“እነሆ ልጆች የእግዚአብሔር ሥጦታዎች ናቸው የሆድም ፍሬ የእርሱ ዋጋ ነው” የሚለው ቃል ስለ ልጅ ሲወራ ከአፋችን ከማይጠፉ ቃላት አንዱ ነው:: (መዝ. 127፡3) ቃሉን ምን ያህል አምነንበት ልጆቻችንን እንደሥጦታ ተመልክተን እያኖርናቸው እንደሆነ እና የሰውን ልጅ የመፈጠር እና የመኖር ትርጉም ገብቶን የእግዚአብሔርን መንገድ እያሳየናቸው እንደሆነ ግን በእርግጠኝነት መናገር ያስቸግራል::
እግዚአብሔር ቸርነቱን እና በረከቱን ከምናይባቸው ነገሮች ውስጥ የልጅ ሥጦታ አንዱ ሲሆን በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥም እግዚአብሔር “በልጅ ባረካቸው፣ ልጅንም ሰጣቸው” የሚሉ ታሪኮች ልጆች የእግዚአብሔር ጸጋዎች እንደሆኑ እና በምድርም የሰው ልጆች የደስታ ምንጭ እና የዓይን ማረፊያ እንደሆኑ ያሳያሉ፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ልጅ የሌላቸው ሰዎች ያለ ዕረፍት እና ድካም ልጅን ለማግኘት አምላካቸውን ደጅ ሲጠኑ እና ሲማልዱ መታየታቸው የልጅን ታላቅ ሥጦታነት የሚያሳይ ነው፡፡ ከምንም በላይ ግን የልጅን ነገር ልጅ ያለው ያውቀዋል እና ብዙም ስጦታነቱ የሚያከራክር አይደለም፡፡
ልጆችን ጸጋ አድርጎ ወደምድር ሲያመጣ በእናት ማህፀን በአባት አብራክ ሲያስቀምጥ እኛን አምኖ በመንገዱ እንድንመራለት አደራ ቢሠጠንም የነፍሳቸው እና የሥጋቸው ባለቤት ፣ ፈጣሪ እና አስገኚያቸው፣ በፈቀደው ሊያኖርም ሊወስድም ሥልጣን ያለው ግን የልጆቻችን አምላክ እግዚአብሔር ነው፡፡ የአንድ ንብረት ባለቤት ንብረቱን በምን እና እንዴት ልንጠቀም እና ልንገለገል እንደሚገባ መመሪያ የመሥጠት መብት እንዳለው ሁሉ እግዚአብሔርም ልጆችን የሠጠን ከ”የአስተዳደግ መመሪያቸው (Manual) ጋር ነው – ካስተዋልነው…፡፡
እግዚአብሔር በመጽሐፍ ቅዱስ ላይ ልጅህን “ይሄን ይሄን አብላው” ብሎ የምግብ ዝርዝርን አላስቀመጠም:: “ይሄን አጠጣውም” ብሎ ስለ እናት ጡት ወተት ጥቅሞችም አልዘረዘረም:: “ይሄንንም አልብሰው” ብሎ ስለ አለባበስ ሁኔታውም አላጻፈም፡፡
ይህን ሁሉ በፍጥረቱ አስተካክሎ ገና የተወለደ ጨቅላ ሕፃንን ጥርስን ነስቶ በእናትም ጡት የሚታኘክ ሳይሆን የሚጠጣ ወተትን ከሚያስፈልገው ነገር ሁሉ ጋር ፈጥሯልና ለሚማር ሌላ ጽሑፍ እና ትንተና ሳያስፈልገው በተፈጥሮ ተምሮ ልጁን ያበላል፡፡ ብቻ እግዚአብሔር ያለህን እንደምታበላው፣ የቻልከውን እንደምታለብሰው እና ደስታው ያስደስትሃልና አቅም በሰጠህ ልክ እንደምታጫውተው አምኖ ተፈጥሮንም በሚገባ እንዲያግዝህ አድርጎ በልጅ ይባርክሃል፡፡ ነገር ግን ምን እየነገርክ እና እያስተማርክ እንደምታሳድገው ዝም ብሎ ሊተውልህ አይችልም፡፡ “ልጁ አድጎ ምን ዓይነት ሰው ይሆናል” የሚለው ጥያቄ የነፍሱን መዳን ጉዳይ ጭምር ይወስናልና በልጁ አእምሮው ስለምታስቀምጠው ጉዳይ እንድታስተውል ይነግርሃል፡፡
ፍጡሩን ጠንቅቆ ያውቃልና የልጆችን ተፈጥሯዊ ጠባይ እንዴት ማደግ እንዳለባቸው እና ያላቸውን ቦታ አንዳንዴ በታሪክ፣ አንዳንዴ በቀጥታ አንዳንዴም ደግሞ በምሳሌ አድርጎ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ አስቀምጦልናል፡፡ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በአንድ ዐረፍተ ነገር የተገለጹ ሃሳቦች የእልፍ ጥናቶች ፣ የብዙ መጻሕፍት እና ፅንሰ ሃሳቦች መፍለቂያ ሊሆኑ ችለዋል፡፡ አንዳንድ ተፈላሳፊ እና ተመራማሪዎች መጽሐፍ ቅዱስ ላይ ያለውን ሃሳብ በማብላላት እና ሰፊ ትንታኔዎችን በመሥጠታቸው ብቻም የፅንሰ ሃሳቡ ባለቤቶች (theory pioneers) ተብለው ስማቸውን ተክለውበት አልፈዋል፡፡
ሁሉን ትተነው በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ብቻ የሚገኙትን እንኳን ብንመለከት አብዛኛውን የሳይንሱ ዓለም ግኝት በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ በጉልሕ ተጽፎ እናገኘዋለን፡፡ ለአብነት እንዲሆነን ጥቂቶቹን በዚህ ጽሑፍ እናነሣለን::
ስለ ልጆች አስተዳደግ ሲነሣ የማይቀረው እና ሁሌም የሚጠቀሰው ታዋቂ የመጽሐፍ ቅዱስ ቃል በመጽሐፈ ምሳሌ 22:9 ላይ ያለው “ልጅን በሚሔድበት መንገድ ምራው በሸመገለም ጊዜ ከእርሱ ፈቀቅ አይልም” የሚለው ኃይለ ቃል ነው::
ይህ ቅዱስ ቃል ዛሬ ላይ ሁሉም የልጅነት ዕድገት እና ትምህርት ባለሙያ ያለ ምንም ክርክር እና የሃሳብ ልዩነት የሚስማማበትን “የልጅነት ጊዜን ወሳኝነት እና በልጅነት የተማርነው ነገር ስናድግ ለሚኖረን ማንነት መሠረት እንደሆነ እንዲሁም አብዛኛው እኛነታችን ተሠርቶ የሚያልቀው በለጋ እድሜአችን ነው” የሚለውን ሃሳብ የሚገልፅ ቃል ነው፡፡ ይህንንም ሃሳብ አብዛኞቹ አዋቂ እና ታዋቂ ፅንሰ ሃሳብ አፍላቂዎች የሚያምኑበት ጉዳይ ነው፡፡ እንደ ሲግመንድ ፍሮይድ አና ዢን ፒያዤ ያሉት ምሁራን ሃሳባቸውን በደረጃ በመክፈል (Stage Theories of development) ከውልደት እስከ ጉርምስና መግቢያ ድረስ ያለው ዕድሜ ላይ በማተኮር የሠሩት ለዚህ ነው፡፡ ባስ ሲልም ፍሮይድ እያንዳንዱን የልጅነት ጊዜ ጠባይ ከአዋቂት ጠባይ ጋር ሁሉ በማዛመድ በጠባይ ደረጃ በመተንተን ሃሳቡን አስቀምጧል፡፡ ለምሳሌ፡ በልጅነቱ ጡት ያልጠገበ ልጅ ሲያድግ ምግብ አብዝቶ ይወዳል፣ ሱሰኛ ሆኖ ሲጋራ ያዘወትራል … ወዘተ
ታዋቂው ገጣሚ William Wordsworth በ1802 በፃፈው “My Heart Leaps Up” በሚለው ግጥሙ ላይ “The Child Is The Father Of The Man” (ሕፃን የትልቁ ሰው ወላጅ አባት ነው) የሚል ስንኝ በማስገባት “በልጅነት ጊዜ የሚኖረን ጊዜ እና ሁኔታ ወደፊት የሚኖረንን ማንነት ላይ ወሳኝ ጉዳይ ነው” የሚለውን ሃሳብ በአጭር ሥነ ጽሑፋዊ ጥበብ በመግለጹ በሙያው ውስጥ በተደጋጋሚ ተጠቃሽ ሰው አድርጎታል፡፡ ታዲያ ይህ ዓለም ያለ ልዩነት የተስማማበት ሃሳብ በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ምንም ሳይሸራረፍ እና ሳይቆራረጥ በምሳሌ 22፤9 ተቀምጦ የነበረ መሆኑ አስደናቂ እውነታ ነው፡፡
በዚያው በምሳሌ 3፡11-12 “ልጄ ሆይ የእግዚአብሔርን ትእዛዝ አትናቅ በገሠጸህም ጊዜ አትመረር እግዚአብሔር የወደደውን ይገሥፃልና አባት የወደደውን ልጁን እንደሚገሥፅ” የሚል ቃል እናገኛለን፡፡ በሌላም ቦታ “ልጅህን ቅጣ ዕረፍትንም ይሠጥሃል ለነፍስህም ተድላን ይሠጣታል” ይላል:: (ምሳሌ 29፡17)” ሳይንስ ከእነዚህ ጥቅሶች የወሰደው ሃሳብ የKohlberg’s Theory of Moral Development በመባል የሚጠራው ነው፡፡ ይህ ፅንሰ ሃሳብ የሕፃናት ሥነ ምግባር እና ሥርዓታዊ ማንነት እንዴት እንደሚያድግ እና እንደሚገነባ የሚያትት ሲሆን በልጅነት ጊዜ ሕፃናት ትክክል እና ስኅተት የሚለውን ነገር የሚያውቁት በሚኖረው የቅጣት እና ያለ መቀጣት ግብረ መልስ ነው:: ስለዚህ ቅጣትን እና ተግሣፅን በመፍራት ትክክለኛውን ነገር ያደርጋሉ” ይላል፡፡
ሕፃናት ወደዚህ ምድር ሲመጡ ንጽሐ ባሕርይ (የተፈጥሮ ንጽሕና) ያላደፈባቸው ቅዱሳን ፍጡራን ናቸው፡፡ በብጫቂ ጨርቅ ተጠቅልለው በእጃችን ከታቀፍናቸው ቀን ጀምሮ ታዲያ በአንድም በሌላ በኩል መልካሙንም ክፉውንም ይማራሉ ፣ ያውቃሉ፡፡ አንዳንዱን በማየት ፣ አንዳንዱን በመሞከር አንዳንዱንም ከእኛው ተመልክተው ሁሉን ለማድረግ እና ስለ ሁሉ ለማወቅ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ ትክክለኛውን እንዲለዩ ስንል በመናገር ፣ በቁጣ፣ ከፍ ሲልም በተገቢ ቅጣት ልናስተምራቸው እንሞክራለን፡፡
ይህንን መልካም ያልሆነን የልጅ ጠባይ በተግሣፅ የማስተካከል እና የመመለስን ሥራ እግዚአብሔር የሠጠው ልጁን ለሚወድ አባት ነው፡፡ በተግሣፅ እና በቁጣ ውስጥ ፍቅርን ያስቀመጠ አምላክ በዚህ ዘመን ልጅን መገሠፅ እና መቅጣት ኃጢአት መስሎ ለሚታያቸው እና የሰባት እና ስምንት ዓመት ልጆቻቸው አሸንፈዋቸው “እምቢ አለኝ ኮ” የሚል ጉንድሽ ምክንያት ለሚያቀርቡ ወላጆች ያስቀመጠው ግልፅ መመሪያ ልጅን በአግባቡ መቅጣት ተገቢ እንደሆነ ነው:: በዘመናችን እናቱን የሚሰድብ ፣ ዕቃ ወርውሮ የሚመታ ሕፃን ማየት እየተለመደ ነው:: ባስ ሲልም ወላጅ ራሱ ስድብን ለልጁ አፍ መፍቻ አድርጎ እየሳቀ “እንዲህ በላት” ሲል ማየት ምንኛ ያምም ይሆን? ዘመናዊነት በሚል ብሂል ሥርዓት አልበኝነትን እንድናስፋፋ የማይፈቅደው አምላክ ግን “ልጆችህን ቅጣ” ብሎ ትርጓሜ እና ፍቺ፣ አውድ እና አገባብ በማያስብል እና በማያሻማ መልኩ ቀጥ ያለችን ትእዛዝ ስለ ልጆቻችን አዝዞን ነበር፡፡
ዓለም ልጅን መቅጣት ወንጀል አድርጋ ትነግረናለች፡፡ በእርግጥ ልጅህን የምትቀጣው የቁጣ ስሜትህ እንዲበርድልህ ከሆነና ዓይን እግር ሳትል የዱላን ናዳ ካወረድክበት እውነትም ወንጀል ሊሆንብህ ይችላል፡፡ እንኳንስ የዓለም ሕግ ቀርቶ ልጅህን ቅጣ ያለው እግዚአብሔርም በልክ እና ባግባብ እንዲሆን ሲናገር “ልባቸው እንዳይዝል ልጆቻችሁን አታስቆጧቸው” ይላል:: (ቆላ. 3፡21) በተረፈ ግን ዛሬ በጥቂት ማጥፋት የጀመረው ልጅ ነገ አድጎበት ከዘላለማዊ አባቱ ጋር እንዳይቆራረጥ ፣ መልካም እና ክፉን እንዲለይ ፣ ማንነቱን ለማስተካከል ፣ ተገቢውን ያህል በተገቢው ቦታ ብትቀጣው ጽድቅ ሆኖ ይቆጠርልህ ይሆናል እንጂ ወንጀልስ አይሆንብህም፡፡ ምክንያቱም እግዚአብሔር እንዲህ ይላል “ሕፃንን ከመቅጣት ቸል አትበል ፤ በበትር ብትመታው አይሞትምና፣ በበትር ትመታዋለህ ነፍሱንም ትታደጋለህ” (ምሳሌ 23፡13-14)
የፓቭሎቭ እና ስኪነር Behaviourist theoryም ሃሳብ ከዚህ መጽሐፍ ቅዱሳዊ መርሕ ጋር የተያያዘ ነው፡፡ ምንም እንኳን ጥናታቸውን በአይጥ እና በውሻ ቢጀምሩትም ተመራማሪዎቹ በመጨረሻ የደረሱበት ነጥብ “ጠባይ የሚገነባው አካባቢያችን ላይ ባለው ሁኔታ ሲሆን ስለ አንድ ጠባይ ስንቀጣ እናቆማለን፣ ስንሸለም ደግሞ ጠባያችን ይቀጥላል:: ስለዚህም ጠባይ የሚቀየር እና በሰዎች ድጋፍ የሚሠራ ነገር ነው” ይሉናል፡፡ ይህን በመውሰድ ታዲያ ለወላጆች የሚመከር የሁል ጊዜም ምክር ” ልጆቻችሁን ሲያጠፉ ገሥፁ ሲያለሙ አበረታቱ:: ደግመው እንዲያደርጉት ብርታት ያገኛሉና” የሚል ነው፡፡
እነዚህ ሁለት ተመራማሪዎች ደረስንበት ያሉት ሳይንስ ከላይ በተገለጡት ጥቅሶች ላይ የሚገኙትን ኃይለ ቃሎች የሚያጎሉ እና የሚመሰክሩ ናቸው፡፡ በመጽሐፈ ምሳሌ ላይ ብቻ ተንተርሰን የፍሮይድን ሳይኮአናሊቲክ ቲዮሪ (Psychoanalytic theory – 1890 by Sigmund Freud)፣ የፒያዤን ኮግኒቲቭ ዴቨሎፕመንት ቲዮሪ (Cognitive development – 1936 by Jean Piaget )፣ የኮሆልበርግን ሞራል ዴቨሎፕመንት ቲዮሪ (Moral development theory – 1958 by Lawrence Kohlberg) እንዲሁም የስኪነርን እና የፓቭሎቭን ቢሄቪየራል ቲዮሪ (behaviorist theory 1938/48 and 1897 by B.F Skinner and Ivan Pavlov) መነሻ ሃሳባቸውን ብቻ መመልከት ከቻልን እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ትእዛዝ እና አስተምህሮ “ልጅህን ስታሳድግ የዳዊትን መዝሙር እና የሰሎሞንን የጥበብ መፅሃፍት አስተምረው” የሚለውን ተከትለን የዳዊትን መዝሙር እና የቀሩትን የሰለሞን ጥበብ መጻሕፍት ብንመለከት ስለ ልጆቻችን የማያዳግምን እውቀት እና ችሎታ የመንፈስ ቅዱስንም ጸጋ ባገኘን ነበር፡፡
ጊዜ ወስዶ እነዚህን መጻሕፍት በማስተዋል ላነበበ ሰው የትእዛዙ ትርጉም ግልፅ ነው፡፡ የዳዊት መዝሙርን እና አምስቱን የሰሎሞንን መጻሕፍት አንድ ጊዜ እንኳን ቢነበቡ እውነትም በሚያስብል ሁኔታ የሰው ልጅ አፉን ሊፈታባቸው የሚገቡ መጻሕፍት መሆናቸውን መመስከር ይቻላል፡፡ አንድ ክርስቲያን ከአፉ ሊጠፉ የማይገቡ የትሕትና ጸሎቶችን ፣ በችግር እና በመከራ ጊዜ ማንን ማሰብ እንዳለብን እንዲሁም በደስታ እና በማሸነፍም ጊዜ ወደ ማን መዞር እንዳለብን የሚያስተምሩ ድንቅ የጥበብ መጻሕፍት ናቸው፡፡
ከዚህም በተጨማሪ ገሚሶቹ ለልጆቻችን የሚጠቅሙ ትምህርቶች እና ጸሎቶች ሲሆኑ አብዛኛው ክፍላቸው በሚባል ደረጃ ግን ልጆቻችንን ለማስተማር ብለን ስናነባቸው የምንማርባቸው ጥልቅ ምሥጢራትን የያዙ ድንቅ መጻሕፍት ናቸው፡፡ አንድ ክርስቲያን ወላጅ ልጁን እንዴት እንደሚያሳድግ ለማንበብ ቢሞክር እና የዘመናዊ ሳይንስን ቢያገላብጥ የሚጠላ አይደለም፡፡ ነገር ግን የቱን ጥሎ የቱንስ አንጠልጥሎ መጓዝ እንዳለበት የሚለካው ግን በመጽሐፍ ቅዱስ ነውና መጽሐፍ ቅዱስን ማንበብ ይኖርበታል:: ሁልጊዜም በቃሉ ለመመላለስ እና የሚለውን ተረድቶ ለመተግበር የበቃን እንድንሆን እግዚአብሔር ፈቃዱ ይሁን፡፡ አንብበን ልጆቻችንን ለማስተማር እና እኛም ለመማር እግዚአብሔር ይርዳን፡፡
ማስታወሻ :- መሳይት ውበት የሕፃናት ዕድገት እና ትምህርት ባለሙያ (Early childhood development and education specialist) ስትሆን በዘርፉ ሁለተኛ ዲግሪዋን ሠርታለች::
ቃለ ሕይወትን ያሰማልን በጣም ደስ ብሎኛል!
እጅግ በጣም መልካም ፅሁፍ ነው። ራሴን ነው ያየሁበት። በፍቅር ሽፋን ልጆችን ከራሳቸውና ከፈጣሪያቸው የተጣሉ እንዳናደርጋቸው መጠንቀቅ አለብን።
ስለልጆች አስተዳደግ የበለጠ ግንዛቤ እንድናገኝ ይረዳናልልጅሽን ቅጪ ልጅህን ቅጣ እየተባባሉ ለሚወዛገቡ ቤተሰቦች ትልቅ ትምህርት ይሰጣልጽሁፍሽ ማጣቀሻ ያለባቸው በመሆኑ መልካም ነው በዚሁ ቀጥይ
ቃለ ህይወት ያሰማልን።