እየኖሩ መሞት፡ እየሞቱ መኖር

ሞት በክርስትና ትርጓሜው ከእግዚብሔር ጋር በሚኖረን ቅርበትና ርቀት ይተረጐማል፡፡ ከእግዚአብሔር የሚኖረን ቅርበትና ርቀት ከነፍስ በሥጋ መለየት ላይ የተመሠረተ አይደለም፡፡ በእግዚአብሔር አርአያና አምሳል የተፈጠርን ሕያዋን ስለሆነን፡፡ ነፍሳችን ከእግዚአብሔር የመገናኘት ጉልበቷን በሞት አታጣም፣ ሥጋችንም የእግዚአብሔር ጥበቃ አይለየውም፡፡ ሞት መንፈሳዊ ግንኙነትን አያቋርጥም፡፡ በሐዲስ ኪዳን ሞት መሸጋገሪያ እንጂ መለያያ አይደለም፡፡ ሞት መውጊያውን የተቀማ ተሸናፊ እንጂ ባለድል አይደለም፡፡

እውነት ነው፣ የነፍስ ከሥጋ መለየት አለ፡፡ መሞት ማለት ግን ለዘለዓለም መጥፋት ሳይሆን የትንሣኤ ጉዞን መጀመር ማለት ነው፡፡ ከክርስቶስ ትንሣኤ ወዲህ ‹‹ስንሞት በርግማን ለሞት የተሰጠን ሆነን አይደለም፤ በትንሣኤ ሒደት ላይ ሆነን የጌታን ዳግም ምጽአት በተስፋ በመጠባበቅ እንጂ፡፡… when we die we no longer do so as men condemned to death but as those who are even now in process of rising we await the general resurrection of all›› ይላል ታላቁ አባት ቅዱስ አትናቴዎስ ሐዋርያዊ 1ኛ ቆሮ.15፡21 ላይ ተመሥርቶ፡፡ (https://janderebaw.org/on-the-incarnation-by-st-athanasius/)

ቅዱሳን በሞት የማይቋረጥ ኃይልና ቅድስና /continued power and holiness/ አላቸው፡፡ ‹‹ወጻድቃንሰ ርቱዓን ለዓለም የሐይዉ – ቀና የሚሆኑ ጻድቃን ግን ለዘለዓለም ይኖራሉ›› እንዲል (ግእዙ ጥበብ 3፡ 20)፡፡ ቅዱስ ዳዊት ‹‹ዘፃመወ በዓለም የሐዩ ለዝሉፉ እስመ ኢይሬኢ ሙስና›› (መዝ.48፡9) ያለውን አበው ሲተረጕሙ ‹‹ … በገድል በትሩፋት የደከመ ግን ፈጽሞ ይድናል … ጻድቃን በሥጋ ሲሞቱ ባየህ ጊዜ ‹በነሱም ሞት አለባቸውን?› ብለህ አታድንቅ …ጻድቃን በሥጋ ሲሞቱ እንዳየህ አእምሮ ለብዎ (እውቀትና ማስተዋል) የሌላቸው ኀጥአን በነፍስ ሲሞቱ ታያለህና …›› ይላሉ (መዝሙረ ዳዊት፡ ንባቡና ትርጓሜው፣ መዝ.48፡9፣ ገጽ 256)፡፡

በቀናው የክርስትና አስተምህሮ ሞት የምድራዊ ሕይወት ቆይታ ማብቂያ እንጂ የመንፈሳዊ ሕይወት መጨረሻ አይደለም – Physical death is the limit of physical life (GEORGES FLOROVSKY, CREATION AND REDEMPTION, 1976, P.259)፡፡ የቅዱሳን ሥጋዊ ሞት ለዘለዓለም ሕይወት መወለድ ነው፣ ዕለተ ሞታቸው ዕለተ ልደታቸው፣ ዕለተ ሞታቸው ዕለተ ሕይወታቸው ነው፡፡ ቅዱስ አምብሮስ ካረፈ በኋላም በፍሎረንስ ይታይ ነበር (ገድለ አምብሮስ 49-50)፡፡ በአፍሪካ በራዕይ ታይቷል፡፡ መታየቱ የኅብረታችን መቀጠል ማሳያ ነው፡፡ ሰው የሥጋ (የግዙፍ ነገር)ና የነፍስ (ረቂቅ ነገር) ተዋሕዶ ውጤት ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ሞትን በሥነ ሕይወታዊ ትርጓሜው አታየውም፡፡

አካላዊ ሞት የነፍስን ከሥጋ ወይም የነፍስን ከእግዚብሔር መለየትን እንጂ እንዳልተፈጠሩ ሆኖ ከሕላዌ ለዘለዓለም መጥፋትን አያመለክትም (physical death, does not imply annihilation but rather a state of radical separation)፡፡ እንደ ቤተ ክርስቲያን ሞት የሚለው ቃል ለሥጋም ለነፍስም ይነገራል፡፡ ‹‹የሥጋ ሞት፣ የነፍስ ሞት›› እንላለን፡፡ ዛሬ ተዘጋጅተን ካልኖርን ከአካላዊ ሞት በኋላም መንፈሳዊ ሞት ሊጠብቀን ይችላል፡፡ ሞት ለዚህኛውም ለሚመጣውም ዓለም ይነገራልና፡፡

በሞት መንፈሳዊ ትርጕም ውስጥ አንድ ሰው ከዚህ ዓለም ስለተለየ ብቻ እንደ ምዉት፣ በዚህ ዓለም ስላለ ብቻ እንደ ሕያው አይታይም፡፡ በክርስትና የሕይወት ትርጕም ውስጥ ‹እየኖሩ መሞት፣ እየሞቱ መኖር አለ፡፡ አዳም ‹‹በበላህ ቀን ትሞታለህ›› የተባለው ትእዛዝ የተፈጸመበት እንደበላ አካላዊ ሞት በመሞት ሳይሆን ከእግዚአብሔር በመለየት ነው፡፡ ከአካላዊው ሞት ቀድሞ የመንፈሳዊው ሞት ፍርድ ተፈጸመበት (ያረጋል አበጋዝ (ዲያቆን)፣ ኦሪት ዘፍጥረት ማብራሪያ፣ 2015 ዓ.ም.፣ ገጽ 204)፡፡

በሌላ በኩል በእምነት በምግባር አጊጠው ያረፉ ቅዱሳን በአካለ ሥጋ ቢለዩንም በክርስቶስ ሕያዋን ናቸው፡፡ የምሥራቃውያኑ ሊቅ ካሰፈረው ለመዋስ፡- ‹‹ … those in Christ are still alive—even in the state of death. The faithful not only hope for life to come, but are already alive, although all are waiting for Resurrection. – በክርስቶስ የሆኑት በሞት ጥላ ሥር ቢሆኑ እንኳ ሕያዋን ናቸው፡፡ አማንያን የሚመጣውን ሕይወት ተስፋ የሚያደርጉ ብቻ አይደሉም፣ ተስፋ ትንሣኤን እየጠበቁም እንኳ (ሞተውም) ሕያዋን ናቸው፡፡›› (GEORGES FLOROVSKY, CREATION AND REDEMPTION, 1976, P.260)፡፡ ስለ እኛ ይጸልያሉ ይማልዳሉ፣ እኛም ስለ እነርሱ እንጸልያለን እንማልዳለን፡፡

ኀበ ተርኅወ ገነት ወኀበ ተነጽፈ ዕረፍት ይክፍለ ነሀሉ ውስተ በዓቶሙ ለቅዱሳን – ገነት በተከፈተችበት፣ ዕረፍት በተነጠፈበት የቅዱሳን መኖሪያ እንኖር ዘንድ ያድለን፣ አሜን፡፡

Share your love

8 አስተያየቶች

  1. በጣም ደስ የሚል ጽሁፍ ነው። መምህር እግዚአብሔር ጸጋውን አብልጦ ይስጥልን። ቃለ ህይወት ያሰማልን

  2. እግዚአብሔር ይስጥልን። ቃለ ሕይወትን ያሰማልን። አስተማሪ ጽሑፍ ነው በርቱልን 🙏

  3. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን መምህር።
    እዚች ላይ ትንሽ ማብራሪያ ቢሰጡኝ መምህር “አካላዊ ሞት የነፍስን ከሥጋ ወይም የነፍስን ከእግዚብሔር መለየትን እንጂ እንዳልተፈጠሩ ሆኖ ከሕላዌ ለዘለዓለም መጥፋትን አያመለክትም።” ማለትም ከላይ የተነገረው ለነፍስ ነዉ ለስጋ? ለስጋ ከሆነ ስጋ ነፍስ ስትለየዉ በስብሶ ወደ ተገኘባቸዉ ባህርያት መመለሱ ከህላዌዉ ለዘለዓለም መጥፋት ባይሆንም ለጊዜዉ መጥፍትን አያመለክትም ወይ መምህር። አያይዘዉም የነፍስና የስጋ መገናዘብስ እስከ ምን ድረስ ነዉ? ከሞት በኃላ አንዱ የአንዱን ገንዘብ ማድረግ አለ ወይ?

  4. መምህር እግዚአብሔር ጸጋውን አብልጦ ይስጥልን። ቃለ ህይወት ያሰማልን

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *