ደብተራ በአማን ነጸረ ማን ነው? ክፍል-1


ሰው አያውቀኝም በሚል ከሕሊናዬ የሚቃረን ድርጊት ላለመፈጸም ጸሎት አደርጋለሁ

በአማን ነጸረ” በማኅበራዊ ሚዲያ ብቻ ተዋውቀው በቤተ ክርስቲያን አገልግሎት ላይ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ካበረከቱ ጸሐፍት መካከል የአንዱ የብዕር ስም ነው:: 

ወልታ ጽድቅ ፣ ጽንዐ ተዋሕዶ እና ተኀሥሦ የተሰኙ መጻሕፍትን በማበርከትና በሳል መጣጥፎችን በመጻፍ የሚታወቀውን ይህንን ጸሐፊ ጃንደረባው ሚዲያ በሠረገላው ላይ ጭኖ እንዲህ በጥያቄ አስጨንቆታል:: ክፍል አንድ እንዲህ ይነበባል:- 

ጃንደረባው፡- በአምን ነጸረን ለማወቅ ያህል የመንፈሳዊና የአስኳላ የትምህርት ዝግጅትህን ንገረን እስኪ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- መንፈሳዊ ትምህርት የጀመርኩት ባልታሰበ መንገድ ነው፡፡ ከበግ እረኝነት ድንገት ነው ጠፍቼ የሔድኩት፡፡ በተወለድኩበት መርጡለ ማርያም አካባቢ ሌማት የሚባል የድግስ ጊዜ የመተጋገዝ ባሕል አለ፡፡ በሠርግም ሆነ በልቅሶ አንድ ሰው ዝግጅት ሲኖርበት ዘመድና ጎረቤት እህል ውኃ ይዞ ይሔዳል፡፡ የአጎቴ ልጆች ይመስሉኛል በእረኝነት ሳለሁ እንጀራና ጠላ ጭነው ወደ ዐርባ (ተዝካር) ይሔዳሉ፡፡ ለቤተሰብ እንደሚያስፈቅዱ አሳውቀውኝ የጫኑትን አሕያ እየነዳሁላቸው አብሬያቸው ሔድኩ፡፡ የአጎታችን ልጅም አብሮ ነበረ፡፡ እርሱ አስቀድሞ ከገባበት ት/ቤት ወጥቶ ሌላ ት/ቤት ለመግባት እየተዘጋጀ ነበረ፡፡ አብረን እንሒድ አለኝ፡፡ ሰበከኝ፡፡ አግባባኝ፡፡ ልቤ ከእረኝነት ሸፈተ፡፡ እንደተመለስኩ ወንዱ አያቴን ስለምፈራው ሐሳቤን ለሴቷ አያቴ ነገርኳት፡፡ ሐሳቤን ልታስቀይረኝ ጣረች፡፡ እምቢ አልኩኝ፡፡ 

ካላስፈቀድሽልኝ ጠፍቼ ሌላ አገር እሔዳለሁ ብዬ አመፅኩ፡፡ ማምረሬን ስታውቅ አለቀሰች፡፡ ማልቀሷ በሁለት ምክንያት ይመስለኛል፡፡ በገጠር ት/ቤቶች ረኀብም ተስቦም አለ፡፡ በዚህ ላይ የአደራ ልጅ ነኝ፡፡ አባታችን በጤና ምክንያት ቀደም ብሎ ወጥቶ በቤንሻንጉል፣ በወለጋ ሲዘዋወር ቆይቶ በስተመጨረሻ ደቡብ ላይ በአንድ አጥቢያ እንደ አለቃም፣ እንደ ቄሰ ገበዝም፣ እንደ ቀዳሽና ሰባኪም ሆኖ ይኖር ነበረ፡፡ ሔደት መለስ እያለ ነው የተወለድኩት፡፡ እኔ እንደተወለድኩ በሚያገለግልበት አጥቢያ ሚስትህን ካላመጣህ በመባሉ ገና በሁለት ዓመቴ ለአያቶቼ አደራ ሰጥተውኝ እናቴንና ታላቄን ይዞ ወደ አገልግሎት ሥፍራው ተመለሰ፡፡ በዚያ ጊዜ (በደርግ ዘመን) አንድ ካህን ከሰሜን ተነሥቶ ወደ ደቡብም ሆነ ወደ ሌላ ክፍለ ሀገር ሲንቀሳቀስ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ከወረዳ/ቀበሌ የሚጻፍ መጨረሻው ላይ ‹‹ኢትዮጵያ ትቅደም!›› የሚል መፈክር ያለበት የይለፍ ወረቀት፣ ካህን ከሆነ የተክሊል ጋብቻና የክህነት ምስክር  ወረቀት ይጠየቅ ነበረ፡፡ አባታችን በዚህ አልፎ ነው ሲያገለግል የነበረው፡፡ ከይለፍ ምስክር ወረቀቱ በቀር ያ የምርመራ ሥርዓት ዛሬም ሊተገበር የሚገባው ይመስለኛል፡፡

ወደ ጉባኤው ቤት ታሪክ ስመለስ ተማሪ ቤት ገብቼ እስከ ማክሰኞ ዳዊት ደረስኩ፣ በቃል ትምህርትም እስከ ቅዳሜ ውዳሴ ማርያም የተማርኩ ይመስለኛል፡፡ ጥሩ በመማር ላይ ሳለሁ አያቴ እንደፈራችው ታመምኩ፡፡ ለምኖ መብላትም አቃተኝ፡፡ ወደቤት ተወሰድኩ፡፡ በሔድኩበት አያቴ ሁለተኛ ወደ ተማሪ ቤት አልልክም ብላ አገተቸኝ፡፡ በዚህ መካከል አባቴ መጣ፡፡ ‹‹አደራዬን ጨርሻለሁ፣ ልጅህን ተረከብ›› አለችው፡፡ ወደ ደቡብ ክልል ወሰደኝ፡፡ የቀረውን መንፈሳዊ ትምህርት ሙሉ ዳዊት፣ እስከ መልክአ ኢየሱስ ያለውን የቃል ትምህርትና ግብረ ዲቁና ከእርሱ ተማርኩ፡፡ ከዚያም በኋላ በ1983 ዓ.ም. የነበረውን የመንግሥት ለውጥ ተከትሎ ከማንነት ጋራ በተያያዘ ምቾት የሚነሡ ምልክቶች ስለነበሩ በኅዳር 1985 ዓ.ም. ወደ አዲስ አበባ መጥተን ዜማና ቅኔ ከተለያዩ መምህራን ተምሬያለሁ፡፡ የመጣንበት ወቅት ምቹ ካለመሆን ጋራ ተያይዞ ከቤተሰብ ተነጥዬ  ወደ ሁለት ዓመት ለሚጠጋ ጊዜ የሰው እጅ ለማየትም ተገድጄ ነበረ፡፡

ጃንደረባው፡- ማለት?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ተነቃቅቼ የከተማ ልጅ ከሆንኩ፣ ዘመናዊ ትምህርት ጀምሬ ሦስተኛ ክፍል ከደረስኩ በኋላም ቤተሰባችን በቅጡ ባለመቋቋሙ፣ ታላቅ እኅታችን የጤና መታወክ ስለደረሰባት አባቴ ከዚህ በላይ ቁጭ ብሎ ሊያስተምረኝ ስላልቻለ የሙሉ ጊዜ መንፈሳዊ ተማሪ እንድሆን ተወስኖ ገጠር አያቴ ትፈራ ወደነበረው የልመና ሕይወት እንደገና አዲስ አበባ ላይ እንደገባ ግድ ሆነብኝ፡፡ ያ ደግሞ በርካታ ፈተና ነበረው፡፡ መጀመሪያ ትጥቅ ይፈልጋል፡፡ ኮፊዳ/ኮፋዳ፣ በትር፣ አዘነ ጎጃም፣ በረባሶ/ጎማ ጫማ፣ ቁምጣ ማሟላት ነበረብኝ፡፡ የንግግር ቅላጼዬን እንደ ገና የገጠር ማስመሰልና በእንተ ስማ ለማርያም ማለቱንም ማስታወስ ነበረብኝ፡፡ ሁሉንም ካሟላሁ በኋላ ደፍሮ ልመና መጀመሩ ስላስጨነቀኝ … ትዝ ይለኛል … ቅድስት ማርያም ቅፅሩን በስተውጭ ተደግፌ ምርር ብዬ አለቀስኩ፡፡ ቢሆንም ገባሁበት፡፡ 

ስገባበት ሰውነቴ ወፈር ያለና ድንቡሽቡሽ ታዳጊ ስለነበርኩ ጥያቄ ይበዛብኝ ነበረ፡፡ ሰው አያምነኝም፣ የቸገረኝ የራበኝ አይመስለውም፣ እንደ አጭበርባሪ ያየኛል፡፡ ‹‹በዘንቢል እንጀራ ሰብሰብህ ልተሸጥ ፣ አዳሜ ማሳደግ ሲያቅተው …፣ አርፈህ አትማርም፣ ነገ ከነገ ወዲያ ጴንጤ የምትሆኑት እናንተ ናችሁ (ያን ጊዜ ተከሥተ ጌትነት የተባለው የፕሮቴስትንት ፓስተርና ዘማሪ ከቆሎ ተማሪነት ወደ ፕሮቴስታንት ዘማሪነት ተለወጠ ተብሎ ፖስተሩ በየቦታው ተለጥፎ ነበርና በእርሱ ምክንያት ግልገል ደባትር ተጠረጠርን)›› ብዙ ይላል ሰው፡፡

ራሴን እንደ ተማሪ ሳይ ሕዝቡ ግን እንደ ለማኝ ነው የሚያይኝ፡፡ ያ አመለካከት አላስደሰተኝም፡፡ በሰሜን ኢትዮጵያ የአብነት ተማሪ እንደ ለማኝ አይታይም፡፡ ‹‹ተማሪ ቆሟል›› እንጂ ‹‹ለማኝ/የኔ ቢጤ ቆሟል›› አይባልም፡፡ ከአንድ ዓመት ትምህርት ማቋረጥ በኋላ ዘመናዊ ትምህርትም የማታ ገባሁ፡፡ ቀን መንፈሳዊ ትምህርቴን እየተማርኩ ባገኘኋት ክፍተት እለምናለሁ፡፡ እንደገና ልብሴን ቀያይሬ የማታ እማራለሁ፡፡ አንዳንድ ጊዜ ቀን ስለምን ያዩኝ ልጆች ጋራ ማታ አብረን ለትምህርት እንቀመጣለን፡፡ እሱ ነገር ምቾት ይነሣኝ ጀመር፡፡ መለመኑን ችላ አልኩት፡፡ የሰፈር ቆሻሻ ሰብስቦ በመድፋት፣ በመላላክ፣ በበጎ አድራጊዎች እየታገዝኩ ልመናውን ችላ አልኩት፡፡ 

እግዚአብሔር ይስጣቸውና በነጻ የሚያሳድሩኝ እናትም አንዳንድ የጉልበት ሥራ ለስሙ እያዘዙኝ፣ ጸበል እያመጣሁላቸው፣ ድርሳነ ሚካኤል እየደገምኩላቸው እራቴን ሙሉ ለሙሉ ቻሉኝ፡፡ ከባዱ ጭንቅ ራት ማግኘት ነበር፡፡ አበው ሲመርቁ ‹‹ራትና መብራት አያሳጣችሁ›› ማለታቸው የተፈተነ እውነት ነው፡፡

ጃንደረባው፡- በዘመናዊ ትምህርትስ እስከምን ደረጃ ደርሰሃል?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- እንዳልኩህ ቀን ቀን መንፈሳዊ ትምህርት እየተማርኩ በተጓዳኝ በማታው ክፍለ ጊዜ እስከ 8ኛ ክፍል ተማርኩ፡፡ በዚያ ጊዜ የማታ ተምሮ አስራ ሁለተኛ ክፍል ውጤት የሚያመጣው ጥቂት ስለነበረ፣ ያለፈ ሕይወቴና አባቴ ያሳለፈው ሕይወትም ስላስጨነቀኝ ዘመናዊ ትምህርት ገፋ አድርጌ መማር እንዳለብኝ ወሰንኩ፡፡ አባቴ ጋራ አወራን፡፡ አሁን የእርሱም አቅም ተሻሽሏል፡፡ ዘመናዊ ትምህርቴን ሳጠናቅቅ እንደገና ወደ መንፈሳዊው እንድምመለስ ተስማምተን 9ኛ ክፍል የቀን አስገባኝ፡፡

ጥሩ ውጤት አምጥቼ ዩኒቨርሰቲ ገብቼ በሕግ ተመረቅሁ፡፡ ከምርቃት በኋላ በኮሌጅ መምህርነትም፣ በረዳት ዳኝነትም፣ በተቋማት ውስጥ  ከፍተኛ የሕግ ባለሙያ ሆኜም ስሠራ ቆይቼ በአሁኑ ጊዜ በግሌ ጥብቅና በመሥራት በሥርዓተ ተክሊል ከመሠረትኩት ትዳር የተገኙ ሁለት ሕፃናት ወንድ ልጆቼን በማሳደግ ላይ እገኛለሁ፡፡ የዘመናዊ ትምህርቴ ላይ በሕግ 2ኛ ዲግሪ ጨምሪያለሁ፡፡ ቲዎሎጂ ብጀምርም የመስክ ሥራ በመብዛቱ ለማቋረጥ ተገድጃለሁ፡፡ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ለመቀጠል አስባለሁ፡፡

ጃንደረባው፡- በአማን ነጸረ የሚለውን ለምን መረጥከው? የተለየ ምክንያት አለህ?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- ስሙ እንደዚህ አብሮኝ ይቆያል ብዬ የገባሁበት አይደለም፡፡ ያወጣሁትም እንዲሁ በብልጭታ ነው፡፡ ስሜን ማን ልበለው ስል ድንገት አንደበቴ ላይ መጣ፡፡ የማኅበራዊ ሚዲያውን ተሳትፎ ስጀምረው እንደ ቤተ ክህነታዊ አክቲቪስት ያደርገኝ ነበረ፡፡ በርካታ ጓደኞቼና ቤተሰቦቼ ከዘመደ ካህናት ስለሆኑና እኔ ደግሞ በዓለማዊ የሥራ ዘርፍ ስላለሁ በመዝገብ ስም መጠቀሙን ከእነርሱ ጋራ ከሚኖረኝ ግንኙነት፣ ከራሴ የሥራ ቦታና የቤተሰባችንን ሰላምና ስም ከመጠበቅ አንጻር አልፈለግሁትም፡፡ ስሙን የመረጥኩት በግራ ቀኝ ከሚነገሩት ነገሮች ውስጥ እውነተኛው ይህ ነው ለማለት ነበረ፡፡ እየቆየሁ ስሔድ ይህ ነገር (ለካህናት ድምፅ እሆናለሁ ማለቱ) ሐሜትና መወቃቀስ ጋበዘብኝ፡፡ ያላሰብኩት ቡድናዊ ስሜትና የማላውቃቸው የተለያዩ ተፋላሚዎች መካከል ከተተኝ፡፡ ሥራዬና ስሙ እንዳይጣጣም የሚያደርግ ተግባር ውስጥ እንዳለሁ ተሰማኝ፡፡ የአእምሮ ሰላምም አልሰጠኝም፡፡ ከሽኩቻው ቀስ በቀስ ራሴን አወጣሁ፡፡ የአስተዳደር ጉዳይ ይቀያየራል፡፡ እዚያ ላይ ቆሜ ‹‹በአማን ነጸረ›› ማለት እየከበደኝ ሔደ፡፡ ስለዚህ ትኩረቴን ወደ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ አደረግሁ፡፡ የእምነት ነገር ዘለዓለማዊና የማይለወጥ ስለሆነ፣ የቤተ ክርስቲያንን አስተምህሮ ከልዩ ልዩ እይታዎች አንጻር ለመመስከርና ያልተገቡ አስተያየቶችን ለመመከት በቂ ምንጭ ስላለ የመረጥኩትን ስም ይመጥንልኛል ወዳልኩት ጉዞ አተኮርኩ፡፡

ጃንደረባው፡- ‹አንባቢው የጸሐፊውን ስም ማወቅ ይገባዋል› ከሚለው መርሕ አንጻር በአንባቢው ላይ በደል ፈጽመሃል ተብለህ ብትከሰስ መልስህ ምንድን ነው?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡-  ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅን በመጥቀስ የሚቀርበውን ክስ እቀበላለሁ፡፡ በተለይ ከነገረ ሃይማኖት ጋራ የተያየዙ ጉዳዮች ላይ እንደማተኮሬ ጥያቄውና ወቀሳው ትክክል ነው፡፡ በንባብ ውስጥ ጸሐፊ፣ ጽሕፈትና አንባቢ አሉ፡፡ ጸሐፊውን ማወቅ ጽሕፈቱን ለመረዳት ያግዛል፡፡ ቅዱስ ሉቃስ ጌታ ስለፈጸማቸው የፈውስ ተአምራቶች ገፋ አድርጎ መጻፉን ያዩ ሊቃውንት ጽሕፈቱን ከሐኪምነቱ ጋራ አያይዘው ይረዱታል፡፡ ጸሐፊውን ማወቅ ጽሕፈቱን ብሩሕ ያደርገዋል፡፡ ያንን ክፍተት ለመሙላት ነው ለኅትመት የሚውሉትን መጻሕፍት ለጉዳዩ ትኩረት ይሰጣሉ ለምላቸው ወንድሞች የማሳየው፣ የትምህርት፣ የሥራ፣ የቤተሰብ የመደብ ጀርባዬን በአገኘሁት ሁሉ የምጠቋቁመው፡፡ አንዱ ማንነት ያ ስለሆነ፡፡ ከአሳታሚዎች ጋራ አካላዊ ትውውቅ አለኝ፡፡ ከሁሉም በላይ በመዝገብ ስም አለመጠቀሜን እንደ መልካም አጋጣሚ ተጠቅሜ ከሕሊናዬ የራቀ ነገር ላለመናገር የተቻለኝን ያህል ጥረት አደርጋለሁ፡፡ ሰው አያውቀኝም በሚል በሰውም ሆነ በተቋም ላይ ከሕሊናዬ የሚቃረን ድርጊት ላለመፈጸም ጥረት ብቻ ሳይሆን ጸሎትም አደርጋለሁ፡፡ 

በዘወትር ጸሎቴ ውስጥ ‹‹የምናገረውን የምጽፈውን እኔንም ሰውንም የሚያንጽ አድርግልኝ›› እላለሁ፡፡  በመዝገብ ስም አለመገለጤ ጥፋት ቢሆንም እነዚህ አካሔዶቼ ቅጣቱን እንደሚቀንሱልኝ አምናለሁ፡፡

ጃንደረባው፡- በአካል አለመታወቅህ ምን ጠቀመህ? የጎዳህስ ነገር ይኖር ይሆን? ሳያውቁህ በፊትህ ያሙህ ወይም ያመሰገኑህ ይኖሩ ይሆን?

ደብተራ በአማን ነጸረ፡- በአካል አለመታወቄ የሰው ፊት ሳላይ በእግዚአብሔር ፊት እውነት ይሆናል ያልኩትን እንድጽፍ፣ ጽሑፍና ንባብ ላይ ብቻ እንዳተኩር፣ ለዕለት ኑሮዬ የምሠራውን ዓለማዊ ሥራ በነጻነት ማንነቴ ሳይታወቅ እንዳከናውን፣ የቤተ ክርስቲያን መምህራንን እንደ ልብ ለማነጋገር፣ በጉዞ ጊዜ ሰዎችን በነጻነት ለማነጋገር አስችሎኛል፡፡ ዓለማዊ ሥራዬ ጉዞ የበዛበት ነበረ፡፡ በርካታ ሥፍራዎችን በሥራ አጋጣሚ ረግጫለሁ፡፡ በዚያ ያሉ ጉባኤዎችን በትኩረት እጎበኛሁ፣ እጠይቃለሁ፣ በቦታው ብቻ የሚሸጥ የሃይማኖት ወይም የገዳም/ደብር ታሪክ የያዘ መጽሐፍ ካለ እገዛለሁ፡፡ የጉባኤ ቤት ሰዎችን ቀስ ብዬ በዚያው በቤተ ክህነቱ ቋንቋ ለያዝኩት ርእስ የሚሆን ምሥጢር ከጉባኤ ቤት ድንገት ወጥቶ እንደ ቀረ ደቀ መዝሙር ሆኜ እጠይቃለሁ፡፡ በነጻነት ይነግሩኛል፡፡ ቢያውቁኝ ይኽንን ዕድል የማገኝ አይመስለኝም፡፡ አለመታወቄ በነጻነት ለመጠየቅ ጠቅሞኛል፡፡ ጥያቄዬን ለአንድ ምዕመን እንደሚያስረዱ አድርገው በዝርዝር ይመልሱልኛል፡፡ ብታወቅ ይኽንን ዕድል ማግኘቴን እጠራጠራለሁ፡፡ ባለመታወቄ በአካል ከመነቀፍም ከውዳሴ ከንቱም አምልጫለሁ፡፡ የቅብዓቶች መጽሐፍ ተወግዞ በድብቅ በሚሸጥበት ጊዜ ተራ ሰው መሆኔ መጽሐፉን ከጥርጣሬ ነጻ ሆኜ ለማግኘት ችያለሁ፡፡ የቃል መረጃዎችን በኢመደበኛ መንገድ ሰብስቤያለሁ፡፡

በጉዳት በኩል ሕሊናዬን አሁንም ቢሆን ይጎዳኛል፡፡ የኃጢአተኛነት ስሜት ይሰማኛል፡፡ ራሴን ብገልጥ ደግሞ ከዚህ በላይ እጎዳለሁ ብዬ ስለምፈራ ብቻ መደበቄን ተቀብየዋለሁ፡፡ ሰዎች እንዳወቁኝ ሲነግሩኝ ሳይሆን ምልክት ሲሰጡኝም በጣም እረበሻለሁ፡፡ አለመታወቄ እታወቅ ይሆን የሚል ቀጣይነት ያለው ስጋት ውስጥ ከቶኛል፡፡ ትልቁ ጉዳት ግን እንደ አዋቂ ተቆጥሮ የመታየት ሸክም ነው፡፡ በጊዜ ብዛት እየጠፋብኝ ከመጣ የዜማ ትምህርትና ሰምና ወርቅ ቅኔያት ሲደረጉ አድምጦ ከመደነቅ ያለፈ የቅኔ ቤት ቆይታ የዘለለ የጉባኤ ትምህርት የለኝም፡፡ እንደ ማንኛውም ምዕመን ያነበብኩትንና በሕሊናዬ የተመላለሱ ጥያቄዎችን በሚመለከት አባቶች የጻፉትንና የሚተረጕሙትን በትውልዱ ቋንቋ ለማቅረብ እሞክራለሁ፡፡ እንደ መምህራን በጉባኤ ወስኜ በአእምሮዬ ያብላላሁትን አይደለም የምጽፈው፡፡ አደን እንደሚያድን ሰው ቀራርሜ ነው የምናገር፡፡ ያደንኩት ሲያልቅ ሌላ አደን እወጣለሁ፡፡ መምህራንን በበረታቸው ብዙ በጎች እንደያዙ አርቢዎች ውሰዳቸው፡፡ አንባቢው ግን እንደዚያ አይረዳኝም፡፡ ያለችኝን አንድ ጊዜ በጽሑፍ ስወረውር ሌላ ቀሪ የለኝም፡፡ ለአንድ ርእስ ግብዓቶቼን ሳገላብጥ የምነካካቸው ነጥቦች ቢኖሩ ከርእሱ ጋራ ስለተዛመዱ የተነሡ እንጂ ያንን ርእስ ጠንቅቄ አውቄ፣ እንደ ሰዎች ወስኜው አይደለም፡፡ ለትሕትና አይደለም ይኽን የምናገረው፡፡ ከልቤ ነው፡፡ በመሆኑም ሰዎች ሳያውቁኝ ደብተራ ከሚለው ቅጽል ወጪ የሚሰጡኝ ስያሜ ይረብሸኛል፡፡

በአካል ሳያውቀኝ የሚያማና የሚተች አጋጥሞኛል፡፡ ከቅርብ ቤተሰብ ጀምሮ፡፡ ካሙኝ ውስጥ፡- ወልታ ጽድቅን አጻጻፉን ካደነቁ በኋላ ‹‹የተተረጐመ የፈረንጆች መጽሐፍ ይመስላል›› ያሉኝ የምወዳቸው መምህር አሉ፡፡ የሚገርመው እመቤታችን ጥንተ አብሶ አለባት ወይስ የለባትም በሚለው ክርክር ውስጥ በተደጋጋሚ አነጋግሬያቸው በመጽሐፉ የእርሳቸውን አባባሎች አካትቻለሁ፡፡ አቀራረቡ በመጠኑ ዘመናዊ ስለሆነ ይመስለኛል ትችቱን ያቀረቡት፡፡ በማቀርባቸው ጽሑፎች ሁለት ተካራካሪ አካላት ካሉ የሁለቱንም ሐሳብ በራሳቸው አነጋገር እንደ ወረደ ካቀረብኩ በኋላ ነው ወደ ንጽጽርና ትችት የምገባው፡፡ ይኽ አቀራረብ በአንድ በኩል የተወገዘውንም ሐሳብ የተቀበልኩ ተደርጎ እየተሳለ የመተቸት፣ ውጉዙን ሐሳብ በያዙት ዘንድም የእነርሱን ሐሳብ እንደ ደገፍኩ አድርጎ መውሰድ አለ፡፡ ከዚያ የሚነሡ የቅሬታ ሐሳቦች ለራሴም ቀርበውልኝ ያውቃሉ፡፡ ‹‹እንዴት እንደዚህ ይጽፋል!›› ብሎ ማንነቴን ሳያውቅ ራሴን ለራሴ የሚተች ሰው ገጥሞኛል፡፡ ‹‹ይላሉ›› ብዬ ምንጭ ጠቅሼ ያኖርኩትን የእኔ ሐሳብ አድርጎ ወስዶት በቁሜ አማኝ፡፡ እየተሳቀኩኝ ለሐሜት መነሻ የሆነውን የእኔን መጽሐፍ ሳይሆን በመጽሐፌ ምንጭ የሆኑትን ምንጮችና ርእሰ ጉዳዩን ብቻ በመያዝ ሐሜቱን ለማስወገድ ጣርኩ፡፡

በውዳሴ በኩል ራሴ የጻፍኩዋቸውን መጻሕፍት እንዳነብ ጥቆማ ተሰጥቶኝ ያውቃል፡፡ መጻሕፍት ለመግዛት መጻሕፍት መደብር ስሔድ ‹‹ብርሃኑ አድማስ አስተያየት የሰጠበት አሪፍ መጽሐፍ ነው›› በሚል የራሴን መጽሐፍ በማሻሻጫ ሊሸጡልኝ ሞክረው ብርሃኑን አመስግኜ አውቃለሁ፡፡  በሀይቅ እስጢፋኖስ የመጽሐፍ መደብር ከሚሸጡት መጻሕፍት አንዱ ጽንዐ ተዋሕዶ ነበረ፡፡ ሌሎችም በቅርብ ወጥተው እዚያ የደረሱ መጻሕፍት አሉ፡፡ 

አዲስ አበባ ያጣኋቸው መጻሕፍትንም በዚያ አግኝቼ ገረመኝና ስለንባብ ባሕላቸው፣ ይኽንን ሁሉ መጽሐፍ ማን ሊገዛቸው እንደሚችል ጠየቅኋቸው፡፡ በገዳሙ አዳዲስ መጻሕፍት ሲወጡ አድኖ የማንበብ ልምድ መኖሩን ነግረውኝ ከተነበቡ መጻሕፍት በምሳሌነት ጽንዐ ተዋሕዶን ጠቀሱልኝ፡፡ ከዚያ አያይዘው እዚህ ብዙ ሰው ይመጣል፣ እከሌም እዚህ ሱባኤ ሰንበቶ ነው የሔደው ብለው ታዋቂ የቤተ ክርስቲያን ጸሐፊ ስም ጠቀሱልኝና ‹‹ማን ያውቃል?! እዚህ የሚረግጠው ብዙ ነው፣ እርስዎም ከእነዚህ መጻሕፍት የአንዱ ጸሐፊ ሊሆኑ ይችሉ ይሆናል›› አሉኝ፡፡ እንደ መደንገጥ ብዬ በገዳሙ ከመጻሕፍት መደብሩ ጎን ለበረከት ከሚሸጠው አትክልትና ፍራፍሬ የምችለውን አስመዝኜ ወጣሁ፡፡ 

አንድ የቤተሰባችን አካል ስለ ደቂቀ እስጢፋኖስ ካምፓስ ውስጥ ከሌላ እምነት ተከታይ ጋራ ባደረገው ክርክር ወልታ ጽድቅን እንዴት አድርጎ እንደተጠቀመ ካብራራልኝ በኋላ ‹‹ደብተራ በአማንን ታውቀዋለህ?›› ብሎ አፋጥጦኝ መጽሐፉን እንጂ እርሱን እንደማላውቀው ክጄ ተናግሬያለሁ፡፡ ይኽንን በምናገርበት ጊዜ ሰውነቴ ሽምቅቅ ሲል ይታወቀኛል፡፡ በብዕር ስም መጻፍ ኃጢአቱ ይህ ነው፡፡

ጃንደረባው፡- ደብተራ የሚለውን ብዙ ሰዎች ከአምልኮ ባዕድ ጋራ ያይዙታል፡፡ አንተ ደግሞ ድብትርናን በኩራት መጠሪያህ አድርገህ ልታከብረው ሞክረሃል፡፡ ለመሆኑ ደብተራ የሚለው ስም ትርጕሙ ምንድን ነው? ከአምልኮ ባዕድ ጋራ የሚያያዙት ሰዎችስ መነሻ የላቸውም ትላለህ? ከቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚፈጸም አምልኮ ባዕድ፣ መተት፣ ምስሐብ፣ ድግምት፣ ወዘተ. አለ ብለህ ታምናለህ? ካለ ምንጩ ምንድን ነው? መፍትሔውስ?

ደብተራ በአማን ነጸረ- ደብተራ የሚለው ቃል ምንጩ ግሪክ ነው፡፡ የተወጠረ ብራና እንደ ማለት ነው፡፡ በግእዙ ድንኳን የሚል ትርጕም አለው፡፡ በልማድ ከግብሩና ከሕዝባዊ እይታ የሚነጭ የተለያየ ትርጓሜ ይሰጠዋል፡፡ በጎጃም አካባቢ የአብነት ተማሪ ደብተራ ይባላል፣ ክህነቱ የፈረሰበት ካህንም ደብተራ ይባላል፡፡ በሸዋ ከጉባኤ መምህር በመለስ ያለው መዘምር ደብተራ ሲባል አይቻለሁ፡፡ ሲቀጠር በመምህርነት ሳይሆን በዘምርነት ነው፣ መዘምርነት ሲቀጠር ‹‹ድብትርና አገኘ›› ይባላል፡፡ እንደ መጠሪያ ሰጪ የለውም፡፡ አፈ ሊቅ፣ ሊቀ ጠበብት፣ ሊቀ መዘምራን፣ አጋፋሪ፣ መጨኔ፣ ቀኝ ጌታ፣ ግራ ጌታ የመሳሰሉ ከአገልግሎት ጋራ የተያያዙ መዓርጋት ሰጪ አላቸው፡፡ ደብተራ የወል ስም ነው፡፡ እኛ ከማኅሌት አገልግሎት ጋራ እናያይዘዋለን፡፡ በቀደመው ዘመን ጸሐፍትም ራሳቸውን ደብተራ አከሌ እያሉ ይጠራሉ፡፡ 

ደብተራ ዘነብ ታዋቂ ስም ነው፡፡ መጽሐፈ አክሱም እንደሚናገረው የድብትርና መሬት የሚባል ሥሪት ከዘመነ አክሱም ጀምሮ ነበረ፡፡ በመካከለኛው ዘመን ድብትርና ማኅበረሰቡ ውስጥ ካሉት መደቦች አንደኛው ነበረ፣ ማለትም ነገሥታቱ ቋሚ መናገሻ ከተማ ሳያበጁ ይዟዟሩ ስለነበረ ለቅዳሴ ማስቀደሻ ተንቀሳቃሽ ድንኳንን (ደብተራን) ይጠቀማሉ፣ በዚያ ድንኳን (ደብተራ) እያደሩ የሚያገለግሉ በማደሪያው ‹‹ደብተራ›› ተብለው ተጠርተዋል (‹‹በስመ ማኅደር ይጼዋዕ ኀዳሪ›› መሆኑ ነው)፡፡ በዘመኑ ደብተራ በክብር የሚጠራ፣ ማኅበረሰባዊ መደብ ያለው ማለትም ሰዎች የትውልድ ሐረጋቸውን ሲገልጡ ‹‹እምዘመደ ደብተራ፣ እምካህናተ ደብተራ›› እያሉ የሚናገሩለት መደብ ነበረ፡፡ በአመዛኙ ከመናንያን በተለየ በዓለም እየኖረ ቤተ ክርስቲያንን የሚያገለግለውን የቤተ ክህነት ወገን ይወክላል (ፕ/ር ታደሰ secular clergy) የሚሉት ድብትርናን ማእከል በማድረግ ይመስለኛል፡፡ በአውሮፓ clerics ይሏቸዋል፡፡ ዘመኑን ዓለሙን ያጤኑ የቤተ ክህነት ወገኖች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያ ሥነ ጽሑፍ ደብተራ የራሱ አሻራ አለው፡፡ ደብተራ ማለት ሌላ ትርጕሙ ጸሐፊ ማለት ነው፡፡ ደስታ ተክለ ወልድ ‹‹ደበተረ›› የሚለውን ቃል ‹‹ጻፈ›› ብለው ይፈቱታል፡፡ በዘመነ መሣፍንትና በዘመናዊት ኢትዮጵያ ጅማሮ የነበሩ የቤተ ክህነት ጸሐፍት በዚህ ስም ተጠርተዋል፡፡ ደብተራ አሰጋኘኝ፣ ደብተራ ፍስሐ ወልደ ጊዮርጊስ (በትግርኛ ሥነ ጽሑፍ የተከበረ ስም ያላቸው)፣ ደብተራ ደስታ ነገዎ (ኋላ አለቃ የተባሉት የሠዓሊ ገብረ ክርስቶስ ደስታ አባት)፣ ደብተራ ዘነብና ደብተራ ተወልደ መድኅንና የመሳሰሉት ይጠቀሳሉ፡፡ ፕ/ር ባሕሩ በፋና ወጊዎቹ (The Pioneers of Change) መጽሐፋቸው ደብተራ የሚለውን ቃል የመደብ ጀርባቸው ከቤተ ክህነት የሆነ የቤተ መንግሥት ቀራቢ የ1920ዎቹ የቅድመ ጣሊያን ወረራ ‹‹ተራማጅ›› ልሂቃንን ለመግለጥ ተጠቅመውታል፡፡ በደርግ ጊዜም ጸገየ ወይን ገብረ መድኅን የሚባል የኢህአፓ የጦር ክንፍ አመራር የነበረ መሪጌታ ነበረ፡፡ በቅጽል ስሙ ‹‹ደብተራው›› ይባላል፡፡ ርእሷን ከአንቀጽ ብርሃን የወሰዳት ‹‹ናስተማስለኪ›› የምትል ገናና ግጥም አለቺው፡፡ በሕወሓት ታጋዮች ዘንድ ደባትር ነበሩ፡፡ ጎጃም ቀራንዮ መድኃኔዓለም የነበሩት መልአከ መልአክ ተስፋ የቅኔ ጉባኤ ላይ በ1983 ዓ.ም.

አንድ ደብተራ በተማሪነት ገብቶ ጥቂት ቀናት ቀጽሎ ጠፋ፡፡ ደብተራው ቀለም የለየ፣ የተማረ፣ ነገር ግን ቅኔውን ለማደላደል የመጣ ዓይነት ነው፡፡ ወር ቆይቶ ከጠፋበት መጣ፡፡ ሲመጣ ግን ልብስና ትጥቅ ቀይሮ ጦር እየመራ ነበረ፡፡ ለካስ አሁን የሕወሓት ታጋዮች አዋጊ የሆነ የቀድሞ መሪጌታ ነበረ፡፡ በደርግ ጊዜ የአብነት ተማሪዎች እየታፈሱ ደባትሩ ወታደሮች ሆነዋል፡፡ ዐፄ ኃለ ሥላሴ ላይ መፈንቅለ መንገሥት ለማድረግ ያሤሩትና ስማቸውን የኢህአፓው ብርሃነመስቀል ረዳ የብዕር ስም አድርጎ የተጠቀመበት ፊታውራሪ ታከለ እንጦጦ ራጉኤል የተማሩ ደብተራ ነበሩ፡፡ ደብተራ ከሕይወት የራቀ ሐሳባዊ ፍጡር አይደለም፡፡ ቃሉ በአመዛኙ ለመንፈሳዊ አገልግሎትና ዕውቀት ነክ ለሆነ የጽሕፈት ሥራ የተሰጠ አዎንታዊ ትርጉም ያለው ቃል ነው፡፡ በታሪክ ለነውር የሚውል መጠሪያ አልነበረም፡፡

አልፎ አልፎ ግን በማኅበረሰቡ ዘንድ በአሉታ ይጠራል፡፡ መምህራችን የነገሩንን ምሳሌ ላንሳ፡፡ ሲማሩ የብራና ድጓ ይጽፋሉ፡፡ ድጓውን ለመጻፍ ትንሽ ወረት (ካፒታል)ና እህል ውኃ፣ ቢቻል አናትም ስለሚደርቅና ዐይን ስለሚቦዝ ቅቤ ይፈልጋል፡፡ ስለዚህ አንድ መላ ፈለጉ፡፡ ከድጓው ጎን ለጎን ልፋፈ ጽድቅ እየጻፉ ለማኅበረሰቡ ያቀርባሉ፡፡ በምላሹ የዕለት ምግባቸውንና የአናት ቅቤያቸውን በዓይነት ያገኛሉ፡፡ በአንድ ጽሕፈት ሁለት ዐላማ፣ ሁለት ስያሜ መጣ፡፡ የንታ ቤተ ክርስቲያን ሲቆሙ የሚሰጣቸው ስምና ማኅበረሰቡ የሚሰጣቸው ስም ይለያያል፡፡ በድብትርና ስም የሚሠራ ኵሸት አለ፡፡ የሚሠሩት በብዛት በሥራቸው አያምኑበትም፡፡ ኵሸት፣ ኃጢአት፣ ውሸት መሆኑን ያውቃሉ፡፡ ግን ሰይጣን ለሚፈልገው ቅርብ ነው እንደሚባለው ይደረግልናል ብለው ለሚያምኑት እንዳመኑት ይሆንላቸዋል፡፡ ሰዉ ይፈታተናል፡፡ ራሴ በልመና በምዟዟርበት ጊዜ ‹‹የሆነ ደብተራ መስተፋቅር ጀምሮልኝ ጠፍቷልና ጨርስልኝ›› ተብዬ አውቃለሁ፡፡ በልጅነቴ አፈ ሕፃን ለሚባል የጋኔን መነጋገሪያ ሊጠቀመኝ የሞከረ ሰው ነበረ፡፡ በአንድ እጅ መስታወት፣ በአንድ እጅ ጋኔኑ እንዳይጣላኝ የሚያደርግ ዕፅ ተሰጥቶኝ ጋኔን ሳቢው በውጭ አረቄውን ይዞ በድግምት እየተማፀነ ጋኔኑ በመስታወቱ ተከሥቶ የሚነግረኝን ለሳቢውና ለባለጉዳዩ እንዳስተላልፍ ተነገረኝ፡፡ ቢጠበቅ ቢጠበቅ ሰይጣኑ ሳይከሠት ቀረ፣ ሳቢው ችሎታ የለህም ወይም ድርጊቱ ውሸት ነው መባልን ስላልፈለገ ‹‹ሕፃኑ ዐይነ ጥላ አለበት›› ብሎ አበሳውን በዐይን አፋሩ ታዳጊ ላይ ደፍድፎ ተገላገለ፡፡ እኔ ግን ድርጊቱ ስላላመረኝ በውስጤ ሰላም ለኪን እደግም ነበረ፡፡ ይኽን ያደረገውም ያስደረገውም ሁለቱም የቤታችን ሰዎች ናቸው፡፡ ለገበያ፣ ለመስተፋቅር፣ ለጉዞ፣ ለመስተባርር፣ መቅትል፣ ወዘተ. እየተባለ ኵሸቱ ብዙ ነው፡፡ የሰመረ ድርጊት አይቼም ሰምቼም አላውቅም፡፡ ለገበያ ግን ያጋንኑታል፡፡ የሚያጋንኑት ገበያተኞች ብቻ አይደሉም፡፡ በቤተ ክርስቲያን መዋቅር ያልታቀፈው ክፍል፣ ሥጋዊ ፈውስን ከዘለዓለማዊ ድኅነት እያምታታ እንጀራ የሚያበስለው ሁሉ የአንዳንድ አፈንጋጭ ደባትርን ድርጊት ከፍ ሲል እንደ ቤተ ክርስቲያን መገለጫ፣ አነስ ሲልም የደብትርና ዋነኛ ገጽታ አድርጎ ሊሥለው ይሞክራል፡፡ በችግር መነገድ መሆኑ ነው፡፡ 

ዓለማውያን ምሁራንም ራሳቸውን ተራ በምንለው አረዳድ ላይ አቁመው መላውን ትውፊታዊውንና ኦርቶዶክሳዊውን እምነትና ሥርዓት ለማነወር እንደ አሉታዊ ጅምላ ስያሜ ይጠቀሙበታል፡፡ ‹‹ደብተራ!›› ብሎ በስድብ ስሜት መጠቀም የቤተ ክርስቲያን ሰዎችን ማነወሪያ የኮድ ስም አድርገው የያዙ ጥቂቶች አይደሉም፡፡

ድርጊቱን ፈጻሚዎች ከቤተ ክርስቲያን የወጡ ቢሆኑም ድርጊቱ የቤተ ክርስቲያን አይደለም፡፡ ሲጠናም ኅቡዕ ሥነ ጽሑፍ (underground literature) እየተባለ ነው፡፡ ኅቡዕ የሆነው ቤተ ክርስቲያን ስለምታወግዘው ነው፡፡ በመጽሐፈ ሲኖዶስ፣ በቀኖና ሐዋርያት የተወገዘ፣ ከዚያ አልፎ ጦማረ ትስብእት በሚባል መጽሐፍ በዝርዝር የተነቀፈ ድርጊት ነው፡፡ አንድ ካህን ሰክሮ ብናይ ስካሩን የግሉ እንጂ የክህነቱ መገለጫ አድርገን አናየውም፡፡ ይህ አመክንዮ ለደብተራም ይሠራል፡፡ ወንጀልና ኀጢአት ግለሰባዊ እነደሆነ ሁሉ ጥንቆላም ግለሰባዊ ኀጢአት ነው፡፡ ለግለሰቡ ድርጊት ደብተራ የተባለው ሁሉ አይቀጣም፡፡ ቤተ ክርስቲያን ድርጊቱን በዘለዓለማዊ ውግዘት አውግዛለች፡፡ ከተወገዘ ጋራ መተባበር ራስን መበደል ነው፡፡ በሌላ በኩል ዕፀውን በመቀመም ለመድኃኒትነት ማዋል እንደ ጥበብ እንጂ እንደ ጥንቆላ ሊታይ አይገባም፡፡ የሆነ ሆኖ ስሙን የተጠቀምኩት የማያሳፍር መሆኑን ለማሳየት ነው፡፡ ገብረ እግዚአብሔር ኪደ ጋራ ተነጋግረን በእርሱ ‹‹በእንተ ሐውልታት›› መጽሐፍ ላይ አስተያየት ስሰጥ በይፋ መጠቀም የጀመርኩ ይመስለኛል፡፡ 

ስጀምር ‹‹ኒዮደብተራ›› የሚል ትችት ነበረ፡፡ አሁን ላይ ግን አንድ ወንድሜ እንዳለኝ ስሙን (ደብተራን) እንደ አዲስ በአዎንታ ለማስተዋወቅ (rebrand ለማድረግ) መንገድ የጠረግን ይመስለኛል፡፡ በዚህም ከመፍትሔው አንዱን እያደረግሁ እንዳለሁ ይሰማኛል፡፡

ይቀጥላል … 

Share your love

13 አስተያየቶች

  1. መልካም ቃለመጠይቅ ነው
    ኢቺን አስተካክሉ
    “””ጃንደረባው፡- ደብተራ የሚለውን ብዙ ሰዎች ከአምልኮ ባዕድ ጋራ ያይዙታል፡፡ አንተ ደግሞ ድብትርናን በኩራት መጠሪያህ አድርገህ ልታከብረው ሞክረሃል፡፡ ለመሆኑ ደብተራ የሚለው ስም ትርጕሙ ምንድን ነው? ከአምልኮ ባዕድ ጋራ የሚያያዙት ሰዎችስ መነሻ የላቸውም ትላለህ? ከቤተ ክርስቲያን ጥላ ሥር የሚፈጸም አምልኮ ባዕድ፣ መተት፣ ምስሐብ፣ ድግምት፣ ወዘተ. አለ ብለህ ታምናለህ? ካለ ምንጩ ምንድን ነው? መፍትሔውስ?””””
    ይሄኛው ጥያቄ ተደግሟል

  2. ግሩም ታሪክ እና መሠረት ያለው ትምህርት ነው ። እኔ ለንባብ ዐዲስ ነኝ ብል ይቀለኛል ። ከማደርጋቸው ነገሮች መካከል አንዱ መጽሐፍ ስገዛ የማውቃቸውን ጸሐፊዎች እና ሰዎች የጠቆሙኝን ብሎም ስለ መጽሐፉ የተሠራውን ማስታወቂያ በማየት ነው ። እና የደብተራ በአማን ነጸረ ስም ከአንዴም ኹለት ሦስቴ ግራ ገብቶኝ ያውቃል ። እንዳውም ካለማወቄ የተነሣ ጐጃም አካባቢ የቅኔ መምህር ይመስሉኝ ነበር ። ስማቸው በራሱ ይገርማል ።
    ደብተራ – ድንኳን
    በአማን – በእውነት
    ነጸረ – ተመለከተ እና ዐዲስ ለሚያውቃቸው ሰው እንደዚህ በስማቸው እየተደነቀ መጽሐፋቸውን ሳያነብ በስማቸው ሲፈላሰፍ ቀኑን ሙሉ ቁጭ ብሎ ሊውል ይችላል ።

    የዛሬው ንባብ እኔን እጅግ አስደንቆኛል። እንዲህ እያደረጋችኹ ጸሓፊዎቻችን ታስተዋውቁን ዘንድ በርቱልን!

  3. አንድ ካህን ሰክሮ ብናይ ስካሩን የግሉ እንጂ የክህነቱ መገለጫ አድርገን አናየውም

  4. የጃንደረባው ትውልድ አባላት እያደረጋችሁት ስላለው ሁሉ እግዚአብሔር ያክብርልን!ትልቅ ነገር ነውና እያደረጋችሁት ያለው። እግዚአብሔር ያበርታችሁ!

  5. እግዚአብሔር ያክብረልን ውድ ወንድሞቻችን!!!! ለመምህራችንም ቃለ ሕይወት ያሰማልኝ በሉልኝ!!!

  6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን ፤ ብዙ ያተረፍኩበት ኾኗል እግዚአብሔር ያክብርልን።

  7. ስለ እውነት ባነበብኩት ደስ ብሎኛል። ብዙ የቤተክርስቲያን ማዕረጋት እና ስሞች ባልተገባ መልኩ ሲብጠለጠሉ ኖረዋል ይህን ደግሞ ልናስተካክል የምንችለው እንዲህ ባለው መልኩ በእውቀት ታግዘን ስሙን ተጠቅመን(ከተገባን) ስንመልስ ነው።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *