ይሄ ፈተና ከምን መጣ? ፈተናው ከእኛ ጋር ካሉት ይልቅ በእኛ ላይ ለምን በዛ? ምንጭ የሌለው ፈተና ባይኖርም ምንጩን ሳናውቀው በመጣ ፈተና ነፍሳችን ደከመች። ሰውነታችን ኑሮን ሰለቸች። ፈተናው አስመርሮናል፤ መከራው ከብዶናል ነገር ግን የፈተናውን ምክንያት ሳናውቅና ሳንመረምር ከፈተና ወደ ፈተና ስንሸጋገር እንኖራለን። በመጀመሪያው ማስቆም ሲቻል የመጀመሪያው ፈተና ይኸው ለቀጣይ ፈተና አሳልፎ ሰጥቶን በፈተና እንናወጣለን። በዚህ መንገድ አልፈው ብዙዎቹ ለሚፈልጉት ስኬት ደርሰዋል እኛ ግን አቃተን። በኛ ዘንድ ምናኔም ፈተና ሆኖብናል፤ ትዳርም ፈተና ሆኖብናል። ለምን?
ትዳር በእኛ አልተጀመረም። ከሴት ጋር መኖር ለብዙዎች በረከት ነው። መጽሐፍም “መወደዷ ከወርቅ ይመረጣልና ብልህና ደግ የሆነች ሴትን አትጥላ” ሲራ 7፥19 ብሎ ከቀይ ወርቅ ይልቅ የተወደደ ጸጋ ያላት መሆኑን ይናገራል። ቢሆንም እኛ ዘንድ ሲመጣ ፈተና ያልሆነብን ምን ነገር አለ? ቅዱሳን ሐዋርያት “በጌታ ዘንድ ሴት ያለ ወንድ፤ ወንድም ያለ ሴት አይሆንም” 1ቆሮ 11፥11 ብለው እያስተማሩን እኛ ግን ከዚያ ውጭ በሆነ ሕይወት መኖር እንደነበረብን እያሰብን ነው ያለነው።
የፈተናዬ ምንጭ እሷ ናት ወይም እሱ ነው እየተባባሉ የሚኖሩ ብዙዎች ናቸው። ባል ሚስቱን፤ ሚስትም ባሏን፤ ወንድም ወንድሙን ወይም አንዱ በሌላው ምክንያት ይህ ፈተና እንደመጣበት ሊያስብ ይችል ይሆናል። ዳሩ ግን የፈተና ምክንያት ብዙ ጊዜ በክርስትና ወጣንያን በሆኑ ሰዎች ሕይወት ውስጥ የራሳችን ፍላጎት እንጅ ከሰው ወይም ከሰይጣን የሚመጣ ፈተና እምብዛም የለብንም።
ከዕለታት በአንድ ቀን ጴጥሮስና ዮሐንስ ክርስቶስን ተከትለው ወደ አንድ ስፍራ ተጓዙ። ደብረ ታቦር ወይም ደብረ ዘይት ተከትሎ እንደመሄድ ያለ ቀላል መንገድ ግን አልነበረም። የሰው ገጠመኙ ብዙ አይደል? መንገዶች ሁሉ ወስደው፣ ወስደው የሚያጋፍጡን የሕይወት ግጥሚያ የተለያየ ነው። የነዚህም ቅዱሳን ሰዎች ጉዞ ከዚህ በፊት ከእርሱ ጋር ሲያደርጉት እንደነበረው ያለ ቀና መንገድ አልሆነላቸውም። እስካሁን በተጓዙባቸው ቦታዎች ሁሉ መለያየት አልታየባቸውም ነበር፤ በሁሉም መንገዶቻቸው ዕኩል ተጉዘው አብረው በደስታ ይመለሱ ነበር። ለሌላው የማይነግሩት ድንቅ ምሥጢር ተገልፆላቸው ይመለሱ ነበር። የዛሬው ግን ይለያል። አንዱን ከአንዱ የለየ ታሪክ የተስተናገደበት፤ ወንድማማቾች አብሮ ጀምሮ አብሮ መጨረስ ያልቻሉበት ፈታኝ ጉዞ ነበር። የጸና ብቻ ካልሆነ የተጓዘ ሁሉ የማያሸንፍበት መንገድ።
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተያዘባት ሌሊት ከደቀ መዛሙርቱ መበተን በኋላ ከመበተን ተርፈው ሁለቱ ጴጥሮስና ዮሐንስ ብቻ እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ ተከትለው መሄዳቸውን ቅዱስ ዮሐንስ በጻፈው ወንጌል ላይ ተጽፏል ዮሐ 18፥15 የጴጥሮስ መከተል በተናገረው ቃል መሠረት ነው ሉቃ 22፥33። የዮሐንስ ግን የሚደንቅ ነው። በአፉ ሳይናገር ሠርቶ የሚያሳይ ሰው እንዴት የታደለ ነው። ስላልነገሩን፣ ስላልጻፉልን፣ የጻፍነውን like share ስላላደረጉልን እንጅ በልባቸው የሚወዱን ስንት ሰዎች አሉ መሰላችሁ።
ከጴጥሮስ ቀድሞ በልቡ ከክርስቶስ ጋር ለመሞትም ሆነ ለእስራት ሊሄድ በልቡ ቃል የገባ ዮሐንስ ነው ነገር ግን በጉባኤ መካከል ከመናገር ተቆጥቦ ጉባኤው ከተፈታ በኋላ ሲያደርገው ታየ። ሕዝብ ሲሰበሰብ፣ ጉባኤው ሲሰፋ ማያደርጉትን ሚቀባጥሩ፤ እጃቸው ላይ የሌለውን ዘር ሊዘሩ የሚሞክሩ፤ በራበው ሕዝብ መሳለቅ ልምድ ሆኖባቸው ሊጎርስ አፉን ለከፈተ ሕዝብ እንጀራ ያልጠቀለሉበትን እጃቸውን የሚዘረጉ፤ የሕዝቡ መሰብሰብ ብቻ ገፋፍቶ የማያውቁትን የሚያናግራቸው፤ ከመናገራቸው በፊት ያላሰቡትን ተናግረው የሚያስቡ ሰዎች ይገርሙኛል። እንደ ዮሐንስ ያሉት ክርስቲያኖች ግን ሁሉን ነገር በጊዜውና በቦታው ካልሆነ አያደርጉትም። የቅዱስ ጴጥሮስ ፈተና የሚጀምረው ከዚህ ነው − የማያደርጉትን ከመናገር።
የማትፈጽሙትን ቃል ኪዳን አትግቡ። ከባድ ፈተና በሕይወታችሁ ይዞ ይመጣና ሕይወታችሁን ይበጠብጣል። ቃል ኪዳናችሁ ከመፈጸም ዐቅማችሁ በላይ ሊሆን አይገባም።
ለማንኛውም የጴጥሮስ ፈተና ቀጠለ። እስከ ሊቀ ካህናቱ ግቢ በር ድረስ አብሮ ቢመጣም ክርስቶስ በገባበት የመከራ በር አብሮ መግባት ከበደው። ለነፍሱ ሳስቶ ከበር ውጭ ቆሞ ቀረ። በሰዎቹ ዘንድ በመታወቅ ቢሆን ኖሮ ከዮሐንስ የሚበልጥ እሱን የሚያውቀው አልነበረም። “በሊቀ ካህናቱም ዘንድ የታወቀ ነበረ” ተብሎ የተጻፈው ለዮሐንስ ነውና። ግን ዮሐንስ በልቡ ጨክኖ ስለነበር ከክርስቶስ ፍቅር የሚለየው ምንም ነገር አልነበረም። ጴጥሮስ ገና ለዚህ መዐርግ አልደረሰም። የበረታው ዮሐንስ ያልበረታውን ወንድሙን ሊያበረታ ወደ ውጭ ወጥቶ ለበረኛይቱ እንድታስገባው ነገረለትና ገባ።
የበረታ ባልንጀራ ማለት ወንድሙን አንድ እርምጃ ወደ ክርስቶስ ማቅረብ የቻለ ነው። ግን አሁንም ሁኔታዎቹ ለጴጥሮስ ምቹ አልነበሩም። ቀኑ በጣም ውርጭ ነበርና የመጣበትን የክርስቶስን ነገር ረስቶ እሳት አንድደው ከሚሞቁ የሊቃነ ካህናቱ በለሟሎች ጋር ተሰልፎ ነፍሱን ለጊዜው ከሚደርስባት ጭንቅ ማዳን ፈለገ። የእሳቱ ወጋገን በገለጠላቸው ብርሃን ተመርተው ሂደው እየተመላለሱ መላልሰው ሃይማኖቱን አስካዱት። ያሳዝናል! በጥቂቱ የተጀመረ ፈተና አሁን ይኸው እዚህ ደረሰ። በትንሹ ያላጠፋነው ኃጢአት ለትልቅ ኀጢአት አሳልፎ ይሰጣል።
አሁን በሕይወታችን ለገጠመን ለዚህ ሁሉ ፈተና መነሻ የሆነውን ነገር እንዳትረሱ፤ ያ በመጀመሪያ ከልብ ጨክነን የማንፈጽመውን ቃል መግባታችን ነው። ብዙዎች ጥሩ ባለትዳር ሊሆኑ ሲችሉ ወደ ምንኩስና ገብተው ራሳቸውን ፈተኑ። አንዳንዶቹ ደግሞ ጥሩ መነኮሳት ሊሆኑ ሲችሉ ወደ ትዳር ገብተው ለራሳቸውም ለትዳር አጋራቸውም ፈተና ሆኑ። አንዳንዶቹ አለቅነት አልተሰጣቸውም። ለአለቅነት መሐላ ሲፈጽሙ ተዉ የሚላቸው ጠፍቶ ነው እንጅ ዛሬ እንዲህ የማይወጡት ፈተና ውስጥ ወድቀው አይቀሩም ነበር። ይሄን ሁሉ የትዕቢት፣ የፍቅረ ንዋይ፣ ድሆችን የመጥላት፣ ያለ ጊዜ መብላት መጠጣት እና ሌሎችም ፈተናዎች ከወዴት መጡ? ከምንችለው በላይ ማሰባችን፣ የማይገባ ንግግራችን የሚያመጣብን ፈተና ነው። ከቆንምለት ዐላማ መዛነፋችን፣ መንገዳችንን መሳታችን፣ ጅማሬአችንን ከፍጻሜችን የተለየ አድርጎታል።
ብዙዎቻችን አሁን በምንኖረው ሕይወት የጠበቅነውን ኑሮ ማግኘት አልቻልንም። ከዓለም ወጥተን ወደ ቤተ ክርስቲያን መጠጋታችን፤ ከመሸታ ቤቶች ይልቅ ቤተ ክርስቲያን አካባቢ ለማምሸት መምጣታችን፤ በችግራችን ሁሉ ካህናትን ለማማከር መወሰናችን፤ ለሕመማችን ቅዱስ ቊርባንን እንደ መፍትሔ ማሰባችን አሁን የደረሰብን ፈተና እንዳይደርስብን በመስጋት ነበር። ነገር ግን ካሰብነው በተቃራኒ ሆነ። ፈተናው መልኩን ቀይሮ መጣ። ለምን? አንዳንዶቻችን የፈተናው ምንጭ ራሳችሁ መሆናችሁን ላስረዳችሁ።
ከዓለማዊነት ወጥታችሁ ቤተ ክርስቲያን አዘውታሮች መሆናችሁ መልካም ነበር፤ ነገር ግን ትንሽ ከቆያችሁ በኋላ ለድኅነት ብላችሁ በተጠጋችኋት ቤተ ክርስቲያን ከድኅነቱ ድኽነቱ ይቅደም ብላችሁ BUSINESS መሥራት ጀመራችሁ። ዛሬ ለናንተ የታቦት መውጣት በጉጉት የምትጠብቁት የገቢ ምንጭ ሆኗል። ከመሸታ ቤት መውጣታችሁ መልካም ነበር፤ ነገር ግን አሁንም መጠጡ ነው እንጅ የቀረው የመሸታ ቤቱን ወሬ ይዛችሁት ቤተ ክርስቲያን ገብታችኋል። አዳራሽ ውስጥ በተቀመጣችሁ ጊዜ የምታወሩት ፌዝና ቧልት ከመሸታ ቤት ሰዎች በምን ይለያል? ያኔ ወደ እግዚአብሔር ፊታችሁን እንድትመልሱ ወንጌል የሰበኩላችሁና የዘመሩላችሁ ሰዎች ዛሬ የጫወታ ማድመቂያዎቻችሁ ናቸው።
ለሕመማችሁ ቅዱስ ቊርባንን መድኃኒት ማድረጋችሁ መልካም ነበር፥ ነገር ግን እንደ ቆረበ ሰው የኖራችሁት ኑሮ ወዴት አለ? ያለ ልክ ትናገራላችሁ፤ ሰክራችሁ ትታያላችሁ፤ አድማ ትሠራላችሁ፤ ሰውን ትጠላላችሁ። ታዲያ እንዴት በቊርባኑ ትጠቀማላችሁ? አንድ ሐኪም ባዘዘው መሠረት ያልተወሰደ መድኃኒት በሽታ የመከላከል ዕድል ሊኖረው ይችላልን?
ችግራችሁን ለመፍታት ካህናትን ማማከራችሁ መልካም ነበር “የማይፈታውን እንፈታ ዘንድ ሥልጣንን የሰጠኸን….” ብለው በመጽሐፈ ኪዳን ሲጸልዩ የሰማናቸው ካህናት ካልፈቱት ችግራችንን ማን ሊፈታው ይችላል። ነገር ግን ስህተታችሁ ምን እንደሆነ ታውቃላችሁ? ከእውነተኞች መምህራን ትምህርት ይልቅ እንደ ሥነ ልቡና ባለሙያ ትችላለህ፤ ሕልም አለህ፤ የጌታ ልጅ ስለሆንህ ሁሉ ያንተ ነው፤ ጠላትህ የተወጋ ይሁን፤ ዐይነ ጥላ ተደርጎብሀል፤ ድግምት ተደግሞብሀል ወዘተ የሚሏችሁን ትከተላላችሁ። እውነተኛ ትምህርት ከመስማት ፈቀቅ ብላችኋል። የአጥማቂ፣ የነገር አዋቂ፣ የጎሳ፣ የጎጥ የምናምን አምላኪ ትሆናላችሁ። ክህነት በዘር ይወርድ ይመስል ከብሔሩ ውጭ በሆነ ካህን መባረክ የማይፈልግ ምዕመን እንዴት ብሎ ነው ከፈተና መውጣት የሚችለው? ምን ቢሆን ነው እግዚአብሔር ምሕረቱን ለሰው ሊሰጥ የሚችለው?
ለማንኛውም የፈተናው ምንጭ ራሳችን ከሆንን ራሳችንን እናስተካክል። ክርስቶስን ብለን የጀመርነውን ክርስትና በተለያየ ምክንያት የምንፈተንበት እንዳይሆን ከዐላማችን ፈቀቅ ልንል አይገባንም። ዐላማችን ክርስቶስን ተከትለን ወደ ቀራንዮ መድረስ ነው። ዮሐንስ ይህንን ሁሉ ፈተና መልስ ሳይሰጥ ስላለፈው ነው እንጅ ሌሊቱ ነግቶ በቀራንዮ ያየነው ዝም ብሎ እንዳይመስላችሁ። ድካም ካዩባችሁ ፈታኞቻችሁ ብዙ ናቸው። እንደ ዮሐንስ እያለፋችሁ መሄድን ልመዱ። ቀራንዮ ላይ በረከት ይጠብቃችኋል። ክርስቶስ ከምድር ከፍ ብሎ ታገኙታላችሁ። ማርያምን በእናትነት ትቀበላላችሁ። በገነት ለመኖር ዕድል ታገኛላችሁ። ለፈተና አሳልፈው የሰጡንን ድክመቶቻችንን ካወቅን ፈተናውን ማለፍ እንችላለን።
አቤቱ ወደ ፈተና ከሚወስዱ ክፉ ሀሳቦች አድነን!
ማስታወሻ:- ሊቀ ሊቃውንት ስምዐ ኮነ መልአክ የአራቱ ጉባኤያት መምህርና የባሕር ዳር ሀገረ ስብከት የሊቃውንት ጉባኤ ሰብሳቢ ሲሆኑ የመጻሕፍት ደራሲም ናቸው:: ሊቅ ሊቃውንት የጃንደረባው ሚዲያ ዐምደኛ ሲሆኑ ጽሑፎቻቸው ዘወትር ሰኞ የሚነበቡ ይሆናል::
እውነት መምህር ቃለ ህይወት ያሰማልን ይሄን በምፅፍ ሰዓት እራሱ ከእራሴ ጋር ብዙ ሙግት ውስጥ ሆኞ ነው ከቅርብ ጊዜ ወዲህ መንፈሳዊ ህይወቴን እያጣሁት ነው እንጃ ብቻ ይሄ ድንቅ ፅሑፍ እራሴን እንዳይ እያደረገኝ ነው ማንበብ አነበብኩት ግን መተግብሩ ነው ያቃተኝ እግዚአብሔር እንደ እርሶ ያሉትን ያብዛልን 🤲
አቤቱ ወደ ፈተና ከሚወስዱ ክፉ ሀሳቦች አድነን!
ቃለ ሕይዎት ያሰማልን!
ቃለ ህይወት ያሰማልን
እንደ ዮሐንስ እያለፋችሁ መሄድን ልመዱ። ቀራንዮ ላይ በረከት ይጠብቃችኋል።
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምሕር
ቃለ-ሕይወትን ያሰሰማልን!🙏
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መልካምና ጥሩ እይታ ነዉ ከመጽመፍ መምህር የሚጠበቅ ነገርግን የወንድማማችነት መንፈሳችሁን ማን ወሰደዉ በአገልግሎት ስለምን ትነቃቀፋላችሁ ከንዱ አጥማቂ ለላኛዉ ደብተራ ስለም በሚዲያ ትባባላላችሁ ምዕመንን ለሁለት ከመክፈልም አልፎ ያጠፋል ስለምን በሒወት መንገድ ለክርስቶስ ኢየሱስ የምንሆን አርጋችሁ አታሳዩንም እኔ ሁሉንም መጠየቅ ወደድኩ ክርስቶስ ወንጌል ሲያስተምር አልተቸም አዎ መጽሐፍትን ተርጉሟል እርሰዎና መሰሎችዎም የተማራችሁትን እንደምትተረጉሙ አዎ ክርስቶስ ሰይጣንን በስሙ አናዞ አስወጥቷል ዛሬም እንደሚያደርጉት ስለምን ሀለቱንም ይዞ የሚመጣ ጠፋ ????
“የበረታ ባልንጀራ ማለት ወንድሙን አንድ እርምጃ ወደ ክርስቶስ ማቅረብ የቻለ ነው።”..
ቃለህይወት ያሰማልን የኔታ!!!
ቃለ ህይወት ያሰማልን አባታችን
ቃለ-ሕይወትን ያሰሰማልን!🙏
የፈተናው ምንጭ ራሳችን ከሆንን ራሳችንን እናስተካክል
እግዚአብሔር ይስጥልን ቃለ ሕይወትን ያሰማልን
የእውነት አባታችን እያነበብን እና እየተማርን ነው
በርቱልን
ቃለ ህይውት ያሰማልን መምህር
አሜን አሜን አሜን
ቃለ ህይወት ያሰማልን
ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር🙏🙏🙏
ቃለ ሕይወት ያሰማልን