ጸሎት እና ቀቢጸ ተስፋ

ጸሎት እየጸለይን: ለጸሎታችን መልስ ሳናገኝ ስንቀር ለቀቢጸ ተስፋ ይዳርጋል። አንዳንድ ጊዜ ዝምታውም መልስ እንደሆነ ለማይረዳ ሰው ወይም ደግሞ ፈቃድህ ይሁን ብሎ ለማይጸልይ ሰው የጸሎት መልስ ጊዜው ሲረዝም ተስፋ ወደ መቁረጥ ውስጥ ያስገባል። ማለትም “ፈቃድህ ይሁን” የሚለውን መስመር አባታች ሆይ የሚለው ጸሎት ላይ ለሚዘላት ሰው ማለት ነው። ጌታችን ራሱ ያስተማረንን “አባታችን ሆይ” የሚለውን ጸሎት ስንጸልይ፤ የጸሎቱን አካሄድ አስተውለነው ይሆን?

መጀመሪያ ምን በሉ አለ :- 

 “አባታችን ሆይ” ይህንን ስንል የልጅነታችንን ቦታ ማወቃችን ነው፤ ልጆች ካልሆንን አባታችን ብለን መጥራት አንችልምና። በጣም እኮ ከባድ ናት፥ “አባታችን ሆይ” ብለን ካወጅን ከዚያ በታች ያለው ነገር እንደሚሆንልን ፣ እንደሚደረግልን አንጠራጠር፣ እንመን፤ መጀመሪያ “አባታችን ሆይ” ለማለት ተፈቅዶልናል ። ከዚህ በላይ የሚፈቅድልን ነገር የለምና፥ “አባታችን ሆይ” ከማለት በላይ። “አባታችን ሆይ” ማለትን የፈቀደልንን አምላክ ታች ዝቅ ብለን “የእለት እንጀራችንን ስጠን” በሚለው ለምን እንጠራጠረዋለን? ከፈተና እንደሚያወጣን ለምን እንጠራጠራለን? መጀመሪያ “አባታችን ሆይ” ብለነዋላ! አባት አንድንለው ፈቅዶልናል።  አባታችን እንድትሉኝ የፈቀድኁላችሁ የእለት እንጀራችሁን ልሰጣችሁ፣ ከክፉ ላድናችሁ፣ መንግስቴን ላወርሳችሁ ነው እያለን ነው። ከላይ ልጅነታችንን ካወቅንና፣ ልጅነታችንን ካስጠበቅን ከታች ያለው ሁሉ የእኛ ነው ምንም አይቀርብንም። ለዚህ ነው ቅዱስ ጳውሎስ በመልእክቱ “አባታችን ሆይን” መዘርዘር አልፈለገም፤ “አባ አባት ብለን የምንጮህበትን የልጅነት መንፈስ ተቀብለናል” ነው ያለው። ቀጥሎ ደግሞ “ልጆች ከሆንን ደግሞ ወራሾች ነን” አለ። (ሮሜ 8 ፥15-17)

በቃ! ልጆች ከሆንን ወራሾች ነን። የፈቃድ መብት አይደለም፤ የልጅነት መብት ( Birth Right ) ነው ያለን። አባታችን ሆይ የምትለዋ ነገር ከገባችን ፣ እውነትም የምንጮኸው በልጅነት መንፈስ ከሆነ፥ አይ ግድ የለም ይሰጠው ተብሎ አይደለም የሚሰጠን፤ የእኛ ስለሆነ እንወስዳለን እንወርሳለን እንጂ፤  ከእኛ የሚጠበቀው ልጆች መሆናችንን ማረጋገጥ ብቻ ነው። ቅዱስ ጳውሎስ አሁንም “እንግዲያስ ከእንግዲህ ወዲህ ከቅዱሳን ጋር ባለ ገሮችና የእግዚአብሔር ቤተ ሰዎች ናችሁ እንጂ እንግዶችና መጻተኞች አይደላችሁም” ይለናል። ኤፌ.2፥19

 “በሰማያት የምትኖር” ስንል ምንን ነው የምንገልጸው? ክብሩን ፣ ገናንነቱን፣ እኛ እንደምናስብ የማያስብ፣ እኛ እንደምንሠራ የማይሠራ ፣ ሀሳቡ ፈቃዱ ከእኛ የሰማይና የምድር ያህል ከፍ ያለ እንደሆነ ነው፤ ልብ በሉ ምን ያህል እምነት እየገነባን እየመጣን እንደ ሆነ። አባታቸን ሆይ ብለን አባትነቱን ተቀብለን፣ ልጅነታችንን አረጋግጠናል፤ ከእኛ ሀሳብ የእርሱ ሀሳብ፤ ከእኛ ፈቃድ የእርሱ ፈቃድ የተሻለ እንደሆነ መስክረናል ስለዚህ “ፈቃድህ ይሁን” እንለዋለን። ከዚያ እንደውም ጸሎቱን እዚህ ጋር ማቆም ነበረብን። ምክንያቱም ከዚያ በኋላ ያለውን ፍቃዱ ከሆነ ይሰጠናል ፈቃዱ ካልሆነ አይሰጠንም፤ ሁለቱንም ፈቃድ እንቀበላለንና።

አሁን አሁን እየተለመደ የመጣ ትርጒሙ ምን ማለት እንደ ሆነ የማይታወቅ ጸሎት አለ:: ጀጀጀ ፈፈፈ ቀቀቀ ወዘተ እየተባለ የሚፀለይ። ምንድር ነው? ሲባል “ከክፉ የሚጠብቅ ነው” ይባላል፤ ግን ተመልከቱ አባታችን ሆይ የሚለውን ጸሎት እያወቅን፣ ትርጉም እየሰጠን የጸለይነው ጸሎት ካልጠበቀን፤ እስቲ ንገሩኝ ስንጸልይ ትርጉም ያልሰጠን ጸሎትማ እንዴት ነው የሚጠብቀን? “ቅሰፈን” እያልነውም እኮ ሊሆን ይችላል። ስለዚህ ከዚህ ዓይነቱ የልተገባ ድርጊት ልንጠበቅ ይገባል።

“አባታችን ሆይ” የምትለዋን ጸሎት በትክክለኛው ከጸለይናት ሁሉ ነገር እዚያ ጋር አብቅቷል፤ ከዚህ “ከአባታችን ሆይ” ጸሎት የሚወጣ ምንም ጸሎት አንጸልይም፤ ከዚህ ውጪ ጸሎት የለምና። ሌላው ጸሎት ሕሊናችን ከእግዚአብሔር ጋር እንዲቆይ የቆይታ ማለማመጃ ነው። ዳዊትንም እዩት፣ ውዳሴ ማርያምንም እዩት፣ ሌላውንም እዩት፤ ከዚህ “ከአባታችን ሆይ” ጸሎት አይወጣም። ለዚህ ነው ባለቤቱ ቅንብብ አድርጎ የሠራልን ። 

አባቶቻችን ስለ “አባታችን ሆይ” ጸሎት ሲናገሩ :- “ቋሚ ፣ ለጓሚ፣ ገረድ ፣ ደንገጡር ፣ በቅሎ ሳቢው፣ እንጨት ለቃሚው ፣ ውኃ ቀጂው መጸለይ አልቻልኩም ብሎ ሰበብ የማይሰጥባት፥ አጭር የሕሊና ጸሎት ሰጠን” ይላሉ። 

አሁን “አባታችን ሆይ” የማይጸልይ ሰው ማማረር አይችልም፤ በሥራ ብዛት ነው ያልጸለይኩት ማለት አይችልም፤ የአንድ ደቂቃ ጸሎት ስለሆነች፤ የጉልበት ሠራተኛም ቢሆን እንኳ ዕቃውን ተሸክሞም መጸለይ ይችላል። የግድ ቆመህ ዳዊት ዘርጋና ጸልይ አይባልም። እንደውም “የአፍአ ያይደለ የውስጥ፣ የከንፈር ያልሆነ የሕሊና ጸሎት ሰጠን” ይላሉ አበው።

እግዚአብሔር እንዴት መስማት እንዳለበት ከመበየናችን በፊት፤ እኛ እንዴት መናገር እንዳለብን ነው ማወቅ ያለብን ። ብዙ ጊዜ ግን እኛ እንዴት እየተናገርን እንደ ሆነ አይደለም የምንፈትሸው፤ የእርሱ አሰማም ላይ ነው ቅሬታ የምናቀርበው። 

እኛ እንዴት መናገር እንዳለብን ካወቅን፤ እርሱ እንዴት መስማት እንዳለበት ጠንቅቆ ያውቃል። 

እኛ እንዴት መለመን እንዳለብን ካወቅን፤ እርሱ እንዴት እና መቼ መስጠት እንዳለበት ያውቃል። 

እኛ እንዴት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብን ካወቅን፤ እርሱ ይቅር ማለትን ያውቅበታል። 

ስለዚህ ከእኛ የሚጠበቀው እንዴት መጸለይ፣ እንዴት መለመን፣ እንዴት ይቅርታ መጠየቅ እንዳለብን ማወቅ ብቻ ነው። ሐዋርያትም ያሉት “እንዴት እንድንጸልይ አስተምረን” ነው:: ሉቃ 11፥1 ይህንን ነው በውስጣችን መያዝ፤ እንደዚያ ከጸለይን ስለሚሰማንና ስለሚመልስልን ወደ ቀቢጸ ተስፋ ውስጥ አንወድቅም።

ጌታ እግዚአብሔር ለጸሎታችን ሁሉ እኛ የምንፈልገውን መልስ መስጠት አይጠበቅበትም፤ ትክክለኛውን መልስ መስጠት እንጂ። አንዳንድ ጊዜ ግን በተስፋ መቁረጥ ተይዘን ከሃሊነቱን ወደ መጠራጠር ስንሄድ የሚሰጠን ነገር የክህደትን ያህል እንደማይጎዳን ሲያውቅ የጠየቅነውን ይሰጠናል። ሥጦታው ግን ፈቃዱ ስላልነበር አንጠቀምበትም። ስለሆነም ልመናችን “ፈቃድህ ይሁን” ቢሆን የበለጠ እናተርፋለን። አባታችን ነውና የሚጠቅመንን አይነሳንም:: ጌታችን “ወይስ ከእናንተ ልጁ ዳቦ ቢለምነው ድንጋይን የሚሰጠው ከእናንተ ማን ነው?፤ ዓሣስ ቢለምነው እባብን ይስጠዋልን? እንኪያስ እናንተ ክፉዎች ስትሆኑ ለልጆቻችሁ መልካም ስጦታ መስጠትን ካወቃችሁ በሰማያት ያለ አባታችሁ ለሚለምኑት እንዴት አብልጦ መልካም ነገርን ይሰጣቸው?” በማለት የሰማዩ አባታችን ስጦታ የተሻለ እንደሆነ ያስረግጥልናል:: ማቴ 7፥9-11 

ይልቁንም ጸሎታችን ከልመና ይልቅ ምስጋና ቢሆን የተሻለ ነው። ልመና ስህተት አያጣውምና፤ በምስጋና ግን ስህተት የለም። ለምኖ “የምትለምኑትን አታውቁም” ከመባል የእርሱን ፈቃድ በምስጋና መቀበል ማትረፊያ ይሆናል።

ጌታ እግዚአብሔርን እንደሚገባው ባለማመስገናችን እንጠየቅም፤ ምክንያቱም አንችልምና። እርሱን እንደሚገባው ለማመስገን እንኳን እኛ ምድራውያን ነቢያትና ሐዋርያት፣ ጻድቃንና ሰማዕታት የሰማይ መላእክትም አይችሉም። በዚህም እግዚአብሔር ቅር ብሎት አያውቅም። ግን ቢያንስ ባለማማረራችን እንኳን ለፈቃዱ ተገዢዎች መሆናችንን ማሳየት ከእኛ ይጠበቃል::

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

8 አስተያየቶች

  1. ይህ ስሜት(ተስፉ መቁረጥ) ትናንት በሰርክ በጉባኤ ላይ ለምዕመናን የተደረገላቸውን ተዓምር ስሰማ ተሰምቶኝ ነበር መቼ ነው ለኔ መልስ የምትሰጠኝ እያልኩ አሁን ግን በሚገባ መልስ ተሰጥቶኛል እንደውም ቀስ እያልኩ እያጣጣምኩት ነው የምፀልየው አልቸኩልም። ቃለ ህይወት ያሰማልን ለመምህራችን ለሚዲያው።

  2. ቃለ ሕይወት ያሰማልን። መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን።

  3. ስለሆነም ልመናችን “ፈቃድህ ይሁን” ቢሆን የበለጠ እናተርፋለን። አባታችን ነውና የሚጠቅመንን አይነሳንም::
    ይልቁንም ጸሎታችን ከልመና ይልቅ ምስጋና ቢሆን የተሻለ ነው። ልመና ስህተት አያጣውምና፤ በምስጋና ግን ስህተት የለም።
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን!

  4. ቃለ ህይወት ያሰማልን ቀሲስ። ቀሲስ እንዲህ ይላሉ “እግዚአብሔር የሚያስተምረን እና የጠራን አስተምሮ ሊቃውንት ሊያደርገን ሳይሆን አምነን ፣እና በህይወት ኖረን የመንግስቱ ወራሾች እንድንሆን ነው።” ለህይወት ይሁነን።

  5. “ፈቃድህ በሰማያት እንደሆነች እንዲሁ በምድር ትሁን”
    ቃለ ህይወትን ያሰማልን መምህር!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *