ደብተራ በአማን ነጸረ ማን ነው? ክፍል-2

ማንኛውንም መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ በመጀመሪያ ባለሁበት ቆሜ ለጸሐፊው አቡነ ዘበሰማያት እደግምለታለሁ

በደብተራ በአማን ነጸረ በጃንደረባው ሠረገላ የቆየው ቆይታ ቀሪ ጊዜ ይኼንን ይመስላል:- 

ጃንደረባው፡- ከአንባብያን ጋራ የተዋወቅህባት የመጀመሪያ ሥራ ወልታ ጽድቅ ነበረች፡፡ ጥንስስና ሒደቱን እስኪ ንገረን?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ከ2000 ዓ.ም. እስከ 2010 ዓ.ም. ባለው ጊዜ የተሐድሶ እንቅስቀሴ በዲጂታሉ ዓለም፣ በተለይ በብሎጎች (መጦመሪያዎች) አይሎ ነበረ፡፡ ከተያዘው ስልት አንዱ በቤተ ክርስቲያን ሊቃውንት መካከል የተለያየ ሐሳብ ተይዞባቸዋል የሚባሉ ርእሶችን መርጦ አንደኛውን የደገፉ መስሎ አንደኛውን ማጥላላት ነበረ፡፡ የደቂቀ እስጢፋኖስና የጥንተ አብሶ ጉዳይ ለዚሁ ተብሎ ይራገባል፡፡ ስለሁለቱም ግንዛቤ አልነበረኝም፡፡ በምሠራበት መሥሪያ ቤት በሕግ ክፍል ኃላፊ ደረጃ የነበረና የተሐድሶዎች እንቅስቃሴ የወራረፈው ሰው ደቂቀ እስጢፋኖስን የተመለከተ የተሐድሶ መጽሔት ይዞ በምንጭነት እየጠቀሰ ቤተ ክርስቲያን ላይ የነቀፋ ቃል ይናገራል፡፡ እንዲህ ማድረጉ በቤተ ክርስቲያን ማደጌን ስለሚያውቅ በተዘዋዋሪ እየሰበከኝ መሆኑ ነው፡፡ ሌላኛው ጓደኛዬ (በእምነት የማይመስለኝ) ደግሞ የደቂቀ እስጢፋኖስን ሶፍት ኮፒ ‹አንብበህ ፍረድ› በሚመስል መልኩ ከሌሎች የሕግ ማጣቀሻ መጻሕፍት ጋራ ቀላቅሎ ሰጠኝ፡፡ አጋጣሚዎች መደጋገማቸው የባዶነት ስሜት ፈጠረብኝ፡፡ የደቂቀ እስጢፋኖስን ንባብ ተያያዝኩት፡፡ 

ተሐድሶዎች የደቂቀ እስጢፋኖስን እንቅስቃሴ ከማርቲን ሉተር ጋራ ማያያዛቸውን ለመተቸት የፕ/ር ጌታቸውን ጽሑፍ መግቢያና ኅዳግ ቸል ብሎ መጽሐፉን ማንበብ በቂዬ ነበረ፡፡ ልቤን በመጠኑ አሳረፍኩት፡፡ ተሐድሶዎች በደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ የሚያነሡት የይገባኛል ጥያቄ በቀላሉ የሚፈርስ እንደሆነ ተረዳሁ፡፡ ችግሩ ግን የደቂቀ እሰጢፋኖስ ታሪክ ከፖለቲካም፣ ከቤተ አይሁድም ከወቅታዊ ብሔረሰባዊ እንቅስቃሴ ጋራም ተሳስሯል፡፡ ስለዚህ እንደ አንድ ኦርቶዶክሳዊ ምዕመን በሃይማኖት ዐይን መታየት አለበት በሚል ተከታታይ ጽሑፎችን በማኅበራዊ ሚዲያው በመጻፍ በሚገኝ ምላሽ ጽሑፉ እየዳበረ ሔደ፡፡ ንባቡን ከተዘማጅ ጥናቶችና ከታተሙት ገድላት በተጨማሪ ያልታተሙትን የገዳሙን ገድላት በበይነ መረብ አፈላልጎ በማንበብ፣ ሌሎች በገዳሙ የተጻፉ ምንጮችን በማገላበጥ፣ እነርሱ ከመነሣታቸው በፊትም ሆነ በተነሡበት ጊዜ የተጻፉ ገድላትን ማንጸሪያ በማድረግ፣ የወንድሞችን አስተያየት በግብዓትነት በመውሰድ የደቂቀ እስጢፋኖስ ጉዳይ ተጠቃለለ፡፡

በሒደቱ አንደኛው ፈተና ከፕ/ር ጌታቸው ጋራ መጋፈጡ ነበረ፡፡ ትርጉሙን ካነበብኩ በኋላ በፕ/ር ጌታቸው ላይ ተቆጥቼ ነበረ፡፡ ‹‹በጉባኤ ያላለፈ ሰው›› የሚል የትምክሕት ቃል እስከ መናገር ድረስ፡፡ እንደዚያም ሆኖ ግን ጸሐፊውን ማወቅ አለብኝ በሚልና መጽሐፋቸው ሌላ ተልእኮ የሌለው ጥናታዊ ጽሑፍ መሆኑን ለማረጋገጥ የታተሙም ሆነ በሶፍት ኮፒ ይገኛሉ የሚባሉ ሥራዎቻቸውን እያፈላለኩ መግዛትና ያልታተመውን ኮፒ አድርጌ ማንበብ ጀመርኩ፡፡ እያነበብኩ ስሔድ በፕ/ር ጌታቸው ላይ የያዝኩት አቋም በተለይም የወጣትነት ትምክሕቴ ለራሴ አሳፈረኝ፡፡ የቁጣ ቃላቶቼን አለዝቤ ከጥንተ አብሶው ጽሑፍ ጋራ ለብርሃኑ አድማስ ላክሁት፡፡ ብርሃኑ የሰጠኝ አስተያየት ወደ 1/3ኛ የሚጠጋውን ይዘት እንደገና እንድከልስ የሚያስገድድ ሆነ፡፡ ያንን አደርገው ይሆናል፡፡ ነገር ግን ብርሃኑ አድማስ እኔ በምጽፈበት ርእስ ከጻፍኩት በላይ እንደሚያውቅ ገባኝ፡፡ ይህም ‹‹በዚህ ርእስ ለምን እርሱ አይጽፍም? እርሱ እያለ በዚህ ጉዳይ የእኔ መጻፍ ጥቅሙ ምንድን ነው?›› የሚል መታወክ ውስጥ ከተተኝ፡፡ አበረታቶኛል’ኮ! ግን አልተዋጠልኝም፡፡ ሙልጭ አድርጎ አርሞና በየመስመሩ አስምሮ ሲያበቃ መልሶ ያበረታታኛል፡፡ አንድ ጊዜ ስለጀመርኩት የግዴን ቀጠልኩበት፡፡

ጥንተ አብሶን በሚመለከት በርእሱ ዙሪያ የምጠይቃቸው ሰዎች የዐውደ ምሕረት ስብከትና ለብቻ ስጠይቅ የሚሰጡኝ መልስ አለመመሳሰል እንደማስጨነቅ ብሎኝ የገባሁበት ርእስ ነው፡፡ በአደባባይ ‹‹የለባትም›› ይላሉ፣ ለየብቻ ስጠይቅ ይላሉብኛል፣ ይወላውሉብኛል፡፡ እቤት ያገኛኋቸውን ምንጮች ሳገላብጥ ደግሞ ርእሱ መካሰሻ ብቻ ሆኖ ታየኝ፡፡ ዋናውን ርእስ አድምቶ ከማቅረብ ይልቅ አንዱ ሌላውን ሲከስ አጃቢ እየሆነ ከክስ ዝርዝሮች እንደ አንዱ እየሆነ ይቀርባል፡፡ ለክሱ መልስ ሲሰጥ ቀደምት ሊቃውንት፣ ሃይማኖተ አበው፣ ቅዱስ ያሬድ፣ የኮፕቶችና የምሥራቃውያን አቋም እየተጠቀሰ ከሳሾችን አላዋቂዎች አድርጎ ማቅረብ ይታያል፡፡ በልምድ እንዳየሁት በውጭ ሀገር ቲዎሎጂ የተማሩት የቤተ ክርሰቲያን ልጆች እመቤታችን እንደ ማንኛውም ሰው አበሳ ነበረባት ነገር ግን በቅዱስ ገብርኤል ብሥራት ‹‹መንፈስ ቅዱስ ወደ አንቺ ይመጣል የልዑል ኃልም ይጸልልሻል›› ስትባል ነጽታለች ይላሉ፡፡ ነባሩ የቤተ ክርስቲያን ትውፊት ይኽንን አይቀበልም፡፡ 

ከወልታ ጽድቅ መውጣት በኋላ ያነበብኩት የሳሙኤል ጎባት የጉዞ ማስታወሻ ላይም በጥንተ አብሶ ጉዳይ ከፕሮቴስታንቶች ጋራ ንግግር ተደርጎ በሔራውያን ሊቃውንት እመቤታችን ከጥንተ አብሶ ነጻ እንደሆነች እንደሚያምኑ መናገራቸውን ተገንዝቤያለሁ፡፡ ቤተ ክርስቲያን በይፋ እመቤታችን ከጥንተ አብሶ ነጻ ናት ብላ ታምናለች፡፡ ውስጥ ለውስጥ ግን የሚታዩ፣ ሆኖም የማይገለጡ ልዩነቶች አሉ፡፡ እኔ ያደረግሁት እነዚህ የልዩነት ሐሳቦች በምን በምን ጥያቄዎች ዙሪያ እንደሚያተኩሩ፣ መነሻውን፣ ዋና ዋና ጥቅሶችን፣ በየአብያተ ክርስቲያናቱ ያለውን የጎላ አመለካከት በመንቀስ መነሻ ማስቀመጥ ነው፡፡

ጃንደረባው፡- የፕ/ር ጌታቸውን መጽሐፍ መነሻ አድርጎ የተጻፈው ወልታ ጽድቅ ከደቂቀ እስጢፋኖስ አንጻር ግቡን መትቷል?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- እንዳነበብኩት በቤተ ክርስቲያናችን ሁለት የመነኮሳት ቤቶችና ሦስት ዐበይት የመነኮሳት እንቅስቃሴዎች ተመዝግበዋል፡፡ ቤተ ተክለ ሃይማኖትና ቤተ ኤዎስጣቴዎስ ሁለቱ ቤቶች ናቸው፡፡ በእንቅስቃሴ ደረጃ ቤተ ተክለ ሃይማኖት፣ ቤተ ኤዎስጣጤዎስና ደቂቀ እስጢፋኖስ ይጠራሉ፡፡ በደቂቀ እስጢፋኖስ ጎላ እንጂ ‹‹ደቂቀ እከሌ›› እየተባሉ መጠራት በሁለቱም ቤቶች አለ፡፡ ደቂቀ እስጢፋኖስ በቤት ረገድ ከቤተ ተክለ ሃይማኖት የተነሣ እንቅስቃሴ ነው፡፡ እንቅስቃሴው መነሻው ላይ አፈንጋጭ ሐሳቦች ያሉበት መሆኑ እንደ ተጠበቀ ሆኖ በሌሎች ጥያቄዎች ዙሪያ ከሁለቱ ቤቶች ያን ያህል የተለየ አልነበረም፡፡ በመካከለኛው ዘመን የተነሡት ሁለቱም ቤቶች አምስት ዋና ዋና ጥያቄዎችን ማንሣታቸው የተለመደ ነው፡፡ እነርሱም፡- (1)ገዳማዊ ነጻነት ይከበር፣ (2)የቤተ ክህነትና ቤተ መንግሥት ግንኙነት ይስተካከል፣ (3)ንጉሥ እንደ ማንኛውም ክርስቲያን ለቤተ ክርስቲያን ሕግ ይገዛ፣ (4)መሬት የእግዚአብሔር እንጂ የንጉሥ አይደለም፣ (5) በዓላትን መደንገግ የቤተ ክርስቲያን እንጂ የንጉሥ ሥልጣን አይደለም የሚሉ ናቸው፡፡ ከጸጋ ስግደት ጋራ ተያይዞ ከተነሣው በቀር የደቂቀ እስጢፋኖስ ጥያቄዎች ከዚህ የወጡ አይደሉም፡፡ ስለዚህ በዘመኑ በነበሩት ከነገሥታቱ የተጋጩ ቅዱሳን እንደ አባ ፊልጶስ ዘደብረ ሊባኖስ፣ ገድለ አባ ተክለ ሐዋርያት፣ ገድለ ኤዎስጣቴዎስ፣ ገድለ አኖሬዎስ፣ ገድለ ቀውስጦስ እየተናበቡ ሊጠኑ ይገባል ብዬ አምናለሁ፡፡ ያደረግሁትም እርሱን ነው፡፡

ከግብ አንጻር የመጀመሪያ እቅዴ ደቂቀ እስጢፋኖስ ከማርቲን ሉተር ጋራ እየተነጻጸሩ ባልዋሉበት መንገድ እንዳይጠሩ በራሴ የተረዳሁትን (ይኽንን ዲ/ን ያረጋል ቀድሞ በመድሎተ ጽድቅ ቅጽ አንድ ጠቅሶታል) በአጽንኦት ማሳወቅ ነበረ፡፡ የተሳካ ይመስለኛል፡፡ ቢያንስ ከተሐድሶዎችም ዘንድ ‹‹ምንም እንኳ አባ እስጢፋኖስና ሉተር ሙሉ ለሙሉ ተመሳሳይ ሐሳብ አንሥተዋል ባይባልም …›› የሚል ሐረግ የመጠቀም አዝማሚያ አይቻለሁ፡፡ ከቤታችን ውጪም ወልታ ጽድቅ በተሐድሶዎችና በፕሮቴስታንት አንባብያንም ዘንድ ከተወሰነ ተዐቅቦ ጋራ መነበቧን ታዝቤያለሁ፡፡ ወልታ ጽድቅን ጨምሮ ሦስቱንም መጻሕፍት ያነበቡ ካቶሊካዊ አባት ጽሑፎቹን አበረታተው ዕቅበተ እምነት ቢበቃህና ወደ ጥናቱ ደግሞ ብታተኩር ብለውኛል፡፡ በማበኅራዊ ሚዲያም ወልታ ጽቅን በማስተጋባት ብዙ ስለተጯጯኽን የደቂቀ እስጢፋኖስ ታሪክ በአንድ ቦይ እንዳይፈስ አድርገናል ብዬ አምናለሁ፡፡ 

ፕ/ር ጌታቸውም ደቂቀ እሰጢፋኖስን በዘመኑ ከሚራመደው ማርቲን ሉተርን የሚናፍቅ የተሐድሶ እንቅስቃሴ በማራቅ ማስተባበያ አውጥተዋል፡፡ ማስተባበያው በዚያው በደቂቀ እስጢፋኖስ መጽሐፍ እንዲወጣ ቢታሰብም ኮፒ ራይቱ ለአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ስለተሰጠ ለማካተት ባለመቻሉ ረቂቁን ለእኔና ለብርሃኑ አድማስ ልከውልን ‹‹አንዳፍታ ላውጋችሁ›› ከተሰኘው ግለ ታሪካቸው ጋራ ወጥቷል፡፡ ማስተባበያውን ያወጡት በእኔ ብቻ ሳይሆን ከብርሃኑ አድማስ ጋራም ዘለግ ያለ ውይይትና ምናልባትም ክርክር አካሒደው ይመስለኛል፡፡ ቅሬታችንን ለፕ/ር ጌታቸው መነገር ባለበት መንገድ ነግረን የመደመጥና የመነበብ ዕድል ማግኘትም አንድ ትልቅ ግብ እንደሆነ ይሰማኛል፡፡ ምላሻቸውን በአንዳንድ ነጥቦች ባልረካበትም በአዎንታ እመለከተዋለሁ፡፡

ጃንደረባው፡- ከወልታ ጽድቅ በኋላ ስለታተሙት ጽንዐ ተዋሕዶና ተኀሥሦ ጥቂት ማለት ይቻል ይሆን?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ጽንዐ ተዋሕዶ ረዘም ያለ ጊዜ የወሰደ ማዕከሉን ነገረ ክርስቶስ ያደረገ መጽሐፍ ነው፡፡ ከነገረ ክርስቶስ ጋራ በተያያዘ በኢትዮጵያ የተካሔዱ ጉባኤያት፣ ክርክሮችና ኃይል የተቀላቀለባቸው ጠቦች፣ ቅኔያት፣ ምዕላዳትና ለጉዳዩ ተገቢነት ያላቸው የውጪና ያገር ውስጥ ምንጮች ሰፋ ባለ ልብ ተዳስሰውበታል፡፡ ከእኔ ሐተታ ይልቅ መጻሕፍቱ እንዲናገሩ በመመኘት በርከት ያሉ ሊቃውንትን ምንጭ አድርጌ ያቀረብኩበት ሥራ ነው፡፡ ገጹ እንዲበዛ ባልፈልግም ምንጮቹ ስለበዙ ካሰበኩት በላይ ሆነ፡፡

ወደ ይዘቱ ስንመጣ በሐዋርያውያን አበው ዘንድ ስለ ነገረ ድኅነት ሲነገር ቀራንዮ ላይ የሆነልን ብቻ ሳይሆን ቃል ሥጋ ሆነ ማለትን የሚተነተንበት ምሥጢረ ሥጋዌም በተለየ ትኩረት ይጠናል፡፡ የቅዱስ አትናቴዎስ ዐቢይ ሥራ በሃይማኖተ አበውና በድርሳነ ቄርሎስ ‹‹በእንተ ሥጋዌ ቃል /On the Incarnation/›› እየተባለ የሚጠቀሰው ትምህርቱ ነው፡፡ ቃል ሥጋ ሆነ ስንል በርካታ ምሥጢሮች በአንድ ጊዜ ተፈጽመዋል፡፡ እመቤታችን ለመልአኩ ብሥራት እንደ ቃልህ ይሁን ባለች ጊዜ ያለጊዜ ልዩነት፡- አካላዊ ቃል ከሥጋዋ ሥጋን ነሥቶ ፍጹም ባሕርያዊ ተዋሕዶን ተዋሕዷል፣ በተዋሕዶው ሥጋ አምላክነትን ገንዘብ አድርጓል፡፡ ባሕርያዊ (natural) ስንል ተዋሕዶው የጸጋ ወይም የሹመት ወይም ደግሞ ከውጭ በሌላ አካል የተሰጠ አለመሆኑን ያሳያል፡፡ ቅዱስ ሳዊሮስ ዘአንጾኪያ፡- መከፈል፣ መዋሕድና መክበር አንድ ጊዜ ተከናወኑ ይላል፡፡ ያ ባሕርያዊ ተዋሕዶ ቃል ለነሣው ሥጋ የባሕርይ አምላክነትን፣ ለእኛ ደግሞ አምላክ ዘበጸጋ መሰኘትን አስገኝቶልናል፡፡ በአዳም በደል የጠፋ ማንነታችን ባሕርያችንን ባሕርዩ ባደረገው ክርስቶስ ተመልሶልናል፣ ፍጹም ሰው በሆነው ፍጹም አምላክ መካከለኛነት ዳግም ከእግዚብሔር ጋራ ታርቀናል፡፡ የመካከለኛነት ዋና ጭብጡ በነገረ ሥጋዌ ክርስቶስ ፍጹም ሰው የሆነ ፍጹም አምላክ (አምላክ ወሰብእ) መሆኑን ማስረገጥ ነው፡፡

በሀገራችን የነበሩ የነገረ ክርስቶስ ክርክሮች ልዩነት ለሥጋዌው ትኩረት ካለመስጠት የመጣ አይደለም፡፡ ትኩረት ይሰጣሉ፡፡ ነገር ግን ሥጋ /ትስብእት/ አምላክነትን ገንዘብ ያደረገ በሌላ አነጋር የከበረ እንዴት ነው? የሚለው ጥያቄ ብዙ አፋጅቷቸዋል፡፡ የሚጠቀሙት ጥቅስ መመሳሰልና ቀደምት ሊቃውንቱንም እንደ ጋራ አባቶቻቸው መጠቀማቸው ጠቡን የዘመድ ጠብ አድርጎ አካርሮታል፡፡ በእኔ እምነት የነገረ ክርስቶስ ክርክሮች በየስልቱ ኩነታዊ/ውስጣዊ (Ontological Christology) እና ገብር ተኮር/ውጫዊ (Functional Christology) ተብለው ቢተነተኑ፣ በምሥጢረ ሥላሴም ስለግብር በምንናገር ጊዜ ውስጣዊ (Immanent Trinity)ና ውጫዊ ግብር (Economic Trinity) በሚል የቅርብ ጊዜ የጉባኤ መምህራን ጸሐፊዎች እያደረጉት እንዳሉት ተተንትኖ ቢቀርብ ነገሩን ብሩህ ያደርገዋል ብዬ አምናለሁ፡፡

ብዙ ያጨቃጨቀን ‹‹ተቀብዐ›› የሚል ቃል ቅብዓቶች እንደሚሉት ትስብእት በተዋሕዶ ያላገኘውን የባሕርይ አምላክነት በመንፈስ ቅዱስ ከአብ ተቀብቶ አገኘው (በቅብዓት ወልደ ባሕርይ) ማለት ሳይሆን ሥጋ ለብሶ የፈጸመውን የማዳን ሥራ /ተልእኮ/፣ ፍጹም ሰውነቱን፣ ፍጹም ተዋሕዶውን (ጽንዐ ተዋሕዶን) የሚያመለክት፣ ለግብር ተኮር ነገረ ክርስቶስ እየተሰጠ ከፅንሰቱ እስከ እርገቱ እንደየአውዱ የሚተረጐም ንባብ ነው፡፡ 

በወንጌሉም ሆነ በሐዋርያት ሥራ ተቀብዐ የሚለውን ግስ ደጋግሞ የሚጽፈው ቅዱስ ሉቃስም ከኩነት ይልቅ ለግብር ተኮር ይልቁንም ፈረንጆቹ የክርስቶስ ፍጹም ሰውነት ላይ ያተኮረ (Low Christology) ለሚሉት ዓይነት ነገረ ክርስቶስ ትኩረት ይሰጣል የሚባል ወንጌላዊ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ ወንጌላዊን በአንጻሩ የቃል ዘለዓለማዊነት (Pre-existence of Word)ና ፍጹም አምላክነት (High Christology) ላይ ያተኮረ ነገረ ክርስቶሳዊ ይዘት አለው ይሉታል፡፡ 

ቅብዓቶች ግን የተቀብዐን ንባብ ከያለበት አሰባስበው በማጨቅ ወደ ኩነት ማለትም ትስብእት አምላክነትን ለማግኘት የመንፈስ ቅዱስን ቅብዕነት/አክባሪነት የሚሻበት አድርገው ያቀርቡታል፡፡ ጸጎች ቅብዓቱ ለትስብእት ሳይሆን ለቃል የተነገረ የሹመት ንባብ ነው ይላሉ፡፡ ይህም በተዋሕዶ ከሆነው ክብር በቀር አፍአዊ ክብርን አይሻም ከሚለው ቄርሎሳዊ አስተምህሮ ጋራ አይሔድም፡፡ ጸጎች ነባርና ሐዲስ ተብለው ሊከፈሉ የሚችሉ ናቸው፡፡ አዳዲሶቹ ደፍረው ሁለት ባሕርይ፣ ሁለት ግብር እስከማለት ይጓዛሉ፡፡ አስቀድሜ እንዳልኩት በተዋሕዶ በማኅፀነ ድንግል የዕለት ፅንስ መሆን፣ የቃል ከሥጋ መዋሐድና መክበር ያለ ጊዜ ልዩነት እንደ ዐይን መከፈትና ማየት በአንድ (ቅፅበታዊ) ቋንቋ የሚነገሩ ምሥጢራት ናቸው፡፡ ተዋሕዶ የሚለው የግእዝ ቃል ገላጭነት በውጭ ሀገር የነገረ መለኮት ጸሐፍትም ዘንድ ተከብሮ በቁሙ የሚወሰድ ቃል ነው፡፡

በክርስቶስ የማዳን ሥራ የሦስቱ አካላት አንድ ፈቃድ አለ፣ ይህም ውጫዊ ግብር የሚባለው ነው፣ ስለዚህ ቀባው ወይም ቅብዓት ሆነው የሚሉ ቃላት በንባብ ለአንዱ ተሰጥተው (by appropriation) ቢነገሩ እንኳ በውጫዊ ግብር ሦስቱም በአንድነት በአንዲት ባሕርያዊ ግብር የሚፈጽሟቸው ናቸው፡፡ በዚህ አንጻር በነገረ ክርስቶስ ስለ መንፈስ ቅዱስ የተነገሩ ምንባባትን በውጫዊ ግብር ማለትም ሦስቱም አካላት እንደሚተባበሩባቸው ምንባባት ካለመውሰድ፣ አንዳንድ ዐውዶችንም (ለምሳሌ ሮሜ.1፡4) ‹‹መንፈስ›› የሚለው ቃል መለኮት ተብሎም እንደሚተረጐም ካለማስተዋል፣ ተቀብዐ የሚለው ተምሳሌታዊ አነጋገር በማኅፀን ብቻ ሳይሆን በተልእኮውና በትንሣኤው፣ በነገረ ክርስቶስ ብቻ ሳይሆን በምሥጢረ ሥላሴና በነገረ መንፈስ ቅዱስም በልዩ ልዩ መንገድና በየዘመናቱ እንደ ተነሡ ተቃዋሚዎች ጥያቄ በየዐውዱ መነገሩን ካለማስተዋል፣ ይልቁንስ ደረቁን ንባብ ከየተነገረበት ዐውድ በማውጣት ብቻውን አቁሞ በግሳዊ ዘይቤ ብቻ በመቀነን (dogmatizating the term)፣ በያሰኝብሃል አንዱ ለሌላው የራሱን ሐሳብ ፈጥሮ ሌላው ላይ በመጫን (false attribution) ፈሊጥ በጎደለው መንገድ ብዙ ጉልበት እንደባከነ አምናለሁ፡፡ 

አሁንም እየባከነ ነው፡፡ የተቻለኝን ያህል ከሙግታዊው ውርስ ወጥቼ ቃሉ በየዘመናቱ የተነገረበትን ነገረ መለኮታዊ ዐውድ ለማሳየት የሞከርኩት ለዚህ ነው፡፡ አቀራረቡ በተካራካሪነት መንፈስ ሳይሆን በኀሠሣ መንገድ ነበረ፡፡ ግን ያም ደግሞ ቅን ያልሆነ አንባቢ ካለ አላግባብ ለመጠቀስ ያጋልጣል፡፡ እኔም ካቀረብኩት ውስጥ ለራሳቸው የመረጡትን ብቻ በመውሰድ ከዐውዱ የወጣ ንባብን ሲፈልጉ እኔን ጠቅሰው፣ አንዳንዴ ጠቃሹን (እኔን) አልፈው ጥቅሶቹን እንደ ራሳቸው አዲስ ግኝት አድርገው የሚያቀርቡ ሰዎች ገጥመውኝ አዝኛለሁ፡፡ በኢትዮጵያ ነገረ ክርስቶስ የተነሡ ዋና ዋና ጭብጦችን ከነታሪካቸው ለማወቅ መጠነኛ ፍንጭ የሚፈልግ ሰው ካለ አሁንም መጽሐፉን እንዲያነብ፣ ከበረታ ያጣቀስኳቸውን ሰዎች ሥራዎች እንዲመለከት፣ ሙሉ መጽሐፉን ማንበብ የሚደክመው ካለም ምዕራፍ ሰባትን ብቻ አንብቦ ቀሪውን በቀጠሮ እንዲያሳድር እመክራለሁ፡፡ ተኀሥሦ ከእኛ ቤተ ክርስቲያን ውጪ ስላሉ ሰዎች የጻፍኳቸው ጽሑፎች በፌስቡክ እንደ ጥላቻ ንግግር ተቈጥረው ስላስቀጡኝ በግዳጅ ወደ ኅትመት ተሰደው የመጡ ስዱዳን ስበስብ ናት፡፡

ጃንደረባው፡- እንደ ጸሐፊ የዚህን ዘመን አንባቢው እንዴት ታየዋለህ? ምንስ ትመክራለህ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ጸሐፊ የሚለው ይቆይ፡፡ ልቤ አይቀበለውም፡፡ እንደ አንባቢም ለመምከር የሚያስችል ቁመና ላይ አይደለሁም፡፡ ተመክሮዬ ከጠቀመ ልናገር፡፡ ከጊዜ ወዲህ የመጽሐፍ መወደድና የኑሮ ሁኔታ ቢያናጥበኝም ላለፉት 11 ዓመታት በየወሩ ከደመወዜ ለመጽሐፍ ብዬ ወርኃዊ ወጪ ከ100-500 እየመደብኩ ስገዛ ቆይቻለሁ፡፡ ስገዛ ማውጫውንና ማጣቀሻዎቹን እንዲሁም ገልበጥ ገልበጥ በማድረግ ይዘቱን አያለሁ፡፡ ይዘቱ ካሉኝ መጻሕፍት የተለየ መሆኑን ስረዳ እገዛለሁ፡፡ 

የገዛሁትን መጽሐፍ የግድ አንብቦ የመጨረስ ግዴታ ራሴ ላይ ጥያለሁ፡፡ መደርደሪያዬ ላይ ያላነበብኩት መጽሐፍ ሲኖር የጥፋተኝነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ ሳነብ የዜማ ተማሪዎች ‹‹ማመልከት›› እንደሚሉት እያመለክትኩ ነው የማነበው፡፡ በእርሳስ ምልክት አደርጋለሁ፡፡ መጽሐፉ የተውሶ ከሆነ እላዩ ላይ ማመልከት (መጻፍ) ስለማልችል ፎቶ እያነሣሁ እይዛለሁ፡፡ መጽሐፉን ስጨርስ የተመለከቱትን ቃላት ለቅሜ በደብተር እገለብጣለሁ፡፡ ሶፍት ኮፒ ከሆነ ስክሪን ሾት እያደረግሁ መጨረሻ ላይ የተመረጡትን ገጾች ፕሪንት አደርጋለሁ፡፡ ተመሳሳይ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት ኮምፒተር ላይ የየራሳቸው ፎልደር አሰናድቼ አስቀምጣለሁ፡፡ የመስክ ሥራ ስወጣም ሆነ የትም ቦታ ስሔድ እንደ ሠርግና ልቅሶ ዓይነት ለንባብ የማይመች ሥፍራ ካልሆነ በቀር የሚኖረኝን ክፍት ጊዜ ለመጠቀም መጽሐፍ እይዛለሁ፡፡ 

ስለ አንድ የተለየ ርእስ ለመጻፍ ወይም ለማወቅ ካሰብኩ አንድን መጽሐፍ ደጋግሜ አነባለሁ፡፡ ሃይማኖተ አበውን፣ መድሎተ አሚንን፣ መጽሐፈ ምሥጢርን፣ የቤተ ክርስቲያን ታሪክ በዓለም መድረክን የመሳሰሉ መጻሕፍትን አንድ ጊዜ ተነበው እንደሚያልቁ መጻሕፍት አላያቸውም፡፡ ደጋግሜ በዝግታ አነባቸዋለሁ፡፡ እንደገና ከዚህ በፊት የያዝኩትን ማስታወሻ ትቼ በአዲስ መንፈስ አነባቸዋለሁ፡፡ የዶግማ ይዘት ያላቸውን መጻሕፍት አንድ ጊዜ መዝለቅን አንብቦ ከመጨረስ አልቈጥረውም፡፡ የዶግማ መጻሕፍትን ያህል ባይሆንም የታሪክ መጻሕፍትንም በማስታወሻ በመታገዝ አነባለሁ፡፡ ለማወቅ ፈልጌ በከበደኝና በታወክሁበት ርእስ ዙሪያ ላነብ የምፈልጋቸውን መጻሕፍት ለፍልሰታ ቀጠሮ አስይዛለሁ፡፡ የፍልሰታን ምንባብ ለአንድ ርእስ ወይም ለአንድ መጽሐፍ የመስጠት ልምድ አለኝ፡፡ እንደ ብፅዓት (ስለት) ነው፡፡

በንባብ ራሴን በመንፈሳዊው ብቻ አልገድብም፡፡ በጊዜ ሒደት እየቀነስኩ ቢሆንም ከሙያዬ፣ ከአገራዊ ፖለቲካና ታሪክ ጋራ የተያያዙ መጻሕፍትን እንዲሁም የጥበብ ውጤቶችንና ሚዲያዎችን እከታተላለሁ፡፡ 

በዓለም እስከኖርኩ ድረስ የተቻለኝን ያህል ዓለምን ማወቅ አለብኝ፣ ዓለምን ማወቅ ማለት ግን ዓለም የሆነውን ሁሉ መሆን አይደለም ብዬ አምናለሁ፡፡ ዓለማውያን ተቋማትና አደረጃጀቶች ቤተ ክርስቲያንን እንዴት እንደሚያዩዋት ለማወቅና ለማረም የምንችለውም ከዚያ በኩል የሚጻፍና የሚነገረውንም ስናውቅ ነውና፡፡

ጃንደረባው፡- የዚህን ዘመን አንባቢ እንዴት ታየዋለህ? ምንስ ትመክራለህ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- እይታዬ አዎንታዊ ነው፡፡ የእኛ ትውልድ የራሱ ሸክም ያለበት ነውና በርኅራኄና በበጎነት አየዋለሁ፡፡ ወላጆቻችን ያለፉበት ዘመን ለመንፈሳዊ ሕይወት ምቹ አልነበረም፡፡ መንፈሳውያን መጻሕፍት በ1960ዎቹ በመጠኑ ብቅ ብለው ድርግም ካሉበትና ከተደበቁበት በዚህ ትውልድ ነው ያንሰራሩት፡፡ ለዚህም ማኅበረ ቅዱሳንና ሰንበት ት/ቤቶች ትልቅ ድርሻ እንደተወጡ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን የመንፈሳውያን መጻሕፍት ዋነኛ መዳረሻ የሆነው ሰሜን ኢትዮጵያ በጦርነት መጠመድ፣ በወረቀትና ተያያዥ የኅትመት ውጤቶች መወደድ የተነሣ የመጻሕፍት ገበያ መናር፣ የማኅበራዊ መዲያው ጊዜን መሻማት ገዝቶ ለማንበብ ያለውን ተነሳሽነት ወደ ኋላ እየመለሱት ይመስለኛል፡፡ ከ2013 ዓ.ም. ወዲህ የኅትመት ገበያው መታወኩን ታዝቤያለሁ፡፡

በይዘት ረገድ መደበላለቆች አሉ፡፡ የምዕመኑን ቅንነትና ብሔራዊ ቁጭትን ለመበዝበዝ በሚመስል መልኩ የፈውስ፣ ሚቶሎጂን ከታሪክና ልብለወለድ ያስተሳሰሩ ሥራዎች፣ ኅቡዓት የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን የጥበብና የምርምር መጻሕፍት አስመስለው ወቅት እየጠበቁ በቤተ ክርስቲያን በመታከክ ወደ ገበያ የሚመጡ ሥራዎች አሉ፡፡ 

የእነዚህ ኅትመቶች የማይናቅ ተቀባይነት ማግኘት የቤተ ክርስቲያንን ምስል የማጠየምና አስተምህሮዋንም የመበረዝ ውጤት እንዳይኖራቸው ያሰጋል፡፡ አንባቢው በዚህ ረገድ ማጣቀሻ ከሌላቸው ሥራዎች ራሱን ቢጠብቅ እመኛለሁ፡፡

በንባብ ውስጥ ጸሐፊ፣ ጽሑፍና አንባቢ አለ ብለናል፡፡ አንባቢ የምንለው ክፍል በስፋት ብቻ ሳይሆን በእይታም ይሰፋል፡፡ አንድን ጽሑፍ ጸሐፊው ካየበት አድማስ በላይ የማየት አቅም አለው፡፡ አንባቢው ጸሐፊውን በማረቅ፣ በማትጋት፣ በማረም፣ በመገሠጽ ድርሻ አለው፡፡ ጸሐፊውን እንደ ፍጹም ማየት የለብንም፣ ድክመት ሲኖር በጥንቃቄ እንዳይሰበር አድርጎ ማቅናት ያስፈልጋል፡፡ አንዲት ሕፀፅን ከመላው ንባብ ፈልቀቆ ማጠየም እናያለን፡፡ ያርማሉ የተባሉት ወገኖች የሚነቅሉ ሆነው የሚገኙበት ጊዜ አለ፡፡ እንደታዘብኩት መጽሐፍ ማሳተም የትሩፋት ሥራነቱ ያይላል፡፡ ለጥቂት ሰዎች ካልሆነ በቀር የሚያስገኘው የገንዘብ ጥቅም በሌላ መስክ ተሠርቶ ከሚገኘው ገንዘብ አንጻር የሚያበረታታ አይደለም፡፡ ጸሐፍያንን በተለይም መንፈሳውያን መጻሕፍትን የሚጽፉ ወንድም እኅቶችን እንደ ነጋዴ ማየት ደስ አይለም፡፡ እንደ አገልግሎት ነው መታየት ያለበት፡፡

አንባቢው በንባብ አድማስ መስፋት ይገባዋል፡፡ የኛ አንባቢ ወደ ታሪክና ዕቅበተ እምነት ያደላ ይመስለኛል፡፡ የኦርቶዶክሳዊ ቤተሰብ፣ ኦርቶዶክሳዊ የገንዘብ አጠቃቀም፣ ኦርቶዶክሳዊ አመራር፣ ኦርቶዶክሳዊነትና ፖለቲካ፣ ኦርቶዶክሳዊነትና በጎ አድራጎት፣ ኦርቶዶክሳዊነትና ባሕላዊ ማንነት፣ ኦርቶዶክሳዊነት በ21ኛው ክፍለ ዘመን፣ ኦርቶዶክሳዊነትና ሚዲያ፣ ወዘተ. እየተባለ ዘርፉን ሁሉ የሚቀድስ ጸሐፊ እንዲወጣ አንባቢውም መስፋት አለበት፡፡ የነገረ መለኮት ምሁራንና የአብነት መምህራን ሚና በአንባቢነትና በቅን ኀያሢነት ላይም ሊታይ ይገባል፡፡ መደበኛው ካህን በንባብ ላይ ያለው ሱታፌ የሚያስመካ አይደለም፡፡ ዋነኛው አንባቢ ማኅበረ ቅዱሳንና ሰንበት ት/ቤቶች የፈጠሩት ትውልድ ሆኖ ነው የሚታየኝ፡፡

በግሌ ማንኛውንም መጽሐፍ አንብቤ ስጨርስ በመጀመሪያ ባለሁበት ቆሜ ለጸሐፊው አቡነ ዘበሰማያት እደግምለታለሁ፡፡ ቦታው ካልተመቸኝ የመጨረሻዋን ገጽ ሳልጨርስ አቆይና ለአቡነ ዘበሰማያት መድገሜያ ምቹ ቦታ ሳገኝ ጨርሼ አቡነ እላለሁ፡፡ ለማንኛውም ጸሐፊ የማደርገው ነው፡፡ መጽሐፉ መበረታታት አለበት፣ ወይም ጸሐፊው ወደፊትም መጻፍ ይገበዋል ብዬ ሳስብ የተቻለኝን ያህል በማኅበራዊ ሚዲያ ስሜቴን አጋባለሁ፡፡ ሌሎች አንባብያን ይኽንን ቢያደርጉ እወዳለሁ፡፡ በፊት ጥንካሬውን ብቻ ሳይሆን ቢታረም የምለውንም በቅንነት ለመጠቆም እሞክር ነበር፡፡ ነገር ግን ቢታረም ያልኩትን እንደ ሕፀፅ ቈጥረው ጸሐፍያንን የሚነቅፉ ሰዎች ስለገጠሙኝ መታረም አለበት የምለውን ለጸሐፊው ለብቻ መንገርን ወደመምረጡ አዘንብያለሁ፡፡

ጃንደረባው፡- ከጸሐፊነትህ ባሻገር በኀያሲነትና በአርታዒነትም በብዙ መጻሕፍት ላይ የመግቢያ ጽሑፎችና የጀርባ አስተያየት ትሰጣለህ፡፡ በዚህ ሥራህ ወቅት ምን ታዘብክ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ሁሉንም አይደለሁም፡፡ ረቂቅ ጽሑፍ ለሚልኩልኝ ሰዎችም እናገራለሁ፡፡ አስተያየቴ ከአንባብያን እንደ አንዱ ብቻ እንዲወሰድ አስጠነቅቃለሁ፡፡ አርታዒነትና ኀያሲነት ሙያዊ ተግባር ስለሆነ፡፡ በጎውን ትቼ ቢታረም የምለውን ትዝብቴን ለማካፈል ያህል ጸሐፍቱን ከአብነት ጉባኤ የወጡ፣ የነገረ መለኮት ምሩቃንና ከሁለቱም ያልሆንን ብዬ በሦስት ልለያቸው፡፡ ከጉባኤ ቤት በሚወጡ ጸሐፍት ዘንድ በተወሰነ ደረጃ በተመሳሳይ ርእስ ላይ ተደጋጋሚ ጽሑፍ ማዘጋጀት ማለትም የርእስና የይዘት መደጋገም፣ ከሚገባው በላይ ከአንድ ሰው ሥራ ላይ ወስዶ ለደራሲው ዕውቅና አለመስጠት፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኅትመት መስፋፋት ምክንያት እንደ ቀድሞው ጉባኤ ጽፎና ደጉሶ መመረቅን ስለማያስገድድ ለመልክዐ ፊደል አለመጠንቀቅና የአጻጻፍ ሥርዓትን አለመጠበቅ፣ በበቂ ተዛማጅ ንባብ ሳያጎለብቱ በጉባኤ በያዙት ልክ ብቻ ወደ ኅትመት መምጣት፣ ለርእስ ታማኝ አለመሆን፣ ታሪክን እንደ ዶግማ አድርጎ መያዝ፣ በተወሰነ መልኩም አስተያየቶችን እንደ ነቀፋ ማየት፣ በጉባኤ ቤት የሚሰጠውን የትርጓሜ ትምህርት እንደ መጨረሻና ብቸኛ ዕውቀት በማየት ወደ አማርኛ ለተመለሱ የቀደምት ሊቃውንት ትርጓሜያት ቦታ አለመስጠትና እንደ ሥርዋጽ በመመልከት እይታን ማጥበብ ያጋጥማል፡፡ እንደዚያም ሆኖ በርካታ ወጣት የአብነት መምህራን እየመጡ በመሆኑ ችግሩ በመቀረፍ ላይ እንደሆነ አስባለሁ፡፡

የነገረ መለኮት ሰዎች ዋና ችግር እንደሚጠበቀው አለመጻፋቸው ነው፡፡ ለጻፉት ክብር አለኝ፡፡ በዚያ በኩል የሚሰማኝ የውጪ ጽሑፎችን ከይዘትና ከቋንቋ አጠቃቀም አንጻር ከኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ማስማማት ላይ ጥረት ማነሱ ነው፡፡  በተለይ የምሥራቅ ኦርቶዶክሳውያን ምንጮች አጠቃቀም ላይ የተወሰኑ ጥንቃቄዎች ያስፈልጋሉ፡፡ የነገረ ድኅነት መሠረታውያንና ትውፊት ላይ ጸሐፊዎቻቸው (የምሥራቆቹ) ብርቱዎች ናቸው፡፡ ከነገረ ክርስቶስ አንጻር ግን ባሕርይን፣ ፈቃድንና ግብርን የሚገልጡባቸው የምንታዌ ቃላትና አመከንዮዎች አልፎ አልፎ ብቅ ስለሚሉ እነርሱን መጠንቀቅ ያስፈልጋል፡፡ ዶግማ ላይ ያለንን ልዩነት ማጤን መልካም ይመስለኛል፡፡ በተኀሥሦ ስለ ግብርና ፈቃድ የቤተ ክርስቲያናችን አስተምህሮ ምን እንደሚመስል ለማኖር የሞከርኩት እነዚህን ምልከቶች ታዝቤ ነው፡፡

ከሁለቱም በሌለንበት እኔንና እኔን የመሳሰሉት ዘንድ ያነበብናትን እንደ መጨረሻ እውቀትና እምነት ማየት፣ ግራ ቀኝ ሳያጣሩና ሳይጠይቁ ለብይን መቸኮል፣ የተጋነነ የያሰኝብሃል ወይም እንዲህ ከሆነማ እንዲህ መሆኑ ነው የሚል ቅጥልጥል አመክንዮ መሳይ ክርክር ውስጥ መግባት፣ የሳቱትን ከማዳን ይልቅ የጽዩፍነትንና የፍረጃ ቋንቋዎችን መጠቀም፣  በቀናዒነትና በእውቀት መካከል ሚዛን ጠብቆ አለመጓዝ፣ ለድምዳሜ መቸኮል፣ መንፈሳዊ ጉዳይን ወደሚያውቁት ርእስ መጎተት (እኔ በወልታ ጽድቅ የወንጀል ሕግን አንድ ቦታ ላይ አላግባቡ እንዳስገባሁት)፣ ለርእስ አለመታመን፣ ፊደልና ንባብ አለመጠንቀቅ ያጋጥማል፡፡ እነዚህን ስሕተቶች እኔም ፈጽሜያቸው ረቂቁን ባነበቡልኝ ታላላቆቼ የታረምኩባቸው አሉ፣ ከእርማት ያመለጡም አይጠፉም፡፡

ጃንደረባው፡- ለጀማሪ ጸሐፍት ምን ትመክራለህ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- የንባብ አድማስን ማስፋት፣ ጽሑፋቸው ድግግሞሽ እንዳይሆን መጠንቀቅና አንዳች ክፍተትን የሚሞላ መሆኑን ማየት፣ ጽሑፋችን መሠረታውያን የቤተ ክርስቲያን ትውፊቶችንና ዶግማን እንዳያፋልስ መጠንቀቅ፣ የሰዋስውንና የቋንቋን አቅም ማሳደግ፣ በትርጕም መጻሕፍት ከትውፊታችን የማይገጥም ንባብ ሲገኝ በኅዳግ ማስታወሻ ማሳወቅ፣ ለምሳሌ አንዳንድ እንደኛ ከሕገ ኦሪት ያልመጡ የቀደምት ሊቃውንት ጽሑፎች ቀዳሚት ሰንበትን እንደ ሰንበት ላያዩ፣ የሚበሉና የማይበሉ ምግቦችን እንደኛ ላይጠነቅቁ ይችላሉና እንደዚያ ያሉ ጽሑፎች ሲያጋጥሙ በኅዳግ ማብራራት፣ አንባቢውን መፍራትና ማክበር፣ ስለምንጽፍበት ርእስ ከእኛ በላይ የሚያውቅ በርካታ አንባቢ እንዳለ ማመን፣ በሽያጭም ሆነ ስለ መጻሕፍቱ በሚሰጡ ምላሾች አለመደንገጥ ወይም አለመዘናጋት ከላይ እንዳልኩት ‹‹የምናገረውንና የምጽፈውን ራሴንም ሰውንም የሚያንጽ አድርግልኝ!›› ብሎ መጸለይ፣ ለርእስ ታማኝ መሆን፣ የጽሕፈት ሥራ አገልግሎት መሆኑን መቀበል፣ ቢቻል ጽሑፎቻችንን ከአኃትና ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት አንጻር እየቃኙ ማቅረብ፣ ዘመኑ የፈቀደውን የንባብና የምንጭ ዕድል ለበጎ መጠቀም፣ ለሚጠቀሟቸው ምንጮች እውቅና መስጠት፣ በአጻጻፍና በምንጭ አጠቃቀም ከእኛ ቀደም የጻፉትን ጸሐፊዎች ፈለግ መከተል፡፡

Share your love

20 አስተያየቶች

  1. I learnt a lot from you Beaman Nesere. Keep your strength.

    Thanks Janderebaw for your mature efforts. Keep your strength.

  2. እግዚአብሔር ይስጥልን የብዙዎችን አመለካከት ሊቀይር የሚችል ቃለ መጠይቅ ነው።
    ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።

  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

    ደብተራ በአማን እናመሠግናለን።

    ጃንደረባው ሚዲያ ጉዟችሁ አይቋረጥብን።

  4. It is an honor to get a glimpse of who he really is through this interview!
    I love what he said about using the teachings of Eastern Orthodox when it comes to Christology! Many of us do not know the clear difference and follow the name Orthodox as simple Union! I have seen tons of Ethiopian Orthodox following Mar Emanuel’s sermon’s /who is Nestorian/.
    Thank you Janderebaw media!

  5. ደስ የሚል አስተማሪ ነው ።ለእኔ የሚሆነኝን የምዕመነተት እውቀቴን ዕይታዎች እንዳሰፈ የሚጠቅም ሆኖ አግኝቼዋለው።
    ደብተራ በአማን ነጽር እና ጃንደረባው ሚዲያ ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

    • እጅግ በጣም አስተማሪ ጽሁፍ ነው ። ራስን ከፍ አድርጎ ከማየት ትህትናን ፤ መሆን የሚገባንን ያሳየ በመሆኑ እናመሰግናለን ።

  6. ቃለሕይወትን ያሰማልን 🙏

    በጣም ግሩምና በፅህፈታቸው ብቻ የምናውቃቸውን መምህር ደብተራ በአማን ነፀረ የበለጠ እንድናውቃቸው፣ ካላቸውም የህይወትና የአገልግሎት ትልቅ ልምድ ብዙ እንድንማር አድርገውናል።

    ጃንደረባው ሚዲያም እንዲህ ሳቢና ለማንበብም የሚስብና ለአንባቢውም የማያደክም ፅሁፎችን ስለምታቀርቡልን እናመሰግናለን።
    #እንዳላነብ የሚከለክለኝ ምንድን ነው?
    #አንባቢ ትውልድ

  7. እግዚአብሔር ያክብረልን ውድ ወንድሞቻችን!!!! ለመምህራችንም ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ በሉልኝ!!!

  8. ግሩም ውእቱ!

    እንዴት ያለ ተግባራዊ ዕውቀትን አካፈላችኩን!
    ጃንደረባው የሚጠይቃቸው ጥያቄዎች እና ደብተራ በአማን ነጸረ የሚመልሳቸው መልሶች ለእኔ ለግሌ እስኪመስለኝ ድረስ ለስሜት እጅግ ቅርብ ናቸው ።

    እናመሰግናለን!
    ለቀጣይ የጃንደረባው ሠረገላ ላይ ተቀምጦ የሚያስተምረን በጕጕት እንጠብቃለን ።

  9. የመምህር በአመን ነጸረን ቃለ መጠይቅ በጉጉት ጠበኩት።ደርሶም አነበብኩት።ገና ጥቂቱን ያነበብኩ እየመሰለኝ ማለቁን አረጋገጥኩ።

    በዘመናችን በዚህ ልክ ማስተዋልን የታደሉ፤እጅግ ደስ የሚል እምነት ከእውቀት ጋር አሰተባብረው የያዙ፤ሊፃፍበት የሚገባውን ርዕሰ ጉዳይ ትውልዱ ሊረዳው በሚችለው ልክ ለማቅረብ እጅጉን የሚተጉ መምህራን መንኖራቸውን ስመለከት ደስታ ይሰማኛል።

    …ግና እኛ /አሁን ያለው ትውልድ/ እነ በአማን ነጸረን የመሰሉ መምህራኖችን አውቀናቸው ምን ያህል እንጠቀምባው ይሆን ?..?

  10. ጃንደርባው ሚዲያምን፣ መምህር በአማን ነጸረንም ከልብ እናመሰግናለን ። የሁላችኹንም የአግልግሎት ዘመን እግዚአብሔር ይባርክላችሁ!
    ድንቅ ሥራ ነው ሳትሰለቹ ቀጥሉበት በቅርብ ፍሬውን ታዩበታላችሁ!

  11. በቃለ መጠይቅ ውስጥ ያለ እና ያልተወለደ መፅሐፍ ይታየል። በቁጥር አንድ በነበረው ቃለ ምልልስ የነበረውን በዚህ ደግሞ ከጠያቂውም አስተዋይነት እና አጠያየቅም ይሆናል። ብቻ ሀሳቡን ከፍ አድርጎት ነው የመጣው። ለኦርቶዶክስ አሁን እና ለሚመጣው ትውልድ ያሉበትን የቤት ስራ ያስቀመጠ እና የጠቆመ ገለፃ ነው መምህር የሰጡን። ለዛውም በሚገርም ሁኔታ በኦርቶዶክሳዊ የለዘበ አነጋገር። እዚህ ጋር ቃለ ምልልሱን ወደ ፅሑፍ የቀየረውንም ሳናመሰግን አናልፍም።

  12. በጣም መልካም የሆነ ቃለ መጠይቅ ነዉ፡፡ ደብተራ በአማን አንብቦ ብታነቡት ይጠቅማል ብሎ የሚያጋራቸዉን መፅሀፍት ሁሉንም ባይሆን ባብዛኛዉ ሆነ ብዬ እየገዛሁ አነባለሁ፡፡ አንድም ግዜ ባልገዛሁት ያልኩት መፅሀፍ የለም እና ይህንን በማድረጉ ታላቅ ምስጋና አለኝ፡፡ የጃንደረባዉ ሚድያም የቃለመጠይቅ ይዘታችሁን ወድጄዋሁ እና በርቱ ግን ስለዚህ ዌብ ሳይት ብዙ ሰዉ ማወቁን እጠራጠራለሁ እና በደንብ አስተዋዉቁት፡፡

  13. የምዕመኑን ቅንነትና ብሔራዊ ቁጭትን ለመበዝበዝ በሚመስል መልኩ የፈውስ፣ ሚቶሎጂን ከታሪክና ልብለወለድ ያስተሳሰሩ ሥራዎች፣ ኅቡዓት የሥነ ጽሑፍ ውጤቶችን የጥበብና የምርምር መጻሕፍት አስመስለው ወቅት እየጠበቁ በቤተ ክርስቲያን በመታከክ ወደ ገበያ የሚመጡ ሥራዎች አሉ፡፡

  14. እግዚአብሔር ይስጥልን መምህር
    ጃንደረባው ሚዲያ በርቱልን በጣም ትልቅ ስራ ነው

  15. እንደቀልድ ጀምሬው ሳላስበው አንደኛውን ከዚያም ሁለተኛውን ክፍል አንብቤ ጨረስኩት:: እግዚአብሔር በጸጋ ይጠብቅልን:: ሰው ሲያውቅ አረማመዱን እየመረጠም እንደሚረግጥ አየሁበት::

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *