ራሴን ላጠፋ ስለሆነ ንስሓዬን ይቀበሉኝ

“ራሴን ላጠፋ ስለሆነ ንስሓዬን ይቀበሉኝ” 

| ጃንደረባው ሚድያ | ጥቅምት 2016 ዓ.ም.|

✍🏽 ዲያቆን ዶ/ር ዳዊት ከበደ እንደጻፈው

በአንድ ከተማ የሚያገለግሉ ካህን ከከተማ 400 ኪ.ሜ ርቀው በገጠር የሚኖሩ አረጋዊ እናታቸው ስልክ ደውለው ወደ ቤተክርስቲያን ተሻግረው የሚሄዱበት ድልድይ በመሰበሩ ስለተጨነቁ መጥተው ሕዝቡን አስተባብረው ድልድዩን እንዲያስጠግኑላቸው ተማጸኗቸው:: እኚህ አባት ምንም ያሉበት አገልግሎት ፋታ የማይሰጥ ቢሆንም የእናት ነገር ስለሆነባቸው በማግስቱ ወደዚያች የገጠር ከተማ አቀኑ:: 

ወደ እናታቸው መንደር ሲደርሱ ግን የገጠማቸው የተለየ ነገር ነው:: ከተማዋ ካህን ካየች ስለቆየች ንስሓ ለመግባት ብዙ ሕዝብ ፈልጎ የርሳቸውን መምጣት በጉጉት ይጠባበቅ ነበር:: ካህኑ የመጡበት ዋነኛ ዓላማ ድልድይ አስተባብረው ለማስጠገን ቢሆንም ሌላ ለነገ የማይባል የነፍስ ጉዳይ ገጠማቸው። የብዙ ነፍሳትን ንስሓ ከተቀበሉ በኋላ በመጨረሻም የመጡበትን ጉዳይ ለመፈጸም ድልድዩ ወደሚገኝበት ሥፍራ ባስ ተሳፍረው ጉዞ ሊጀምሩ ሲሉ አንድ ታላቅ ጩኸት ከባሱ በፍጥነት እንዲወርዱ  አስገደዳቸው።

አንድ ዕድሜው በሃያዎቹ የሚገመት ወጣት በኃይል እየጮኸ ትንፋሹ እየተቆራረጠ ” ራሴን ላጠፋ ነውና ንስሓዬን ይቀበሉኝ” አላቸው:: በፍጥነት ሹፌሩን አስቁመውት ከባሱ ወርደው ወጣቱን አንድ ጥላ ፈልገው ማነጋገር ጀመሩ:: ይህ ወጣት ቤተሰቦቹን በአደጋ ምክንያት እንዳጣ ይቅር ሊባል በማይችል ኃጢአት እንደተዘፈቀ እና ካለበት ውስብስብ ችግር ሊያወጣው የሚችል አንዳች ኃይል እንደሌለ ለካህኑ በዕንባ ጭምር አስረዳቸው:: 

የልቡን ዘርዝሮ ያለበትን ሸክም ወደ አምላኩ  እንዲያራግፍ ምንም ሳያቋርጡት ካዳመጡት በኃላ አባታዊ ምክራቸውን ቀጠሉ:: ከሰአታት ጸሎት እና ምክር በኋላ ወጣቱ ወደ ልቡ ተመለሰ:: የተቆረጠ ድልድይ ሊቀጥሉ የሔዱት አባ ቀን የተቆረጠላት እና  ተስፋ የቆረጠች ነፍስን በረቂቅ ሥልጣናቸው መቀጠል ጀመሩ:: ይህ ወጣት የመሞቻ የይለፍ ካርድ ሊቀበል መጥቶ በንስሓ የመኖርን ተስፋ አግኝቶ ተመለሰ:: ንስሓ ዘማዊውን እንደ ድንግል ብቻ አይደለም የምታደርገው የሞተውን ጭምር ታስነሳለች:: 

ብዙ ሰዎች ራስ ማጥፋትን አጀንዳ አድርጎ መወያየት ራሳቸውን ለማጥፋት ሐሳብ ያላቸው ሰዎችን ያበራክታል ወይም አንድ ሰው ራሱን ለማጥፋት ከወሰነ ማንም ሊመልሰው አይችልም ይላሉ:: ነገር ግን ይህ አስተሳሰብ ከእውነት ፈጽሞ የራቀ ነው:: አብዛኞቹ ራሳቸውን ያጠፉ ሰዎች እንዲህ ያለ ውሳኔ ላይ የሚደርሱት መኖርን ካለመፈለግ ሳይሆን ካለባቸው ስቃይ እረፍት ለማግኘት የተሻለ አማራጭ መስሎ ስለሚታያቸው ነው ።በዚህም ራስን ስለማጥፋት በግልጽ የሚደረግ ውይይት ራስን በማጥፋት የሚከሰት ሞትን  ይቀንሳል።

በዓለም ላይ በዓመት ከ 700,000 ሺህ በላይ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ ይሄውም በየሰኮንዱ ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎች አሉ ማለት ነው:: ከ80 በመቶ በላይ የሚሆኑት ራሳቸውን የሚያጠፉ ሰዎችም የሚኖሩ ዝቅተኛ እና መካከለኛ ገቢ ያላቸው ሀገራት ውስጥ እንደሆነ ጥናቶች ያሳያሉ:: ሌሴቶ ከዓለም ሀገራት ብዙ ራሳቸው የሚያጠፋ ሰዎች ያለባት ሀገር ስትሆን ከአፍሪካ ደቡብ አፍሪካ በቀዳሚነት ትመደባለች:: ኢትዮጵያ ውስጥም በዓመት ከ11 ሺህ በላይ ሰዎች ራሳቸውን ያጠፋሉ:: 

የአእምሮ ጤና መቃወስ፥ አደንዛዥ ዕጽ እና አልኮልን አብዝቶ መጠቀም ፥ ድባቴ (Depression) ፥ የቤተሰብ እና የማኀበረሰብ ድጋፍ ማጣት፥ ከልክ ያለፈ ጭንቀት ወይም ሐዘን ፥ ሥራ አጥነት ፥ ዘላቂ የሆነ ሕመም (chronic medical illnesses) እንዲሁም ራስን ለማጥፋት የሚጋብዙ አባቢያዊ ተጽዕኖዎች በዋነኝነት እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳሉ። 

በመጽሐፍ ቅዱስ ላይም ስድስት ሰዎች ራሳቸውን በተለያየ ምክንያት እንዳጠፉ ተመዝግቧል:: ከእነዚህ ውስጥ መጀመሪያው አቤሜሌክ (መጽ፥መሳ 9፥54)፥ ንጉስ ሳኦል (መጽ፥ዜና መዋዕል ቀዳ፥10፥4) እና ከጌታ ልደት በኋላ ደግሞ ይሁዳ (ማቴ 27፥5)  ይጠቀሳሉ:: በቤተክርስቲያንም በአራተኛው መቶ ክፍለ ዘመን የግኖስቲክስ (gnostic) እና ስቶዬክ (stoic) የፍልስፍና አስተሳሰቦች በአንድ አንድ የዘመኑ ክርስቲያኖች ላይ ይንጸባረቅ ነበር:: ይኸውም የክፋት ሁሉ መንስኤው ሥጋ ነው ብለው ስለሚያስቡ ሥጋን አብዝቶ ማጎሳቆልና ፈጥኖ በመሞት ወይም ለከተማው እንግዳ የሆኑ ሰዎችን በመተናኮል ሰማእት ለመሆን ይመኙ ነበር። አባቶቻችን ተጠናቁሎ ሰማእትነት የለም እንዲሉ ሥጋን ፈጽሞ በመጥላት ለመሞት የሚደረግ የክርስቶስን ቤተመቅደስ የማፍረስ ተግባር እንጂ ሰማእትነት እንዳልሆነ እና አትግደል የሚለውን የእግዚአብሔርን ህግ መሻር መሆኑን በመናገር ሊቁ አውግስጢኖስ እና ቀሌምንጦስ ዘእስክንድሪያ ራስን ማጥፋትን አውግዘው ጽፈዋል።  

በዓለም ላይ ያለን ይህች አጭር የእንግድነት ዘመን በደስታ የተሞላች እንዳልሆነች ክርስቶስ ይነግረናል ” በእኔ ሳላችሁ ሰላም እንዲሆንላችሁ ይህን ተናግሬአችኋለሁ። በዓለም ሳላችሁ መከራ አለባችሁ፤ ነገር ግን አይዞአችሁ፤ እኔ ዓለምን አሸንፌዋለሁ።” 

(የዮሐንስ ወንጌል 16: 33)። ቅዱስ ጳውሎስም ምንም ዓይነት ፈተና ቢገጥመን ተስፋ መቁረጥ እንደሌለብን  ” በሁሉ እንገፋለን እንጂ አንጨነቅም፤ እናመነታለን እንጂ ተስፋ አንቆርጥም፤” (2ኛ ቆሮ 4: 8) እያለ  በፈተና እንድጸና ያበረታታናል::  የክርስትና እምነት መሠረቱም ከሞት በኃላ ያለ ክርስቶስ ለወዳጆቹ ያዘጋጀው ሕይወት ነው:: 

ከክርስቶስ ሞት በኃላ ሞት የደስታ ምንጭ ነው:: እንደ ፈቃዱ ሆነው የሚሞቱ በሚሞቱባት ሰዓት  ነፍሳቸው ከሥጋቸው በገነት መዓዛ ደስ እያላት ትለያለች ከዛም የምትናፍቀውን ክርስቶስን ታየዋለች ነገር ግን ራሳቸው የሚያጠፉ ቅዱስ ዮሐንስ አፈወርቅ እንደተናገረ ነፍሳቸው ከሥጋቸው በመሪር ሐዘን ትለያለች። ከእንዲህ ያለ የጠላት ምክር እግዚአብሔር ይጠብቀን:: 

ብዙ መከራ ደርሶብህ መውጫ ቀዳዳ ያጣህ ፥ ነገን ስታየው ምንም ብርሃን የማይታይህ በመኖር እና በመሞት መካከል ያለህ ወንድሜ /ያለሽ እህቴ ጌታ በሉቃስ ወንጌል ምዕራፍ 10:26  ምሳሌ ሰጥቶ ያስተማረበትን ያንን ከኢየሩሳሌም ወደ ኢያሪኮ ሲወርድ ወንበዴዎች አግኝተው ልብሱን አራቁተው በሞት እና በሕይወት መካከል ጥለውት የሔዱትን ሰው ታሪክ አስታውሰው።

ለራስህ እዘንለት ለራስህም ምሕረት አድርግ ባልንጀራው ሁንለት:: እንደ ኦሪቶቹ ካህናት እና ሌዋውያን ራስህን ዓይተህ አትለፈው። ይልቁኑ አንተው ለራስህ እንደ ደጉ ሳምራዊ ሁንለት:: ቁስልህን እንደምንም አሻሽገህ እና ያለችህን የመጨረሻ አቅም ተጠቅመህ ወደ እንግዶች ማረፊያ ቤተ ክርስቲያን ተሸክመህ አምጣው:: በዚያ የተቆረጠን ተስፋ የሚቀጥሉ የሞትን ደብዳቤ ወደ ሕይወት የሚለውጡ ፥ ወደ የትም ሪፈራል የማይጽፉልህ በነፍስ ላይ የሰለጠኑ ሐኪሞችን ታገኛለህ:: ወደዚች የእንግዶች ነፍስ የተጨነቀች ነፍስ ማረፊያ እንደምንም ብለህ ስትደርስ የዚህን ዓለም ብቻ ሳይሆን የዘለዓለም ሕይወትንም ጭምር ይዘህ ትመለሳለህ ::

አንተ ሸክምህ የበዛ አሁኑኑ መጥተህ በአምላክህ ላይ አራግፈው:: እስኪ አንድ እድል ለአምላክህ ስጠው። ወደዚች ምድር እያለቀሰች የመጣችውን ነፍስህን እያለቀሰች አትሸኛት:: ራስን በመግደል የሚታገስ ሕመም የለም ፥ የሚቋረጥም ስቃይ የለም። በዚህች ምድር እውነተኛ ደስታ እውነተኛም ሐዘን የለም ከሞት በኃላ ካለው ሕይወት ጋር ሲነጻጸር የዚህ ዓለም ኑሮ ኢምንት የማስታወቂያ ያክል ነው:: 

ራስህን ለማጥፋት ስትወስን ተስፋ የቆረጥከው በራስህ ብቻ አይደለም በአምላክህም ጭምር እንጂ:: የአምላክህ የቸርነቱ መጠን የምህረቱም ብዛት ከአንተ ችግር እጅጉን ይበልጣል:: መንፈስ ቅዱስን መሳደብ እግዚአብሔር አይምረኝም ማለት ነው  እንዲህ ያለው ክፍ ሐሳብ ከአንተ ከቶ ይራቅ:: 

ግድ የለም ከጊዜያዊ መከራ ለመዳን ብለህ ወደ ዘለላም መከራ አትሸጋገር:: ቅዱስ ጳውሎስ እንዲህ ይልሀል ” በዚህች ሕይወት ብቻ ክርስቶስን ተስፋ ያደረግን ከሆነ፥ ከሰው ሁሉ ይልቅ ምስኪኖች ነን።” (1ኛ ወደ ቆሮንቶስ ሰዎች 15: 19) 

በአንድ ወቅት ራሱን ያጠፋ አንድ ግለሰብ በመጨረሻ የጻፈው ነገር ብዙዎችን አሳዝኗል:: ይህ ወጣት ራሱን ሊያጠፋ በመጓዝ ላይ ሳለ ለራሱ አንድ ነገር ብቻ ሐሳቡን ሊያስቀይረው እንደሚችል አሳምኖት ነበር። ይኸውን በመንገዱ ላይ “የአንድ ሰው ሰላምታ ማግኘት”  ነበር ። ነገር ግን አንድም ሰላም የሚለው ሰው ባለማግኘቱ ራሱን አጠፋ:: አንዲት የእግዚአብሔር ሰላምታ የአንድን ሰው ሕይወት የመታደግ አቅም አላት::

 ራሳቸውን ከማጥፋት በሰዎች እርዳታ የተረፉ ሰዎችም የሆነ የሚጨነቅላቸው ሰው ማግኘታቸው ለመኖራቸው ምክንያት እንደሆናቸው ይናገራሉ:: በጭንቀት በድብርት እና ተስፋ በመቁረጥ ውስጥ ያሉ ወገኖቻችንን እንቅረባቸው፥ እናዳምጣቸው፥ ከጎናቸው እንደሆንን እናሳውቃቸው በዚህ ብዙ ነፍሳትን ከሥጋ እና ከነፍስ ሞት እንታደጋለን::

Share your love

15 አስተያየቶች

  1. በእውነቱ መልካም እና ወቅታዊ መልዕክት ነው ያስተላለፉት ዲያቆን ፡ ዶክተር።
    ቃለ ህይወት ያሰማልን ፤ ተስፋ መንግስተ ሰማያትን ያውርስልን።

  2. አንዲት የእግዚአብሔር ሰላምታ የአንድን ሰው ሕይወት የመታደግ አቅም አላት :: በእውነት ዘውትር የምንታደጋትን ነፍስ እያሰብን የምንኖር ያድርገን ። ቃለ ህይወት ያሰማልን

  3. ቃለ ሕይወት ያሰማልን።እኔም ለብዙ አመታት በተስፉ መቁረጥ ነበር ሕይወቴን የምመራው ምክንያቱ ደግም አንድ ልተዋት ባልቻልኳት ኃጢአት ነበር እና አንድ ጊዜ ይህ ሀሳብ መጥቶብኝ ነበር ራሴን ጠልቼው ስለነበር ነገር ግን እድለኛ ሆኜ ጥሩ ንስሐ አባት ነበሩኝና ነገርኳቸው ከዛም የፍልሰታ ፆምን ተጠቅሜ ወደ ራሴ ተመለስኩ ከዛም በሂደት የተፈጠርኩበትን ዓላማ አወኩት አሁን ይህን ዓላማ ለማሳካት በምችለው እየታገልኩ ነው።በፀሎታችሁ አስቡኝ።

  4. በጣም አስተማሪ ፅሁፍ ነው ቃለ ህይወት ያሰማልን።
    በዚሁ ቀጥሉበት የብዙዎች የህይወት ጥያቄ ሚመልስ ትምህርት ነው 🤲❤

  5. Kale hiwot yasemalen. Gn 1 tyake alegn. Yemetaser semat tesemton bihones? Be egziabhr ena befeterachew truna metfo ngroch tasren ye esun alem sanod baged eyenornew ketesenans? Fekadeja lalhonbet fetena hule endenezegagn lmn enderegalen? Lmndnw ke enatachn belay yemiwoden amlak be fkr megzat kegelege netsanetachnn eske alemefeter,exist alemadrg drs yalfekedew? memot wym alememot gehaneb wym mengeste semayat becha lmn hone? Huletunem alfelegm malet lemen aychalem? Endazi aynt tyake senteyek lmn kemot bwala yemenaakw ewket ale slezi tagesu enbalalen? If there was a choice to not exist in the world God created, the evil adn the good things, would there be any suicide at all?

    • Wendime,, Egziabher fitretin fetro sichers 1 ዘፍጥረት 31: እግዚአብሔርም ያደረገውን ሁሉ አየ፥ እነሆም እጅግ መልካም ነበረ። esu melkamun hulu ferual,, Ye esu ewket ke egna yibeltalna le egna yemihonewn hulu fetereln ,,, egna sewoch ke kifu hasabochachn ena ke metfo migbarachn,, kifuwn hulu bezih midir lay abezan,,, Yefeteren eko egnan ablito silewededen nw,,, mefeterachn eko ye fikru meglecha nw,, enji ende dingay binihon,, ende dimet ,,wisha tefetro endaltefetere mehonm eko ale,, gn zuryachn yeminisemachew keminayachew negeroch wichi,, ye egna mefeter ye sint sew hiwet wist ale? mefeterach eko lezich midir asfelagi silehonin,, be eyandandachn maninet Egziabiher siraw endigelet nw,,, ke hulum neger belay gn hulum yemihonew neger le egna tikim nw,,, ke mengiste semayat yebelete mircha le ene yelem,, sew kechale hulem ke abatu gar menor yiwedal hitsanat enkuan le sira bilew abatochachew kebet siwetu bizu yaleksalu,,, sewm ke amlaku ke abatu gar mehon le esu melkam nw,, wendime hoy memarhn metsihaf kidusn,, ye betechrstian timihrtochn memarhn ketil ye Kirstosn yemadanun neger abziteh atna,, keza esun lemayet tinafikaleh,, Egziabher ke ante gar yihun.

    • Yeh tyake enem bzu guadegnochem tefetroben lememeles bzu mokrenal, Kahnaten senteyek ateyku enbalalen weym wendme endalew stmotu ymelesal ybalal, leloch memhranem atgabi mels alsetunem. Betekrstian mels endalat amnalew enam melsun aderajtachu belela blog btsefulen.

  6. ቃለ ሕይወት ያሠማልን ፀጋውን ያብዛልህ ወንድማችን ጥሩ ወቅታዊ መልዕክት ነው 🙏🙏🙏

  7. ቃለ ህይወት ያሰማልን ; ጊዜውን ያገናዘብ ፅሑፍ ነው ::
    ጃንደረባዎች በርቱልን 🙏

  8. መልካሙን የህይወት ስንቅ ላስያዙን መምህራችን ቃለ ህይወት ያሰማልን ።

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *