የነፍስ ምግብ

ምንም እንኳን አንዳንድ አባትና እናቶች በይበልጥም ገዳማውያን እግዚአብሔርን እያመሰገኑ ስለሚኖሩ ያለ ምግብና ውኃ ለረጅም ጊዜ መቆየት ቢችሉም፥ አካሄዳችንን ከዓለም ጋር ያደረግን እኛ ግን በተለመደው ሰዓት ካልተመገብን ረሃብና ጥም በቀላሉ ያጎሰቁለናል::  ሰውነታችን በለመደው ሥርዓት በትክክል እንዲሠራ ምግብ እና ውኃን ይሻል። ስለሆነም ከምንም ነገር በላይ የመመገቢያ ሰዓታችን እንዳይዛባ ተጠንቅቀን እንመገባለን።  

 ሰውነታችን እነዚህ ነገሮች እንደሚያስፈልጉት ሁሉ ነፍሳችን ደግሞ የነፍስ ምግብዋ የሆነውን ክርስቶስ ትሻለች፥ ምክንያቱም ሕይወቱን ያለ እግዚአብሔር የሚኖር ሰው የሞተ ሰው ነውና። ይህ እንዴት ነው ቢሉ “በሥነ ፍጥረት እግዚአብሔር ዓሣን መፍጠር በፈለገ ጊዜ ባሕርን፣ ዛፎችን መፍጠር በፈለገ ጊዜ ምድርን እንደዘረጋ፤ ሰውን ሊፈጥር በፈለገ ጊዜ ግን ወደ ራሱ ተመለሰ ከእራሱም ጋር ተነጋገረ። ‘እግዚአብሔር ፣ ‘’ሰውን በመልካችን፣ በአምሳላችን እንሥራ፤ በባሕር ዓሦች፣ በሰማይ ወፎች፣ በከብቶች፣ በምድር ሁሉ ላይ፣ እንዲሁም በምድር በሚሳቡ ፍጡራን ሁሉ ላይ ሥልጣን ይኑራቸው’’ አለ።’ (ዘፍጥረት 1፥26) አንድ ዓሣ ከውኃ ውስጥ ከወጣ እንደሚሞት፣ አንድን ዛፍም ከአፈር ውስጥ ስንነቅለው እንደሚጠወልግ እና እንደሚሞት እንዲሁ የሰው ልጅ ከእግዚአብሔር ከተለየ ይሞታል።”

የተፈጠርነው በእርሱ ፊት እንድንኖር ነውና እግዚአብሔር የተፈጥሮ አካባቢያችን ነው። ከእርሱ ጋር መገናኘት አለብን ምክንያቱም ሕይወት ክርስቶስ ነው።

“ምስኪን ነፍሴ! አልቅሽ፣ ጸልዪ፣ እና የተባረከውን የክርስቶስን ቀንበር በላይሽ ለመሸከም ትጊ፣ እናም በሰማያዊ መንገድ በምድር ላይ ትኖሪያለሽ። ጌታ ሆይ ፣ ብርሃንን እና መልካም ቀንበርን እንድሸከም ስጠኝ ፣ እና ሁል ጊዜም በዕረፍት ፣በሰላም ፣ በደስታ እና ሐሴት እኖራለሁ። ከጌታም ማዕድ የሚወድቀውን ፍርፋሪ እንደሚበላ ውሻ ከሰማያዊው ማዕድ የወደቀውን ፍርፋሪ በምድር ላይ አጣጥማለሁ።” ይላል ከአኃው አንዱ::

በቀን ቢያንስ ሁለት ጊዜ ከእግዚአብሔር ጋር የማይገናኝ ሰው “እግዚአብሔር በሕይወቴ አያስፈልገኝም” እንደማለት ይሆንበታል። በማለዳ ካልጸለይን ቃል አውጥተን አንበለው እንጂ ተግባራችን ክብር ይግባውና “ጌታ በህይወቴ አታስፈልገኝም። ሌሊቱን በራሴ ኃይል በሰላም ተኝቼ አድሬ ተነሥቻለሁ ስለሆነም ቀኑንም እንዲሁ በራሴ ኃይል መዋል እችላለሁ!” እንደማለት ይሆንብናል። ወደ መኝታ ከመሔዳችን በፊት ካልጸለይንም እንዲሁ “ቀኑን በራሴ ኃይል እንደዋልሁ በተኛሁም ጊዜ (ክብር ይግባውና ክርስቶስን) የአንተ ጥበቃ አያስፈልገኝም” እንደማለት ይሆንብናል።

በሌላ በኩል ብዙዎቻችን ህልውናችን በውጫዊ ቁመናችን ላይ የተመረኮዘ ይመስል ስለሱ በይበልጥ እንጨነቃለን። ነገር ግን ልብ ላለ ሰው ከውጪያዊው ቁመናችን ይልቅ የዘላለም ሕይወታችን ህልውና የተመረኮዘው በነፍሳችን ቁመና ነው። በምድር ላይ ነፍሳችንን የሚያሳየን መስታወት ቢኖር ኖሮ ብዙዎቻችን ነፍሳችንን ለማየት ድፍረት ባልኖረን ነበር። ምክንያቱም በዕለት ተዕለት ሕይወታችን በእግዚአብሔር መንፈስ እጥረት ነፍሳችን ጠቁራ እና ቀጭጫ መመልከታቸን ስለማይቀር ነው። ስዊዘርላንዳዊው የሥነ አእምሮ ሐኪም እና የሥነ ልቦና ባለሙያ ካርል ጁንግ :-  “ሰዎች የራሳቸውን ነፍስ ላለመጋፈጥ ሲሉ ምንም ያህል የማይረባ ነገር እንኳን ያደርጋሉ” ይላል::

ስለዚህ ጉዳይ በይበልጥ ለመረዳት ይህን የወንጌል ክፍል እንውሰድ “በዚያን ጊዜ ንጉሡ በቀኙ በኩል ያሉትን እንዲህ ይላቸዋል፤ ‘እናንት አባቴ የባረካችሁ ኑ፤ ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ የተዘጋጀላችሁን መንግሥት ውረሱ፤ ምክንያቱም ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤ እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤ ታርዤ አልብሳችሁኛል፤ ታምሜ አስታምማችሁኛል፤ ታስሬ ጠይቃችሁኛል።” (ማቴ 25: 34-36)

ይህ ቃለ እግዚአብሔር በዋናነት እርስ በእርሳችን መዋደድ/መተሳሰብ እንዳለብን ይናገራል። ይህም ለሌሎች የምናደርገውን ክርስቶስ ለእርሱ እንደምናደርግ አድርጎ ስለሚቆጥረው ነው። ይህንንም በግልጽ ሲነግረን “እውነት እላችኋለሁ፣ ከእነዚህ አነሥተኛ ከሆኑት ወንድሞቼ ለአንዱ ያደረጋችሁት፣ ለእኔ እንዳደረጋችሁት ነው።” (ማቴ 25፥40)። ይህ በእንዲሁ እንዳለ ለታናሾቻችሁ ተብሎ የተነገረውን ከወትሮው በተለየ እና ከዋናው የመጽሐፍ ቅዱስ አንድምታ በተጨማሪ ለነፍሳችን የተባለ አድርገን ብንወስደው ለጉዳዩ ያለንን እይታ ሊቀይረው ይችላል።

01 .የነፍስ ረሃብ እና ጥማት

* እግዚአብሔርም አለ “ተርቤ አብልታችሁኛል፤ ተጠምቼ አጠጥታችሁኛል፤” (ማቴ 25፥35) ነፍሳችን ክርስቶስን መራብ እና መጠማት ብቻ ሳይሆን ክርስቶስ በማጣት (Deficiency of Christ) እየተሰቃየች ነው።

ቅዱስ አትናቴዎስ እንዲህ ይላል :-  “በጎ ምግባር እና መጥፎ ድርጊቶች የነፍስ ምግብ ናቸውና ከእነዚህ ከሁለቱ አንዱን መብላት እና ከሁለቱ ወደ አንዱ ማዘንበል ትችላለች። እንደ ራሷ ፈቃድ ለበጎነት ካደላች በበጎነት፣ በጽድቅ፣ በጨዋነት፣ በየዋህነት እና በጥንካሬ ትኖራለች። ‘የእኔ መብል በሰማያት ያለውን የአባቴን ፈቃድ አደርግ ዘንድ ነው’ ያለው የጌታችን ሁኔታ እንዲህ ነበር (ዮሐ. 4፡34)። ነገር ግን ነፍስ እንዲህ ካልሆነ እና ወደ ታች ዘንበል ካለች፣ ከኃጢአት በቀር ምንም አትመገብም” 

በሌላ በኩል፣ የኢየሱስ ክርስቶስንና የደቀ መዛሙርቱን ንግግር እናገኛለን፡- “‘ጌታ ሆይ፣ ይህን እንጀራ ሁልጊዜ ስጠን’ አሉት። ኢየሱስም እንዲህ አላቸው፡- የሕይወት እንጀራ እኔ ነኝ፤ ወደ እኔ የሚመጣ ከቶ አይራብም በእኔ የሚያምን ከቶ አይጠማም።” (ዮሐ 6፥34-35)

ሥርዓተ ቅዳሴን፣ መዝሙርን፣ ቅዱሳት መጻሕፍትን ማንበብ፣ ወዘተ… ለነፍስ እንደ መብልና መጠጥ ይቆጠራሉ። ነገር ግን ከሁሉም በላይ እርሱ እንደገለጸው መብላትና መጠጣት ያለብን ኢየሱስ ክርስቶስ ራሱን ነው፤ ይህም ቅዱስ ሥጋውና ክቡር ደሙን ነው።

02, የነፍስ እንግድነት

* እግዚአብሔርም አለ “እንግዳ ሆኜ ተቀብላችሁኛል፤” (ማቴዎስ 25፥35) ነፍሳችን በገዛ ሥጋዋ እንግዳ እና ስደተኛ ሆናለች።

ሥጋችን ስንሞት የምንለየው የነፍስ ዋሻ /ልብሷ በመሆኑ ነፍሳችንን በተሻለ ሁኔታ መንከባከብ በተገባን ነበር፤ እኛ ግን ነገሩን የተገላቢጦሽ አደረግነው ወንጌል “ሕይወቱን የሚወድድ ያጣታል፤ በዚህ ዓለም ሕይወቱን የሚጠላ ግን ለዘላለም ሕይወት ይጠብቃታል” ትላለች። (ዮሐ 12፥25)።

በእውነት፣ በዚህ ዓለም ውስጥ እንግዶች መሆናችንን ማሰብ አለብን። በተስፋይቱ ምድር ለመኖር በመዘጋጀት ነፍሳችንን በደግነት መንከባከብ አስፈላጊ ነው። በሰው አይኖች ያልታየች፣ ጆሮ ያልሰማት እና በሰው ልቡናም ያልታሰበች ውብ አለም፣ በእግዚአብሔር ፊት፣ በመላእክቱ እና በቅዱሳኑ ተከበን፣ መንፈሳችን ከዚህ አላፊ መኖሪያ ከወጣ በኋላ የዘላለም መኖሪያንው ያገኛል።

03, የነፍስ መታመም

– “እግዚአብሔርም አለ “ታምሜ አስታምማችሁኛል፤” (ማቴዎስ 25:36) ነፍሳችን ይህ ዓለም አስመስሎ በሚሰጠን መርዝ ታምማለች፣ አንዳንድ ጊዜ ጌታ ነፍሳችንን ከኃጢአት/ ከነፍስ ሕመም ለማንጻት ጊዜያዊ ቅጣትን ይልካል። “እግዚአብሔር የሚወደውን ይገሥጻልና” (ዕብ. 12፡6)።

እያንዳንዱ ኃጢአት “የወደዳቸውን እስከ መጨረሻ ወደዳቸው።” ተብሎ በተነገረለት የፍቅር አምላክ ላይ የሚደረግ አመጽ ነው፤ ይህም ነፍሳችንን በራሳችን እኩይ ተግባር በሚደርስብን ቁስል እና ስቃይ እንድትታመም ያደርጋታል። (ዮሐ. 13፥1)

በዚህ ከሕይወት ወደ ሞት በምናደርገው ጉዞ በኃጢአት እየተበላሸን፣ የዘላለም ሞት እያንዣበበ፣ ሕይወታችን ከሆነው ከክርስቶስ ያርቀናል። እግዚአብሔርም ይህን ችግራችንን አውቆ ለነፍሳችን ፈውስ ይሆን ዘንድ ደዌን/ መከራ እና ኀዘንን ለሥጋችን ይልካል።

አንድ አባት የሆኑት ስለዚህ ኀዘን / ሕመም ሲናገሩ “ሕመም ወይም ኀዘን፣ ከእግዚአብሔር ሲመጣ፣ ለነፍሳችን እንደ መራራ መድኃኒት ነው፣ ሥጋዊ ጾሮቿን፣ አሉታዊ ልማዶቿን፣ እና ዝንባሌዎቿን ያክማል” የክርስቶስ ሥጋ እና ደም ነፍስን መፈወሱ እንዳለ ሆኖ ለዚህ ፈውስ እንበቃ ዘንድ የሥጋ በሽታን/ ኀዘንን መታገሳችን በስተመጨረሻ በክርስቶስ ሥጋ እና ደም የምናገኘውን ፈውስ ከምንም በላይ እንድናከብረው እና ትልቅ ቦታ እንድንሰጠው ይሆንልናል ይህም እውነተኛ ሰላምን ያድለናል።

ስለዚህ ጥቅም ስላለው ሕመም / ኀዘን ቅዱስ ጳውሎስ ሲናገር “አሁን ግን ደስ ብሎኛል፤ ደስታዬም ስላዘናችሁ ሳይሆን፣ ሐዘናችሁ ንስሓ ለመግባት ስላበቃችሁ ነው፤ ምክንያቱም ሐዘናችሁ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ እንጂ ከእኛ የተነሣ ምንም አልተጐዳችሁም። እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነ ሐዘን ወደ ድነት ለሚያደርስ ንስሓ ያበቃል፤ ጸጸትም የለበትም። ዓለማዊ ሐዘን ግን ለሞት ያበቃል። ይህ እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሆነው ሐዘን እንዴት ያለ ትጋት፣ እንዴት ያለ መልስ የመስጠት ችሎታ፣ እንዴት ያለ ቍጣ፣ እንዴት ያለ ፍርሀት፣ እንዴት ያለ ናፍቆት፣ እንዴት ያለ በጎ ቅናት፣ እንዴት ያለ ተግሣጽ እንዳስገኘላችሁ ተመልከቱ። በዚህም ጕዳይ ንጹሓን መሆናችሁን በሁሉ ረገድ አስመስክራችኋል።” በማለት በትዕግሥት ካለፍነው ወደ ተሻለ ነገር እንደሚያደርሰን ይናገራል። (2 ቆሮ 7፥9-11)።

04, የነፍስ መታሰር

– “እግዚአብሔርም አለ “ታስሬም ወደ እኔ መጥታችሁ ጠይቃችሁኛልና” ቃሉ ከሥጋዊ እስራት በላይ ይናገራል፣ ይህም በዓለም ማራኪ ነገሮች የነፍሳችንን መታሰርን ያመለክታል። ነፍሳችን ነጻነትን ትሻለችና።

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሳልሣዊ ስለ ነፍስ ነጻነት ሲያስተምሩ ይህ ነፃ መውጣት መንፈስ ከሥጋ ስለመለያየት ሳይሆን በውስጥ ካሉ ሸክሞች ስለመላቀቅ እንደሆነ ያን ጊዜ ብቻ ጥልቅ ሰላምን ማግኘት እና ያለሸክም እንደ እግዚአብሔር ልጆች ሕይወትን መኖር እንደምንቸል አስቀምጠዋል።

ይህን አስብበት፦ ከጥምቀት በኋላ፣ ከአብራከ መንፈስ ቅዱስ ስንወለድ ዳግማዊ አዳም ክርስቶስ ሰው ሆኖ በምድር በተመላለሰ ጊዜ የነበረውን ንጽህና እንላበሳለን በጸጋ የአምላክ ልጆች፣ የጸጋ አምላክም እንሆናለን። ይሁን እንጂ ዓለም፣ ልማዷ እና አካባቢያችን ቀስ በቀስ ያጎድፈናል። አለም ወደ አምላካችን የምናደርገውን ጉዞ በሚያደናቅፉ ስሜቶች እና ፈተናዎች ኃጢአትን ከሥጋችን ጋር አንድ ይሆን ዘንድ ታስተምረዋለች።

በፍቅሩ የተማረኩ ሁሉን ስለ እርሱ ብለው የሚያደርጉ የእግዚአብሔር ልጆች ከዚህ ሁሉ ነፃ መውጣት፣ ነፍሳቸውን ከዓለምና ከአካባቢው እስራት እንዲሁም ከስሜትና ከአለም ጥበብ ለመላቀቅ ይተጋሉ። እኛም ይህን አርአያ ተከትለን ነፍሳችንን መንከባከብ ብቻ ሳይሆን ከዓለም ወኅኒ ነፃ ማውጣት አለብን። ክርስቶስ በወንጌል “እውነት እላችኋለሁ፣ ካልተመለሳችሁ፣ እንደነዚህ ህፃን ካልሆናችሁ ወደ መንግሥተ ሰማያት ከቶ አትገቡም።” (ማቴ 18፥3)። ብሏልና መንፈሳችን ከምድራዊ ሰንሰለት ነፃ አድርገን፣ ሳትታሰር ወደ እግዚአብሔር እንድትበር መታገል አለብን። ታድያ በዚህ የማይቋረት ትጋት ውስጥ ሆነን ነፍሳችንን ነፃ ስናደርጋት፣ ክርስቶስን መስለን ንጽሕናን ተላብሰን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንቀርባለን።

05, የነፍስ መራቆት

– [ ] እግዚአብሔርም አለ “ታርዤ አልብሳችሁኛልና፤” በተመሳሳይ፣ ነፍሳችን ጸጋ እግዚአብሔርን ሲርቃት ትታረዛለች፣ በኃጢአተኝነት ብርድ ውስጥ ሆና ትንቀጠቀጣለች።

“እንግዲህ የተቀደሳችሁና የተወደዳችሁ የእግዚአብሔር ምርጦች እንደ መሆናችሁ ርኅራኄን፣ ቸርነትን፣ ትሕትናን፣ ጨዋነትንና ትዕግሥትን ልበሱ፤” (ወደ ቆላስይስ 3፥12)። ይህም ልብስን ለሥጋችን ብቻ ሳይሆን መልካም ሥራን ነፍሳችን መልበስ እንዳለብን ሲነግረን ነው። በሌላ ቦታም “ይልቁንም ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን ልበሱት፤ ምኞቱንም ይፈጽም ዘንድ ለሥጋ በዐሳባችሁ አትመቻቹለት።” (ወደ ሮሜ 13፥14)። ሲለን፣ ልብሱ በጨርቅ ሳይሆን በመንፈሳዊነት መቃኘትና መለኮትን መጎናጸፍ እንዳለብን ይጠቁመናል።

የሐዋርያው ጳውሎስ እንዲህ ይለናል “እንግዲህ በመንፈስ ኑሩ እላለሁ፤ የሥጋንም ምኞት አትፈጽሙም። ሥጋ መንፈስ የማይፈልገውን፣ መንፈስም ሥጋ የማይፈልገውን ይመኛልና፤ እነዚህ እርስ በርሳቸው ስለሚጋጩ፣ የምትፈልጉትን አታደርጉም። በመንፈስ ብትመሩ ግን፣ ከሕግ በታች አይደላችሁም። የሥጋ ሥራ ግልጽ ነው፦ ይኸውም ዝሙት፣ ርኩሰት፣ መዳራት፣ ጣዖትን ማምለክ፣ ሟርት፣ ጥላቻ፣ ጠብ፣ ቅናት፣ ቍጣ፣ ራስ ወዳድነት፣ መለያየት፣ አድመኝነት፤ ምቀኝነት፣ ስካር፣ ዘፋኝነት፣ እንዲሁም እነዚህን የመሰለው ነው። አስቀድሜ እንዳልሁ፣ አሁንም አስጠነቅቃችኋለሁ፤ በእንዲህ ሁኔታ የሚኖሩ ሁሉ የእግዚአብሔርን መንግሥት አይወርሱም።” (ገላትያ 5፥16-21)

ልክ ማየት ችግር ያለበት ሰው የተሻለ ለማየት መነፅርን እንደሚያደርግ፣ እኛም በመንፈስ ለመመላለስ ጌታ ኢየሱስ ክርስቶስን መልበስ አለብን። ይህ ድርጊት ነፍሳችንን የሚፈውስ ብቻ ሳይሆን ነፍሳችንንም ሆነ ከእግዚአብሔር ጋር ያለንን ግንኙነት ከሚጎዱ ኃጢአቶች የሚጠብቀን ነው። ከዚህም በላይ፣ ነፍሳችንን ተንከባክቦ፣ መንፈሳዊ እድገትን እና ትሩፋንን ያላብሰናል።

ይህም ልክ ቅዱስ ጳውሎስ በሚያምር ሁኔታ እንደገለጸው “የመንፈስ ፍሬ ግን ፍቅር፣ ደስታ፣ ሰላም፣ ትዕግሥት፣ ቸርነት፣ በጎነት፣ ታማኝነት፣ ገርነት፣ ራስን መግዛት ነው። እንደነዚህ ያሉትንም የሚከለክል ሕግ የለም። የክርስቶስ ኢየሱስ የሆኑት ሥጋን ከክፉ ምኞቱና መሻቱ ጋር ሰቅለውታል። በመንፈስ የምንኖር ከሆን፣ በመንፈስ እንመላለስ።” ነው። (ወደ ገላትያን 5፥22-25)። እነዚህ በጎ ተግባራት በመንፈስ መመላለስ የሚያስገኛቸው ፍሬዎች ሲሆኑ ይህም ከአምላክ ጋር የተገናኘች ነፍስ የምትላበሰው/ መገለጫዎቿ ናቸው። በክርስቶስ ኢየሱስ ሆና መንፈሱ የምትመላለስ ነፍስ ደግሞ፣ ከአምላክ ትእዛዝ ጋር ተስማምታ ሥጋዊ ምኞቶቿንም ድል ማድረግ ትችላለች።

ቅዱስ ዻውሎስ “እውነተኛ በሆነው ጽድቅ እንዲሁም ቅድስና እግዚአብሔርን እንዲመስል የተፈጠረውን አዲሱን ሰው እንድትለብሱ ነው።”

(ኤፌሶን 4፥24)። ሲልም በጽድቅ ኑሮ የእግዚአብሔር አምሳል የሆነውን አዲሱን ማንነት በመላበስ፣ ነፍሳችንን ከመለኮት ጋር በማስተካከል፣ መንፈሳዊ ማንነታችንን በማሳደግ በመንፈስ በጎነት እናበራለን። ይህ ተግባር እኛን ብቻ የሚለውጥ ሳየሆን፣ ልክ ክርስቶስ “እናንተ የዓለም ብርሃን ናችሁ፤… በተራራ ላይ ያለች ከተማ ልትደበቅ አትችልም፤ እንደዚሁም ሰዎች መልካሙን ሥራችሁን አይተው በሰማይ ያለውን አባታችሁን እንዲያከብሩ ብርሃናችሁ በሰዎች ፊት ይብራ።”  (ማቴዎስ 5፥14፣ 16)። እንዳለው ከአምላክ ጋር ባለን ግንኙነት የተነሳ ፍቅራችን፣ ሰላማችን እና ደግነታችን በዙሪያችን ያበራል።

ይህ ብርሃን ግን ከኛ የመነጨ ሳይሆን ልክ ብጹህ ወቅዱስ አቡነ ሺኖዳ ሣልሳዊ ክርስቶስን በፀሐይ እኛን በጨረቃ መስለው እንዳስተማሩት “በውስጣችን የምናገኘው ማንኛውም በጎ ነገር ከእኛ ሳይሆን ከእግዚአብሔር ብቻ ነው ምክንያቱም እርሱ ብቻ በመጨረሻ ጥሩ፣ፍጹም እና ቅዱስ ስለሆነ ‘ከአንዱ በቀር ቸር ማንም የለም።’ ( ማቴ. 19:17)። ብርሃናችን እንደ ጨረቃ ነው እና ሙሉ ጨረቃ እስክሆን ድረስ ብርሃናችን ሊጨምር ይችላል ነገር ግን ጨረቃ ጨለማ ሳተላይት እንደመሆኗ መጠን ብርሃኗን ከፀሐይ ካላገኘች በራሷ ብርሃን የላትም። እኛም ልክ ያለፀሐይ ጨረቃ በባሕርይዋ ጨለማ እንደሆነች  ያለ ክርስቶስ ብርሃንነት ኃጢአት እና ክፋት እንጂ መልካም ነገር በውስጣችን የለም።

ይህ ሁሉ ሲባል ግን መዘንጋት የሌለብን የሥጋን ድርሻ ለማጣጣል አልያም ሥጋ ወደኋላ የሚያስቀረን ባዕድ ነገር ነው ለማለት አይደለም:: ይልቁንም አድልዎአችን ወደ ነፍስ እንዲሆን እና ሥጋ እና ነፍሳችንን ማቻቻል እንዳለብን ለመጠቆም ነው:: 

ስለዚህ ውሕደትም ብፁዕ አውግስጢኖስ ሲያስረዳ “ሶዲየም ክሎራይድ በሁለት ንጥረ ነገሮች የተዋቀረ ነው። ክሎሪን እና ሶዲየም ሁለቱም መርዛማ እና ገዳይ ናቸው። ግን አንድ ላይ ተጣምረው ለዕለታዊ ምግባችን አስፈላጊ የሆነውን ጨው ይፈጥራሉ። ከዚህም በላይ ክርስቲያን በሁለት አካላት ማለትም በመንፈስና በአካል የተዋቀረ ነው።  በኃጢአት ምክንያት ከተለያዩ ሰላማቸውን ያጣሉ እንደ ሙታንም ይሆናሉ በዚህም ይህ ሰው ለሌሎች እንቅፋት ይሆናል። ስለዚህ ጌታ ኢየሱስ በመንፈሱ እውነተኛ ሰላም ይሰጠን ዘንድ ይገኛል። 

ጌታ መንፈስንም አካልንም የፈጠራቸው ለአንድ የተዋሐደ አንድነት እንዲገዙ አድርጎ ነው፤ ይህም የሰው ልጅ ሁሉ ለሌሎች ሰዎች ጣፋጭነት ምስጢርና የእውነት ምስክር ይሆን ዘንድ ነው። መንፈስ አካልን በመንፈሳዊነት እንደሚመራው ሁሉ አካሉም በተራው ሲቀደስ መንፈሱን ይረዳዋል፣ ይደግፈዋል ያ ከሆነ ሰው በመንፈስም በአካልም በመቀደስ ይኖራል። በውስጡ ያለውን አንድነት በጌታ የእግዚአብሔርንም ሥራ በሌሎች ፊት ያውጃል። በዚህ ዓለም ውስጥ እንግዶች ነን ስለዚህ ነፍሳችንን የምታርፍበት ቦታ(ሥጋችን) ለነፍሳችን የተስማማ መሆን አለበት።  ጌታ ራሱ የነገረንን አድምጡ “ከእኔ ተማሩ እኔ የዋህ በልቤም ትሑት ነኝና ለነፍሳችሁም ዕረፍት ታገኛላችሁ።” (ማቴ.11፥29)። በዚህች ምድር ላይ ክርስቶስን ማዕከል ያላደረገ ዕቅድ አቅጣጫ የሌለው ጉዞ ነው፤ ይህም ትርፉ ድካም እንዲሁም ከንቱ ነው” በማለት ያስቀምጠዋል።

Share your love

6 አስተያየቶች

  1. “መንፈሳችንን ከምድራዊ ሰንሰለት ነፃ አድርገን፣ ሳትታሰር ወደ እግዚአብሔር እንድትበር መታገል አለብን። ታድያ በዚህ የማይቋረጥ ትጋት ውስጥ ሆነን ነፍሳችንን ነፃ ስናደርጋት፣ ክርስቶስን መስለን ንጽሕናን ተላብሰን ወደ መንግሥተ ሰማያት እንቀርባለን።” … ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምሕር።

  2. የሁላችንም ድክመታችንን መለስ ብለን እንድናይ የሚያደርግ ትምህርት ነው ቃለ ህይወት ያስማልን ወንድሜ !!!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *