በመቃብር ድምፁን መስማት

መቃብር ምንድን ነው? መቃብርን ስናስብ ከቤተ ክርስቲያን ቅጥር ጀርባ የሚገኘው ቦታ አእምሮአችን ላይ እንደሚመጣ ግልጽ ነው በእውኑ ግን ከዛም የዘለለ ነገር ይኖረው ይሆን ?

መቃብር ነፍስ ከሥጋ ስትለይ ሥጋችን የሚያርፍበት ማደሪያ እንደሆነ ሁሉ በሌላ በኩልም ሕይወታችን ከእግዚአብሔር የተለየ ሲሆን መቃብር ውስጥ እንዳለን ማሰብ ያስፈልጋል:: አንዳንድ ጊዜ በሕይወታችን በእኛና በእግዚአብሔር መካከል እንደ ግድግዳ ቆሞ መቃብር የሆነብን ሰብረን መውጣት ያቃተንና እንደ ሙት ይዞን ሕይወትን እንዳናገኝ የሚያደርግን የተቆለለ የኃጢአት ክምር አለን:: እንደ እግዚአብሔር ሀሳብና ፍቃድ አለመኖር በራሱ መቃብር ውስጥ ያለ ሰውን እንደሚወክል ልብ ልንል ይገባል:: 

ሕይወትን ከእግዚአብሔር ጋር ለማድረግ ደግሞ የመጀመሪያ ማድረግ የምንችለው ነገር ማንነታችንን በትሕትና መካድ ነው :: የማቴ 16:24 “ በዚያን ጊዜ ኢየሱስ ለደቀ መዛሙርቱ እንዲህ አለ፦ እኔን መከተል የሚወድ ቢኖር፥ ራሱን ይካድ መስቀሉንም ተሸክሞ ይከተለኝ”እንዳለ ጌታ ።

ራስን መካድ የሚጀምረው ደግሞ ራስን ባዶ ከማድረግ ነው:: ማቴ 5-3 “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” በመንፈስ ድሆች የተባሉት ምናልባትም በየቤተክርስቲያኑ ቅጥር ስር ቁጭብለው የሚለምኑትን ነው ብለን እንደምናስበው አይደለም በመንፈስ ድሆች የተባሉት ገንዘብ ፣ እውቀት ፣ ውበት ፣ ዝና እና የመሳሰሉት ነገሮች እያሉአቸው የለንም ያሉ ወይንም እንደሌላቸው የሆኑ ባላቸው ነገርም የማይመኩትን ነው ፤ ለዛም ነው በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ ድሆች የተባሉት እኛም ብፁዕነት ላይ ለመድረስ ካሰብን የምንመካበትን ነገር ትተንልባችንን ባዶ ማድረግ ይገባናል:: ምክንያቱም ራሳችንን ባዶ እድርገን ካልጠበቅን ፈጣሪንስ ሁልጊዜ በፀሎት የምንጠራውና ወደ ህይወታችን እንዲመጣ የምንፈልገው መጥቶ ምን እንዲሞላልን ነው ?

እዉቀትን እንኳን ብናይ ራሳችንን ለፈጣሪ አሳልፈን እንዳንሰጥ ወይንም ወደ ሀይማኖት የማይመራን ማንኛውም አለማዊም ሆነ መንፈሳዊ እውቀታችን የውሸት የሆነ አታላይ እውቀት እንደሆነ ማወቅ ይገባናል:: ይሄ እውቀት እግዚአብሔርን ከመጠየቅና በሩን ከማንኳኳት የሚከለክለን የዲያብሎስ ማታላያም ጭምር ነው:: 

[ “ ነገር ግን እግዚአብሔር ጥበበኞችን እንዲያሳፍር የዓለምን ሞኝ ነገር መረጠ፤ ብርቱንም ነገር እንዲያሳፍር እግዚአብሔር የዓለምን ደካማ ነገር መረጠ፤ እግዚአብሔርም የሆነውን ነገር እንዲያጠፋ የዓለምን ምናምንቴ ነገር የተናቀውንም ነገር ያልሆነውንም ነገር መረጠ፥ ሥጋን የለበሰ ሁሉ በእግዚአብሔር ፊት እንዳይመካ”1ኛ ቆሮ 1:27-29] ያለው እግዚአብሔር ሞኙንና ደካማውን የመረጠው እርሱ እኛ ላይ መስራት ስለሚፈልግ ነው:: እግዚአብሔር አሁንም ያልተማሩ ዓሳ አጥማጆችን ሐዋርያት እና ወንጌላውያን አድርጎ ሊጠራ ይችላልና እውቀት አለኝ ብለን አንመካ::

እግዚአብሔርን ለመስማትም ደግሞ ከመቃብር መውጣት ያስፈልጋል:: መቃብር የተባለ ጥላቻ ፣ ቅናት፣ ጥርጣሬ፣ ርኩሰት፣ ሱስ፣ ፀብ ፣ ዝሙት፣ ጣዖት አምልኮ ፣ አለማመን፣ ተስፋ መቁረጥ ፣ ስንፍና ፣ ትእቢት ፣ስርቆት እንዲሁም የሥጋ ፍቃዶች ሁሉ ናቸው:: ከዚህ መቃብር እስካልወጣን ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር እንድነትን ማድረግ አይቻለንም::

 ከዚህ መቃብር ለመውጣት ደግሞ በመጀመሪያ የእግዚአብሔርን ድምፁን መስማት ያስፈልጋል::[ ይህንም ብሎ፡ በታላቅ ድምፅ፦ አልዓዛር ሆይ፥ ወደ ውጭ ና፡ ብሎ ጮኸ” ዮሐ 11- 43 ] አልዓዛር የኢየሱስን ድምፅ ሰምቶ ከመቃብር እንደወጣ እኛም የእግዚአብሔርን ቃሉን በመስማትና ገንዘብ በማድረግ እንደ መቃብር ከያዘን ሀጥያታችን መውጣት አለብን:: አብዛኞቻችን ጌታ በብዙ መንገድ ተናግሮን ነገር ግን እስካሁን ከመቃብር መውጣት ያልቻልን ጎስቆሎች ነንና እግዚአብሔር ፀጋ ወደጎደለው ህይወታችን በምህረቱና በርህራሄው ይምጣልን:: እግዚአብሔር ወደ ህይወታችንና ወደ ኑሮአችን ካልመጣ ርኩሰቱ ፣ አመፃው ፣በሽታው፣ ጦርነቱ፣ እልቂቱ ሁሉ ነገር ይቀጥላል::  “ ስለዚህም ጌታ፦ ከመካከላቸው ውጡና የተለያችሁ ሁኑ ርኵስንም አትንኩ፡ እኔም እቀበላችኋለሁ፥ ለእናንተም አባት እሆናለሁ እናንተም ለእኔ ወንድ ልጆችና ሴት ልጆች ትሆናላችሁ፤ ይላል፤ ሁሉንም የሚገዛ ጌታ” 2ኛ ቆሮ 6:17-18

ሌላውና ዋናው ከመቃብር የምንወጣበት መንገድ ደግሞ ንስሓ ነው:: በመጀመሪያ በዚህ ምድር ላይ የእግዚአብሔርን ፍቅር የሚይሸንፍ ምንም አይነት ሀጥያት እንደሌለ መገንዘብ ያስፈልጋል:: [ “የበደላችሁትን በደል ሁሉ ከእናንተ ጣሉ አዲስ ልብና አዲስመንፈስም ለእናንተ አድርጉ፤ የእስራኤል ቤት ሆይ፥ ስለ ምን ትሞታላችሁ? የምዋቹን ሞት አልፈቅድምና፥ ይላል ጌታ እግዚአብሔር፤ ስለዚህ ተመለሱና በሕይወት ኑሩ”ሕዝ 18:31-32] እግዚአብሔር በእውነትም የኛን ሞት ስለማይፈልግ በንስሃ ተመልሰን በቅዱስ ቁርባን ታትመን በአባቱ ቤት እንዳለ ልጅና ፍቅር እንደበዛለት ብላቴና ወደ አባታችን እቅፍ እንመለስ ዘንድ ያስፈልጋል:: ብዙዎቻችን ልባችንን ስተናል ከመንገድም ወጥተናል እንደ እግዚአብሔር በጎ ሀሳብና ፍቃድ መኖር ተስኖን ለአለም የተሰጠንና ራሳችንን ያጎሳቆልን ፍጥረቶች ሆነናል::

ሌላው እግዚአብሔር እኛ ላይ እንዲሠራ መፍቀድ አለብን:: የእርሱ ፈቃድ በእኛ ሕይወት ላይ ይገለጥ ዘንድ እሺታችንን ከሰጠነው እርሱ የማይሠራበት ምንም ነገር የለም:: ከዚህ ውጪ ግን እግዚአብሔር እኛን ሊባርክ ወደ ሕይወታች እንዲመጣ እርሱ በሚያየን ስፍራ ላይ መቆም ያስፈልጋል:: 

ትንቢተ ዕንባቆም 2-1 “ በመጠበቂያዬ ላይ እቆማለሁ፥ በአምባ ላይም እወጣለሁ፤ የሚናገረኝንም፥ ስለ ክርክሬም የምመልሰውን አውቅ ዘንድ እመለከታለሁ” እንዳለ እግዚአብሔርን በመጠበቂያው ቦታ ላይ ልንጠብቀው ይገባል:: መጠበቂያው ቦታ ደግሞ ኃጥያት ርኩሰት ስንፍና ጣዖት አምልኮ አይደለም:: የእግዚአብሔር መጠበቂያ ቦታ ሀይማኖት ትሕትናና ትጋት ነው እንጂ:: በመሰረቱ እግዚአብሔር ያመኑትን በጎች በረሀ ላይ ለአውሬ ትቶ የሚሄድ እረኛ አይደለም ለዛም ነው በመንገዳችን ልናስቀድመው የሚገባው እርሱ ስለእኛ ያስባልና:: 

 “እርሱ ስለ እናንተ ያስባልና የሚያስጨንቃችሁን ሁሉ በእርሱ ላይ ጣሉት” 1ኛ ጴጥ 5-7

ስለዚህ መቃብርን መክፈትና ሙትን ማስነሳት የማይሳነው ሞት ይይዘው ዘንድ ያልቻለው ክርስቶስ በልባችን የሞተውን ፅድቅን ያስነሳልን እና አዲሱን ማነታችንን ይመልስልን ዘንድ በፆምና በፀሎት መበርታት ይጠበቅብናል:: ምሳ 29 -1 “ ብዙ ጊዜ ተዘልፎ አንገቱን ያደነደነ ድንገት ይሰበራል፥ ፈውስም የለውም” እንዳለ መጽሐፍ እግዚአብሔር በፍርዱ ሳይመጣብንና ሳንሰበር ፈሪሳዊነታችንን አስወግደን ከያዘን መቃብር እንወጣ ዘንድ እግዚአብሔር ያስችለን::  “ኃይልን በሚሰጠኝ በክርስቶስ ሁሉን እችላለሁ” ፊል 4-13

“በመቃብር ያሉቱ ሁሉ ድምፁን የሚሰሙበት ሰዓት ይመጣል፤ መልካምም ያደረጉ ለሕይወት ትንሣኤ ክፉም ያደረጉ ለፍርድ ትንሣኤ ይወጣሉና በዚህ አታድንቁ” ዮሐ 5:28-29

Share your love

22 አስተያየቶች

  1. “እግዚአብሔርን ለመስማትም ደግሞ ከመቃብር መውጣት ያስፈልጋል:: መቃብር የተባለ ጥላቻ ፣ ቅናት፣ ጥርጣሬ፣ ርኩሰት፣ ሱስ፣ ፀብ ፣ ዝሙት፣ ጣዖት አምልኮ ፣ አለማመን፣ ተስፋ መቁረጥ ፣ ስንፍና ፣ ትእቢት ፣ስርቆት እንዲሁም የሥጋ ፍቃዶች ሁሉ ናቸው:: ከዚህ መቃብር እስካልወጣን ድረስ ከእግዚአብሔር ጋር እንድነትን ማድረግ አይቻለንም::”

    የሕይወትን ቃል ያሰማልን
    እህቶች ይበረታቱ👏

  2. ራስን መካድ የሚጀምረው ደግሞ ራስን ባዶ ከማድረግ ነው:: ማቴ 5-3 “በመንፈስ ድሆች የሆኑ ብፁዓን ናቸው፥መንግሥተ ሰማያት የእነርሱ ናትና” ቃለ ሕይወት ያሰማልን

  3. ቃለ ህይወት ያሰማልን
    ቤቲዬ የልጅነት ጎደኛዬ በጣም ኮርቼብሻለሁ እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠውን ጥበብና ሞገስ ይጨምርልሽ ድንግል ማርያም ያገልግሎት ጊዜሽን ትባርክ🙏🙏🙏

  4. በእውነት እግዚአብሔር ምሳሌነትሽን ይስረዝምልን ቃለህወትንም ያሰማልን በጣም ውብ፣ግልፅ እና እውነት ከእውቀት ጋር የሞላ የነብስ ምግብን ነው እና ያካፈልሽን እግዚአብሔር ይስጥልን

  5. ቃለ-ህይወት ያሰማልን
    ግልፅ እና የሃሳብ ፍሰቱን የጠበቀ ትምህርት ነበር!

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *