ሥጋችንን መልካም ነገር ካስለመድነው ያንኑ ነገር ይጠይቀናል አምጡ ይላል

‘አያሌው ዘኢየሱስ እንደተረጎመው’ የሚል ጽሑፍ በሽፋናቸው ላይ ያለባቸው መጻሕፍት በመንፈሳዊ መጻሕፍት መደርደሪያዎች ላይ መታየት ከጀመሩ ሁለት ዐሠርት ዓመታትን አስቆጥረዋል፡፡ መምህር አያሌው ዘኢየሱስ አርባ አራት መጻሕፍትን ከእንግሊዝኛ ወደ አማርኛ በመተርጎም በኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን የቅርብ ዘመናት የትርጉም ሥራ ላይ ቀዳሚውን ድርሻ የያዙ ሲሆን በኢትዮጵያና በግብፅ ቤተ ክርስቲያን መካከል ዘመናት የዘለቀው ግንኙነት በአዲሱ ትውልድ ውስጥ እንዲሠርፅ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያደረጉ ጸሐፊ ናቸው፡፡ መምህር አያሌው በጃንደረባው ሠረገላ ላይ ያደረጉት ቆይታ የመጀመሪያ ክፍል የሚከተለውን ይመስላል፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :- ልጅነታችን ‘ሀብታም ሆነው የተወለዱ’ የሚባሉ ልጆች ያሉት ቤተሰብ ዓይነት ነበር፡፡ አባቴ በጣም ሀብታም ነበር፡፡ በንግድ ሳይሆን በትምህርት እንግሊዝ ሀገር economics ሠርቶ የመጣ ነበረ፡፡ ከመጣ በኋላ ቦታ ስላላገኘ ወደ አየር ኃይል ገብቶ ነበረ፡፡ ከተወሰነ ጊዜ በኋላ ደግሞ MAAG (military assistant and advisory group) የሚባል ጦር ሃይሎች ሆስፒታል አሁን ያለበት በፊት ልዕልተ ፀሐይ ነበር፡፡ እዚያ ፊት ለፊት ላይ መከላከያዎች ነበሩ፡፡ ለአሜሪካውያን በሲቪል ይሠራ ነበር፡፡ ጥሩ ዶላር ይሰጡት ነበር፡፡ በዚህ ምክንያት ኑሮአችንም ከአሜሪካውያን ጋር ነበረ፡፡ በፊት ከእሱ ጋር የሠሩ ወዳጆቹ በዕረፍት ቀናት እኛ ጋር እየመጡ ያሳልፉ ነበረ፡፡ 

ያሳደገን ትልቅ ግቢ ተከራይቶ ነበር፡፡ የምንማረው አግአዚያን ትምህርት ቤት ነበር፡፡ የምንውለው በሾፌር ከቤት ወደ ትምህርት ቤት ከትምህርት ቤት ወደ ቤት ስለነበረ የልጅነት ሕይወታችን ያ ብቻ ነበረ፡፡  ሰባት ልጆች ነበርን፡፡ የእኔ ብቻ ሳይሆን የሁላችንም አስተዳደግ  ከማኅብረሰቡ ጋር ምንም ዓይነት ግንኙነት ሳይኖረን ነበረ፡፡ ውሎአችን የተዘጋ ደጅ ውስጥ ነበረ፡፡ እዚያም ትምህርት ቤትም እዚህም መውጣት አይቻልም ነበር፡፡

       አባታችን በቅምጥል ነበር ያሳደገን፡፡ ሁኔታው አሜሪካዊ ይመስል ነበር፡፡ በጣም ፐርፌክት እንግሊዝኛ ይናገራል፡፡ አንባቢ ነበር ፤ እውቀቱም  አለው፡፡ ግድግዳውን የሞላ ሼልፍ አለው፡፡ በጣም በጣም በጣም መጽሐፍ አንባቢ ነበር፡፡ አሜሪካውያኑ ይመጣሉ፡፡ ውስኪ አለ ፣ ሥጋ ይበላሉ ፣ ውስኪ ጠጥተው ወደ ስፖርት መወዳደር ፑሽ አፕ መሥራት ምናምን ይሔዳሉ፡፡ እሱ አየር ኃይልም ስለነበረ እንደዚ ዓይነት ነገር ያደርጋሉ፡፡ መሳሳቅ ነው መጫወት ነው፡፡ በቃ በጣም የቅምጥል ሕይወት ነበር ያሳለፍነው፡፡ ደርግ ስድሳ ስድስት ላይ ሲመጣ አሜሪካውያኑን ውጡልኝ አላቸው፡፡ ያን ጊዜ የእኛም ሕይወት ተቀየረ፡፡ ይህን ይመስላል ልጅነታችን፡፡ አይበቃም?

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :- ትምህርት አማካይ የሚባል ተማሪ ነኝ፡፡ የተወሰነ የትምህርት ዓይነት ላይ እንደ እንግሊዘኛ ያለው ጥሩ ነው፡ A ነበር የማገኘው፡፡  ኤለመንተሪ አግአዚያን ተምሬያለው፡፡ አቡነ ባስልዮስ ትምህርት ቤት ተምሬያለው፡፡ መለስተኛ ሁለተኛ ደግሞ ተስፋ ኮከብ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አካባቢ ተምሬያለው፡፡ ከዚያ አዲስ ከተማ በፊት ልዑል መኮንን የሚባለው አዲስ ከተማ መርካቶ ፣ ከዚያም በኋላ ደግሞ ወንዶ ገነት ነው ፎረስትሪ ዲፕሎማ ተማርሁኝ፡፡ 

ያስተማሩኝ ስዊድኖች ነበሩ፡፡ ሂሳብ አልወድም ነበርና F ነበር ያመጣሁት፡፡  ሌሎቹን ትምህርቶች ጥሩ ነኝ፡፡ የግድ መድገም ነበረብኝ፡፡ በእኛ ጊዜ  ሂሳብ እንግሊዝኛና አማርኛ ሦስቱ ግዴታ ነበረ፡፡ አለዚያ ያስደግማሉ፡፡ እንደ አሁኑ በአንዴ በካልቾ ብሎ ማባረር የለም፡፡ ደጋግሞ ማትሪክ መውሰድና አጠራቅሞ በሦስት ሰርተፍኬት ይዞ ማስደመር ይቻላል፡፡ የሦስት ዓመት ተደምሮ የሆነ ኮሌጅ ይገባል፡፡ ውጤታማም የሚሆኑ አሉ፡፡ እንግዳ የሆነ ነገር ነው አሁን የመጣው፡፡ እኔ አሁን ሂሳብ ስለወደቅኩኝ ሌላ ነገር አላውቅም ማለት አይደለም፡፡ ግን አማርኛ B ነበር እንግሊዘኛ A ነበር እና B እና C C ነገሮች 2.6 ምናምን መጣልኝ፡፡ ከዛ አሻሽዬ የገባሁ፡፡ ወንዶ አባሮ የሚባል ተራራ አለ፡፡ ለሁለት ዓመታት እዚያ የተማርኩ፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :- ከአንዲት እኅታችን በስተቀር ሁላችንም ክርስትና የተሠጠነው ለቅዱስ ጊዮርጊስ ነበረ፡፡ እናታችን በጣም ጸሎተኛ ናት፡፡ መንፈሳዊነት አላት፡፡ አባቴ ሁሉ ነገሩ አሜሪካውያኑን ሆኖ ነበር፡፡ እናታችን ደግሞ በጣም ዝምተኛና ጭምት ናት፡፡ የቅንጦት ኑሮ ላይ ስለነበርን መንፈሳዊ ሕይወት ላይ እምብዛም አልነበርንም፡፡ በዓመት አንድ ጊዜ ብቻ መድኃኔዓለምን ዝክር እንደግሳለን፡፡ እናታችን በጣም ብዙ ሰው ጠርታ ታበላ ነበር፡፡ ከዚያ ያለፈ ነገር ግን ካደግን በኋላ ነው እንጂ በልጅነታችን አልነበረንም፡፡

በኋላ ግን እናታችን ወደ ቤተ ክርስቲያን እየያዘችን መሔድ ጀመረች፡፡ የምታስቀድሰው ልደታ ነበር፡፡  ስትመጣ ሐመር መጽሔት ይዛ ትመጣለች፡፡ ቀስ በቀስ ወደ ቤተ ክርስቲያን ሒዱ የእግዚአብሔርን ቃል ትለን ጀመር፡፡ ያኔ ሦስት ቁጥር ማዞሪያ ቶታል ነበርን፡፡ ከዚያ ብሥራተ ገብርኤል መሔድ ጀመርን፡፡

ከሦስት ቁጥር ማዞሪያ አሊ ዳገት የሚባል አለ፡፡ በዚያ በእግራችን ቀስ ብለን ነበር የምንሔደው፡፡ ሳር ቤት ድረስ ቴሌ ድረስ እንራመድና ተመልሰን ብሥራተ ገብርኤልን ደጁን ተሳልመን እናልፋለን፡፡ ከዕለታት በአንዱ ቀን አባ ኃይለ ገብርኤል የሚባሉ አባት (የኋላው አቡነ መልከ ጼዴቅ) ሲሰብኩ ውጪ ድረስ ይሰማ ነበር፡፡ ትንሽ ቆም አልን እና ማዳመጥ ጀመርን፡፡ ስለ ቤተክርስቲያን ስለ አባቶች ሕይወት ሲናገሩ ቆመን በትኩረት መስማት ጀመርን፡፡ አብረውን የነበሩ ሰዎች እንሒድ እንሒድ አሉንና ትንሽ ሰማናቸውና ሄድን፡፡ በሚቀጥለው ግን ተመልሰን መጣን ስብከታቸውን ደጅ ላይ ቆመን መስማት ጀመርን፡፡ 

ሲጠሩንም ሰዎቹን ሒዱ አልናቸው፡፡

ከዛ ቀስ እያልን ወደ ቤተ ክርስቲያን ገባንና አደባባይ ነገር አለች እዚያ ጋር መቀመጥ ጀመርን፡፡ ቀጠልንንና ቆመው ከሚማሩት ጋር ከወንድሜ ጋር ቆምን፡፡ ከዛ በኋላ በዚያው ሰምጠን ቀረን፡፡ አቡነ መልከ ጼዴቅ (መጀመሪያ ስማቸው አባ ኃይለ ኢየሱስ ነበረ፡፡ አንድ ቀን ሲሰብኩ ወንድም እኅቶቻችሁን ይዛችሁ ኑ አሉ፡፡ በተጨማሪም እሑድ እሑድ ሰንበት ትምህርት ቤት መማር ጀመርን፡፡

       ያን ጊዜ አብሮኝ የነበረው ታናሽ ወንድሜ በአሁኑ ሰዓት የምሁር ኢየሱስ ገዳም አበ ምኔት አባ ዘኢየሱስ ናቸው፡፡ አባ ዘኢየሱስ በዕድሜና በመንፈሳዊነት ቢበልጡኝም እኔ በቁመትና በውፍረት የምበልጣቸው ታናሽ ወንድሜ ናቸው፡፡ ከ13 መቶ ክፍለ ዘመን ጀምሮ የተገደመ ገዳም ሲሆን አሁን ደግሞ እንደ አዲስ ተገድሞ ትልልቅ አባቶች እየወጡበት ነው፡፡ እዚያ አበምኔት ሆነው መንኩሰዋል፡፡ አባቴ ስለሆኑ አንቱ ብላቸውም ያን ጊዜ አብረን ከቤት እስከ ብሥራተ ገብርኤል በእናታችን ምክር ስንሔድ አብረውኝ ወደ እግዚአብሔር የተጠሩት ታናሽ ወንድሜ ናቸው፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :-  ልክ ነው፡፡ ያኔ እኔ ሠላሳ ዓመቴ ነበር ፤ በዐውደ ምሕረት ከምንማረውም ፣ ከሰንበት ትምህርት ቤት ልጆችን ሰበሰቡንና የሰባኪያን ኮርስ ሰጡን፡፡ ከራሳቸው ሌላም ሌሎች አባቶች ወንድሞችን ጭምር  መጠተው እንዲያስተምሩን አደረጉ፡፡ ኮርስ ወሰድን ፤ ሰባኪያን ሆንን ማለት ነው፡፡ ሀብታሞቹን ለልጆቼ ቀሚስ ግዙላቸው ብለው አስገዝተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ መጥተው መረቁን፡፡ ይህ ዓይነቱን ሥልጠና በሁለት ዙር ሠጡ፡፡ የትም ቤተ ክርስቲያን እንደዚህ አይነት ነገር አልተሠራም፡፡

       ሰባኪነት የተማርነው ክርስትና ቤት ውስጥ ነበር፡፡ ክርስቲያኖች ይጠለሉበት በነበረው ዋሻ ስም ካታኮምብ ብለን ሰይመናታል፡፡ አባታችን ሲያስተምሩን እግዚኦታ ይባልና የማታ የሰርክ ፀሎት ይደረጋል፡፡ ከዚያ እርሳቸው ይቀመጣሉ፡፡ ጥቅስ አንብቡ ይላሉ ፤ ጥቅስ አንብቡ ማለት በቃላችን ወንጌልን መውጣት ነው፡፡ ከወንጌል አንብበን በቃላችን ሸምድደን ይዘን እንመጣለን፡፡ እገሌ ተነሥ ይላሉ፡፡ ያጠናችሁ ይባላል፡፡ ወጥተን አንዳንድ ጊዜ እኔን ከሚያክል ልጅ ጋር አብሬ እያጠናሁ እኔ ሠላሳ ዓመት ላይ ነበርሁ፡፡ መንፈሳዊ ሕይወት ግን ሁሉንም ነገር ገርዞ ይጥላልና በዚህ መልኩ ወደ አገልግሎት ገባሁ፡፡

       ከንባብ በኋላ የዐሥር ደቂቃ ስብከት እንሰብካለን፡፡ አንድ ሰባኪ ከዐሥር ደቂቃው አንድ ደቂቃ  ካሳለፈ አቁም አቁም ይባላል፡፡ በዘጠኝ ፣ በስምንት መጨረስ አለበት፡፡ ከገፋ ዐሥር ደቂቃ ድረስ ከዚያ እሱ ሲያቆም ሌላ ይቀጥላል፡፡ የሠላሳ ደቂቃ ሰባኪ ደግሞ አንዱ ይቀጥላል፡፡ እሱም ከሠላሳ ደቂቃ ማለፍ የለበትም፡፡ ሁለቱ ሰብከው ምሥጢር ካለው አመስጥረው፡፡ እርሳቸው ፊት ጥሩ ነገር ለመናገር ፣ ምሥጢር ለማምጣት ውድድር ነበረ፡፡ 

ሁለቱ ሰባኪያን ካስተማሩ በኋላ እሳቸው ይነሣሉ፡፡ አልባሽ ይባላል፡፡ ከየት እንደሚያመጡት አይታወቅም በተሰበከው ላይ የሚገርም ምሥጢር ያመጡና ያስተምራሉ፡፡ በእኔ ገጠመኝ ኢትዮጵያ በስብከት እሳቸውን የሚያህል አባት አላየሁም፡፡

       ከዚያ በኋላ በቃ መንፈሳዊ ሕይወት በዚህ እየጨመረ መጣ፡፡ ሆለታ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን ደግሞ አለ፡፡ በሌላ ዙር ላይ ከሌላ አጥቢያችን ዙሪያ ያሉትን መካኒሳ አቦ አድርገው እንደገና ሰብስበው ጠቅላላ ለሰባ ምናምን ተማሪዎች ኮርስ ሠጡ፡፡ ካህናትን ጨምረው ኮርስ ሠጥተው አስመረቁ፡፡ አለቃም ስለነበሩ መሰማትም ስለነበራቸው ጥሩ ነገር ሠርተዋል፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ ፦ አብዛኛው አገልግሎታችን ስብከትና ጽሑፍ ነበር፡፡ ከዓመት እስከ ዓመት እንደዛ አይነት ጽሑፎች ከ1988 ጀምሮ እየጻፍኩኝ ነው፡፡ ፋንፕሌት ነው የምትሏቸው? የልደት ዕለት ለሕዝቡ ይበተናል፡፡ የአዳር ፕሮግራም አለ ፤ ፕሮግራሙ ሁሉም ቤተክርስቲያን ያለ ይመስለኛል፡፡ እዚያ ውስጥ ተደርጎ መሀል ላይ ጌታ ተወለደ ሲባል ከከረሜላ ጋር ከብስኩት ጋር ለልጆች ጽሑፉም ተደርጎ ይበተናል፡፡ 

 ሌላው አገልግሎታችን ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን ሙሉ ጉልበታችንን መሥጠት ነበር፡፡  ጊዜውም ነበረን እንዳሁኑ ጊዜ ውድ አልነበረም፡፡ የቤተ ክርስቲያን አጥር መቀባት ጣራ ጉልላቱ ድረስ በቃ ማንም ሰው ተቀጥሮ አይሠራም ነበር፡፡ ወጣቶች እኛ ነን ሰንበት ትምህርት ቤት ሆነን አንድ ላይ እንሠራ ነበር፡፡ ቤተ ክርስቲያን ማፅዳትም ነበረ፡፡ በብዛት ግን በአብዛኛው ሳገለግል የቆየሁት እስካሁንም የማገለግልበት በስብከትና በሥነ ጽሑፍ ሥራ እና በትርጉም ሥራ ነው፡፡ 

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :- የታተሙት አርባ አራት ናቸው፡፡ አሁን እጄ ላይ ደግሞ ገና የሚታተሙ አሉ፡፡ አሁን የመጽሐፍ ኅትመት ውድ እየሆነ መጣ አይደለ? ማሳተም ከባድ እየሆነ ሲመጣ ከዚያ በኋላ ዝም ብዬ ሰውነቴ ስለለመደ እሠራለሁ፡፡ የምሠራው ማታ አምስት ሰዓት መድኃኒት ስለምወስድ እስከዚያ ድረስ ቆይቼ እውጥና ወደ ሥራ የምመለሰው ዘጠኝ ሰዓት ነው፡፡ 

አብዛኞቹ መጻሕፍት የተጻፉት ዘጠኝ ሰዓት ላይ ስነሣ ነው፡፡ ከሌሊት ዘጠኝ ሰዓት እስከ ጠዋት ሦስት ሰዓት ድረስ ለእኔ ምቹ ሰዓት ነው፡፡ በቃ ጸጥ ያለ ነው፡፡ ኮሽ የሚል የለም ፤ ምንም የለም፡፡

       አሁን ያን ነገር ሥጋዬ ስለለመደ ዘጠኝ ሰዓት ላይ መነሣት አለብኝ፡፡ ሥራ አይጠፋም የትርጉም ሥራ አይጠፋም ፣ ቢጠፋ ቢጠፋ ሌላም ነገር እንደ አሁን ታሪካዊ የሆነ ነገር እሠራለሁ፡፡ አሁን ለምሳሌ ይሄንን ሮበርት ሉድለም ይባላል ‘ዘማተር ኢዝ ሰርክል’ ይላል ይህንን ተርጉሜዋለሁ፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :- ፎንቱን ልብ በሉት ፤ ይሄ ቢያድግ ወደ ዘጠኝ መቶ ገጽ ሊደርስ ይችላል፡፡  ስጋህን ካስለመድከው ክፉ ነገርም ከለመደ ክፉ ሥራ ሲሠራ ነው የሚገኘው፡፡ ያው ሥጋችን ሰውነታችን መልካም ነገር ደግሞ ካስለመድነው ያንኑ ነገር ይጠይቀናል አምጡ ይላል፡፡

መምህር አያሌው ዘኢየሱስ :-  የመጀመሪያው ‘የተራራው ስብከት’ ነው፡፡ Contemplation on the Sermon on the Mount  የሚለው ነበር፡፡ መጋቤ ሠናያት ወንድማችን አለ ከእኔ ጋርም በዕድሜ የምንቀራረብ ነን፡፡ ልጅ ወልዶ ክርስትና ጠራን፡፡ ብሥራተ ገብርኤል አገልጋይ ነው፡፡ እሱ እንደውም የብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የእርሳቸውም ልጅ ነው፡፡ የአባታችንም ልጅ ነው፡፡ ልጅ ወለደ ፤ ሴት ልጅ ክርስትና ጠራናንና ሔድን፡፡ ስንሔድ ሁሉን ነገር የሚደረገው ተደርጎ ተዘምሮ ተበልቶ ተጠጥቶ በሚካሄድበት ጊዜ እኔ የአቡነ ሺኖዳን መጽሐፍ አየሁ፡፡ (የተራራው ስብከትን) የእንግሊዝኛ መጽሐፍ ሳይ ገርሞኝ ልተርጉመው አልሁት በዚያ ተጀመረ፡፡

       ከዚያ በፊት ‘ድንክዬዎቹ የባሕር አውሬዎች’ የሚል ከሰላምታ መጽሔት ላይ ስለ ዶልፊኖች የተረጎምሁት አንድ ጽሑፍ ነበረ፡፡ ቀጥሎም ዘሰቨን ሴክሬት የሚል መጽሐፍ በሂትለር እና ሚስቱ ኤቫ ብራውን ዙሪያ የተጻፈ ነበረ፡፡ እሱንም ተረጎምኩት፡፡ ‘የተራራው ስብከት’ ሲመጣ ግን ከበደኝ፡፡ ሁለት ወር ተኩል ፈጀብኝ፡፡ የመጀመሪያ መንፈሳዊ የትርጉም ሥራዬ ስለሆነ ማለት ነው፡፡ እንደምንም ጨረስሁት፡፡ ገንዘብ ግን አልነበረም እና ወንድሜ ያዕቆብ ሰንደቁ ‘አንተ ዝም ብለህ ሥራ ብር አይጠፋም’ አለኝ፡፡ ከአንድ ሀብታም አምስት ሺህ ብር በብድር ተወሰደ፡፡ ያኔ ደህና ነበር ማተሚያው፡፡ እኔ ያንን ጨራረስኩኝና ወደ መቀሌ ለፊልድ ሥራ ሔድኩኝ፡፡ 

 ወንዶ ገነት በተማርሁበት ፎርስትሪ ነበር የምሠራው፡፡ መጽሐፉ ታትሞ አለቃዬ በመኪና ሲመጣ ይዞልኝ መጣና እንኳን ደስ ያለህ ብሎ ሠጠኝ፡፡ የሰው ብድር መለስኩኝ፡፡ ከዚያ የትርፉ ገንዘብ ራሱን መጽሐፎቼን ማሳተም ጀመረ ማለት ነው፡፡እንዲህ እያለ የትርጉም ሥራው ቀጠለ ‘የዲያቢሎስ ውጊያዎች’ ‘የነፍስ አርነት’ ‘ሀብታምና ደሃ’ ‘የተስፋ ሕይወት’ እያለ ቀጠለ ማለት ነው፡፡ በዚህ ዓይነት መልኩ ነው ወደ ትርጉም ዓለም የገባሁት፡፡

ይቀጥላል

ማስታወሻ :- የመምህር አያሌው ዘኢየሱስን የትርጉም መጻሕፍት በትረካ ለማዳመጥ ይህንን ይጫኑ:: 

Share your love

14 አስተያየቶች

  1. የምር እንባዬን ሳልቆጣጠረው ነው ያነበብኩት … አባ ዘኢየሱስ ለካ በዚህ ሕይወት ውስጥ አልፈው ነው ከ ከንፈራቸው ማር ሚፈልቀው … ሁል ጊዜ አንተን ማወቅ እፈልግ ነበር ምን አልባት ተሳክቶልኝ ባገኝህ ምን ያህል ደስ ባለኝ?? የምሁሩ አበምኔት አባታችን እስካገኛቸው እጅግ ጓጉቻለሁ ከመንፈስቅዱስ በእርሳቸው በኩል በሚፈሰው ቃል እጠጣ ዘንድ… የቅዱሳን ቤተሰብ አምላክ ይጠብቃቹ

  2. በእውነት በሚተረጉምልን መጻሕፍት የብዙዎቻችንን ሕይወት ተቀይሩዋል እግዚያአብሔር ይስጥልን። ረዥም የአገልግሎት እድሜ ይስጥልን።

  3. መምህር እንኳን ወደ ሠረገላው በደህና መጡ ። እወነት ነው አቡነ ሽኖዳን ያወቅናቸው በእርስዎ በኩል ነው ። ስለተሠጦት መክሊት የሚያደርጉት ትጋት ብዙሐንን አትርፏል። ክቡር ጠያቂ ከአቡነ ሽኖዳ ጋር መምህር የተገናኙበትን ሁኔታ በክፍል 2 ቢጠየቁ ደስ ይለኛል።

  4. በጣም ደስ የሚል ጭውውት ነበር። እግዚአብሔር ይስጥልን።

    ቀጣይ ክፍል ቢኖረው?

  5. በእውነት እጅግ ድንቅ ነው።እረጅም እድሜ ይስጦ መምህር።
    ኢጃቶች በርቱልን እነዚህ ታሪካዊ የሆኑ ቃለ መጠይቆች እንደ መፅሔት ቢታተሙ መልካም ይመስለኛል።ትልልቅ ታሪክ ናቸውና።

  6. betam new nEgziabheren mameseginew lante besetew tsega Ahunem tena setoh bizuwoch mimarubeten metsaf taberekitelin zed tatochih lay Menfeskidus yinur tseliyelegn

  7. ቃለ ሕይወት ያሰማልን መምህር ፣ በእድሜ በጸጋ ይጠብቅልን።መፅሃፎችህ በህይወቴ ውስጥ ትልቅ ቦታ አላቸው፡፡

  8. ተመስገን እንዲህ ያለ የቤተክርስቲያን ሀብት እግዚአብሔር ይጠብቅልን ። ረጅም እድሜ ከጤና ጋር ይስጥልኝ ።

  9. ቃለ ሕይወትን ያሰማልን። በእውነት ከመምህር አያሌው ዘኢየሱስ ብዙ ትምህርት አግኝተናል። በመጽሐፍት ደግሞ ስለሚሠሩት መልካም ሥራ እግዚአብሔር መልካሙን ዋጋ ይክፈልልን🙏💐

አስተያየትዎን ያስቀምጡ

Your የኢሜል አድራሻ አይታተምም። Required fields are marked *