የ“at least” ክርስትና

በእውነታ ላይ የተመሠረተ ምናባዊ ጽሑፍ

በቅርብ በቅዱስ ጋብቻ አንድ ከሆኑ ጥንዶች ጋር ስለ ክርስትና ሕይወታቸው አባታችንን ለማወያየት ፈልገው በቤታቸው ተገናኘን፡፡ በውይይታችን ከተነሡት በርካታ ጉዳዮች የዘመኑን የክርስትና ሕይወት አጉልቶ የሚያሳዩ ሁለት ነጥቦችን እነሆ፡-

የመጀመሪያው ከእንግዶቹ የተነሣው ሐሳብ “ከአንዳንድ ወንድምና እኅቶች ጋር ስለ መንፈሳዊ ሕይወት ስንመካከር በክርስትና ሕይወት ስንኖር ‘at least’ እነዚህ የመሰሉ ነገሮችን ልንፈጽም እንደሚገባ ነግረውናል፡፡ እርስዎስ ምን ይመክሩናል?” በማለት አባታችንን በጠየቋቸው ጥያቄ ውይይታችንን ጀመርን፡፡ 

አባታችን በተቀመጡበት ትንሽ በዝምታ ከቆዩ በኋላ እንዲህ ሲሉ ጀመሩ፡፡

“የጌታ እግዚአብሔር ፈቃዱ የተገለጠባቸውን ቅዱሳት መጻሕፍት በኅሊናዬ ለመዳሰስ ሞከርኩ፡፡ እናም ላገኘው ያልቻልኩት ነገር ቢኖር ‘ቢያንስ (at least)’ በሚል ቀዳሚ ቅጽል የተቀመጠን ትእዛዝ ነው፡፡ መንግሥተ እግዚአብሔርን ለመውረስ የተቀመጠ ‘አነስተኛ መሥፈርት (minimum requirement)’ ምን እንደሆነ ማወቅ ብችል ብዬ አሁንም ለማሰብ ሞከርኩ፤ ግን አሁንም መልስ ማግኘት አልቻልኩም፡፡” አሉን ትክዝ ባለ ድምፅ፡፡ 

“ምክንያቱም…” ሲሉ ቀጠሉ “ምክንያቱም ያ መሥፈርት መንግሥቱን ለመውረስ ካበቃ ‘ዝቅተኛ መሥፈርት’ ሊሆን አይችልም፡፡ ነገር ግን በተለምዶ አንዳንድ መምህራነ ወንጌል ‘ክርስቲያኖች ከሆንን ቢያንስ (at least) ይህን ልንፈጽም ይገባናል’ እያልን ስለምናስተምር፣ የነፍስ አባቶችም ልጆቻችንን ስንመክር ‘ልጆቼ ቢያንስ ይህንና ይህን ለማድረግ ሞክሩ’ ስለምንል ምእመኑን የ‘ቢያንስ (at least)’ ክርስትና ውስጥ አመቻቸነው፡፡ ምእመኑም ለሚበልጠው ጸጋ ከሚተጋ ይልቅ ‘at least’ ይህን ይህን እየፈጸምኩ ነው በማለት ለራሱ የጽድቅ መሥፈርት አስቀምጦ ተዘናጋ፡፡ ከእነቅዱስ ጳውሎስ የተማርነው ግን “ … እኔ ገና እንዳልያዝሁት እቆጥራለሁ፤ ነገር ግን አንድ ነገር አደርጋለሁ፡፡ በኋላዬ ያለውን እየረሳሁ በፊቴ ያለውን ለመያዝ እዘረጋለሁ፡፡” የሚል ነው፡፡ (ፊልጵ. 3÷13)

በመጽሐፍ ቅዱስ ‘አድርግ አታድርግ፤ ሁን አትሁን’ እንጂ፤ ‘at least’ ይህን አድርግ ይህን አታድርግ፤ ‘at least’ ይህን ሁን ይህን አትሁን’ የሚል የለም፡፡ወጥመድ የማይመስሉ የክፉውን ማዘናጊያና የምኞታችንን ማባበያ ትተን “ንቁ! በሃይማኖት ቁሙ፣ ጠንክሩ” (1ኛቆሮ. 16÷13) የሚሉትን የአባቶቻችን የሐዋርያትን ምክር መስማት ካልቻልን ሊውጠን ፈልጎ በዙሪያችን ለሚያገሳው አንበሳ ጥሩ ታዳኝ እንሆናለን፡፡

ለአባታችን ያነሣነው ሁለተኛው ነጥብ ዓለም ዛሬ የሚቀበለው ማስረጃ የሚቀርብበትን ጉዳይ ስለሆነ ይህን አካሄድ ከእምነት ጋር ማስማማት የሚቻልበት ምን መንገድ ሊኖር እንደሚችል ነበር፡፡ ከልምዴ እንደማውቀው አዲስ ነገር ሊነግሩን ሲሉ እንደሚያደርጉት ፈገግታ የተቀላቀለው ረዥም ትንፋሽ አወጡና “በየጊዜው የእግዚአብሔርን ቃል ለማሰማት በቆምኩባቸው ጉባኤዎች ሁሉ እየታዘብኩ የመጣሁት ምእመናኑ በእያንዳንዱ ጉዳይ ላይ ‘ማስረጃ’ እንዲቀርብ ያለው ፍላጎትና መምህራንም ምእመኑን በማስረጃ እያበለጸግን በእምነት ግን እያደኸየን መምጣታችንን ነው፡፡ ይህ በሊቃውንት (በኢትዮጵያ ሊቃውንት ዘንድ ብቻ ማለቴ አይደለም) ዘንድ ‘ቶማሳዊነት’ ይባላል፡፡ ‘ጌታ ተነሥቷል ሲባል ጣቴን በችንካሩ ካላገባሁ፤ በእጆቼም የተወጋ ጎኑን ካልዳሰስኩ አላምንም’ ማለት ነው፤ ለሁሉ ማስረጃ ፍለጋ! ጌታችን ለዚህ መልስ ሲሰጥ “ሳያዩ የሚያምኑ ብፁዓን ናቸው” ነው ያለው፡፡ (ዮሐ. 20)

እምነትና ማስረጃ ፍጹም የተለያዩ መንገዶች ናቸው፡፡ እምነት የማስረጃ ጥገኛ አይደለም፡፡ በራሱ ጸንቶ የቆመና ጸንቶ ለማቆምም መሠረት መሆን የሚችል ነው፡፡ በክርስትና ለሁሉ ነገር ማስረጃ ከፈለግን ከማመን ይልቅ ለመካድ ቅርብ እንሆናለን፡፡ መምህራንም ያሳመንን እየመሰለን በማስረጃ ጋጋታ ከእምነት ምእመኑን እያራቆትነው ነው፡፡(ይህ ሲባል እንደው ጠቅሎ ማስረጃ አያስፈልግም ለማለት አይደለም፤ የማስረጃ ጥገኝነታችን ልኩን እያለፈ መምጣቱ ለእምነት የሚፈጥረውን እንቅፋት ለማመልከት እንጂ፡፡ ለሚያምን “ጸሎተ ሃይማኖት በቂው ነው” እንዲሉ አበው፡፡) ማስረጃ አንድን ነገር እውነት ወይም ሐሰት መሆኑን ያሳውቀናል፡፡ ማስረጃ ከዕውቀት ጋር እንጂ ከእምነት ጋር ባሕርያዊ መስመር አያገናኛቸውም፡፡ በክርስትና በእምነት እንጂ በማስረጃ ምንም ያህል ርቀት እንደማንሄድ ብዙ ማስረጃ ማምጣት ይቻላል፡፡ ግን ከዘረዘርኩ አሁንም ማስረጃ ላቀርብ ነውና በሐሳቤ ተቃርኖ ላይ ልቆም ነው፡፡ ስለዚህ እመን!!!

ይህ በሽታ ሲጀምር አንድ ቃለ እግዚአብሔር በተነገረ ቁጥር ‘ምን ላይ ተጽፏል?’ በማለት ይጀምራል፡፡ ይህ ማለት በሚያስተምረን መምህር ላይ እምነት የለንም ማለት ነው፡፡ ግን እኮ መምህሩ ለጠቀሰው ጥቅስ እንጂ ለሰጠው ማብራሪያና ትንታኔ፣ ላመጣው ትርጓሜና ላመሠጠረው ምሥጢር ማስረጃ አላቀረበም፡፡ ወይስ ጥቅሱን ማሳየቱ ብቻውን ያቀረበውን ትንታኔና የተረጎመውን ትርጓሜ ትክክል ያደርገዋል? ያለው አማራጭ አንድ ነው፡፡ መምህሩን ካመንከው አዳምጠው ካላመንከው አታዳምጠው፡፡ (የኦርቶዶክሳዊው አስተምህሮ ዋና መለያ “understanding scriptures through the eyes of the fathers” – መጻሕፍትን በአበው የትርጓሜ ቅኝት መረዳት የሚል ነው፡፡ አበው ብለን የምንቀበላቸውም ከሐዋርያት ለጥቀው የተነሱ በይበልጥ “በሃይማኖተ አበው” ደገኛ እምነታቸው የተመሰከረላቸውን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያንንና እነርሱን የመሰሉትን ነው፡፡ እንዲህ ዓይነቱን መምህር ለመለየት የአበውን መንገድና ትምህርተ ሃይማኖትን የሚገልጡበትን የአነጋገር ዘይቤ የሚጠቀሟቸውንም ቃላት ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ለአምልኮ መሥዋዕት የሚቀርቡ ከአትክልትም፣ ከአዝርዕትም፣ ከዕፅዋትም እንዳለ ሁሉ ለነገረ መለኮት ማመሥጠሪያ የተመረጡ ቃላትና የአነጋገር ዘይቤም አለ፡፡ እውነተኛ መምህር በኑሮው ብቻ ሳይሆን በንግግር ፍሬውም ይታወቃል፡፡)

በሽታው እያደገ ሲሄድ ምሥጢራትንና በምሥጢራት የምናገኘውን ጸጋ መጠራጠር እንጀምራለን፡፡ ይህም ‘እምነት አልቦ ክርስቲያኖች’ የምንሆንበት ደረጃ ነው፡፡ የሚታይብንም በልማድ የምንፈጽመው ሥርዓት እንጂ በመንፈስ በእውነትና በእምነት የሆነ አምልኮ አይደለም፡፡ የሥርዓት ክርስቲያኖች(Canonical Christians) እንጂ መንፈሳዊ ክርስቲያኖች (Spiritual Christians) ለመሆን እንቸገራለን፡፡ ፍጻሜውም የጸጋው ባለቤት የሆነውን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስን መጠራጠርን ያመጣል፡፡ 

ዛሬ በቤተክርስቲያን ለምናየው ፍሬ ሃይማኖትና መዓዛ ምግባር መታጣት አንዱ ምክንያት ይሄ ነው፡፡ አገልጋዩና ምእመኑ አይተማመኑም፡፡ (አገልጋዩ ከምእመኑ በትምህርተ ሃይማኖት የተሻለ ሆኖ ካልተገኘ፤ ለምእመናን ጥያቄ መልስ ለመስጠት ለሕይወታቸውም አቅጣጫ ለማሳየት የማይበቃ ከሆነ በሹመቱ እንጂ በትምህርቱ ቁጥሩ ከምዕመናን ይሆናል፡፡ “እልል በሉ” ንማ ሁሉም ያውቀዋል፡፡ ሁለተኛው በእምነት፣ በምግባርና በትሩፋት ከእነርሱ ተሽሎ ካልተገኘ ተግሣጹን ይንቁታል ምክሩን ያቃልሉታል፡፡ በመሆኑም ደግ የሃይማኖት መምህር በትምህርቱም በሕይወቱም ላቅ ብሎ መታየት ይኖርበታል፡፡) ስለዚህ የምንማረውም ሆነ የምናስተምረው ወደ ክህደት ለመድረስ ነው፡፡ ሳናውቀው!!!”

ማስታወሻ :- ቀሲስ ታምራት ውቤ የቴዎሎጂ ዲግሪና የሳይኮሎጂ ሁለተኛ ዲግሪ አላቸው:: ከክህነት አገልግሎታቸው በተጨማሪም ደራሲና የሥነ ልቡና ባለሙያ (Clinical Psycologist) ናቸው:: ኤጲፋንያ በተሰኘ ቻናልም በቪድዮ ያስተምራሉ::

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

2 አስተያየቶች

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *