ደም ላነሳት ደም ልገሳ

መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የ 12 ዓመት ታዳጊ የነበረችዋን የኢያኢሮስን ልጅ ከሕመሟ ለመፈወስ ሲጓዝ በመንገድ ብዙ ሕዝብ ያጨናንቀው ነበር። ከሚተራመሰው ሕዝብ የተወሰነው ተአምራት ሊያይ፤ ገሚሱ ሕብስት ሲያበረክት ጠብቆ ሊበላ፤ ሌላው መልኩን ሊያይ፤ ደግሞ ለበላይ አለቆች ያየና የሰማውን መረጃ ለማቀበል፤ የተቀረው ትምህርቱን ሊሰማ ይጋፋ ይዟል። ጌታችንም የሚጓዝ ይህ ሁሉ ሕዝብ እያጋፋው ነበር። 

ይህ ሕዝብ እስከ ምጽዓት ክርስቶስን የሚከተሉ ሰዎችን የሚወክል ማሳያ ነው። ዛሬም በቤተክርስቲያን ለሆዱ ሲል ወይም በዚያ ያለው ሥርዓት ማርኮት፤ ደግሞም ትምህርት ለመስማት ብቻ፤ ተአምራት ለማየት ወይም ለተቃዋሚዎች ወሬ ለማቀበል የሚጋፋ አለ። 

በጉዞው መካከል ጌታችን ድንገት ቆሞ “የዳሰሰኝ ማነው?” ሲል ጠየቀ። ደቀ መዛሙርቱ ይህ ሁሉ ሰው እያጋፋው ሳለ እንዲህ ብሎ መጠየቁ “መምህራችሁ ምን ማለቱ ነው?” ለሚል ትዝብትና ትችት እንዳይዳርጋቸው ቶሎ ብለው “አቤቱ ሕዝቡ ያጨናንቁሃል ያጋፉህማል፤ የዳሰሰኝ ማን ነው ትላለህን?” በማለት ያለበትን ሁኔታ ሊያስታውሱት ምከሩ። ዙሪያውን የተሰበሰበ ሁሉ አብሮት እንዳልሆነ የሚዳስሰውም ሁሉ ግንኙነት እንደማይፈጥር ከእርሱ ከራሱ በቀር የሚያውቅ የለም። ብዙዎች ዙሪያውን ቢያጋፉትና ቢያጨናንቁትም ከእርሱ ጋር በምሥጢር ግንኙነት መፍጠር የሚችሉ በጣም ጥቂት ናቸው። የማዳን ኃይል የፈውስ ኃይል ከእርሱ እንዲወጣ በእንባ፣ በጸሎት፣ በጾም፣ በስግደት፣ በሱባዔ፣ በምህላ፣ ወዘተ. . . ቀርበው የሚዳስሱት በእምነት የሚኖሩ ብቻ ናቸው። 

ለአሥራ ሁለት ዓመታት ባለማቋረጥ ደም የሚፈሳት በዚህ ችግሯም ገንዘቧንና ትዳሯን ሁሉ የከሰረች ምስኪን ሴት ነበረች። በዘመናዊው ዓለም እንዳለው የሴቶችን ተፈጥሯዊ ክብርና የሥነ ልቡና ልዕልና እንዳይጎዳ፤ ያለ ምንም መሳቀቅም ዕለታዊ ተግባራቸውን እንዲያከናውኑ የሚያግዝ የንጽሕና አጠባበቅ መንገድ ባልነበረበት ዘመን እንደ ሰው መቆጠር ናፍቋት ትኖር ነበር። ሰዎች ብቻ ሳይሆኑ ሕጉ ራሱ “ማንም ሰዉ ከሥጋው ፈሳሽ ነገር ቢወጣ ስለሚፈስሰው ነገር ርኵስ ነው” “ሴትም ከመርገም ቀን ሌላ ደምዋ ብዙ ቀን ቢፈስስ፤ ወይም ደምዋ ከመርገምዋ ወራት የሚበልጥ ቢፈስስ፤ በመርገምዋ ወራት እንደ ሆነች እንዲሁ በፈሳሽዋ ርኵስነት ወራት ትሆናለች፤ ርኵስ ናት” በማለት ተፀይፏት፣ ገፍቷት፣ አግልሏት ኖረች። ዘሌ. 15 

ይህን ጭንቅ የኖረው ብቻ ያውቀዋል፤ ታሪክንስ ከባለ ታሪኩ በላይ ሊተርከው ለማን ይቻለዋል? እነዚያን አሥራ ሁለት ዓመታት፤ መቶ አርባ አራት ወራት፤ ስድስት መቶ ሃያ አራት ሳምንታት፤ አራት ሺህ ሦስት መቶ ሰማንያ ቀናት፤ መቶ አምስት ሺህ አንድ መቶ ሃያ ሰዓታት፤ ስድስት ሚሊዮን ሦስት መቶ ሰባት ሺህ ሁለት መቶ ደቂቃዎች እንዴት አሳልፋቸው ይሆን? ስድብና ንቀትን ጠግባለች፤ የሚፀየፏትን ምራቅ መቀበል በእርሷ እንደ የዘወትር ሰላምታ ነው። ገንዘቧ አልቋል፤ የልጅነት ባልዋ ጥሏት ሄዷል፤ አብሮ አደጎቿና ቤተሰቦቿ በደም ኩሬዋ ውስጥ ጥለዋት ሸሽተዋል። እርሷ ከቆሙት በታች ሆና ብትሞትም፤ ተስፋዋ ግን አልምተም!!! “ሥጋዬ በተስፋ ያድራል” እያለች መቼና እንዴት እንደሚሰማትና እንደሚመልስላት ወደማታውቀው በለሆሳስ ትጣራላች። በቀናቱ ርዝማኔ ድምጿ ቢሰልልም በዝምታው እምነቷ ቢፈተንም ከመጣራት ግን አታርፍም። መዝ 15 (16)፥9

አንድ ቀን ድንቅ ከተደረገላቸው ሰዎች ወሬ ሰማች። የትኛውንም ዓይነት ደዌ ስለሚፈውሰው ለምፃሞችን ሳይቀር ስለሚዳስሰው ሰማች፤ ስለ ናዝሬቱ ኢየሱስ!!! የእርሷ ዓይነት ችግር ስለ ገጠማቸው ሰዎችና በምን መልኩ እንዳስተናገዳቸው ግን ምንም መረጃ ማግኘት አልቻለችም። ተመኘች . . . ደግሞ አመነታች:: ልታገኘው ፊቱ ልትቆምና ራራልኝ ልትለው ጓጓች . . . ግን ደግሞ ፈራች። ወደ እርሱ ለመቅረብ ለሚሻ ልብ የመንገዱ ጠባይ ይኸው ነው:: ፈውስ በደጇ ሲቀርብ የረሃብ ጠኔ ፀንቶበት ሳለ ምግብ እንደሸተተው ሰው የመዳን ናፍቆቱ አንገበገባት፡፡ ወደ ፊት የሚጠብቃትን እስካሁን ካሳለፈችው ሕይወት የባሰ አድርጎ፤ የኖረችበትን ውርደትም ገጥሟት የማያውቅ አስመስሎ ካለችበት እንዳትንቀሳቀስ ሊያስራት ታገለ። ወሰነች!!! 

የመጀመሪያዎቹን ጥቂት እርምጃዎች ዝሆን ተሸክማ የምትሄድ እስኪመስላት ከብዷት ነበር። ኋላ ግን እንዴት እንደሆነ ልትገልጸው በማትችለው ተአምር ሕዝቡን ሁሉ ጣጥሳ አልፋ ቀሚሱን ልትነካ በሚያስችላት ርቀት ላይ ራሷን አገኘችው። በሥውር ቀሚሱን ዳሰሰች . . . ያለ መሳቀቅ ዳነች!!! 

የነካኝ ማነው? ብሎ ሲጠይቅ ከእርሱ ልትሰወር እንደማትችል ውስጧ ሲነግራት ታወቃት። ቀስ ብላ ሰውነቷን ስታዳምጥ ከረዥም ጊዜ በፊት የምታውቀው ጥንካሬና ጤንነት ተሰማት። ከፊትና ከኋላ አንዳች ነውር እንዳይገኝባት ቀሚሷን ተመለከተች። የሚያሳቅቅ . . . የሚያሸማቅቅ ነገር የለም፤ ሁሉ ደኅና ሆኗል:: ለእርሱ እየተንቀጠቀጠች ሰገደች፤ ለሕዝቡ ቀና ብላ መሠከረች። መልስ ያገኘ ሕይወት ይህ ነው። 

ለሕዝቡ ስለ አዲሱ ሙሽራዋ እንዲህ አለቻቸው :- የልጅነት ፍቅሬ ጥሎኝ ሄደ፤ የእርሱ ፍቅር ግን ከእርጅናዬ አደሰኝ። ንጹሕ ሳለሁ ያቀፈኝ ባሌ በሕመሜ ወራት ተፀየፈኝ፤ እርሱ ግን ከነ ደሜ አቀረበኝ። የራሄልን ዕንባዋን በአርያም የተቀበለ እርሱ የእኔን ደም ያደርቅ ዘንድ ወደ ምድር ወረደ። ደሜ አልቆ ወደ ሞት ጎዳና ስሄድ በመስቀል ላይ እጁን ዘርግቶ በችንካሩ ገመድ (tube) ደሙን ለገሰኝ፤ ወትሮም ደም አንሶት ሕይወቱ አደጋ ለተጋረጠበት የሚለገስ ደም ነውና። በሰው ፊት ይዞኝ ከመወጣቱ በፊት በምሥጢር ጫጉላችን ሰውነቴንና ቀሚሴን አጥቦ አዘጋጀኝ። ሕግ ገፋኝ ፍቅር ግን አቀፈኝ። 

አንቺ ማን ነሽ? ሙሽራሽስ ማነው? ለምትሉኝ በዲያብሎስ የኃጢአት ሾተል ቆስዬ ደሜን ሳዘራ የኖርሁ፤ በአሕዛብ ተንቄ በእኔነቴ ተሳቅቄ የኖርሁ እኔ ቤተክርስቲያን . . . እኔ ምዕመን . . . እኔ ክርስቲያን ነኝ! ሙሽራዬም ኢየሱስ ክርስቶስ ነው! 

በዕለተ ዓርብ ደሜን ያደረቀው መሸራዬ ከደፋው የእሾህ አክሊል በሚንዠቀዠቅ ደም ፊቱ ተሸፍኖ አየሁት። ከእርሱ ውጪ የአይሁድ ጥላቻም ሆነ የሮማ ወታደሮች ጭካኔ ሊታየኝ አልቻለም። እንዲዋጀኝ ቀሚሱን ለያዝኩት ለሙሽራዬ የፊት መሸፈኛ ክንብንቤን ፈትቼ ፊቱን ጠርጎ እንዲሰጠኝ አቀበልሁት። ሴት መሸፈኛዋን የምትገልጥ ሙሽራዋ ፊት ነውና። እኔና እርሱ በደም ተሳስረናል። ውዴ የእኔ እኔም የእርሱ ነኝ። የፊት መሸፈኛዬን በቆይታ ሳያው በልቤ የተሳለው የፊቱ መልክ በደም ታትሞበት ነበር፤ እስከ ወዲያኛው!!!

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

9 አስተያየቶች

  1. ቃለሕይወት ያሰማልን መንግስተ ሰመያት ያውርስል ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልን!

  2. “ሕግ ገፋኝ ፍቅር ግን አቀፈኝ። ”
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን።

  3. “ሕግ ገፋኝ ፍቅር ግን አቀፈኝ። ”
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህራችን።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *