ስለ ሲ ኤስ ሉዊስ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ መጽሐፍ እንደጀመርኩ የእውቀት እና የመንፈሳዊ ሕይወት ዓርአያዬ የሆነ የመንፈስ ታላቅ ወንድሜ ሲ ኤስ ሉዊስ ለቅዱስ አትናቲዎስ ነገረ ሥጋዌ መጽሐፍ ትርጉም የጻፈውን መግቢያ እንዳነበበው እና በሉዊስ እንደተደመመ ነገረኝ። እኔም ወዲያው ያን መግቢያ ፈልጌ ማንበብ ጀመርኩኝ።
በዐሥራ ስደስተኛው ክፍለ ዘመን ስለተጻፉ የእንግሊዘኛ ከድራማ በቀር መጽሐፎች ለኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ለመጻፍ በ፩፮ኛው ክፍለዘመን ውስጥ በእንግሊዘኛ የተጻፉ ሁሉንም፣ አዎ ሁሉንም መጽሐፎች ያነበበው ሉዊስ የአትናቴዎስን የነገረ ሥጋዌ መግቢያ ስለመጽሐፍ ንባብ ነበር ያደረገው። ሉዊስ የአትናቴዎስን መጽሐፍ እስካሆን ለምን ብዙ ሰዎች እንዳላነበቡት በመብሰልሰል የጻፈው ነበር። ለዚያ ዋነኛ ምክንያቶቹ ደግሞ ሰዎች ለጥንታዊ መጽሐፎች የሚሰጡት ዋጋ (ገበያ ተኮር ስላልሆኑ)፣ በሚረዱት መልኩ ቀሎ ለቀረቡላቸው መጽሐፎች ማዘንበላቸው እና አንድን ነገር በፍጥነት ለመረዳት የማሰብ የስንፍና ዝንባሌ ነው። የሉዊስ መግቢያ እኔ በሕይወቴ የንባብ ልምዴ የተቀየረበት ምክር ጋር ሙሉ ለሙሉ ይመሳሰላል።
ከዛሬ አስር ዓመት በፊት ነበር። ዶ/ር ዳኛቸው አሰፋ በኤግዚብሽን ማዕከል በተዘጋጀ በንባብ ላይ ባተኮረ መርሐግብር ተገኝቶ ስለንባብ ፍልስፍናዎችን እና የእሱን ዕይታ ያካፍል ነበር። ከንግግሩ የማስታውሰው ይሄን ብቻ ነው። “ባይገባችሁም እንኳ ከባድ እና የድሮ መጽሐፍ አንብቡ። ደካማ መጽሐፍ ገብቷቹ አንባቢ ተብላችሁ ከሚያስኮፍሳቹ ፥ ለጥቂት ጊዜያት ሳይገባችሁ እንኳ ከባድ መጽሐፍን አንብቡ። ከጥቂት ጊዜ በኋላ ለእናንተ ለመረዳት የሚከብዳችሁ ሀሳብ አይኖርም” አለ።
ሉዊስ በዚህ ደረጃ ባይናገርም ፥ ከዘመናት በፊት ሁለት ሺ ዘመናት አልፎ ተነባቢ ለሆነ መጽሐፍ መግቢያ ሲጽፍ ተመሳሳይ ምክር ነበር የሰጠው።
ሰው ማንበብ ያለበት መረዳት የሚችለውን መጽሐፍ ብቻ ነው የሚል የሰነፎች ፍልስፍና ከየተ እንደተጣባኝ ባላውቅም፣ ደራሲ እንዳለ ጌታ በጻፈው አንድ መጽሐፉ ላይ ደራሲ ስብሃት ገብረ እግዚአብሔር ወልቂጤ መጥቶ አንድ ወጣት የሱን መጽሐፍ ለማንበብ ብዙ ጊዜ ቢፈልግም ስለማይገባው ሊገፋለት እንዳልቻለ እና ምን ማድረግ እንዳለበት ጠየቀው። የስብሃት መልስ እንደዘወትር ቀላል ነበር። ራስ ተኮር። “የኔ መጽሐፍ ካልገባህ ተወው ፥ ስንት የሚገባህ መጽሐፍ እያለ። ያንድ ሽማግሌ መጽሐፍ ብታነብ ባታነብ ምን ልታጣ ነው” አለው። ያ እንዳለ ጌታ የከተበው የስብሃት መልስ መጽሐፍ ሲከብደኝ ለስንፍናዬ ያለሰቀቀን መሽሎኪያ ነበር። የሚገባኝን፣ ማለትም በእኔ አቅም ያለን መጽሐፍ አንስቼ ማንበቤን እጀምራለው። በዚህም የገደል ማሚቱ ይሆናል ሁሉ ነገር። ራስን ማድመጥ፣ ራስን መስማት፣ የራስ አስተሳሰብ በሌላ ሲነገር መኮምኮም ብቻ ይሆናል።
በዓመት ከአስር ሚሊዮን በላይ መጽሐፍ በሚታተምበት ዘመን ላይ ነው ያለነው። በዚህ ዘመን እየኖርን ስለንባብ ጥቅም እና ማንበብ እንዳለብን ሳይሆን መነጋገር ያለብን “ምን ዓይነት መጽሐፎችን ላንብብ?” “እንዴት እነዛን መጽሐፎች ልምረጥ?” ነው መሆን ያለበት ውይይታችን። ያ ማለት ግን ቀላል የማይባል ፊደል የቆጠረ ሰው መጽሐፍትን ገልጦ በደስታ ማንበብ ሸክም እንደሚሆንበት ጠፍቶኝ አይደለም። ይልቁስ ምግብ ላጣ ሰው ‘ይሄን ምግብ ብላ’ እያሉ የምግብ ዓይነቶችን መዘርዘር ነው ጤንነትን ተጠየቅ ውስጥ የሚያስገባው እንጂ ቡፌው በምግብ ተጠቅጥቆ ሳለ የምግብ ፍላጎቱ ለተዘጋ ሰው ሳይቀር ቢያንስ አንድ ጉርሻ እንኳ እንዲሞክር የምትጋብዙት እጅግ የሚጥመውን ምግብ ነው። ምክንያቱም ሌሎቹን ባይቀምሳቸውም የሚያጣው እምብዛም ስለሆነ። በተመሳሳይ የትውልዱ አንባቢነት በተለያዩ ምክንያቶች ተዳክሞ ቢታየን እንኳ ፥ እንደው ተሳስቶ እንኳ ካነበበ ከተዘረገፉት መጽሐፎች ውስጥ ማንሳት ስላለበት መጽሐፍ አብዝቶ ማውራት ፥ የንባብ ባህል እንዲዳብር ከመቀስቀስ እኩል ወሳኝ ነው።
ኢትዮጵያኖች ግን ለዚህ ሉዊስም ሆነ የፍልስፍናው መምህር የዶ/ር ዳኛቸው ምክር እምብዛም ባላስፈለገን ነበር። ይሄን ማለቴ ኢትዮጵያዊው ጃንደረባ (ሐዋ ሥራ ፰፥፪፮-፫፱) ለንባብ ባህላችን ምን ያህል ቋሚ ምስክር ፣ ቋሚ ሃውልት ሊሆነን እንደሚችል ሳስብ ነው። ይሄ ታላቅ ሰው ፥ በሚያንገጫግጭ መንገድ ላይ በሰረገላ እየሄደ የሚያነበው የሚያስቅ እና ጊዜ መግደያ የሚሆን ነገር አልነበረም። በሚያንገጫግጭ መንገድ ላይ እየተለወሱ እየሄዱ ይቅርና መጓዛችንን እምብዛም በማይሰማን የአይሮፕላን ጉዞ ላይ ሳይቀር ለመረዳት የሚከብደንን ነገር አንስቶ ማንበብ ምን ያህል እንደሚፈትን ይሄን የሞከራችሁ ታውቃላችሁ። ያ ታላቅ ኢትዮጵያዊ ጃንደራባ ግን ለመረዳት የሚቸግረውን ፥ የታላቁን ነቢይ የኢሳያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር።
ሐዋርያው ፊልጶስ “የምታነበውን ታስተውለዋለህን? ሲለው ያ ጃንደረባ የሚያነበው ምን ያህል እንደፈተነው በግልጽ ነበር የተናገረው። በዚህም ግልብ አንባቢ በሆኑ ሰዎች ላይ ከሚታየው ትዕቢት ኢትዮጵያዊው ምን ያህል እንደተላቀቀ እና በትህትናው ጥልቀት መንፈስ ቅዱስን እንደሳበ እናነባለን። ከባድ እና ለመረዳት የሚያዳግትን ነገር የምናነበው አንድም ለዚህ ነው። የሌሎችን ርዳታ ለመሻት። በኛ ደረጃ ያለን ነገር አብዝቶ ማንበብ ለትዕቢት እና ያነበቡትን ለሌሎች ለመናገር ፍላጎትን ይቀሰቅስ ይሆናል እንጂ ትህትናን አያጋብዝም። ከሌሎች አዋቂዎች ጋር እምብዛም አያዛምድም። ሲከብደን ነው የሌሎች ወዳጅነትን የምንሻው። በዚህም ራስን ዝቅ ማድረግን ብቻ ሳይሆን ፥ የእውቀት ዘመዶችን እንፈጥራለን።
ጃንደረባው የሚያነበው ማንበብን ግብ አድርጎ አልነበረም። ምንም ባለጸጋ እና በንግሥት ህንደኬ ገንዘብ ላይ የተሾመ ቢሆንም ፥ ሕይወት ከቁስ በላይ፣ ሕይወት ከምድራዊ ስልጣን በላይ እና ምቾት በላይ እንደሆነ ስለገባው የነፍሱን ጥማት ለማርካት በማሰብ ነበር የሚያነበው እንጂ ጊዜ ለመግደል እና እስቲ እከሌ እንዴት ነው የሚያስበው፣ ስለዚህ ጉዳይ ምን ይላል በሚል ተራ የእውቀት ጉጉት አልነበረም። ለዚህም ነው ከፊልጶስ ጋር ሲሄድ በመንገዱ ውሃ ሲመለከት ወደ ተግባር ለመዝለል የተጣደፈው።
በዚህ ምድር ላይ በኖርንበት ዕድሜ መጠን ብዙ አንባቢዎችን እና የተማሩ ሰዎችን አይተናል። አንዳንዶቹ በሚያስገርም ብቃት ያነበቡትን እንደ ፎቶ ኮፒ የያዙ እስከ ገጽ ቁጥሩ የሚናገሩ ናቸው። እነዚህ ሰዎች ገጥመውኛል። የሚያሳዝነው ግን ብዙ ጊዜ ሕይወታቸው ከአንድ ያነበበ ሰው የምንጠብቀው አርዓያ የሚሆን አይደለም። ይልቁስ እነዚህ ሰዎች ከንባብ ለተጣሉ ሰዎች እንደ ሰበብ የሚጠቀሱ ናቸው። “ማንበብስ እንዲህ ከሆነ ይቅርብኝ” የሚያስብሉ። ይሄን ነው ዘወትር ለራሴ “ማንበብህ ግብ አይደለም” ብዬ የማሳስበው።
ንባባችን ወደ ሕይወት መተርጎም ካልቻለ፣ የባሕርይ ለውጥ ማምጣት ከተሳነው፣ ካልቀየረን ፥ እውነት ነው ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል። ለኛ ትዕቢት ለሌሎች መሰናክል ብቻ ነው የምንሆነው። ያ ኢትዮጵያዊው አንባቢ ጃንደረባ ግን “ለጠቢብ ቃል ይበቃዋል” በሚለው ብሂል ውሃ ሲያይ ሐዋርያውን መራው። ከንባብ፣ ከእውቀት መሻገር እንደሚፈልግ ገለጸለት። የተግባር ሰው መሆኑን አሳወቀው። የሚያነበው ለመለወጥ እንጂ ለመደሰት አልነበረም። እውቀትን የጨመረ ሀዘንን ይጨምራል። ምክንያቱም በዚህ ምድር ላይ ለደስታ አልተጠራንም። በዚህ ምድር ላይ ደስታን እንደሚፈልግ ጎስቋላ ሰው የለም። አያገኛትም’ና። ይሄ ምድር የጠላት ቀጠና ነው። ንባባችን በበዛ ቁጥር ስለ ጠላት ሥራ እና በሱ ተንኳን ስለሚወድቁ ነው አብዝተን የምናውቀው። በዚህ ለመደሰት ከጠላት ወገን መሆን ያስፈልጋል። ጃንደረባው ለዚህ ነው ዓለምን ሁሉ ቢያተርፍም ፥ ንባቡ ግን ወደ እውነተኛው መንገድ መራው። ለዚህም ራሱን ከምቾት እና ደስታ ነጥሎ የማይረዳውን መጽሐፍ በጭንቀት ጭምር ማንበብን መረጠ።
በመግቢያዬ ወዳነሳውት ሲ ኤስ ሉዊስ ልመለስ። ሉዊስ በንባብ ዓለም ውስጥ ካሉ ሰዎች በላይ ለንባብ አዲስ የሆኑ ሰዎች ጥንታዊ እና ከባድ የሚባሉ መጽሐፎችን ከአዲስ እና ቀላል ከሚባሉ በጽሐፎች በላይ መምረጥ እንዳለባቸው ይመክራል። ለዚህም ምክንያቱ ጥንታዊ መጽሐፎች የጊዜን ፈተና ያለፈ እና በብዙ አዋቂዎች በዘመናት ውስጥ ተመዝነው የተሻገሩ ናቸው። ወጣኒ አንባቢ በዚህ ዘመን የተጻፈ መጽሐፍ አንስቶ ቢያነብ ይሄ መጽሐፍ ባለማወቅም ሆነ በተንኳል ከሚያሰራጨው ስህተት ራሱን መጠበቅ አይችልም።
አዲሱ መጽሐፍ ገና በፍርድ ሚዛን ላይ ነው፣ ገና ዳኞች አንባቢዎች፣ አዋቂዎች አብላልተው ፥ ከጊዜ ጋር ፈትሸው ያላሳለፉት ነው። ይሄን መጽሐፍ የሚያነብ ንዑሰ አንባቢ መጽሐፉ ያነሳው ሀሳብ ሁሉ እውነት ይመስለዋል። በዚህም ሕይወቱን በዚህ በጊዜ ፈተና ተፈትሾ ባላለፈ ሀሳብ ለመምራት ሊዘረጋ ይችላል። ሁላችንም የሆነ ጊዜ ጀማሪ አንባቢ ነበርን። ይሄን ስሜት እናውቀዋለን። ዛሬ ስንበስል ደግሞ የሚማርክ ሀሳብ እንኳ ቢሆን እንዴት ባለ ጥንቃቄ ወደ ውስጣቻን እንደምናስገባው እናስተውላለን። አዲስ እና አሁን የሚወጡ መጽሐፎች መጥፎ ናቸው እያልኩኝ አይደለም። ወይም ሉዊስ እንዳለው አንድ ነገር የድሮ ስለሆነ ብቻ ጥሩ ነው የሚል ብዥታ ውስጥ ገብቼ አይደለም። ይልቁንስ ጊዜ ከሌለን ወይም በቂ የንባብ ጊዜ ካለንም ቢያንስ አብዛኛው የንባብ ቃረሞታችን በየትኛው ማሳ ላይ መሆን እንዳለበት ለመጠቆም እንጂ ክርስቲያኖች በዚህ ዘመን ያሉ እውቀቶችንም ለማግኘት መትጋት አለባቸው።
ከብዙ ጊዜ በፊት የፍራንሲስ ፉኪያማ “The end of history and the last man” የሚለውን መጽሐፍ በታተመ ወቅት የሚያነብ ጀማሪ አንባቢ፣ ፉኪያማ በመጽሐፉ ለዘረገፋቸው ማስረጃዎች እጁን ሰጥቶ ፥ ከዚህ በኋላ የሊብራሉ ዓለም በፍጹም ፍልስፍናዊ የበላይነት እንዳሸነፍ ሊያምን እና የምዕራቡ ዓለም አምላኪ ሊሆን ይችላል። ቀላል የማይባሉም ሆነዋል። ያ መጽሐፍ ከተጻፈ አስር ዓመት በኋላ ከፊኪያማ ይልቅ ሳሙኤል ሀንቲንግተን (“the clash of civilizations”) ልክ እንደነበረ እና በዚህ ዓለም ላይ የባህል እና የማንነት ግጭቶች እና ልዩነቶች መቼም እንደማይቀሩ ያስተውላል። በንባብ እና ሕይወትን በመመዝን (reflection) ስናድግ የትኛውም ስልጣኔ ታላቅ ሆኖ እንደተነሳው ሁሉ ተንኮታኩቶ እንደሚወድቅ መረዳት ላይ እንደርሳለን።
በዚህም የዚህን ዓለም ነገር በራስ ዕድሜ መጠን መመዘን የማቆም ጥበብ ጋር እንገናኛለን። ከዚህ ጥበብ ጋር ነው ታላላቅ እና ጥንታዊ መጽሐፎች የሚያስተዋውቁን። ከጊዚያዊነት ያወጡናል፣ ከዕለታዊነት ያሻግሩናል። ይሄ ሕይወት እኛ ለመጀመሪያ ጊዜ የምንኖረው እንዳልሆነ ደም ሥራችን ድረስ ገብቶ እንዲሰማን ያደርጉናል። በዚህም ዘመናት ወደ ማይሽሩት ፥ ወደ ማይደፈቀው እውነት ይመሩናል።
እጅግ በጣም አስተማሪ ፅሁፍ ነው
እግዚአብሔር ይስጥልን !!!
ድንቅ ኑው በርቱልን!
እግዚአብሔር ጸጋውን ክብርን ያብዛላችኹ!
Thank you sir, for your wonderful post. I am not that much of a reader to judge your opinion, but in my perspective, the habit of reading is something that grows with time, as is our level of understanding. So I believe that it is better to start with books that are simple to understand, and gradually move to those that are beyond our level of understanding with the help of others.
On point it reminded me of what Dr meskerem Lechisa said in one of her interviews, she mentioned that our fathers use to guard the people from western philosophy.
My son, give attention to my words; incline your ear to my sayings. Do not let them depart from your eyes; keep them in the midst of your heart; for they are life to those who find them, and health to all their flesh. Proverbs 4:20–22
🙏መልካም ዕይታ
“…አዲስ እና አሁን የሚወጡ መጽሐፎች መጥፎ ናቸው እያልኩኝ አይደለም። ወይም ሉዊስ እንዳለው አንድ ነገር የድሮ ስለሆነ ብቻ ጥሩ ነው የሚል ብዥታ ውስጥ ገብቼ አይደለም።…”
አማርኛው እንደዚያ መሆኑን ብዙ ባላውቅም ብዙ አንባቢ ጋር ይህ ቦታ ሲተረጎም ሉዊስ አንድ ነገር የድሮ ስለሆነ ብቻ ጥሩ ነው የሚል ብዥታ ውስጥ ገብቷል የሚል እንድምታ መፍጠሩ አይቀሬ ነው። ሉዊስንም እስከማውቀው፣ ጸሐፊውም ሊሉ የፈለጉት ግን እሳቸው ከሉዊስ ጋር ይህን ብዥታ ነቅሰው አውጥተው እንደጣሉት ይመስለኛል።
አመሠግናለሁ::