍ አንባቢ ሆነው እንዴት ያዩታል? ለጸሐፍያንስ ምን ይመክራሉ?
መምህር ግርማ ባቱ :- በጣም ጥሩ እና ተስፋ ያለው ስሜት ይሰማኛል፡፡ በጥልቅ ጥናት የሚጽፉ እንደ ፕ/ር ኃይሌ፣ ፕ/ር መሳይ ከበደ፣ ፕ/ር ማእምር መናሰማይ፣ ፕ/ር አየለ በከሪ ያሉ በርካታ አንጋፎች አሉ፡፡ እነዚህ ጥንታዊውን የኢትዮጵያ ዕውቀት በዘመናዊው አቀራረብ ከሀገራዊ ተቆርቋሪነት ጋር የሚያስነብቡን፣ ወደራሳችንም እንድንመለስ የሚመክሩን ናቸው፡፡ እንዲሁም እንዲያው ስም ሳነሣ ብዙዎችን ልዘነጋ እችላለሁ እንጂ፤ እንደ ቀሲስ ዶ/ር መብራቱ ኪሮስ፣ ደብተራ በአማን ነጸረ፣ ዲያቆን ያረጋል አበጋዝ፣ ዲያቆን ሔኖክ ኃይሌ፣ ያሉ፣ ሌሎችንም በጣም ጥሩ ጥሩ ወጣት ጸሐፊያንን እያፈራ ያለ ዘመን ነው፡፡ ሊቃውንቱም በቃልም በመጻፍም ማስተማር መጀመራቸው የሚደነቅ ነው፡፡ ነባር የቤተ ክርስቲን መጻሕፍትም እንደልብ የማይገኙ የነበሩት አሁን በድጋሚ በመታተምና በመሰራጨት ላይ ናቸው፡፡ ይህ በጣም ጥሩ ነገር ነው፡፡
ጊዜ እና ሁኔታውን በተመለከተ ከተነጋገርን ግን መጻሕፍትን ለሚጽፉ የቤተ ክርስቲያን ልጆች ከባድ ፈተና ያለው መሆኑን ማንሣት ያስፈልገኛል፡፡ የማሳተሚያ ዋጋ ከቁጥጥር ውጪ ሆኗልና ተስፋ ሊያስቆርጥ ይችላል፡፡ ይህን ምክንያ አድርጎ ከዝግጅት መስነፍ አያስፈልግም፡፡ ማድረግ ያለብን ተዘጋጅቶ መጠበቅ ነው፡፡ በእኛ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ መጽሐፍ መጻፍ ቀላል ነገር አይደለም፡፡ እንደሌሎቹ ስሜታችንን እና የመሰለንን መጻፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጠልቆ ማጥናት፣ እይታን ማጥራትና ከደረጃ ሳይወርዱ ማጻፍ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡
“እንደሌሎቹ ስሜታችንን እና የመሰለንን መጻፍ አይቻልም፡፡ ስለዚህ ጠልቆ ማጥናት፣ እይታን ማጥራትና ከደረጃ ሳይወርዱ ማጻፍ ያስፈልጋል እላለሁ፡፡” መምህር በጣም አመሰግናለሁ ረጅም የበረከት እድሜን ያድልልን መፅሐፎትን በጉጉት እጠብቃለሁ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
መምህር ቃለ ሀይወት ያሰማልን ። በእውነት የእርሶ ተማሪ መሆን እንደ እድለኝነት ነው እኔ የማየው ነገረ መለኮት መግቢያ እንዴት አድርገው እንዳስተማሩን መችም አይረሳኝም ለምሳሌ አንድ ክርስቲያን እንዴት ማደግ እንዳለበት ብሎም እግዚአብሔር ወደ መምሰል (Theosis) እንዴት መድረስ እንዳለበት ስያስተምሩን አቤት ይገርማል ስራ ውለን ደክሞን ነው ወደ ት/ት የምንመጣው መምህር ግርማ በቃ እንደ አዲስ ያነቁናል እኔ ሁል ጊዜ ሰዓት መድረሱን ጥያቄ ካላችሁ ብለው ለውይይት ወደኛ ሲመልሱ ኦ ሰዓት አለቀ እላለሁ ።ውድ አንባብያን የነገረ መለኮት መግብያን አንብብቡት እንዲሁም በገነተ ጽጌ ሰንበት ት/ት እና ማሕበረ ቅዱሳን ያቀረቡትን ከድምጡ እና የኔን ስሜት ትጋራለችሁ ። ቆይማ ሳልረሳው EOTC HISTORY የኢ/ኦ/ተ/ቤተክርስቲያን ታሪክ ለመማር ጊዜው ደረሰና መምህር ክላሱን ጀመሩት አቤት መታደል በቃ ሐገሬንና ቤተክርስቲያኔን የበለጠ እንድወዳቸው ተስፋ መቁረጥ የሚባል ነገር ወደ እኔ እንዳይመጣ ስንቱን ልንገራችሁ መጻፋቸውን አንብቡት ያኔ ትረዱኛላችሁ ። እንደ መምህር ግርማ ያሉት ለቤተክርስቲያን ያብዛልን የዝግጅት ክፍሉንም አመሰግናለሁ ።
ቃለሕይወት ያሰማልን
ፈጣሪ በቀለመ ወርቁ ስሞትን ይጻፈው።
ለመመዝገብ ምን ማድረግ አለብኝ