እግዚአብሔር ባይፈቅድ ነው

ካለፉት ቀናት መካከል አንደኛው ቀን የትምህርት ቤት ወንድሜን ለመጠየቅ የሄድሁበት ቀን ነበር። ከተገናኘን ብዙ ቀን ሆኖን ስለነበር ለእግርህ ውኃ ላሙቅልህ፣ ምግብ ይቅረብልህ አላለኝም። እንዲሁ ያለፈውን ዘመናችንን በዛሬ ዐይናችን እያየን በዛሬ ሚዛን እየመዘንን በሚያስቀው ስንስቅ በሚያስጸጽተው ስንጸጸት ቆይተን ለእንግድነቴ የሚገባው ግብዣ ከተደረገልኝ በኋላ ዛሬአችንን ወደ መገምገም ተመለስን። 

የቆሎ ተማሪ አፈር ላይ ተኝቶ ይማራል እንጅ “አፈር ፈጭተን ውኃ ተራጭተን” ይሉት ጨዋታ አያውቅምና ያ አፈር ላይ ተኝቶ አብሮኝ ይማር የነበረው ጓደኛዬ ዛሬ የአንድ ድርጅት ባለቤት ሆኗል። የሚኖሩበት ቤት ፀሐይ ሳትወጣ ብትዘገይ የሚያሞቅ፣ የተመኙትን ነፋስ የሚያነፍስ መሣሪያ የተገጠመለት ዘመናዊ ድንኳን ነው። በመጨረሻ የጠየቅሁት ጥያቄና የመለሰልኝ መልስ ነው ዛሬ ለምጽፍላችሁ ደብዳቤ መነሻ የሆነኝ። “ዜማ ቤት እያለን ማኅሌት በጣም ትወድ እንደነበር አውቃለሁ እንዲያውም ትዝ ካለህ ከማኅሌት ስትመለስ የመጀመሪያ ሥራህ የነበረው ተኝተው ያደሩ ተማሪዎች ላይ ውኃ መድፋት ነበር ዛሬስ እንዴት ነህ?” አልሁት ትንሽ እንደማፈር ሲል አየሁት። 

ትንሽ እንደማሰብ አደረገና “እኔማ አገልግሎት ምን ያኽል እንደምወድ አንተም ታውቃለህ ነገር ግን የምወደውን አገልግሎት ሰዎች አስጠሉኝና ተውሁት። ለጥቂት ቀናት እንዳልሄድ አለመፈለጋቸውን እያወቅሁ ተጋፍቸ ሄድሁ፤ አንድ ቀን መኪናዬን ያልተገባ ነገር አደረጉብኝ ሌላም ልነግርህ የማልፈልገውን አደረጉብኝ፤ ሲሰለቸኝ መቼስ ሰው ይደለሁ? በቃ ማገልገሌን እግዚአብሔር ባይፈቅድልኝ ነው ብየ እርግፍ አድርጌ ተውሁት ይሄው አራት ዓመቴ ማኅሌቱን ከተውሁት አለኝ”። 

እንዲህ አይነት መወሰኛ ቃል እየተጠቀምን ነገሮችን ሁሉ በጅምር የምናስቀር ብዙ ሰዎች መኖራችንን ባሰብሁ ጊዜ እንድጽፍ ተገደድሁ። ብዙ ሰዎች ብትጠይቋቸው ያላገቡት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ነው። ያልቆረቡት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ነው። ሥራቸው ስኬት ያላመጣላቸው እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ነው። የጀመሩትን ነገር ሁሉ ያልጨረሱት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ነው። ሩቅ አስበው ከቅርብ የተመለሱት እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ነው። እንዲህ እያሉ ይቀጥላሉ። ሁሉንም ነገር እግዚአብሔር ስላልፈቀደ ብለው ነው የሚተዉት።

ለአንዳንዶቹ የሚመስላቸው እግዚአብሔር ከፈቀደ ያለምንም ትግል ነገሮች ሁሉ የሚከናወኑ ይመስላቸዋል። እግዚአብሔር ከፈቀደ ነገሮች ሁሉ “ለይኩን” በሚል ትዕዛዝ እንዲፈጸሙላቸው ይፈልጋሉ። እግዚአብሔር የፈቀደልንን ሕይወት ለመኖር ሲባል እኮ ነው ይሄ ሁሉ ተጋድሎ፤ የሰማዕታት ተጋድሏቸው፣ የጻድቃን ምናኔአቸ፣ የደናግል የመነኮሳት ትዕግሥታቸው፣ የሰብአ ዓለም ሕግ መጠበቃቸው፣ የካህናት ትጋታቸው የእግዚአብሔርን ፈቃድ ለማስቀየር የሚደረግ ይመስላችኋል? ይሄ ሁሉ ሩጫ እግዚአብሔር የፈቀደልንን ሕይወት እንዳናጣ ለመሆን ነው። 

ሐዋርያትን “ሑሩ ወመሀሩ” ብሎ ያዘዘ ማነው? ቅዱስ ጳውሎስን “ንዋየ ኅሩየ ረሰይኩከ” ብሎ ያከበረ ማነው? ኃጥአንን ለንስሐ የጠራ ማነው? ነገር ግን በፈቀደላቸው መንገድ ሲጓዙ የሚገጥማቸውን ተጋድሎ ተመልከቱ። ዓለም ሳይፈጠር ጀምሮ መንግሥተ ሰማያት ለሰው የተዘጋጀች ስጦታ ናት ቢሆንም ዓለም ሳይፈጠር የተዘጋጀልንን ስጦታ ዓለምን ካላሸነፍን አናገኘውም ማቴ 25፥34፣ 1ዮሐ 5፥5

የእስራኤል ከግብጽ መውጣት ከእግዚአብሔር ዘንድ የተቆረጠ ነገር ነበር። “በግብፅ ያለውን የሕዝቤን መከራ በእውነት አየሁ፥ ከአስገባሪዎቻቸውም የተነሣ ጩኸታቸውን ሰማሁ፤ ስቃያቸውንም አውቄአለሁ፤ ከግብፃውያንም እጅ አድናቸው ዘንድ፥ ከዚያችም አገር ወተትና ማር ወደምታፈሰው ወደ መልካሚቱና ወደ ሰፊይቱ አገር ወደ ከነአናውያንም ወደ ኬጢያውያንም ወደ አሞራውያንም ወደ ፌርዜወናውያንም ወደ ኤዊያውያንም ወደ ኢያቡሳውያንም ስፍራ አወጣቸው ዘንድ ወረድሁ” ዘፀ 3፥7 ብሎ መውጣታቸው ፈቃዱ መሆኑን ገልጿል። 

ዳሩ ግን እስራኤል የእግዚአብሔር ፈቃድ ስለሆነ ያለምንም ሰልፍ ግብጽን ለቀው መውጣት አልቻሉም። እግዚአብሔር ለእስራኤል መውጣትን እንደፈቀደ ሁሉ የፈርዖንን ልብ እንደሚያጸናም “እኔም የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ” ዘጸ 4፥21። ብሏል። ምን አይነት ነገር ነው? በአንድ በኩል ፈቅጃለሁ እስራኤል ይውጡ ይላል በሌላ በኩል የፈርዖንን ልብ አጸናለሁ ይላል። 

ተመልከተው! የእግዚአብሔር ፈቃድ ታግለህ እንድታሸንፍ ነው እንጅ ለይኩን ተብሎ በቃል በተፈጠረ ዓለም ውስጥ በቃል እንደማዘዝ ቀላል በሆነ መንገድ እንድትጓዝ አይደለም። እግዚአብሔር ከፈቀደልህም በኋላ አስማተኞች ይፈታተኑሃል፤ ፈርዖን ፍርድ ያጠብቅብሃል፤ አስገባሪዎች ግብር ይጭኑብሃል፤ አንዳንዴም ለጸሎት ለዝማሬ ወደ ቤተ እግዚአብሔር ስታቀና ባዩ ጊዜ እንደ ሥራ ፈት ይቆጥሩህና ለማሰናከያ የሚሆን ሽልማት ያለው ሥራ ለምስጋና በተመደበው ጊዜ ያዘጋጁልሃል። እና አንዳንዴ እንዲያውም በቃ የጀመርሁት ጸሎት፣ ሱባኤ፣ ቅዳሴ፣ ቁርባን፣ ኪዳን የበለጠ ፈተናዬን ስላበዛብኝ ከሰይጣን ጋር እልህ ከምጋባ አርፌ ብቀመጥ ይሻለኛል እንድትል ያደርግሃል። እስራኤልም ያሉት እንዲሁ ነበር “በፈርዖንና በሠራዊቱ ፊት ሽታችንን አግምታችኋል፥ ይገድሉንም ዘንድ ሰይፍ በእጃቸው ሰጥታችኋልና እግዚአብሔር ይመልከታችሁ ይፍረድባችሁም” ዘጸ 5፤21 ብለው ሊያድኗቸው ከተላኩ አገልጋዮቻቸው ጋር መጣላት ጀመሩ። የተፈቀደልህ ቦታ እስከምትደርስ ድረስ ላንተ ነጻ መውጣት ከተላኩ ካህናት መነኮሳት ጋር ሳይቀር የሚያጋጭ ፈተና ያጋጥምሃል። 

በአንድ በኩል እግዚአብሔር የላካቸው ሰዎች “እኔ እግዚአብሔር ነኝ ከባርነት ነጻ አወጣችኋለሁ፤ ከተገዥነትም አድናችኋለሁ በተዘረጋ ክንድ በታላቅ ፍርድም እታደጋችኋለሁ ለእኔም ሕዝብ እንድትሆኑ እቀበላችኋለሁ” ዘጸ 6፥6 ብሏል ብለው ይነግሩናል። ግን እግዚአብሔር በሕይወታችን ውስጥ ወዴት አለ? በሥራችን የረዳን፣ መከራችን ያቀለልን፣ ባርነታችንን ያስቀረልን መቼ ነው? እንላለን አይደል? አወ ይቀላል ስንል መከራው እየበዛ ሲሄድ፤ በምንረግጠው ጭቃ ውስጥ የልጆቻችን ደም ተቀላቅሎ ስናይ፤ በከተማው የሚሰማ የገራፊዎች ጅራፍ ድምጽ ብቻ ሲሆን፤ እስራኤል በደሙ ጭቃ አቡክቶ በሚገነባው ፒራሚድ ግብጻዊ ሲያጌጥበት ስናይ ከዚህ ሌላ ስሜት ሊኖረን እንደማይችል ይታወቃል። 

ነገር ግን እውነቱን ከመጽሐፍ ቅዱስ ተረዱት። እግዚአብሔር “ኃይሌን ባንተ አሳይ ዘንድ ስሜም በምድር ሁሉ ይነገር ዘንድ ለዚህ አሰነሣሁህ” ሮሜ 9፥17 ብሎ የኃይ መገለጫ አድርጎታል። እኛ በፈርዖን ላይ የሚገለጠውን ኃይሉን እንጠባበቃለን እንጅ እግዚአብሔር እኛን ለማዳን አልፈቀደም ብለን አናንጎራጉርም። 

የጌታ ፈቃድ እስኪሆን እስኪደረግ ድረስ በብርቱ ትግል ውስጥ እናልፋለን። ከዚህ አስጨናቂ ሕይወት መውጣታችንን ቢወድም ኃይሉን በጠላቶቻችን ላይ እንዲያሳይ የኛ ትዕግሥት ያስፈልጋል። የእግዚአብሔርን ማዳን ገና በሰፊው ስትደረግልን በሕይወታችን ውስጥ እናያለን። ከተፈቀደልን ሕይወት የምንደርሰው በትዕግሥት ነው። 

ከማንጎራጎር ወጥተን በእኛ ላይ የወደደውን ለማድረግ ሥልጣን ያለውን ጌታ የሚያደርገውን ሁሉ በማስተዋል መመልከት ነው። ሸክላ ሠሪ የወደደውን ሊሠራበት በእጁ ያለውን ጭቃ ሥልጣን የለውምን? እግዚአብሒርም በእኛ ላይ የወደደውን የሚያደርግበት ሥልጣን አለው።

በትግል የምትኖሩ ሁሉ እግዚአብሔር በትግል ውስጥ ለምን እንዳኖራችሁ ትግላችሁ ውስጥ እግዚአብሔር እየሠራ ያለውን መልካም ነገር መርምሩና ድረሱበት። ምናልባትም በእናንተ ትግል ውስጥ ፈታኞቻችሁን እየቀጣላችሁ ይሆናል። የእስራኤል መቆየት ለግብጽ ቅጣት ነበር እንጅ ጥቅም አልነበረም። 

ግብጽ በውኃ ፋንታ ደም የቀዳችው፣ ምድሯ በቅማልና በጓጉንቸር የተሞላው፣ ለሦስት ቀናት ብርሃን ከማየት የተከለከለችው፣ ከንጉሡ ቤት ጀምሮ በሁሉም ግብጻውያን ቤት ውስጥ በማለዳ ሬሳ የተገኘው በእስራኤል መቆየት ነው። እስራኤልን መልቀቅ ጥቅሙ ለእስራኤል ብቻ ሳይሆን ለግብጻውያንም ነበር። ፈርዖን ግን ይህንን አላወቀም። 

ሰላም የነሡን ሰዎች ሰላም ቢሰጡን ዕዳ ቆልለው የሚያስጨንቁን ሰዎች ባያስጨንቁን ዕረፍቱ ለሁላችንም ከእግዚአብሑእር ዘንድ ይሆንልን ነበር ግን አስገባሪዎቻችን ይህ አይገባቸውም። እኛማ እግዚአብሔር የፈቀደው ቀን ሲደርስ ከዚህ መውጣታችን አይቀርም። ምክንያቱም በትግል ውስጥ እንድናልፍ ፈቃዱ ቢሆንም በዚያው ውስጥ ሳለን እጃችንን ለሞት እንደንሰጥ ግን አያደርገንም። 

ዳዊት ከተቀባ በኋላ በሳዖል መሳደዱ ዱር ለዱር መንከራተቱ አያስደንቅም? በእግዚአብሔር ፈቃድ ለንጉሥነት የተመረጠው ዳዊት ከዕለታት አንድ ቀን የሚበላው አጥቶ ያልተፈቀደለትን እንጀራ እስከ መብላት ደርሷል። ይህ ሁሉ መሆኑ የዳዊት መንግሥት የጌታ ፈቃድ ባይሆን ነውን? አይደለም! ጨለማውም የሚመጣው በጌታ ፈቃድ ነው። ብርሃንም የሚሆነው በጌታ ፈቃድ ነው። “ያለ እኔ ምንም ልታደርጉ አትችሉም” ዮሐ 15፥5 ማለቱን አስተውሉ!

Share your love

28 አስተያየቶች

  1. ቃለህይወትን ያሰማልን
    መንግስተ ሰማያት ያውርስልን

    የነብስ ምግብ

    • ቃለ ህይወትን ያሰማልን የአገልግሎት ዘመናቸውን ይባርክልን ። ማስተዋሉን ያድለን በፈተና ፀንተን እንድንቆይ ይርዳን🙏

  2. እጅግ በጣም አስተማሪና እንደኔ በስሜት ጀምሮ በትንሽ ፈተና እያቆመ በእግዚአብሔር ለሚያሳብብ ደግሞ መካሪ ጽሑፍ ነው ቃለ ሕይወትን ያሰማልን ።

  3. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን ሊቀ ሊቃውንት! ለእኔ በትክክለኛው ሰዓት ነው እንዳነብ የሆነልኝ። ተስፋ የመቁረጥን ስሜት የሚያርቅ ተስፋን የሚያስቀጥል ነው። እግዚአብሔር ያክብርልን!

  4. አሜን አሜን አሜን ቃለ ሕይወት ያሰማልን የአገልግሎት ዘመን ያርዝምልን

  5. “…እግዚአብሔር እየሠራ ያለውን መልካም ነገር መርምሩና ድረሱበት።”
    ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምሕር።

  6. ቃለ ሕይወት ያሰማልን
    በጣም ጥሩ ትምህርት ነው እኔም ብዙ ግዜ ሳይሆንልኝ ሲቀር እግዚዓብሔር ሳይፈቅድ ነው እላለሁ::

  7. ቃለህይወትን ያሰማልን
    መንግስተ ሰማያት ያውርስልን

  8. ቃለህይወት ያሰማልን🙏🙏🙏
    መምህር ያነሱት የመግቢያ ነጥብ የሁላችንን ችግር ነው: እግአብሔር ልቡና ይስጠን ለሁላችን

  9. እጅግ ድንቅ እና ወቅታዊ ትምህርት ነው ቃለሕይወት ያሰማልን አስበ መምህራን ያድልልን በእድሜ በጤና ያቆይልን።

  10. Kale heywet yasemalen .

    Betam melkam negern eyaregachu nw egzihabher yabertachu .

    FONT SIZEUN BETCHEMRUT aynu lemiyaschegrew sew akatach yehonal BACKGROUNDUM NECHUN betkeyrut le ayne yekelal.

  11. በጣም ግሩም ንባብ ነበር።
    በህይወት እንድኖረው እግዚአብሔር ይርዳን።
    ቃለ ህይወትን ያሰማልን መምህር

    • የኔታ ቃለ ህይወት ያሰማልን
      የሚያበረታና የሚያፀና መልእክት ነው

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *