እግዚአብሔር በምድር ላይ ለማየት ደስ የሚያሰኙ፣ ለመብላት መልካም የሆኑ ዛፎችን ማብቀሉን ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል፤ ከእነዚህ ዛፎች መካከል አንዱ የሕይወት ዛፍ ነው። ዘፍ 2፥9 ገነትን የሚያጠጡ አራቱ አፍላጋት ኤፌሶን፣ ግዮን፣ ጤግሮስ፣ ኤፍራጥስ የሚመነጩት ከዚህ የሕይወት ዛፍ ሥር ነው። ስለዚህ የሕይወት ዛፍ በነገረ ክርስቶስ ያለውን ጥልቅ አስተምህሮ በሌላ ጊዜ የምናነሣው ሆኖ ለዛሬ ግን ልነግራችሁ የወደድሁት በሰዎች መካከል ስለሚገኘው የሕይወት ዛፍ ነው።
ለቅድስና ራሳቸውን የሚያተጉ ሰዎች ወደ እግዚአብሔር ገነት ከመወሰዳቸው በፊት ልቡናቸው ተድላ ደስታ የሚፈስባትን ገነት ትሆናለች። አረጋዊ መንፈሳዊ የተባለው ሊቅ “ልቡሰ ለባህታዊ ገነተ ተድላ ይዕቲ፤ የባህታዊ ልቡ ተድላ ደስታ የሚገኝባት ገነት ናት” ብሎ የተናገረውም ስለዚህ ነው። የጻድቅ ሰው ልቡ ገነት፣ አንደበቱም የሕይወት ዛፍ ናት። የማስተዋል መንፈስ የተሰጠው ሰው ሰሎሞን በገነት መካከል ስላለው ሳይሆን በሰዎች ዘንድ ስላለው የሕይወት ዛፍ እንዲህ ሲል ይናገራል። “መፈውስ ልሳን ዕፀ ሕይወት ውእቱ፤ ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት” ምሳ 15፥4 ይላል።
ዛሬ በገነት መካከል ካለው የሕይወት ዛፍ ይልቅ የሚያስፈልገን ሰሎሞን የተናገረለት የሕይወት ዛፍ ነው። ያኛውማ ከዚህ በኋላ እንዳንፈልገው በክርስቶስ ተተክቷል። ፍሬውን በልተነው የዘለዓለም ሕይወትን የምናገኝበት እውነተኛው የሕይወት ዛፍ ሁልጊዜ በፊታችን እንደተሰቀለ ሆኖ የተሳለው ክርስቶስ ነው። እሁን ለምድራችን ምን ያስፈልጋታል ካላችሁኝ ልቡ ገነት፣ አንደበቱም የሕይወት ዛፍ የሆነችለት ሰው ነው። አራቱ አፍላጋት የተባሉት አራቱ ወንጌላውያን ዙረው የሚያጠጡት ልቡ ገነት የሆነችለት አንደበቱም የሕይወትን ዛፍ የምትመስልለት ይህ ሰው ዛሬ ከወዴት ይገኛል?
ተፈጥሯችንን በእግዚአብሔር ቃል ብንጠብቀው እንዴት ያለ ድንቅ ስጦታ መሰላችሁ? ክርስትና ገነትን በመሻት ተጀምሮ ገነትን ወደ መሆን ማደግ የሚያስችል ሕይወት ነው። ፈውስን የሚሻ ሰው ፈዋሽ የሚሆንባት፣ ምድራዊው ሰው ሰማያዊ ምሥጢር የሚያይባት፣ ደካማው ሰው ኃይልን በሚሰጠው በክርስቶስ ሁሉን የሚችልባት ድንቅ ሕይወት ናት ክርስትና። ቅዱስ ጳውሎስ ለራሱ ፈውስን የሚሻ ድውየ ሥጋ ነው 2ቆሮ 12፥7 ለሌሎቹ ግን በሄደበት ቦታ ሁሉ ፈውስን የሚሰጥ የሕይወት ዛፍ ነው። ቅዱሳን ሐዋርያት በቃላቸው ተናግረው በእጃቸው ዳሰው ከዚያም አልፎ በልብሳቸውና በጥላቸው የፈወሷቸው ድውያን ብዙ ናቸው። ከዚያ ይልቅ በአንደበታቸው የፈወሷቸው ምዕመናን ይበዛሉ። ዓለምን ዙረው ካስተማሩበት ጊዜ ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ ትምህርታቸውን የስሙ ሁሉ ወደ ዘለዓለም ሕይወት ይደርሳሉ።
መልካሙን የምሥራች የሚናገሩ እውነተኛውን ቃል የሚያወሩ አንደበቶች ሁሉ ዛሬ በምድራችን ላይ የበቀሉ የሕይወት ዛፎች ናቸው። ልቡን ከኃጢአት የሚጠብቃት ሰው ለአዳም የተሰጠችውን ገነትን ያደርጋታል። አንደበቱንም ሀሰትን ከመናገር የሚከለክላት የሕይወትን ዛፍ ያስመስላታል። ለሚሰሟት ሁሉ ፈውስን የምትሰጥ እንደዚህ ያለች አንደበት እንድትኖረን ሀሰትና ቁጣን፣ ፌዝና ቧልትን የመሳሰሉ ነገሮችን ሁሉ ከቶውኑ ወደ አፋችን ማስገባት አይገባንም። ቅዱስ ዳዊት “አቤቱ ለአፌ ጠባቂ አኑር የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ” መዝ 141፥3 ብሎ የጸለየው እንዳገኙ መናገር አንደበትን የሚያረክስ ስለሆነ ነው። እንዳገኙ መናገር እንዳገኙ ከመብላትና ከመጠጣት ይልቅ ሰውን የሚጎዳ ልማድ ነው።
ከአንደበታችን በሚወጣው ነገር እግዚአብሔር ሌሎችን የሚፈውስበት ከሆነ አንደበታችንን መጠበቅ ይገባናል ማለት ነው።
አንተ ሰው! እግዚአብሔር ገነትን ባንተ በኩል ሊገልጣት ይፈልጋል፤ አንደበትህም ለብዙዎች ፈውስ ትሆን ዘንድ የሕይወት ዛፍ ሊያደርጋት ይቻለዋል። ራስህን አዘጋጅ እግዚአብሔር ባንተ ልሳን ሊፈውሳቸው የተዘጋጁ ሕሙማን በዙሪያህ መሰብሰባቸውን አትርሳ። እንደዚያ የመቄዶንያ ሰው እርዳታህን ፈልገው የሚጠባበቁ ሰዎች መኖራቸውን አስብ ሥራ 16፥9 አንዲት የሰማርያ ሴት በተናገረችው ነገር ብዙዎች በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ማመናቸውን በመጽሐፍ ተመልከት ዮሐ 4፥39 የተናገረችው ብዙ አይደለም እሷ ስለክርስቶስ ብዙ ትናገር ዘንድ ጴጥሮስን ወይም ጳውሎስን አላደረጋትማ! ቃሉን በሙላት እንደሚናገሩ ሐዋርያት የማስተማር ጸጋን አልሰጣትማ! “ያደረግሁትን ሁሉ ነገረኝ” ብቻ ነው ያለቻቸው። ነገር ግ ን ብዙ ሣምራውያን በክርስቶስ አመኑ። ከሁሉ ይልቅ የሚገርመው ትምህርትና ተአምራት ከጀመረባት ከገሊላ ሰዎች በልጠው በእነርሱ ዘንድ እንዲኖር መለመናቸው ነው።
የሕይወት ዛፍ የሆነች ምላስ ማለት ይህች አይደለቸምን? ብዙዎችን ከሞት ወደ ሕይወት ያሻገረች። አንደበታቸው የሕይወት ዛፍ የሆነችላቸው ሰዎች ብዙ ተናግረው ሳይሆን አንድ ቃልም ቢናገሩ በቂ ነው። የሕይወት ዛፍ የሚያፈራው ፍሬ አንዱ በቂ ነውና። ብዙ መናገር ባትችልም የተናገርሃት አንዷ ቃል ትፈውሳለች ። አከናውነህ መናገር ባይሆንልህም እንደምንም ብለህ ከአንደበትህ ያወጣሃት ቃል እሷ መድኃኒት ትሆናለች ሙሴ ዲዳና ምላሰ ጸያፍ እንደነበረ አስብ እንጅ። አሮን ደግሞ ደኅና አድርጎ እንደሚናገርም አትርሳ ነገር ግን እስራኤልን ለሞት የሰጣቸው የሙሴ ቃል ሳይሆን የአሮን ነው ዘፀ 32፥2
“ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት” ለሰዎች ፈውስ የማይሆን ቃል አትናገር፤ አንደበትህ የሕይወት ዛፍ ትሆንልህ ዘንድ አስቀድመህ ልብህን እንደ ገነት በእግዚአብሔር ቃል የለመለመች መልካም ሥፍራ አድርጋ፤ የሕይወት ዛፍ ከገነት ውጭ በሌላ ሥፍራ አትገኝምና። ከዚህ የሚበልጥ ጸጋ ከወዴት ታገኛለህ? በምድር ሳለህ ልብህን ገነት አንደበትህን የሕይወት ዛፍ ካደረገልህ ሌላ ምን ትሻለህ?
ማስታወሻ :- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
ቃለ ሕይወት ያሠማልን መምህራችን
“ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
ቃለ ሕይወት ያሰማልን! አቤቱ ከአንደበታችን የሚወጣውን ቃል ፈዋሽ ያድርግልን
እግዚአብሔር ያበርታችሁ
መምህር ቃለ ህይወት ያሰማልን።
” ሞት እና ህይወት በአንደበትህ እጆች ናቸው ” እንዳለ ጠቢቡ ፈዋሿን ምላስ ይስጠን አሜን ።
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሠማልን!
“ፈዋሽ ምላስ የሕይወት ዛፍ ናት”
ቃለ ሕይወት ያሰማልን
ለመምህራችን ቃለ ሕይወት ያሰማልን!
ቃለ ሕይወት ያሠማልን
እግዚአብሔር ያበርታችሁ
አባታችን እድሜና ጤና ይስጥልን
ቃለ ህይወት ያሰማልን። የሊቃውንት በረከት አያሳጣን።