የሚያደክሙ አጽናኞች

የኢዮብን መጽሐፍ ለመጀመሪያ ጊዜ ያነበብኩት ምንአልባትም የሃይስኩል ተማሪ እያለሁ ነው። ምዕራፍ ሁለትን እንደጨረስኩ ግን ከዛ በኋላ ምን እየተካሄደ እንደሆነ ለማወቅ ግራ ነው የገባኝ። በተለይ የመጨረሻው ምዕራፍ ፵፪ ላይ ስደርስ እግዚአብሔር በኢዮብ ከመናደድ ይልቅ በሦስቱ ወዳጆቹ ንግግሮች ተቆጥቶ ኢዮብን ስለእነርሱ እንዲጸልይላቸው አዘዘው።

ከዛ በኋላ በአንድ በኩል ያነበብኩትን ያልተረዳሁ ሰው አድርጌ ራሴን ቆጠርኩት ፥ ትንሽ ቆይቶ ደግሞ የምሰማቸው ስብከቶች ሁሉ እግዚአብሔር እንዳደረገው የኢዮብን ወዳጆች መውቀስ እንጂ የተናገሩትን ነገር እየዘረዘሩ ያደረጉት ስህተት ይሄ ነው የሚለኝ አላገኘሁም። ከዛም ብሶ በየሰው ቤቱ ግርግዳ  ላይ የማያቸው ከኢዮብ መጽሐፍ የወጡ ጥቅሶች ፥ እነዚህ የኢዮብ ወዳጆች የተባሉት የተናገሩት ነበር።ለምሳሌ በጣም ከታዋቂው አንዱ በልዳዶስ የተናገረው ይሄ አንዱ ነው “ጅማሬህ ታናሽ ቢሆንም እንኳ ፍጻሜህ እጅግ ይበዛል።”(ምዕ ፰፥፯)። እኛ ብቻ አይደለንም የኢዮብን ወዳጆች ንግግር በመጥቀስ የምንጽናናው፣ ቅዱስ ጳውሎስ ሳይቀር ለቆርንቶስ ሰዎች በጻፈላቸው የመጀመሪያው መልዕክቱ ቴማናዊው ኤልፋዝ የተናገረውን ንግግር ጠቅሶ ነበር ያስጠነቀቃቸው። እንዲህ የሚለውን የኤልፋዝ ንግግር  “ጠቢባንን በተንኰላቸው ይይዛቸዋል፤ የጠማሞችንም ምክር ይዘረዝራል።” “እርሱ ጥበበኞችን በተንኰላቸው የሚይዝ፤ … ተብሎ ተጽፎአልና።” (፩ኛ ቆሮ ፫፥፳)።

የኢዮብ ወዳጆች ብዙ የሚናገሩት ነገር ልክ ነው። ምንአልባትም ሁሉም። ለዚህ ነው በዛ በእውቀትም በመንፈሳዊ ማንነትም ያልዳበረው ማንነቴ የእነዚህን ሰዎች ስህተት በእምነት ከመቀበል ውጪ ምንም ከንግግራቸው እንከን ያላገኘበት። ጭራሽ ለእኔ አስጨናቂ የነበሩት የኢዮብ ንግግሮች ነበሩ። በተለይ ኢዮብ ራሱን ጻድቅ ማድረጉ  “በውስጥህ ኃጢአት ሰርተኸ ሊሆን ይችላል ግድ የለህም ንስኸ ግባ” ብለው ሲመክሩት የሚሰጠው መልስ ብርታት ለእኔ አዕምሮ የሚጸንን ነበር። “እስክሞት ድረስ ፍጹምነቴን ከእኔ አላርቅም። ጽድቄን እይዛለሁ እርሱንም አልተውም፤ ከቀኖቼም ሁሉ ስለ አንዱ ልቤ አይዘልፈኝም።” (ኢዮ ፳፯፥፭)።

ኢዮብ በተግባር ብቻ አይደለም በሀሳቡ ሳይቀር መተላለፍ እንደሌለበት ነበር የተናገረው። ያ ብቻ ግን አይደለም ኢዮብ እግዚአብሔርን ያደረከው ፍትሐዊ አይደለም ለማለት እና ከእሱ ጋር ለመከራከር ሁሉ ጠይቋል። “ከእግዚአብሔርም ጋር ለመዋቀስ እሻለሁ።” (ኢዮ ፲፫፥፪) እና ምዕ ፳፫)። የመንፈሳዊ ህይወት ትህትናን እኔ ከማውቀው እና ከተማርኩበት ውጪ ነበር ከኢዮብ አንደበት ሲወጣ ያነበብኩት።

ኢዮብ ያን ሲናገር ዛሬ ባደምጠው ግን ይህንን ነበር የምለው “አንተ እማ እንዲህ ባትሆን ነበር የሚገርመኝ።” የሲ ኤስ ሉዊስ መፅሐፍ ነው አንድም ይሄንን የአስተሳሰብ ዝንፈት ያጠራልኝ። ለምሳሌ ብዙ ቅርንጫፍ የሌለው ዛፍ ብትመለከቱ ወይም ጠማማ ድንጋይ ብታዩ ይላል ፥ ጥላ ፈልጋችሁ ከሆነ ያን ዛፍ መጥፎ ነው ትሉታላችሁ ወይም ደንጋዩን ለአንዳች ዓላማ ለመጠቀም አስባችሁ ከሆነ ያ ድንጋይ እናንተ የምትፈልጉት ዓይነት ቅርጽ ስለሌለው መጥፎ ድንጋይ ነው ትሉታላችሁ። እያላችሁ ያላችሁት ግን ዛፉም ሆነ ድንጋዩ ለእናንተ ዓላማ የሚስማማ አይደለም እንጂ በራሳቸው መጥፎ ሆነው አይደለም። ዛፉም ሆነ ድንጋዩ ተፈጥሮአቸውን ነው ያከበሩት። በዛ የዓየር ጸባይ ሁኔታ ውስጥ እና አካባቢ መሆን የሚገባቸውን ነው ሆነው የተገኙት። ስለዚህ ከራሳችን ጥቅም አንጻር መጥፎ የምንለው ነገር ልክ ጥሩ እንደምንለው ዛፍ እና ድንጋይ ተፈጥሮአቸውን ያከበሩ ጥሩዎች ናቸው። ሚዛናችን ነበር የከፋፈላቸው።

በተመሳሳይ የኢዮብ ንግግር የከበደኝ የወዳጆቹ ስህተት አልታይ ያለኝ የእኔ ፈጣሪን ያየሁበት፣ መንፈሳዊነትን የተረዳሁበት መነጽር ነበር።

ምን ፈልጌ ወደ ኢዮብ መጽሐፍ ሄድኩኝ ነበር ቁምነገሩ። ወደኢዮብ መጽሐፍ የሄድኩት አንድ በዓለም አንደኛ ሀብታም እና ባለጸጋ የነበረ እግዚአብሔርን የሚያምን ሰው ፥ ያለውን ነገር፣ ሰውነቱን ሳይቀር አጥቶ እንኳ “እግዚአብሔር ሰጠ እግዚአብሔር ነሳ። ሁሉን በሱ እችለዋለሁ ፥ የሆነብኝ ነገር ሁሉ ለበጎ ነው። ሁሉን በደስታ እቀበላለሁ። የሱ እና ከሱ እስከሆነ ድረስ አላማርርም። ይሄን ፍርድ አልጠይቅም ምክንያቱም እሱ እግዚአብሔር ነው” የሚል እና በመጨረሻ ካለው እጥፍ ተጨምሮ የተሰጠው በአዕምሮዬ የፈጠርኩትን ኢዮብን ፍለጋ ነበር የሄድኩት።  በእነዛ ፳፬ ምዕራፎች (ኢዮብ የተናገረበትን ብቻ በመቁጠር ነው) ያገኘሁት ኢዮብ ግን በዓውደምህረት ያልተማርኩት የማላውቀው እውነተኛው ኢዮብን ነበር። ስለዚህ እንደኢዮብ ወዳጆች እኔም ግራ በመጋባት ነበር ያን መጽሐፍ ያጠናቀኩት።

ሌላው በድጋሚ በዚህ መጽሐፍ ላይ ያለኝን ፍላጎት የቀሰቀሰው ካርል ዩንግ ነበር። ዩንግ አህዛብን አፈታሪክ ልክ እንደ ትንቢት ከክርስቶስ ጋር እንዳስተዋወቃቸው እኔንም ከእውነተኛው ኢዮብ ጋር አስተዋወቀኝ።

ይሄን ሁሉ ካልኩኝ በኋላ ግን ወደ ዋናው ነጥቤ ስመለስ ለዛሬ ስለኢዮብ ብዙ አልላችሁም። ስለወዳጆቹ እንጂ። የኢዮብ ወዳጆችን መረዳት በሆነ መጠንም ኢዮብን መረዳት ነው። መሳት የሌለብን ነገር ኢዮብ ሰዎች ጠረኑን ሸሽተው በራቁት ሰዓት፣ የራቁት ደግሞ የእናቱ ልጆች ሳይቀሩ ናቸው (በመከራቸው የረዳቸው ሳይቀሩ ናቸው የሸሹት)፣ ለቀናት በዝምታ ከዛም በተግሳጽ ትንፋሹ እና ጠረኑ ሳይቀረናቸው ከጎኑ ያልተለዩት እነዚህ ወዳጆቹ እንደሆኑ ነው።

ሲቀጥል እነዚህ የታላቁ ኢዮብ ወዳጆች ናቸው:: ኢዮብ ከማን ጋር ሊወዳጅ እንደሚችል ለማወቅ ከፈለጋችሁ ልጆቹ በዖፅ ምድር ከአንዱም ጋር ወዳጅነት እንዳልመሰረቱ እና እርስ በእርሳቸው ብቻ እየተጠራሩ እንደሚገባበዙ ማስተዋል ይበቃል። ይሄም በኃጢአተኞች መካከል እየኖሩ ከእነርሱ ጋር በመሆን ስብዕናቸውን ላለማቆሸሽ ነበር። ኢዮብ ልጆቹ ኃጢአትን በልባቸው ይሰሩ ይሆናል ብሎ ይሰጋ ስለነበር (በተግባር አይደለም) ለዚህም መስዋዕት ያቀርብ ነበር። ይሄ ማለት የኢዮብ ወዳጅን የሚምርጥበት መስፈርት ከልጆቹ በላይ ምን ያህል እጥፍ እንደሚሆን እንድታዩ ነው።

ወዳጆቹ ባሳዩት የነገረ ሐይማኖት እውቀት እና ኢዮብን ለመክሰስ ባሳዩት ድፍረትም በምን ያህል የንጽህና ሕይወት እንደሚኖሩ መገመት ከባድ አይደለም።

ስለዚህ በኢዮብ መጽሐፍ ውስጥ የምታገኙት ንግግሮች በዓለም ላይ ባሉ የመጨረሻ የጽድቅ ጽንፍ ላይ በደረሱ አራት ሰዎች መካከል ነው። ኢዮብ የመጨረሻ በደል አልቦው ሲሆን ወዳጆቹም እንደሱ በታላቅ ጽድቅ የሚኖሩ ነበሩ። ያ ብቻ ግን አይደለም የእናቱ ልጆች የሸሹትን ኢዮብን በዝምታ ለሰባት ቀን አብረው አመድ ለብሰው አፈር ላይ ተቀምጠው ሊያጽናኑትም የፈቀዱ ነበሩ። ያ ብቻ ግን አይደለም ኢዮብ አንደበቱን ከፍቶ የእግዚአብሔርን ፍርድ እስከሚጠይቅ ድረስ አንዳች ያላሉ ታላላቅ ሰዎች ናቸው። ስለዚህ የምናወራው በምዕራፍ ፵፪ ላይ ባገኘነው ቁንጽል እውቀት ብቻ መሆን የለበትም።

ስለእነዚህ ወዳጆቹ በማተት ብቻ አንድ ትልቅ ፅሁፍ/መፅሐፍ ማውጣት ይቻላል ቢሆንም በፍጥነት ወደ ዛሬው ርዕሴ ልመለስ::

የሚያደክሙ አፅናኞች

ምንድነው የኢዮብ ወዳጆች ያደረጉት፣ ምንድነው የተረዱት፣ ምንድነው የሆነው ነገር? መጀመሪያ ኢዮብ ምን አላቸው የሚለውን እንይ።

“እናንተ ሁላችሁ የምታደክሙ አጽናኞች ናችሁ።” (ምዕ ፲፮፥፪)። ኢዮብ ምናለ ዝም ብትሉ፣ ምናለ ባትናገሩ እያለ ነበር በመጨረሻ የለመናቸው። ቁምነገሩ እሱ አይደለም። ቁም ነገሩ እነዚህን የመሰሉ ቃለ እግዚአብሔርን አጥርተው የሚያውቁ፣ በምግባራቸውም የበረቱ ሰዎች እንደምን ኢዮብ “በቁስሌ ላይ ቁስል ጨመሩብኝ” ብሎ እስኪማረር ድረስ መጥፎ አጽናኝ ሆኑ? እንደምን በዖፅ ያሉ ወገነቹ የራቁትን ምስኪን ሰው አብረውት ማቅ ለብሰው የተቀመጡ ሰዎች የእግዚአብሔርን ቁጣ ሳይቀር በኢዮብ ላይ በተናገሩት ቃል አነሳሱ? የተናገሩት ነገሮች በቅዱስ ጳውሎስ ሳይቀር የሚጠቀስላቸው እነዚህ ወዳጆቹ ምንድነው ጥፋታቸው?

የኢዮብ ወዳጆች የታመመ ወገናችንን ወይም ወዳጃችንን ልንጠይቅ ስንሄድ የምንጠይቃቸው ጥያቄዎችን ነው የሚያስታውሱኝ። በደም ግፊት ታሞ የተኛ ወዳጅ ካለን ደም ግፊቱ እንዴት እንደመጣበት በጥያቄ እናጣድፈዋለን። ምን ሲበላ እንደከረመ፣ በዘሩ ውስጥ ደም ግፊት ያለበት ሰው እንዳለ፣ ስብ እና ጨው አብዝቶ እንደሚመገብ እንጠይቀዋለን። ለዚህ ዋነኛ ምክንያቱ ሰውየውን ካከመው ዶክተር የተሻለ የበላውን በመጠየቅ ወይም የአኗኗር ዘይቤውን በማጥናት ልናድነው አስበን አይደለም። ጉዳዩ ስለእኛ ስለራሳችን ነው። ማለትም እንዴት ራሳችንን እሱ ከታመመበት በሽታ እንደምንጠብቅ ለማወቅ ነው። እኛስ ያ ሰውዬው የያዘው በሽታ ይኖርብን ይሆን አይኖርብን ወይም የመያዝ እድላችን ምን እንደሚመስል ለማወቅ ነው። ሁልጊዜ በቻልነው መጠን እራሳችንን ከመከራ መለየት እንፈልጋለንና።

የኢዮብ ወዳጆች ማመን እና መቀበል የከበዳቸው ነገር ያ ነበር። ለኢዮብ ስቃይ እና ከአዕምሮ በላይ ለሆነ መከራ ምክንያት ማግኘት ነበረባቸው። ካለዛ ንጹሁ እና ጻድቅ የሆነ ሰው እንዲህ ሊሰቃይ ይችላል ብሎ ማመን ፥ ነገ እናንተም ትሰቃያላችሁ የሚለውን መልዕክት ነው የሚሰጣቸው። ያን ደግሞ መቀበል አይፈልጉም። ማን እንደ ኢዮብ መሆን ይፈልጋል? ስለዚህ ለኢዮብ ስቃይ ምክንያት ማግኘት ነበረባቸው። ለዚህም ነው ኢዮብ አንደበቱን ከፍቶ እስከሚናገር ድረስ በዝምታ የጠበቁት። ኢዮብ እግዚአብሔር በእርሱ ላይ ያደረገው ነገር የተወለደበትን ቀን በመርገም እና ያ እሱ ኢዮብ የተባለበት ቀን ከቀናት ተርታ ቢሰረዝ ምናለ ብሎ ሲነሳ ፥ ኤልፋዝ እና ጓደኞቹ ሰባት ቀን ሙሉ ሲያስቡት የነበረው ነገር እውነት ነው ብለው ደመደሙ። እሱም ኢዮብ ከሰው የተሰወረ ኃጢአት ስለሰራ ነው ይሄ ሁሉ የደረሰበት ብለው ደመደሙ።

ማማረር፣ እግዚአብሔርን መጠየቅ፣ የውስጥ ምሬትን መግለጽ ላልበቃ ሰው ብቻ እንጂ እግዚአብሔርን በርግጥ ለሚያምን ሰው የተገባ አይደለም የሚለው የተሳሳተ እምነታቸው ስለኢዮብ መከራ አዕምሮአቸው አስቀድሞ ሲያስብ የነበረውን ነገር አስረገጠላቸው።

በዚህም ኤልፋዝ ኢዮብ በድብቅ የሰራውን ኃጢአት እንዲናዘዝ መከረው። በምዕራፍ አራት ላይ ኤልፋዝ ኢዮብ ሆይ “እባክህ አስብ፥ ንጹሕ ሆኖ የጠፋ ማን ነው? ከልበ ቅንስ የተደመሰሰ ማን ነው?” ስለዚህ ኃጢአት ባይኖርብህ ይሄ ሁሉ አይደርስብህም ይለው ጀመር። የኤልፋዝ እምነት መከራ በተለይ የኢዮብ ዓይነት ከኃጢአት ውጪ ሊመጣ የማይችል ነው የሚል ነበር። ሀገር ሰላም በሆነበት፣ ሁሉ በተደላደለበት አንተን ለይቶ የሚያጠቃህ ነገር የመጣው የልብህን ክፋት እሱ ስላወቀው ነው። “ልክ ነህ ጻድቅ ነህ፣ ልክ ነው መልካም ሰው ነህ ግን የደበከው ግፍ አለብህ ፥ እጅህ ንጹህ አይደለም” አለው። ኤልፋዝ ስል አዕምሮ ስለነበረው ኢዮብ እሱን ከሰማ በኋላ የሚመልስለትን ሁሉ እያሰበ ነበር አስቀድሞ የሚናገረው። ኢዮብ “በኃጢአትስ ቢሆን ስንት ኃጢአተኛ፣ ሰው ሁሉ የሚያውቃቸው ግፈኞች እያሉ እንዴት እኔን ለይቶ እንዲህ ባለ ስቃይ ይቀጣኛል” እንዳይለው ፥ ኤልፋዝ አስቀድሞ እንዲህ ይላል “እነሆ፥ እግዚአብሔር የሚገሥጸው ሰው ምስጉን ነው፤ ስለዚህ ሁሉን የሚችለውን የአምላክን ተግሣጽ አትናቅ።” ኢዮብ አንተን ስለሚወድህ እኮ ነው በልብህ የሸሸከውን ኃጢአት ዝም ያላለህ ይለዋል።

እንደዚህ ዓይነት አጽናኞች ገጥመውን አያውቁም? በሕመማችን ሰዓት መጥተው እና ደርሰው ለእግዚአብሔር ጠበቃ የሚሆኑ? ኤልፋዝ፣ በልዳዶስ እና ነዕማታዊው ሶፋር እንደዛ ነበሩ። በአንድ በኩል ኢዮብ ሲያማርር በመስማት ይሄ ሰው ኃጢአተኛ ነው ብለው በውስጣቸው ያለውን ለማውጣት ዕድል አገኙ፣ በሌላ በኩል እንደዚህ ዓይነት መከራ የኃጢአት ውጤት መሆኑ አጽናናቸው ምክንያቱም እነሱ ጋር ሊደርስ እንደማይችል አስበዋልና። በተጨማሪ ግን በዚህ ሰዓት ስለእግዚአብሔር የበለጠ በመናገር እና በመመስከር ከፈሩት እና ካስደነገጣቸው መከራ ለመዳን መልካም አጋጣሚ ሆኖ ታያቸው።  ታላቁ ኢዮብ ግን ይሄ የልባቸው ሀሳብ ተገለጠለት። ለሰባት ቀን በዝምታ አብረውት ሲቀመጡም በመጨረሻ አንደበቱን በመጀመሪያ የከፈተው አንድም በገጻቸው ላይ የተመለከተው “ኢዮብ በድብቅ ኃጢአት ሰርቷል” የሚለው የሰውነት ቋንቋቸው አንዱ ምክንያት ነበር። ለዚህ ነው ኤልፋዝ ከተናገረ በኋላ ይሄን ለእግዚአብሔር ከመቅናት ሳይሆን መከራን ከመፍራት የተነገረን መንፈሳዊ የሚመስለውን  የንግግር መጋረጃ ኢዮብ እንዲህ ሲል የቀደደው “መከራዬን አይታችሁ ፈራችሁ።” ኢዮ ፮፥፳፩።  ይልቁንስ ኢዮብ ተመለሱ እያለ ወዳጆቹን ተማጸነ። ተመለሱ ከራሳችሁ ተመለሱ። ተመለሱ ለማጽናናት የሄደ ሰው ራሱ ላይ አያተኩርም። ተመለሱ። ኑ ይሄ የሆነብኝን ነገር እናንተም ስሙ እና አድንቁ። ተመለሱ ፥ ከሄዳችሁበት ሩቁ የእኔነት ሀገር።

የት እንደሰማውት አላስታውስም ግን ይሄን ዓለም ከመውደድ በላይ የከፋው ራስን ብቻ መውደድ ነው የሚል አባባል አለ። ባልጀራውን እንደራሱ የሚወድ ሰው በባልጀራው ላይ የደረሰውን መከራ የራሱ ለማድረግ ይጥራል እንጂ በዚህ ፍጥነት ባልንጀራውን ከኃጢአት ብትመለስ እኮ፤ በልዳዶስ እንዳለው ከጅማሬኽ በላይ ፍጻሜ ታላቅ ይሆናል እያለ በቁስል ላይ ቁስል አይጨምርም። ይሄ ማለት “እጅግ የምትወደው ልጅ የሞተባትን እናት ዕድሜሽ ገና ስለሆነ ሌላ ልጅ ትወልጃለሽ ስለዚህ ተጽናኚ” የሚል አረመኔያዊ ስሜትን በሐዘንተኛዋ እናት ልብ ውስጥ የሚጨምርን አጽናኝ ይመስላል። ልጅን እንደቁስ የሚቆጥር አጽናኝ ማለት ነው። ኤልፋዝ፣ በልዳዶስ እና ሶፋር አንድ ታዋቂ ሳይኮለጂስት ሰዎች አዝነው ሲያለቅሱ አታልቅሱ የሚሉ አጽናኞች ፥ ብዙ ጊዜ ለሰውዬው አዝነው ሳይሆን ሐዘን እና ለቅሶ ስለሚረብሸን እና ነርቨስ ስለሚያደርገን ነው (ማለትም ስለራሳችን ውስጣዊ ሰላም ስንል ነው) ያለችውን ነው የሚያስታውሱኝ።

ኢዮብ ወዳጆቹን “ምነው ዝም ብላችሁ ብትኖሩ! ይህ ጥበብ በሆነላችሁ ነበር።” (ኢዮ ፲፫፥፭)፣ እንዳለው፤ ለማጽናናት የምንሄድ ሰዎች ባካችሁ ዝም ማለትን ልመዱ ቢያንስ። ብንችል ከአሜሪካዊቷ ሳይኮሎጂስት ቀድሞ ይሄን የተረዳው ብርሃነ ዓለም ቅዱስ ጳውሎስ እንዳለው “ከሚያዝኑ ጋር አብረን እንዘን” (ሮሜ ፲፪፥፲፭)። ካልሆነ ግን ዝምታ እንደ ጥበብ ይሆንልናል።

በመጨረሻ ግን ሲ ኤስ ሉዊስ እንዳለው በክርስትና ቃል የተገባልን ነገር መከራ ነው። ጭራሽ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው” ነው የተባልነው። ፈርመን የገባነው ለዚህ መከራ ነው። ወደ ክርስትና ስንመጣ ደስታን፣ የስኬት ሕይወትን፣ መከራ እና ስቃይ የሌለበትን ሕይወት ትመራላችሁ ብሎ የጠራችሁ ሁሉ መጥፎ ጠሪ ብቻ አይደለም መጥፎ ወዳጅም ነው። “በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” (ዮሐ ፲፮፥፴፫)። ይሄን ያለን ጌታችን ነው።

አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ጥቂት ጀግንነት እንጂ እውቀት አይደለም ይሄን መከራ የሚያሳልፋችሁ እያለን። አይዞችሁ ነው ያለን ማለትም ብዙ ፍቅር ነው ይሄን ጊዜ የሚያስታግሳችሁ እንጂ ሙሁራዊነት አይደለም እያለን ነው። አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ይሄን ስቃይ ማለፍ የሚቻለው በመሰቃየት ብቻ ነው እያለን ነው። አይዞን ክርስቲያኖች። በመጨረሻ እንጽናናለን።

Share your love

22 አስተያየቶች

    • “በክርስትና ቃል የተገባልን ነገር መከራ ነው። ጭራሽ “የሚያዝኑ ብፁዓን ናቸው” ነው የተባልነው። ፈርመን የገባነው ለዚህ መከራ ነው። ” እንግዲህ ምን እንላለን ?
      ቃለ ሕይወት ያሰማልን ። አሜን።

  1. ቃለ ህይወትን ያሰማልን። እውነት ነው ሁላችንም ከምር ካዘነው ጋር ልናዝን፤ ባይቻለን ግን ልቡን ሳናቆስለው ዝም ብንል ተገቢ ነው። እግዚአብሔር ይስጥልን።

  2. ከተናገርክ ከዝምታ የቸሻለ ንግግር ተናገር ካልሆነም ዝምታን ምረጥ እንዲሉ ማለት ነው!

  3. እጅግ ጠቃሚ እና ጥሩ መልክት ነው እናመሰግናለን ግን ዌብሳይቱ dark mode ወይም ጥቁር ጀርባ ቢኖረው አሁን ባለበት ሁኔታ ብርሀኑ አይን ጫና ያሳድራል

  4. የእዮብን መፅሐፍ በጥሞና እንድናነብ የሚረዳ እይታ ቃለህይወት ያሰማልን

  5. ባልጀራውን እንደራሱ የሚወድ ሰው በባልጀራው ላይ የደረሰውን መከራ የራሱ ለማድረግ ይጥራል!
    ቃለ ህይወት ያሰማልን!

  6. በጣም የሚገርም ጽሑፍ ነው። አንተ እንዳልከው እኔም መጽሐፈ እዮብን ካነበብኩ በኋላ ምንም ሳይገባኝ ነበር ያለፍኩት። አሁን ተረዳሁት። እስካሁን ያልተዳሰሰ ጉዳይ እንደሆነ ይሰማኛል ቆንጆ አድርገህ ነው የጻፍክልን ተባረክ። ቃለ ሕይወት ያሰማልን።

  7. ድንቅ ነው። ቃለ ሕይወትን ያሰማልን።

    በጭራሽ መጽሐፈ ኢዮብን እንዲህ ተረድቼው አላውቅም።

    • ቃለሕይወትን ያሰማልን መንግሥተ ሰማያትን ያውርስልን 🙏🙏🙏

  8. አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ጥቂት ጀግንነት እንጂ እውቀት አይደለም ይሄን መከራ የሚያሳልፋችሁ እያለን። አይዞችሁ ነው ያለን ማለትም ብዙ ፍቅር ነው ይሄን ጊዜ የሚያስታግሳችሁ እንጂ ሙሁራዊነት አይደለም እያለን ነው። አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ይሄን ስቃይ ማለፍ የሚቻለው በመሰቃየት ብቻ ነው እያለን ነው። አይዞን ክርስቲያኖች። በመጨረሻ እንጽናናለን።

  9. “አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ጥቂት ጀግንነት እንጂ እውቀት አይደለም ይሄን መከራ የሚያሳልፋችሁ እያለን። አይዞችሁ ነው ያለን ማለትም ብዙ ፍቅር ነው ይሄን ጊዜ የሚያስታግሳችሁ እንጂ ሙሁራዊነት አይደለም እያለን ነው። አይዞአችሁ ነው ያለን ማለትም ይሄን ስቃይ ማለፍ የሚቻለው በመሰቃየት ብቻ ነው እያለን ነው።” ቃለ ህይወትን ያሰማልን!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *