አንዳንድ ቀን አለ አንጀት የሚያላውስ ፤ የለቅሶ ስሜትን የሚቀሰቅስ ችግር በሰዎች ላይ ሲደርስ የምንገጣጠምበት፤ ታዲያ በዚህ ሰዓት ምነው “እግዚአብሔር ሀብታም ቢያደርገኝና በሰጠኋቸው” ብለን እንመኛለን። ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ የማይገባ ምኞት ነው ይለዋል። እግዚአብሔር ቢያስፈልግ ኖሮ ካንተ ቀድሞ ይህንን ሳያስብ የሚቀር ይመስልሃል? ለአንዳንዶቹ ድህነታቸው ከእግዚአብሔር ጋር የሚገናኙበት መንገዳቸው መሆኑንም አትርሳ። መራብና መጠማታቸው ስለክርስቶስ ብለው ያደረጉት ከሆነ “ስለጽድቅ የሚራቡ ብፁዓን ናቸው” ተብለው ይመሰገኑበታል።
አንተ ግን ከዚያ ይልቅ በምትችለው የተቸገሩትን እርዳ። የሚበሉትን የሚጠጡትን መስጠት ባትችል ልብሳቸውን እግራቸውን አጥበህ ማገልገል ትችል እንደሆነ እሱን አድርግ። እጅና እግራቸውን ማጠብ ባትችል ቤትህ አስገብተህ ማሳደር ትችል ከሆነ ይህንንም አድርግ። ይህንን ሁሉ ማድረግ ካልቻልህ ደግሞ ካለው እንዲያደርሳቸው ጸልይላቸው። እግዚአብሔር የሚወቅስህ የምትችለውን ባለማድረግህ እንጅ የማትችለውን ስላላደረግህ አይደለም። ያ ክፉ ባሪያ የተቀጣው በተሰጠው ገንዘብ ጌታ እንደሌለው አድርጎ ከሰካራሞችና ከቀራጮች ጋር ገንዘቡን ስላበላሸው ነው እንጅ ባልተሰጠው ነገር አልነበረም ማቴ 24፥48።
እግዚአብሔር ለጽድቅ ሥራ በቂ የሆነ ነገር አሟልቶ ሰጥቶናል። ገንዘብ ሳይሰጥ “ብራብ አላበላኸኝም” ብሎ አይፈርድብንም። ነገር ግን ቀዝቃዛ ውኃ የማያገኝ የለምና “ብጠማ አላጠጣኸኝም” ብሎ ሊፈርድብን ይችላል። በዙፋን ካለ ንጉሥ በዐደባባይ እስከወደቀ ጽኑስ ውኃ የማያገኝ የለምና። ባለጠጎች ልብስ ስላላቸው የታረዘ አልብሰው፣ ምግብ ስላላቸው የተራበ አብልተው፣ ቤት ስላላቸው እንግዳ አሳድረው {የድሮ መተርጉማን እንግዳ ብሆን አልተቀበላችሁኝም የሚለውን የድሆች አንቀጽ አድርገው ተርጉመውት ነበር በዘመናቸው ድሀ ማለት ምግብና ልብስ የሌለው እንጅ ቤት የሌለው ሰለማይኖር ጥያቄ ውስጥ የሚገባ ስላልነበረ ነው} የሚወርሷትን የእግዚአብሔርን መንግሥት ድሆች የተጠማ አጠጥተው፣ የታሰረ ዋስ ሁነው አስፈትተው፣ የታመመ ጠይቀው ይወርሷታል። ለሁለቱም የተሰጠው የመጽደቅ ዕድል ዕኩል ነው።
ገበሬው በወይኑ እርሻ ውስጥ የተከላትን በለስ ቆርጣችሁ ጣሏት ብሎ ሠራተኞችን ያዘዘው በለስ ስላላፈራች እንጅ ስንዴ እንድታፈራ ፈልጎ አልነበረም። ተፈጥሮዋን ያውቃል። ይህንኑ የበለሱን ፍሬ መስጠቷ በቂ ነበር ችግሩ እሱን አለማድረጓ ነው:: ሉቃ 13፥6
ያንተም ችግር ገንዘብ ኑሮህ የድሀውን ችግር አለመቅረፍህ ሳይሆን በክፋትህ እያሳደድህ ረሀቡን ታግሦ እንዳይተኛ በተናዳፊ ምላስህ ማባረርህ ነው። ቸግሮት አንገቱን ቢደፋ አውቆ ነው አስመሳይ ነው፤ እርቦት ዝም ቢል አድር ባይ ነው ፤ ቀን እስኪያልፍ ብሎ ካገሩ ቢወጣ ስደተኛ ነው፤ ቢታገሥ ፈሪ ነው፤ እንደዚህ ባሉ የመውጊያ ብረት ቃላቶችህ ባታደማው የበለጠ የረዳኸው ያክል ይሰማው ነበር። ይሄ ሁሉ የሀገራችን ድሀ የቸገረው የሚበላው የሚጠጣው ብቻ ይመስላችኋል? እህልና ውኃንስ ለምነው ያገኙታል ደግ ሰውን ከወዴት ያገኙታል? የሚሰማው ሁሉ ስድብ ሁኖበት በጎ ቃል ለመስማት የሚጓጓ ስንት ሰው አለ መሰላችሁ? ፤ በጎ ሰው ማግኘት የሞቱ እናትና አባቱን የማግኘት ያክል ተስፋ አስቆርጦት መልካም የሚያደርጉለትን ሰዎች ሁሉ የሚጠራጠርበት ዘመን ላይ ነዋ ያለው!
የሌለህን ገንዘብ ቢኖረኝ እሰጠው ነበር ብለህ ከምትመኝ ያለህን ፍቅርን ስጠው ያንጊዜ ኑሮውን ፍጹም ታደርግለታለህ። አንተም እውነተኛ የክርስቶስ ደቀ መዝሙር መሆንህ በዚህ ይታወቃል። ጌታ “እርስ በእርሳችሁ ብትዋደዱ ሰው የኔ ደቀ መዛሙርት መሆናችሁን በዚህ ያውቃሉ” ብሎ ተናግሯልና። ልብ በሉ! ሙት ብታነሡ፣ ድውያንን ብትፈውሱ፣ እንጀራ አበርክታችሁ ብታበሉ፣ ውኃ ከዐለት ላይ አፍልቃችሁ ብታጠጡ፣ ሁሉን ትታችሁ ለምናኔ ብትወጡ አላለም። እርስ በእርሳችሁ ብትዋደዱ ነው ያለው።
ቅዱስ ዮሐንስ አፈ ወርቅ በሦስተኛው ተግሣጹ “ይደልወነ ንትፋቀር በበይናቲነ እስመ ዛቲ ሀብት ታበጽሐነ ኀበ ኩሎን ምግባራት ሠናያት፤ እርስ በእርሳችን ልንዋደድ ይገባናል ፍቅር ወደ በጎ ሥራዎች ሁሉ ትመራናለችና” ይላል። ፍቅርን ከመስጠት የሚቀድም ስጦታ የለም።
ከልባችን የሚፈልቀውን ፍቅር በመስጠት ካልታመን በምድር ላይ ያለ የትኛውንም ሀብት ቢሰጠን ልንታመን አንችልም። ይልቁንም በትንሹ እንታመን በትልቁ መስጠት እንድንችል ያደርገናል። ጽድቃችንን ፍጹም ለማድረግ ያልተሰጠንን መሻት ከመጣብን እመኑኝ በተሰጠን ጸጋ እያገለገልን አይደለም ማለት ነው። አንዳንዱ ሰው በትዳር እየኖረ እንደ ልቡ ለማገልገል መነኩሴ መሆን እንደነበረበት ያስባል። የባል፣ የሚስት፣ የልጆች፣ የሀብት ጉዳይ አላሰናዝር ብሎት እንጅ ወጥቶ ወርዶ ቤተ ክርስቲያንን ቢያገለግል እንደማይሰለቸው ሲናገር ልትሰሙት ትችላላችሁ።
አብርሃም በደግነቱ፣ ሙሴ በመልዕክቱ፣ አሮን በክህነቱ፣ እንጦንስ በምንኩስና፣ ርዕሰ ባህታውያን አባ ጳውሊ በብህትውና በኩል አድርገው ገነት እንዲገናኙ ነው እግዚአብሔር ያዘዛቸውና ይህንኑ ሳያንጎራጉሩ አደረጉ ዛሬ በገነት ሁሉም በክብር ናቸው። በደረጃህ በጸጋህ ብታገለግል እንጅ ሊቅ ሆነህ ስላልተረጎምህ፤ ደራሲ ሆነህ ስላልደረስህ፤ ዜመኛ ሆነህ ስላላዜምህ፤ ድምጽህ አምሮ ስላላንጎራጎርህ፤ ባለጠጋ ሆነህ እንዲህ እንደምታያቸው ሰዎች ብቻህን አንድ ቤተ መቅደስ ስላልገነባህ ቅር አይበልህ፡፡ ለገነት መግቢያ ያክል ላንተም ተሰትቶሃል ከንቱ ውዳሴ ቀረብኝ ብለህ ካልሆነ ያለህ ጸጋ ለጽድቅ በቂ ነው።
አሜን አሜን አሜን ቃለ ህይወት ያሰማልን
Feker new yegodelen. Feker kelelen hulum godeleben.
አሜን አሜን ቸሩ መዳህኒተ ዓለም በእድሜ በጤና ይጠብቅልን ቃለህይወትን ያሰማልን።
Amen
ቃለ ህይወት ያሰማልን።
በጣም ደስ የሚል ጽሀፍ ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ድንቅ ነው ።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን። “If you have nothing to give people, give them a warm smile and a kind word, give them love, give them tenderness, give them a word of encouragement; give them your heart” Pope Shenouda III.
እግዚአብሔር ያቆይልን!
“ያለህ ጸጋ ለጽድቅ በቂ ነው።”
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር። እኛም ወንድም እኅቶቻችንን ወድደን፣ በተሰሠጠን ጸጋ አገልግለንበት የመንግስቱ ወራሾች ያድርገን።
ካልተማሩ ማወቅ ካላወቁ መፅደቅ የለም እንዲሉ አበው ትልቅ ትምህርት ነው ያስተማሩን. አሜን እግዚአብሔር ይመስገን ቃለህይወትን ያሰማልን