በክርስትና ትምህርት ሞት የሕይወት ፍጻሜ ሳይሆን የምድራዊ ሕይወት መጨረሻ፤ የሰማያዊ ሕይወት መጀመሪያ ነው። ክርስቲያኖች በሞት ምክንያት የሚመጣ ኃዘን የማይጸናባቸውም ስለዚህ ነው። ከሞት በኋላ ለማንም በምድር ላይ ዕድል ፈንታ የለውም። በእርግጥ ይህ የሚሆነው በዓለም ዘንድ ነው እንጅ በቤተ ክርስቲያን ዘንድ ግን ማንም ቢሆን ከአባልነት አይወጣም። የቤተ ክርስቲያን ኅብረት የስማያውያን መላእክት፣ የምድራውያን ጻድቃንና በገነት ያሉ ነፍሳት ኅብረት ነውና። 

ለዚህም ነው ዛሬ በኅብረት የምናገለግለው። መላእክት ጸሎታችንን መሥዋዕታችንን ያሳርጋሉ፤ ባህታውያንን በገዳም፣ ምዕመናንን በዓለም፣ ሰማዕታትን በዐውደ ስምዕ፣ ካህናትን በጊዜ ቁርባን ይራዳሉ። በዐፀደ ሥጋ ለሌሉ ነፍሳትም በቤተ ክርስቲያን ሁልጊዜ መታሰቢያ ይደረግላቸዋል። ሞት ከዓለም ይለያቸዋል እንጅ የክርስቶስ አካል ከመሆን አይለያቸውምና። 

የሞተ ሰው ቢወዱት የማይደሰት፣ ቢጠሉት የማይቆጭ ነው። 

ሢራክ “ዘሞተሰ አዕረፈ፤ የሞተ ሰውስ አረፈ” ሲል ስንሰማው ሞት የዕረፍት መጀመሪያ እንደሆነ እንረዳለን። ምን እበላለሁ፣ ምን እጠጣለሁ፣ ምን እለብሳለሁ፣ የት አድራለሁ፣ የት እኖራለሁ ማለት የሌለበት፤ ሰዎች ጠሉኝ ወደዱኝ ብሎ መጨነቅ የሌለበት ሕይወት ስለሆነ ደስ የሚል ነው። ብርድና ሙቀት፣ በጋና ክረምት በማይፈራረቁበት ዓለም መኖር መልካም ነገር ነው። ይህን ወደመሰለ ዓለም እስክንመለስ ድረስ በኑሯችን ሁሉ ማግኘትና ማጣት፣ መውደድና መጥላት፣ መሳቅና ማዘን ያጋጥመናል። 

ለማንኛውም ዛሬ ልነግራችሁ የፈለግሁት አንድ ቀን ከየኔታ ጋር ስንጫዎት ያስገረመኝ ጥያቄና መልስ ነው። የኔታ ከምናውቃቸው ጓደኞቻችን የአንዱን ስም በመጥራት የጠየቃቸውን ጥያቄና የመለሱለትን መልስ ሲያወጉን እንዲህ አሉ “እኔ ለሰዎች የማደርገው ነገር መልካም ነገር ነው ሰዎች ግን የሚመልሱልኝ ክፉ ነገር ነው፤ እኔ ሰው እወዳለሁ ሰዎች ግን በተቃራኒው ይጠሉኛል ምን ባደርግ ይሻለኛል” አለኝ። 

እና ምን ብለው መለሱለት አልኋቸው። “የዚህ ዓለም ሰው ምንም አስተያየት ሳይሰጥ አጠገብህ የሚቆም ስትሞት ብቻ ነው” አልሁት አሉኝ። ለጊዜው ባይገባኝም ቤቴ ገብቸ ነገሩን በሀሳቤ ሳመላልሰው በእርግጥም የዚህ ዓለም ሰው ከፊት የሚያስቀድምህ፣ ከኋላ የሚከተልህ ስትሞት ብቻ ነው። ሊሸከምህ እንጅ እንድትሸከመው የማይፈልገው የሞትህ እንደ ሆነ ብቻ ነው። መኖርህን ያልሰሙ ሰዎች ሁሉ መሞትህን ሊሰሙ ይችላሉ። መኖርህ የመሞትህን ያህል ገናና ሆኖ ሊነገር አይችልም። 

ምንም ብትከብዳቸው የሞትህ ቀን ታግሠው ይሸከሙሃል። የሞተን ሰው ከበደኝ ብሎ ማን ያማዋል? ምንም ቢሆን ከሚደርስበት ድረስ ሳያደርሰው ማንም ወደ ቤቱ ላለመመለስ ይሞክራል። ሰው ሲሞት ወዳጁ ይበዛል። የነቀፉት ሁሉ ያመሰግኑታል። ምናልባት በዚያ መካከል እንደ ቅድስት ሐና፣ እንደ ቅዱስ ጴጥሮስ ያለ ንጹሕ ሰው ተገኝቶ ጥላውን ቢጥልበትና ቢነሣ ሀሳቡን የሚቀይር ብዙ ሰው ማግኘት ይቻላል። ጌታ አልዓዛርን ካስነሣው በኋላ መልሰው ሊገድሉት የተማከሩ ሰዎች መኖራቸውን ስለምናውቅ ይህ ነገር ለእኛ እንግዳ ነገር አይሆንብንም:: ዮሐ. 12፥10

ችግሩን ይዞት የሚመጣው መነሣታችን ነው ማለት ነው። አልዓዛር በመቃብር ውስጥ ሳለ ያለቀሱለት ሁሉ ሲነሣ ደስ አላላቸውም። በአልዓዛር መነሣት የእግዚአብሔር ክብር ይገለጣላ! አንተ ተነሥተህ የእግዚአብሔር ክብር ከሚገለጥ ቢቀር ይሻላቸዋል። ትዝ የሚላቸው ያንተ መነሣት ነው እንጅ የእግዚአብሔር ክብር በሕዝቡ ዘንድ መገለጥ አይደለምና። መድኃኔ ዓለም ክርስቶስ በስብከቱ ከትንሣኤው ይልቅ ስለሞቱ ደጋግሞ ተናግሯል። ነገር ግን አይሁድ ያስታወሱት “በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ” የሚለውን እንጅ እሞታለሁ የሚለውን አልነበረም። ለዚህም ነው ገድለነዋል ብለው ሳይዘናጉ ተሰብስበው ሂደው ጲላጦስን “በሦስተኛው ቀን እነሣለሁ እንዳለ ትዝ አለን፤ እንግዲህ ደቀ መዛሙርቱ በሌሊት መጥተው እንዳይሰርቁት ለሕዝቡም ከሙታን ተለይቶ ተነሣ እንዳይሉ መቃብሩ እስከ ሦስተኛው ቀን ድረስ መቃብሩን እንዲጠበቅ እዘዝ” ማቴ 27፥64 ያሉት። ከቻሉ እንዳትነሣ ይደራጁብሃል። ያ ካልሆነላቸው ደግሞ ትንሣኤህን በሰዎች ዘንድ የሚያጥላላ ወሬ ይነዙብሃል። 

የትኩረት አቅጣጫቸው በዙሪያህ ካሉ ካልተነሡ ብዙ ሰዎች ይልቅ ከሞት የተነሣኸው ከመቃብር የተመለስኸው ያንተ ጉዳይ ነው። አልዓዛር በተነሣበት ወቅት ስለማርያም ስለማርታ ማን ያወራል? አልዓዛር ሳይነሣ ግን ሰው ሁሉ የተሰበሰበው ስለማርያምና ስለ ማርታ ብሎ እነሱን ለማጽናናት ነበር ዮሐ 11፥19 ከአልዓዛር ትንሣኤ በኋላ ግን በመነሣቱ ደስ ያላቸውም የሚመጡት እሱን ለማየት ሆነ፤ በመነሣቱ የከፋቸውም የሚመካከሩት እሱን ለመግደል ሆነ። 

የተነሣ ሰው በዚህ ይታወቃል − ዓለምን ከሁለት ይከፍለዋል። ዜናውን የሰሙት ሰዎች ሁሉ ያለ እርሱ በቀር ሌላ ወሬ እንዳይኖራቸው ያደርጋቸዋል። የተነሣ ሰው ለብዙዎች መዳን ምክንያት እንደሚሆን ሁሉ ለብዙዎች ጭንቀትም ምክንያት ነው። አይሁድ ክርስቶስን ለመግደል ከከፈሉት ይልቅ የክርስቶስ ትንሣኤ እንዳይሰማ ያወጡት ወጭ ይበልጣል ማቴ 28፥12። ሞት ጠላት ይቀንስልሃል መነሣትህን ከታወቀ ግን ጠላት ይደራጅብሃል። 

  ማንም ቢሆን ወንድሙን በክብር መግለጥ ካልቻለ እግዚአብሔርን በክብር ሊገልጥ አይችልም። በወንድሙ ትንሣኤ ደስ ካላለው በክርስቶስ ትንሣኤ ደስ ሊለው አይችልም። በአልዓዛር ትንሣኤ ያልተደሰተ በክርስቶስ ትንሣኤ ደስ ሊለው አይችልምና። ነገር ግን በዚያ ዘመን በአልዓዛር ሞት ከተጨነቁት ይልቅ በአልዓዛር ትንሣኤ የተጨነቁት እንደሚበዙ በዚህ ዘመንም በወንድሙ ትንሣኤ ከሚደሰተው ይልቅ በወንድሙ ሞት የሚደሰተው ብዙ ነው። 

 ስለዚህ ወንድሜ ሆይ በትንሣኤ ከኖርህ ብዙ ወዳጅ እንደማይኖርህ ማመን አለብሕ ካልሞትህ በቀር ስላንተ በጎ ነገር ማውራት የማይፈልጉ ሰዎች መኖራቸውን አስብ። ሕያው መሆንህን ሲያውቁ በማይመለከታቸው ሁሉ ይጣሉሃል። ስምህን በክፉ የማያነሡት ከሞትህ ብቻ ነው። ስሜ በክፉ እንዳይነሣ ብለህ እንደ ሞተ ሰው መሆን ትፈልጋለህ?  ካልሞትህ አንወድህም ከሚሉህ ሰዎች ይልቅ “ከእንቅልፉ ላስነሣው እሄዳለሁ” ዮሐ 11፥11 ብሎ አንተን ለማስነሣት ወደአንተ የመጣውን ጌታ ልታከብረው ይገባል። 

መነሣትህ በእግዚአብሔር ፈቃድ ከሆነ ወደ መቃብር ሊመልስህ የሚችል ማን ነው? መነሣትህን ለማያምኑ ሰዎች መልስ መስጠትም አይገባም፤ ክርስቶስ ሞቱን እንጅ ትንሣኤውን በጠላቶቹ ፊት አላደረገውም፤ ነገር ግን ጠላቶቹ በትንሣኤው ማፈራቸው አልቀረም። ለጠላቶችህ ስትል አትሙት። ጠላቶችህ አጋንንት ደስ እንዳይላቸው ብለህ ከገባህበት የሞት ወጥመድ ውጣ − እሱም ኃጢአት ነው።

Share your love

16 አስተያየቶች

  1. መምህሬ ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
    እግዚአብሔር ጸጋውን ያብዛልዎት
    በእድሜ በጸጋ ይጠብቅዎት

  2. መምህራችን እድሜ ከጤና ያድልልን!
    ያገልግሎት ዘመንዎ ይርዘም!

  3. “… ማንም ቢሆን ወንድሙን በክብር መግለጥ ካልቻለ እግዚአብሔርን በክብር ሊገልጥ አይችልም። ”
    ቃለህይወትን ያሰማልን መምህር
    ሰኞን ሁሌም ተብቃታለሁ

  4. ለጠላቶችህ ስትል አትሙት። ጠላቶችህ አጋንንት ደስ እንዳይላቸው ብለህ ከገባህበት የሞት ወጥመድ ውጣ − እሱም ኃጢአት ነው።

  5. ሊቀ ሊቃውንት ስምዐኮነ በጣም እናመሰግናለን የሕይወትን ቃል ያሰማልን ፈረንጆች ሰኞን ጥቁር ይሏታል እኛ ግን በጣም ጓጉተን የምንጠብቃት ብሩህ እለታችን ነች

  6. እፁብ ድንቅ ትምህርት። መምህራችንን ቃለ ሕይወት ያሰማልን፤ ተስፋ መንግሥት ሰማያትን ያውርስልን።
    አሜን።
    💚🧡❤️

    • እግዚአብሔር አምላክ በእድሜ በጤና ጠብቆ ያቆይልን ♥️

  7. ቃለ ህይወት ያሰማልን የተማርነው ትምህርት ወደ ህይወታችን አምጥተን እንድንተገብረው ይርዳን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *