የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ

ገና በአፍላ ዕድሜው እግዚአብሔር በመረጠው ታላቅ ሕዝብ ላይ የነገሠው ጠቢቡ ሰሎሞን በልጅነት ጫንቃው ላይ የወደቀበትን ኃላፊነት እንዴት ሊወጣ እንደሚችል ቢጨንቀው የበጎ ሥጦታዎች ሁሉ ባለቤት የሆነውን የአባቱን የዳዊትን አምላክ ጥበብን እንዲሰጠው ለመነ። ልዑሉም ከእርሱ በፊት ከእርሱ በኋላ የሚነሡ እንዳይተካከሉት ባለ ጠግነትንና መፈራትን ዳረጎት ጥበብን ደግሞ ዋና አድርጎ ሰጠው። የሰሎሞን ትልቁ ተግዳሮት እግዚአብሔር በመረጠው ሕዝብ ላይ መንገሡ ብቻ አልነበረም ይህን ሕዝብ ቀድሞ በንግሥና ሲመራ የነበረው ዳዊትን ያህል የከበረ ሰው መሆኑ ጭምር እንጂ። 

የዛሬ አሳቤ ይህ ጠቢብ ንጉሥ በንግሥና ዘመኑ ስለነበረው ብዙ አስደናቂ ነገር ለመተረክ አይደለም። በጊዜው ከምናየውና ከምንሰማው አንጻር በሕይወቱ መጨረሻ ዘመናት ከተወልን የምክርና የተግሳፅ መጻሕፍቱ በአንዱ ባገኘሁዋት ኃይለ ቃል ቆይታ እንድናደርግ ወደድሁ፤ “የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ” ምሳሌ 11 ፥ 22

ጠቢቡ መልክና ደምግባት ያላት ቆንጆ ሴት ምን ውበቷ ቢያስደነግጥ ጥበብ (ፈሪሃ እግዚአብሔርን ተከትለው የሚመጡ መታመን፣ ትሕትና፣ ትዕግሥት፣ ማስተዋል፣ መልካም ንግግር፣ ትጋትና የመሳሰሉት) ከሌላት በእሪያ አፍንጫ እንዳለ የወርቅ ቀለበት ናት ሲል ያነጻጽራል። ቁንጅና ያለ ጥበብ ያለውን ዋጋ በተረዳ ነገር አሳየን። ይህን መልእክት ውጪያዊ ውበት ጣዖት ሆኖባቸው የራሳቸው የተፈላጊነት ስሜትና የሌሎች ውዳሴ ባሪያ ለሆኑት ትቼ ወደሚበልጠው ልለፍ። 

ሰው በዚህ ዓለም ሲኖር ብዙ በወርቅ ቀለበት ልንመስለው የምንችል ውድ ሥጦታን ከልዑል አምላክ ይሰጠዋል። ድንግልና፣ ትዳር፣ ባለ ጠግነት፣ ዕውቀትና የመሳሰሉት። እነዚህ ሁሉ ግን ጥበብ ካልታከለባቸው በእሪያ አፍንጫ እንደተንጠለጠለ የወርቅ ቀለበት ይሆናሉ። ድንግልና ክብሩን ያጣል፤ ትዳር ይረክሳል፤ ባለጠግነት ለእብደት ዕውቀትም ለጥፋት ይሆናል። አሁንም ይህን በዚህ አቆይቼ ወደ ዋና ጉዳዬ ልሻገር። 

“ነገር በሦስት ይፀናል፤” እንዲል ዛሬ በስሟ ለመጠራት እስኪታፈርባት ድረስ ዜጎቿ የተዋረድንባት ሀገሬ በሦስት ዋና አእማድ (ምሰሶዎች) ጸንታ ትኖር ነበር። እነዚህ ሦስት አእማድ ግብራቸውን ጠብቀው በኖሩባቸው ዘመናት የአንድነት፣ የበረከት፣ የኩራትና የነጻነት መቅደስ ሆና ኖራለች ኢትዮጵያ። እነዚህ በዚህ ልዕልና ኢትዮጵያ እንድትኖር ያደረጓት ሦስቱ አእማድ ክህነት፣ ምንኩስናና ምስፍና (ሀገር ገዢነት) ነበሩ (የአገሬን ገበሬ ረስቼ አይደለም፤ ማጠንጠኛዬ የማኅበረሰብ አእምሯዊ፣ ሥነ ልቡናዊና መንፈሳዊ ማንነት ስለሆነ እንጂ)። 

አንድ በአንድ ልናያቸው እንሞክር :-

ክህነት በኢትዮጵያውያን ማንነት ውስጥ የእምነት፣ የተስፋ፣ የማስተዋል፣ የእርጋታ፣ የደኅንነት፣ የጽናት፣  ወዘተ ምልክት ነው:: በኢትዮጵያውያን ዘንድ በደስታም ሆነ በኀዘን፣ በማግኘትና በማጣት፣ በሰላምና በጠብ፣ በረሃብና በጥጋብ፣ በልደትና በሞት፣ በሰርግና በልቅሶ፣ በመከራና በመደላደል፣ በስደትና በድል ጊዜ ሁሉ ካህናት አሉ። ሕፃናትን በዕውቀት አሳድገዋል፤ ወጣቶችን መንገድ መርተዋል፤ ጎልማሶችን በኃላፊነታቸው ረድተዋል፤ አዛውንትን አስከብረዋል። ከገበሬ ጎጆ እስከ ነገሥታት እልፍኝ ካህናት ነበሩ። 

እነዚያ ካህናት በብዙ ዓመት ልፋት ባጠራቀሙት ዕውቀታቸው፣ ቀን ዕረፍት ሌት እንቅልፍ በማያውቅ አገልግሎታቸው፣ በጾም በጸሎትና በታማኝነት በተገለጠ ሕይወታቸው የታፈሩና የተፈሩ ነበሩ። ለተሸከሙት ቃልና ለተቀበሉት አደራ የታመኑ ስለነበሩ ለቃላቸው የማይታዘዝ አልነበረም። የነፍሱን ለጊዜው ብናቆየው እንኳ በዕለት ተዕለት እንቅስቃሴ ከጓዳ እስከ አደባባይ ለሕዝቡ የኑሮ ሰላምና ደኅንነት ዋስትና ነበር ክህነት። 

አበው በታሪክ እንዳቆዩን ከግራኝ ወረራ በኋላ ሊቃውንቱና ካህናቱ በአብዛኛው በመብራት እየተፈለጉ ተሠውተው የተቀሩትም ዘመነ ሰላም ሲመጣ በራእይ ተገልጦላቸው ቆፍረው ያወጡታል በሚል ጽኑዕ እምነት ቅዱሳት መጻሕፍትንና ንዋያትን ለትውልድ ለማቆየት ከነሕይወታቸው ዋሻ እየተዘጋባቸው አለቁ። የሰላሙ ዘመን ሲመጣ ለጊዜውም ቢሆን ቤተክርስቲያንን የሚከፍትና የሚዘጋ ሕፃናትን የሚያጠምቅ እንዳይታጣ በሚል እሳቤ ለክህነት የሚያበቃውን መሥፈርት የማያሟሉትን መሾም ወይም የጨዋ ክህነት ተጀመረ። የዚህ እርሾ ከተለያዩ ተደራራቢ ምክንያቶች ጋር ተጨምሮ ክብረ ክህነትን አቀለለው። የቤተክርስቲያን ሊቃውንት የፈለገ ችግር ቢኖር እንኳ ” ከእንጨት መርጦ ለታቦት ከሰው መርጦ ለሹመት ” በሚል ሀሳብ እየተመሩ ለከፍተኛ ሹመት (ለአድባራት መምህርነት፣ ለገዳም አበምኔትነት፣ ለእጨጌነት፣ ለንቡረ ዕድነት፣ ኋላም ለጵጵስና ወዘተ) የሚመርጡ በጣም ተጠንቅቀው ነበር ።  

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ቤተክርስቲያንን ከዕውቀት ችግር በተጨማሪ እንደ ነቀርሳ የወረራት ገንዘብ መውደድና ዘረኝነት ከመንፈሳዊ ሕይወት ጨርሶ እንድንራቆት ስላደረገ ክህነትን በይበልጥ እንደ ጵጵስና ያለውን ከፍተኛውን የክህነት ማዕርግ በማይገባቸው ሰዎች ላይ እንዲወድቅ አደረገው። ይህ በመሆኑ መንጋውን ከመጠበቅ ይልቅ የራሳቸው ምቾት የሚያስጨንቃቸው፣ ሥልጣንና ሀብት የሚያስጎመዣቸው፤ በክርስትና አይሁዳዊ ግሪካዊ፣ ሴት ወንድ፣ ጌታ ሎሌ የሚል ልዩነት እንደሌለ ለመረዳት ያሉበት ዕውቀትና የልቡና ክፋት የማይፈቅድላቸው ግብዝ እረኞች ተነሡ። እነዚህ የያዙት ክህነት ነው እንግዲህ የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ ማለት:: 

ሁለተኛው ምንኩስና ነው:: ምንኩስና አንድ ክርስቲያን የግዴታ የሚገባበት ሳይሆን የምርጫ ሕይወት በመሆኑ ዕለት ዕለት ለሚኖረው የተጋድሎ ሕይወት ከፍተኛ ጥብአትና ለመረጠው የሕይወት መስመርም ጽኑ መታመን ሊኖረው ይገባል። ጠቢባን ‘መንኩሶ አለመጽደቅን የሚያህል ኪሳራ የለም’ የሚሉ የመነኩሴ አሳቡ፣ ምኞቱና ሕይወቱ ሁሉ ከሰማያዊው እንጂ ከምድራዊው ጋር መቆራኘት እንደሌለበት ለማስጠንቀቅ ነው። መነኩሴ ለሀብትና ለንብረት፣ ለሥልጣንና ለሹመት፣ ለልብስና ለማዕድ ከጎመዠ፤ ሁሉን በአንድ ዓይን ለማየትም ተስኖት በወገንተኝነት ክፉ ደዌ ከተያዘ ማን መሆኑን ለምን ዓይነት ሕይወትም እንደተጠራ አላወቀም። 

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ተክለሃይማኖት ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በአንድ ወቅት የትውልድ ሥፍራቸው የት መሆኑን ሲጠየቁ ‘እኔ ሀገሬ ኢትዮጵያ መሆኗን ነው የማውቅ፤ ከዚያ ውጪ መነኩሴ ሀገረ ሙላዱ አይጠየቅም’ ብለው መልስ መስጠታቸውን ምንጩን ለጊዜው ማስታወስ ያልቻልሁት መጽሐፍ ላይ ማንበቤ ትዝ ይለኛል። አንድ ሰውም ለቤተክርስቲያን አገልግሎት የቀረበውን ፈተና አልፈው ለቃለ መጠይቅ የደረሱን አንድ መነኩሴ በመጨረሻ ‘ሀገርዎ የት ነው?’ ብሎ ሲጠይቃቸው የትውልድ ሥፍራቸውን በመናገራቸው በፍፁም የመቀጠር እድሉን እንዳያገኙ ቢከራከርም በብዙኃኑ ድምጽ መሸነፉን አጫውቶኛል፡፡ የኚህ ሰው መጨረሻ የሆነው ግን አገልግሎቱን ከመበደል አልፈው የምንኩስና ሕይወትን እስከ መተው መድረስ ነው፡፡

የኢትዮጵያ መነኰሳት ከሀገራቸው አልፈው በሌሎች ሀገራት ጭምር ለምንኩስና ሕይወት ያላቸው ታማኝነት የታወቀ ነበር። አሁንም በገቡት የቃል ኪዳን ሕይወት ጸንተው የሚኖሩ እውነተኞች አሉ። ዛሬ ላይ በይበልጥ በከተማ ልብሱን እንጂ ሕይወቱን የማያውቁት ጨርሶ አርአያ ምንኩስና የማይታይባቸው ግብዞች ክብረ ምንኩስናን ከሚያምኑም ከማያምኑም ሰዎች ልቡና አቀለለባቸው። ምናኔ (ዓለምን መናቅ) በፍቅረ ዓለም ተተክቶ ለሥልጣንና ለሀብት በመቋመጥ ቅዱሱን ሕይወት አጎደፉ።

የቀድሞ መነኰሳት እንኳን በሰብአ ዓለም ቀርቶ በገዳም ትሾማላችሁ ከተባሉ የሚወዱትን የኖሩበትን ገዳም ሳይቀር ጥለው ማንም ወደማያውቃቸው ሌላ ገዳም ይሰደዱ ነበር። በምዕመናን ላይ ሳይፈለጉ አይደለም በስንት አማላጅ ተለምነው ኤጲስ ቆጶስ እንዲሆኑ ግድ ሲሏቸው ምላስና ጆሯቸውን በመቁረጥ ‘አካለ ጎደሎ ለዚህ ሹመት ሊታጭ አይገባም’ ብለው ለሹመት ፊት የነሱ የጽድቅ አርበኞች በነበሩባት ቤተክርስቲያን “ይገባሃል” ሳይሆን “ይገባኛል” ብሎ ራሱን ለሹመት የሚያጭ መነኩሴ ይህቺን የሐዋርያት አጸድ ወረራት። ታዲያ የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ ማለት ይህም አይደል?! 

ሦስተኛው ዐምድ ምስፍና (ሀገር ገዢነት) ነው:: በኢትዮጵያ ላይ ምን ዓይነት ነገሥታት እንደነበሩ ለመተረክ ጊዜው ያጥርብኛል። ከግማሽ ምዕተ ዓመት ወዲህ ግን የገዛ ሕዝባቸውን እንደ ደመኛ የሚያዩ፤ ሀገር መምራት ሕዝብን ማማረር መሆኑን ተቀብለው የሚኖሩ መሳፍንት ተነሡ።   ለከንቱ አእምሮ ተላልፈው ስለ ተሰጡ ወላጆችን ያለ ጧሪ ሀገርን ያለ ተረካቢ እስኪያስቀር በሚዘገንን ደም ከታጠቡ በኋላ ለመተቃቀፍና የድሀይቱን ልጅ ለጦር ለመማገድ በቀሰቀሱበት አንደበት ሲሞጋገሱ ትንሽ ይሉኝታ ያልፈጠረባቸው ላይ ይህቺ የርግማኗ ምክንያት ግራ የገባት ምስኪን ሀገር ወደቀች። የተፈጥሮ ሀብት ሳያንሳት፣ ቅን ዜጋ ሳይጎድላት ልቡናቸው የክፋት ፣ አንደበታቸው የሀሰት እርም የማያውቅ እንደ ተኩላ ይናጠቋት ይዘዋል። ብዙ ትንንሾች ትልቅን ለመጣል ጊዜያዊ ኅብረት ቢያደርጉም በአንድነት ለመኖር ግን ያው ትንሽ አእምሯቸው አይፈቅድላቸውም። ስለዚህ ትልቁን ለመጣል የሚያደርጉት ኅብረት የጥፋታቸው ዋዜማ ነው:: 

ኢትዮጵያ ክህነት ከምስፍና የያዙ፤ ታላላቅ አብያተ መቅደስና አብያተ መንግሥት የገነቡ፤ የሀገር ድንበር ብቻ ሳይሆን የሕዝባቸው ክብር እንዳይደፈር ያደረጉ፤ በሕዝባቸው ከመወደዳቸው የተነሣ ስማቸው የቃል ኪዳን ማሠሪያ መሐላ እስከ መሆን የደረሱ መሪዎች ነበሯት። ሰውን አጋጣሚ ገዢ ሊያደርገው ይችላል መሪ መሆን የሚችል ግን ስሜቱን መግዛትና  ትናንትናን ዛሬንና ነገን አጥርቶ ማየት የሚችል ብቻ ነው:: የራሱ ራእይ የሌለው አጀንዳ አስፈጻሚ ተላላኪ እንጂ እንዴት መሪ ሊሆን ይችላል? ኢትዮጵያ በታሪኳ ለሁከት የምትዳረገው ተላላኪዎች ዙፋን ላይ ሲወጡ ነው:: ይህን እውነታ በነዮዲት ፣ በግራኝ አሕመድና በሱስንዮስ አይተናል። ዮዲት የአይሁድ ፣ ግራኝ የቱርክ ፣ ሱስንዮስ ደግሞ የሮማውያን ተላላኪዎች ነበሩ እንጂ የራሳቸው አጀንዳ አልነበራቸውም፡፡ ከሃምሣ ዓመታት ወዲህ ያለው እውነታም ይኸው ነው::  መሳፍንቱ የኮሚኒዝም፣  የድኅረ ቅኝ ግዛት ሴረኞች፣   የካፒታሊዝም አጀንዳ አስፈጻሚ ናቸው። ይህ አጀንዳቸው እንዳይፈጸም ዋና እንቅፋት ደግሞ የኢትዮጵያዊነት መንፈስ ነው። ኢትዮጵያና ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ሃይማኖት ነፍስና ሥጋ በመሆናቸው ኢትዮጵያዊውን መንፈስ ለመግደልና በሌሎቹ የአፍሪካ አገራት ሕዝቦች እንደሆነ “ስም ያለው ሕያው መሰል ምውት” ለማድረግ የዚህ መንፈስ ምንጭ የሆነችዋን ኦርቶዶክስ ተዋሕዶን ማጥፋት ግድ ይላል። እንግዲህ ኢትዮጵያን የመሰለች ሕዝብ፣ ባህልና መልክዓ ምድር ብቻ ሳይሆን ሌሎች ሊወርሱት የሚችል የማንነት መንፈስ ያላትን ሀገር የመምራት ኃላፊነት በእንዲህ ዓይነት ሰዎች እጅ መውደቁ ነው የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ በሚል ምሳሌ የሚነገር። 

በእኔ ዕይታም ኢትዮጵያ አሁን ላለችበት የእብደት ዘመንና ውጥንቅጡ ለጠፋ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ችግር የተዳረገችው የሦስቱ አእማድ መንቀዝ ነው:: እንግዲህ እንደ ጠቢቡ ቃል የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ ሲሆን የሚታይና የሚሰማው ሁሉ ተስፋ አስቆራጭ የሚሆን እሪያ መቼም ቢሆን የወርቅ ዋጋ የማይገባው ግብሩንም የማይተው መሆኑ ሲሆን፤ መፅናኛው ደግሞ ወርቁ በእሪያ አፍንጫ ላይ መታየቱ ለጊዜው ቢያስከፋም ዋጋውን ግን ሊያረክሰው አለመቻሉ ነው፡፡ የሰማይ አምላክ እስኪያየንና እስኪጎበኘን የወርቁ ዋጋ የገባቸውንም እስኪልክልን ዓይናችን ዕንባን ሳታቋርጥ ከማፍሰስ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?

https://youtube.com/@EpiphaniaTube?si=PNTkqiTwsXLytMYL

ቀሲስ ታምራት የጃንደረባው ሚድያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ረቡዕ የሚነበቡ ይሆናል::

Share your love

10 አስተያየቶች

  1. ”የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ”
    ቃለ ህይወት ያሰማልን

    እኛን እግዚአብሔር የመረጠን ህዝብ፣ መሪዎቹን ልክ እንደ ሰለሞን ጠቢብ ያድርገን-ያድርግልን።

  2. “የወርቅ ቀለበት በእሪያ አፍንጫ” አሜን እግዚአብሔር ይጎብኘን እኛም ተባባሪዎች እንዳንሆን ባለቤቱ ይርዳን!!!
    በእውነት ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን

  3. የሰማይ አምላክ እስኪያየንና እስኪጎበኘን የወርቁ ዋጋ የገባቸውንም እስኪልክልን ዓይናችን ዕንባን ሳታቋርጥ ከማፍሰስ በቀር እንግዲህ ምን እንላለን?

    ቃለ ሕይወት ያሰማልን
    የሰማይ መንግስት ያውርስልን

  4. እግዚአብሔር አምላክ በቸርነቱ ብዛት ሀገራችንን ይታደግልን ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅልን፡፡ ቃለ ህይወት ያሰማልን ቀሲስ

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *